የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የአቅርቦት ሰንሰለቱ ላይ ባለ ችግር ምክንያት የሚፈልጉትን ያህል ቆዳና ሌጦ ማግኘት ያልቻሉት የቆዳ ኢንዱስትሪዎች አዋጁ የሚከለክል ቢሆንም፣ ክልከላው ታልፎ ዕርድ ከሚፈጸምባቸው ቦታዎች በቀጥታ መግዛት እንዲችሉ ፈቀደ፡፡
ሚኒስቴሩ ትናንት ማክሰኞ ሚያዝያ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ከትግራይ ክልል ውጪ ለሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ባለድርሻ መሥርያ ቤቶች በጻፈው ደብዳቤ፣ ፋብሪካዎቹ ደብዳቤው ከተጻፈበት ቀን አንስቶ ለሦስት ወራት በቀጥታ መግዛት እንዲችሉ መፍቀዱን አስታውቋል፡፡
ሚኒስቴሩ ይኼንን ውሳኔ ያሳለፈው፣ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በ2006 ዓ.ም. በወጣው የጥሬ ቆዳና ሌጦ ግብይት አዋጅ ቁጥር 814/2006 መሠረት፣ የሚፈጸመው ግብይት ፋብሪካዎች የቆዳና ሌጦ ምርትን በሚፈለገው መጠንና ጥራት እንዳያገኙ እንቅፋት እንደሆነባቸው በማሳወቁ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መጋቢት 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ አሁን ያለው የበዓል ወቅት ዕርድ የሚፈጸምበት መሆኑን በመጥቀስ አስቸኳይ ውሳኔ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡
በ2006 ዓ.ም. የወጣው የጥሬ ቆዳና ሌጦ ግብይት አዋጅ አንቀጽ አራት ግብይት የሚካሄደው በአዋጁ ላይ እንደተጠቀሰው በመጀመሪያ ወይም ሁለተኛ ደረጃ ግብይት መሆኑን ደንግጓል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ አምስት የመጀመሪያ ደረጃ ግብይትን የሚካሄደው በግለሰብ አምራቾችና አቅራቢዎች፣ በግለሰብ አምራቾችና ባህላዊ ቆዳ አልፊዎች ወይም በአነስተኛ ቄራዎችና አቅራቢዎች መካከል መሆኑን አስቀምጧል፡፡
በዚህ አዋጅ ላይ የቆዳ ፋብሪካዎች በሁለተኛ ደረጃ ግብይት ላይ የተቀመጡ ሲሆን ከአቅራቢዎች፣ ከፍተኛ ቄራዎች ወይም ከኤክስፖርት ቄራዎች ቆዳና ሌጦ መግዛት እንደሚችሉ ደንግጓል፡፡
በዚህ አዋጅ ምክንያት ቆዳ ፋብሪካዎች ከነጋዴዎች እንጂ በቀጥታ ዕርድ ከሚፈጸምባቸው ቦታዎች ቆዳና ሌጦ መግዛት እንደማይችሉ ለሪፖርተር የተናገሩት የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ፍርጀቦ በዚህ ምክንያት ፋብሪካዎቹ ለቆዳ አቅርቦት እጥረት መዳረጋቸውን አስረድተዋል፡፡ ነጋዴዎች በሚፈለገው ልክ መሰብሰብ ባለመቻላቸው ቆዳዎች ባክነው እንደሚቀሩና በየቦታው እንደሚጣሉ ተናግረዋል፡፡
ዳይሬክተሩ፣ የቆዳ ፋብሪካዎች በእጥረቱ ምክንያት ሥራ ላለማቋረጥና የሠራተኞቻቸውን ደመወዝ ለመክፈል በሚል አንድ የበሬ ቆዳን በ500 ብር የበግ ቆዳን ደግሞ ከ100 ብር በላይ በማውጣት ለመግዛት መገደዳቸው ገልጸዋል፡፡
‹‹አሁን አንድ ፋብሪካ ብቻ 20 ሺሕ የበሬ ቆዳ እፈልጋለሁ ብሎናል፡፡ ሌሎቹም ተመሳሳይ መጠን ይፈልጋሉ፣ ነጋዴዎች ደግሞ ይኼንን ያህል መጠን ያለው ቆዳ የማቅረብ አቅም የላቸውም፤›› ያሉት አቶ ብርሃኑ ይኼ ችግር የተፈጠረው በቆዳ እጥረት ሳይሆን በአቅርቦት ችግር ምክንያት መሆኑን አክለዋል፡፡
ፋብሪካዎቹ በዚህ ዋጋ ቆዳ እየገዙ በተወዳዳሪነት መቀጠል እንደማይችሉ የሚገልጹት አቶ ብርሃኑ፣ የምርታቸው ዋጋ ጨምሮ ገዢ ሊያጡ እንደሚችሉ ተናግረው፣ ይኼ ከመሆኑ በፊት መፍትሔ ለማምጣት መጣሩን አስረድተዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለፃ ፋብሪካዎች ከነጋዴዎች ብቻ እንዲገዙ የሚያዘውን አዋጅ የማሻሻል ሥራ በመሠራት ላይ ነው፡፡ ይሁንና በተከታታይ የሚመጡት የክርስቲያንና ሙስሊም እምነት ተከታዮች በዓላት ከፍተኛ ዕርድ የሚደረግባቸው በመሆኑ ፋብሪካዎቹ ይኼ ዕድል እንዳያመልጣቸው ሲባል አዋጁ ከመውጣቱ በፊት እንደነበረው በራሳቸውም ሆነ በወኪሎቻቸው አማካኝነት ቆዳ መሰብሰብ እንዲችሉ መፈቀዱን ተናግረዋል፡፡