ሰሞኑን በሩሲያ ኤምባሲ በር ላይ በርከት ያሉ ሰዎች ተሠልፈው በመታየታቸውና ለወታደራዊ ዘመቻ ሊመዘገቡ ነው መባሉ ከተሰማ በኋላ፣ መንግሥት ጉዳዩን እያጣራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሩሲያና በዩክሬን መካከል እየተደረገ ባለው ጦርነት ሩሲያን ለመደገፍ ጥሪ ቀርቧል በሚል፣ በርካታ ሰዎች በሩሲያ ኤምባሲ በር ላይ ተሠልፈው ታይተዋል። ሪፖርተር በቦታው ተገኝቶ እንደተመለከተው ሰዎቹ የወታደራዊ አገልግሎትና ሌሎች ማስረጃዎቻቸውን በመያዝ በኤምባሲው የተገኙ ሲሆን፣ የኤምባሲው ሠራተኞችም ማስረጃዎችን ሲቀበሉ ታይተዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኤምባሲው በር አካባቢ የታየው ሠልፍ ለምን ዓላማ እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም፡፡ ነገር ግን ሰዎቹ ለምን ጉዳይ እንደተሠለፉ እየተጣራ ነው ብለዋል።
ሪፖርተር በሩሲያ ኤምባሲ በር ተገኝቶ ያነጋገራቸው ለምዝገባ የተሠለፉ ሰዎች፣ ምዝገባውን በማኅበራዊ የትስስር ገጾችና ከተለያዩ ሰዎች መስማታቸውን ተናግረዋል። ‹‹ወደ ሩሲያ ለመዝመት የፈለግኩት ባለብኝ ኢኮኖሚያዊ ችግር ምክንያት እንጂ ለጦርነቱ ፍላጎት ስላለኝ አይደለም፤›› ሲሉ በኤምባሲው በር ላይ የተሠለፉ አዱኛ ከበደ የተባሉ ግለሰብ አስተያየታቸውን ለሪፖርተር ሰጥተዋል።
በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ለ11 ዓመታት ማገልገላቸውንና የሃምሳ አለቃ ማዕረግ እንዳላቸው ገልጸው፣ በ2001 ዓ.ም. ከሠራዊቱ ከተሰናበቱ በኋላ በቂ ገቢ እንደሌላቸው አስረድተዋል። ‹‹በወር ገቢዬ 1,554 ብር ነው፣ የሦስት ልጆች አባት ነኝ፣ አሁን ያለው የኑሮ ውድነት በጣም ከባድ ስለሆነ የተሻለ ዕድል ካገኘሁ ብዬ ነው የመጣሁት፤›› ብለዋል።
ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ሌላ ግለሰብ ደግሞ ከዚህ ቀደም የፖሊስ ባልደረባ እንደነበሩና በቂ ደመወዝ ማግኘት ባለመቻላቸው ከአባልነት እንደለቀቁ ተናግረው፣ ‹‹አሁን ደግሞ ወደ ሩሲያ ለመዝመት የፈለግኩት የተሻለ ዕድል ፍለጋ ነው፤›› በማለት ሩሲያ ኤምባሲ የሄዱበትን ምክንያት ገልጸዋል፡፡
የሩሲያ ኤምባሲ ምዝገባ እያደረገ ያለው ለወታደራዊ ዘመቻ ነው መባሉን አስተባብሏል፡፡ የኤምባሲው ቃል አቀባይ ማሪያ ቸርኑኪና ኤምባሲው ምንም ዓይነት የቅጥር ውል አለማውጣቱን፣ ምዝገባ የሚያደርገውም ለወታደራዊ ምልመላ አለመሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል።
‹‹ሰዎች ለተለያዩ አገልግሎቶች ወደ ኤምባሲያችን ሲመጡ እኛም መዝግበን እናስተናግዳለን፡፡ ምክንያቱም ሰዎች የሚመጡት ለቪዛ ወይም ለሌሎች ጉዳዮች ሊሆን ይችላል፤›› ብለዋል።
ነገር ግን ለወታደራዊ ዘመቻ የሚደረግ ምዝገባ የለም ብለዋል። እየተሠራጨ ያለው መረጃም ትክክል አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡