Monday, March 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቡና ግብይት ትመናን ለማንሳት የሚደረጉ ተግባራት መመርያ የጣሱ እንደሆኑ ቡናና ሻይ አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ምርት ገበያ የቡና ትመና ዋጋን በመሻር መመርያ የጣሰ አሠራር እየተገበረ መሆኑን ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

ምርት ገበያ በበኩሉ መመርያ ስለመጣሱ ያለው ነገር ባይኖርም፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግሮ ቀደም ብሎ የነበረውና በባለሥልጣኑ የዋጋ ገደብ አሠራር ግብይቱ እንዲቀጥል መስማማቱን አስታውቋል፡፡

ከሰሞኑ በምርት ገበያና በቡና ሻይ ባለሥልጣን መካከል በተለይም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት ሥር በሚገኙ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ቅርንጫፎች የቡና ግብይትንና ሽኝትን አስመልክቶ የተለያዩ አለመግባባቶች ሲሰሙ ቆይቷል፡፡

በኢትዮጵያ ምርት ገበያና በፌዴራል ቡናና ሻይ ባለሥልጣን በኩል ግልጽ ባልሆነ መንገድ በተፈጠረ የአሠራር ክፍተት ለከፍተኛ ኪሳራና እንግልት ተጋልጠናል የሚል ቅሬታ ከሸካ ዞን ቴፒ ከተማ ከሚገኙ የቡና ነጋዴዎች እንደቀረበ ከዚህ ቀደም መገለጹ ይታወሳል።

በሌላ በኩል በክልሉ የሚገኘው የሚዛን አማን የምርት ገበያ ቅርንጫፍ፣ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የሚያወጣው የቡና ዋጋ ህዳግ የወቅቱን አገራዊና ዓለም አቀፋዊ የገበያ ሁኔታ ያላማከለ በመሆኑ ተጠቃሚዎች ወደ ቀጥታ ትስስር በመግባታቸው ተገበያዮች መቀነሳቸውን እንዲሁ በቅሬታ መልክ ሲያነሳ ቆይቷል፡፡

የቡናና ሻይ ባለሥልጣን በበኩሉ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተሰጠው ተልዕኮና ተግባር ውጪ የሆነ ተግባርን እያከናወነ እንደሚገኝ አስረድቷል፡፡

 በተለይም ለኤክስፖርት የሚቀርብ የቡና ግብይት የዋጋ ትመና በባለሥልጣኑ በኩል በየሳምንቱ በሚቀርበው የቡና ማነፃፀሪያ ዋጋ መሠረት ምርት ገበያው እንዲያገበያይ የብሔራዊ የኤክስፖርት አስተባባሪ ኮሚቴ ቢያዝም፣ ምርት ገበያው ግን ዕለታዊ የምርት ገበያ የዋጋ ገደብ አሠራር እንዲመለስ መወሰኑን የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ይገልጻል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሚያዚያ 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ለአባላቱና ተገበያዮች ባወጣው ማስታወቂያ ላይ እንዳመላከተው፣ የምርት ገበያው የዳይሬክተሮች ቦርድ በምርት ገበያው በአማራጭነት የሚከናወነው የኤክስፖርት ቡና ግብይት በአቅርቦትና ፍላጎት መርሕ ላይ የተመሠረተ የዋጋ ትምና እንዲኖረው፣ ግብይቱ ከሌሎች አማራጭ የግብይት ሥርዓቶች እኩል የመወዳደሪያ ሜዳ እንዲኖረውና ምርት ገበያውን የመረጡ ተገበያዮች ግብይታቸውን ፍትሐዊ በሆነ ውደድር እንዲያከናውኑ ከተጠቀሰው ቀን አንስቶ ዕለታዊ የምርት ገበያ የዋጋ ገደብ አሠራር እንዲመለስ መወሰኑን አስታውቆ ነበር፡፡

በሌላ በኩልም በቡና ግብይት ውስጥ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድረውን ጥቁር ቡና የምርት ገበያው ማገበያየት መጀመሩ ከመመርያ ውጪ ነው የሚሉት የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ኃላፊዎች፣ ይህ ግብይት የዘርፉንም ሆነ የአገሪቱን ገጽታ የሚያበላሽ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር ለሪፖርተር  እንደገለጹት፣ ባለሥልጣኑ የዘርፉን ግብይት ለማዘመንና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡

 የዘርፉ ችግር በየጊዜው እየተገመገመ የተለያዩ አማራጮችን በተለይም ከግብይት አንፃር እየተሠራ እንደሚገኝ ያስታወቁት አቶ ሻፊ፣ ባለሥልጣኑ በተለይ ከጥር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የቀጥታ ትስስር ቡና ግብይት (Vertical Integration) የሚባል የግብይት አሠራርን ውጤታማ አድርጎ እየሄደበት እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በግብይቱ ለአርሶ አደሩ የደረቅ ቡና የሚባለው በጥሩ ዋጋ እየተሸጠለት እንደሚገኝ ያስታወቁት አቶ ሻፊ፣ ከዚህ ባሻገር እሸት የሚባለውን ቡና ሳይቀር በዚሁ የግብይት አማራጭ አማካይነት በተሻለ ጥቅም እንደሚሸጥ ተናግረዋል፡፡

በቡና ምርት ግብይት ውስጥ ያልተፈለገ የዕዝ ሰንሰለት የጨመሩ ተቋማዊም ሆነ ያለ ተቋም የሚገኙ ደላሎች በመሀል ገብተው ለአርሶ አደሩ መድረስ የሚገባውን ገቢ እየወሰዱ መቆየታቸውን የተናገሩት ምክትል ዳይሬክተሩ፣ የቡና ሪፎርም ዋነኛ ምክንያትም የቡና ግብይት ሰንሰለት መርዘም ወጪ እያናረ ስለሆነ ሊስተካከል ይገባል ከሚል አኳያ በመመርያዎች፣ ደንቦችና አዋጅ ወጥቶ እየተተገበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ሪፎርሙ ሲታሰብ አርሶ አደሩና ትክክለኛ ተዋንያን እንዲጠቀም ማድረግ እንደሆነ ያስታወቁት ምክትል ዳይሬክተሩ፣ ከሰሞኑ በተለይ ቴፒ አካባቢ በሚገኝ የምርት ገበያ ቅርንጫፍ ቡና አልተሸኘልንም በሚል ሲነሳ የነበረው ሐሳብ፣ ጥቂት ሰዎች ግብይቱን ለመረበሽ  ያደረጉት ነገር ነው ተብሎ ሊወሰድ የሚችል ነው ብለዋል፡፡  

የቡና ዋጋ እንዲንር ዋነኛ ምክንያቱ የገበያ እሴት ሰንሰለት ውስጥ ያሉት ያልተፈለጉ አካላቶች ተጠቃሚነታቸው ለማረጋገጥ በሚያደርጉት ጥረት ሳቢያ የሚፈጠር እንደሆነ አቶ ሻፊ የተናገሩ ሲሆን፣ በመሆኑም ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከብሔራዊ የኤክስፖርት አስተባባሪ ኮሚቴ፣ ከንግድ ሚኒስቴር በተሰጠው መመርያ መሠረት፣ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን በራሱ መንገድ ባወጣው መመርያ መሠረት የዋጋ ጣሪያ ተቀምጦ ከአንድ ዓመት በላይ እንደተሠራበት ተናግረዋል፡፡

የዋጋ ጣሪያ መሠራቱ እንደ አገር ውጤታማ አድርጎናል ያሉት አቶ ሻፊ፣ በባለሥልጣኑ ቀርቦ ምርት ገበያው እንዲያገበያይ የተወሰነው የቡና ማነፃፀሪያ ዋጋ ችግር እንኳን አለው ከተባለ ተቋማቶቹ አብረው አንድ ላይ ተነጋግረው የጋራ አቋም ይዘው፣ የሚመለከተውን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትም ሄደው አነጋግረው ከዚያም ባለፈ ለማክሮ ኢኮኖሚ ቀርቦ የትኛው ነው ለአርሶ አደርም ሆነ ለአገር የሚመቸው የሚለው በውሳኔ የሚሻር እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ እንዲገበያይበት የሚያወጣው የቡና ዋጋ ህዳግ የወቅቱን አገራዊና ዓለም አቀፋዊ የገበያ ሁኔታን ያላማከለ በመሆኑ ተገበያዮች ወደ ቀጥታ ትስስር ውስጥ በመግባታቸው ወደ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሚዛን ቅርንጫፍ የሚመጡ ተገበያዮች ባለፈው አንድ ወር ውስጥ እንዳሽቆለቆለ ቅሬታ የቀረበ ሲሆን፣ በዚህም ቅርንጫፉ ከ60 በላይ የሚሆኑ ሠራተኞችን ለመቀነስ እንደተገደደ ተመላክቷል።

በመመርያ የወጣ ነገርን አንድ ተቋም ዝም ብሎ መሻር አይችልም የሚሉት አቶ ሻፊ፣ ስለዚህ ይህ የዋጋ ጣሪያ በምርት ገበያ በኩል በመነሳቱ ገበያው በዘፈቀደ እንዲሄድ ያደረገው ስለሆነ ባለሥልጣኑ ከመመርያ ውጭ ተገበያይተው የሚቀርቡ የቡና ሽኝት አገልግሎት እንዳይሰጥ ያደረገበት አጋጣሚ እንዳለ ተናግረዋል፡፡

 በተቋማት መካከል ያለን ነገር ተቋማት ተነጋግረው ሊፈቱት የሚገባው ነገር እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ለዚህም ንግግሮች ቢጀመሩም፣ ሆኖም ምርት ገበያው ሕግና ደንብ በጣሰ መልኩ የተለያየ ይዘት ያላቸው ማስታወቂያዎች እንደሚያወጣ ምክትል ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኝ ነገራ በጉዳዩ ላይ ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት የተፈጠሩ አለመግባባቶች የመጨረሻ እልባት እንዲያገኙ  ሁለቱ ተቋማት የጋራ ግብረ ኃይል አቋቁመው ጉዳዩ እየተጠና ይገኛል ብለዋል፡፡

ለምርት ገበያም ሆነ ለቡናና ሻይ ባለሥልጣን የተሰጣቸው ሥልጣን (ማንዴት) እንዳለ ያስታወሱት ሥራ አስፈጻሚው፣ ከተናጠል ባሻገር በጋራ መሥራት የሚገባቸውን ጉዳዮች በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ንግግሮችና እንቅስቃሴዎች እንደተጀመሩ አስታውቀዋል፡፡

በተቋማቱ መካከል የሚወዛግበው ጉዳይ ፍሬ ሐሳብ አንዱ ጉዳይ ቡና በምርት ገበያ ውስጥና ከምርት ገበያ ውጭ የሚገበያይበት ዋጋ እኩል አይደለም፡፡ እኩል የመወዳደሪያ ዕድል ይፈጠር የሚል ሐሳብ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ወንድማገኝ፣ በቅሬታ መልክ ሲቀርብ የነበረው ጉዳይ ደግሞ ተነጋግረን ሳንቋጭ ዋጋ ተነሳ የሚል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከጥቁር ቡና ጋር በተገናኘ አገር ውስጥ ፍጆታ ላይ ተጠቃሚ ያለው፣ ከቡና ላይ  የሚወገድ ተረፈ ምርት እንደሆነ የተናገሩት አቶ ወንድማገኝ፣ በመሆኑም ይህንን ተጠቃሚ ያለው ምርት ምን ያህል ፐርሰንቴጅ መቀበል አለብን የሚለው ዋናው ርዕሰ ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

መደበኛ ባልሆነ መንገድ ግብይት የሚደረግበት ይህ ምርት ገበያውን ከሚረብሽና ኮንትሮባንድ ከሚሆን በመደበኛው ገበያ ሕጋዊ ሆኖ ለምን አይገበያይም? የሚለው ጉዳይ ዝም ብሎ የሚወሰን ባለመሆኑ የላኪና የአምራች፣ የአቅራቢ ተወካዮች በተገኙበት ምክክሮ ተደርጎ ፐርሰንቴጁ እንዲጨምር መደረጉን አቶ ወንድማገኝ ተናግረዋል፡፡ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ቅሬታም ለምን እኛ ሳንውቀው ፐርሰንቴጁ የወጣው ወይም ከፍ ያለው፣ እንዲሁም ከኤክስፖርት ምርት ጋር ተቀላቅሎ ኤክስፖርቱን ሊጎዳ ይችላል የሚል እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ጥቁር ቡና በሕገ ወጥ መንገድ ከሚሄድ ሕጋዊ ሆኖ ቢሸጥ የሚለውን ቁጭ ብለን ሁሉንም ባለድርሻ አካላት እናወያይና ምን ያህል መጠን ቢደረግ ነው ለጤናም፣ ኤክስፖርቱንም ሳይጎዳ፣ በኮንትሮባንድ በኩል ሳይሄድ መሥራት የሚቻለው? የሚለውን ነገር አብረን እንየው ወደሚል ሐሳብ መጥተናል፤›› በማለት አቶ ወንድማገኝ አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በነበሩ ውይይቶች ሁለቱን ገበያዎች እንዴት እኩል የመወዳደሪያ ሜዳ ይሆናሉ የሚል ሐሳብ እንደነበር ያስረዱት ሥራ አስኪያጁ፣ ለዚህ መፍትሔ ለማምጣት የተጀመሩት ምክክሮች አሁንም ያልተጠናቀቁ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

ለምርት ገበያው በተለይ ከዋጋ ጋር በተገናኘ በአዋጅና ቦርድ የተሰጠው ሥልጣን አለ ያሉት አቶ ወንድማገኝ፣ ነገር ግን ይህም አተገባበሩ በምክክር ቢሆን ጥሩ ነው የሚል ሐሳብ ስላለ በእሱ ላይ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የቡና ምርት ግብይት ላይ ምርት ገበያው አንዱ የግብይት አማራጭ  እንደሆነ የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በመሆኑም ይህንን የግብይት አማራጭ እንዴት ተደርጎ እንደ አማራጭ የግብይት መንገድ መጠቀም የሚገባው ጉዳይ ዋናው የተቋማቱ የውይይት ርዕሰ ጉዳይ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

ሻጭም ሆነ ገዥ አማራጭ እንዲኖረው፣ ኤክስፖርቱም ሳይጎዳ ነገሮች እንዲሄዱና በአጠቃላይ የጋራ መፍትሔ በአጭር ጊዜ እስኪገኝ ድረስ ለተወሰነ ጊዜ ድረስ የቡና ግብይቱ ቀድሞ በነበረው የዋጋ ገደብ አሠራር እንዲፈጸም መደረጉን አቶ ወንድማገኝ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች