በመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን በአገር አቀፍ ደረጃ በመንግሥት ተቋማት ሥር በሚገኙ የመሬት ይዞታዎች ላይ ሊገነቡ ለታሰቡ የመኖሪያ ቤቶች፣ የስብሰባና የፈረስ መወዳደሪያ ማዕከላት ሁለት የውጭና አራት የአገር ውስጥ ድርጅቶች ፍላጎት ማሳየታቸው ተገለጸ፡፡
የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን በመንግሥት ይዞታዎች ላይ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዙና ጥሩ የፋይናንስ አቅም ካላቸው ኩባንያዎች ጋር በመተባበር፣ ግንባታ ሊያካሂዱ የሚችሉትን አልሚዎች ለማወቅ የፍላጎት መግለጫ ማውጣቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በዚህም መሠረት ለ35 ቀናት በቆየው የአልሚዎች ፍላጎት ማሳያ ዲቪታ ፕሮፐርቲስ ሆልዲንግ፣ ጊፍት ሪል ስቴት፣ ነቤ ሆምስ፣ ቲኤንድኤች ዴቨሎፕመንት ኮንሰልታንት ከአገር ውስጥ፣ እንዲሁም ከውጭ ሚማርልክ ዲኮራሲዮንና ናዋዛሪ አልታካዱም የተባሉ ሁለት የቱርክ ኩባንያዎች ፍላጎት ማሳየታቸውን የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ሌንሳ መኰንን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ፍላጎት ያሳዩት ኩባንያዎች ማንነትና ያቀረቡት የመረጃ ዝርዝር እየተገመገሙ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ በፕሮጀክቶቹ መሠማራት የሚፈልጉትን ፕሮጀክት በመቅረፅ በቀጥታ አቅማቸውን በማየት ወይም ጨረታ በማውጣት ወደ ሥራ እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል፡፡
መረጃቸው በሚገባ ከተገመገመ በኋላ ያስገቡትን መረጃ መሠረት በማድረግ ውይይት ተደርጎ፣ በ2015 ዓ.ም. መጀመርያ ላይ ፕሮጀክት ተቀርፆ ወደ ዋናው ሥራ እንደሚገቡ ወ/ሪት ሌንሳ ተናግረዋል፡፡
ግንባታ የሚካሄድባቸውን ቦታዎች አሁን የቀረበውን ፍላጎት በማየት የሚለይ መሆኑን፣ በታሰበው ልክ መሄድ የሚችል ኩባንያ ከተገኘ እንደ አስፈላጊነቱ ከኮርፖሬሽኑ ድጋፍ ይደረግለታል ብለዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በፌዴራል የመንግሥት ተቋማት ይዞታ ሥር አለ ተብሎ የሚታሰበውን 4.5 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በማጣራት የመመዝገብ ሥራ እያከናወነ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ በመንግሥት ተቋማት የተያዙ ይዞታዎችን የመለየትና የመመዝገብ፣ የባለቤትነት ይዞታቸውን ማረጋገጥና በይዞታዎቹ ላይ ተገቢ የሆኑ ልማቶች እንዲከናወኑ የማድረግ ኃላፊነት የተሰጠው ኮርፖሬሽኑ፣ በአምስት ቢሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመ መንግሥታዊ ድርጅት ነው፡፡