Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የሕዝባችን ዘመን ተሻጋሪ የጋራ እሴቶች ይጠናከሩ!

የሕዝባችን ዘመን ተሻጋሪ የጋራ እሴቶች ይጠናከሩ!

ቀን:

የክርስትና እምነት ተከታዮች የትንሳዔ በዓልን እያከበሩ ሲሆን፣ የእስልምና እምነት ተከታዮች ደግሞ የዓረፋ በዓል እየተቃረበ የረመዳን ፆም የመጨረሻ ሳምንት ላይ ናቸው፡፡ የሁለቱ ታላላቅ እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን በዓላቱን ሲያከብሩ የተቸገሩ ወገኖችን የመደገፍ፣ የታመሙትን የመጠየቅና በሐዘን ውስጥ ያሉትን የማፅናናት ዘመን ተሻጋሪ አኩሪ እሴቶች አሉዋቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ደግሞ በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነትና በተለያዩ ሥፍራዎች በሚከናወኑ ግጭቶች ሳቢያ ሕይወታቸውን ካጡት በተጨማሪ፣ ንብረታቸው ወድሞባቸው የተፈናቀሉ በርካታ ወገኖች የሚቀምሱት አጥተው የወገን ድጋፍ በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን ምንም እንኳ ኑሮ በጣም እየከበዳቸውና ከአቅማቸው በላይ ቢሆንም፣ አሁንም ካለቻቸው ላይ ለማካፈል ወደ ኋላ እንደማይሉ በተለያዩ ጊዜያት በተግባር አሳይተዋል፡፡ ጥቂት አልጠግብ ባዮች ደግሞ የወገን ሰቆቃ አልሰማ ብሏቸው ዝርፊያውን ያጧጧፉት ሲሆን፣ በጦርነት ለተፈናቀሉና በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የተሰናዳ ዕርዳታ ጭምር ሲቀራመቱ ተስተውለዋል፡፡ ከኢትዮጵያውያን መልካም ባህልና እሴት ያፈነገጡትን መውቀስና በሕግ ማለት ተገቢ ሲሆን፣ የኢትዮጵያዊነት አኩሪ ተግባራት እንዲቀጥሉ አንዳንድ ማሳሰቢያዎችን ማሰማት አስፈላጊ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የሚያብበው በመልካምነት ላይ ነውና፡፡

ዜጎች በአገራቸው ጉዳይ በእኩልነት ተሳታፊ የሚያደርግና ልዩነት የማይፈጥር ሥርዓት እንዲሰፍን መግባባት ያስፈልጋል፡፡ መንግሥትም ሆነ የአገር ጉዳይ የሚመለከታቸው ወገኖች በኢትዮጵያ ምድር እኩልነት የማስፈን ኃላፊነት አለባቸው፡፡ እኩልነት የሚጠቅመው አገርን በጋራ ለማሳደግ ነው፡፡ ማንኛውም ዜጋ በሕግ የተረጋገጠለትን መብት፣ ጥበቃና ጥቅም የማግኘት መብት አለው የሚባለው እኩልነትንና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ነው፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያመነጨው ሀብት ጥቂቶችን እያበለፀገ ብዙኃኑን የድህነት አዘቅት ውስጥ መክተት የለበትም፡፡ ዜጎች ሕጋዊ ሆነው በመረጡት የሥራ ዘርፍ ተንቀሳቅሰው የመሥራት መብታቸው መከበር ሲኖርበት፣ ከልፋታቸው ጋር የሚመጣጠን ጥቅም ሊያገኙ ይገባል፡፡ ለአንዱ የተፈቀደው ለሌላው ሲከለከል፣ አንዱ በሕጋዊ መንገድ ጠይቆ እንቢ ተብሎ ሌላው በሕገወጥ መንገድ ሲያገኝ፣ አንዱ ለአገር የሚጠቅም ተግባር እያከናወነ ማግኘት የሚገባውን መብት ሲነፈግ፣ ሌላው አፍራሽ ድርጊት እየፈጸመ መንገዱ አልጋ በአልጋ ሲሆንለት የአገርን ሰላም ያደፈርሳል፡፡ እኩልነትና ፍትሐዊነት የሚረጋገጡት በወረቀት ላይ ሳይሆን በተግባር ብቻ ነው፡፡ 

ኢትዮጵያ አገራችን በዓለም ፊት የሚያኮሯት አንፀባራቂ ታሪኮች ባለቤት ብትሆንም፣ በፀረ ኮሎኒያሊስት ትግል ተወዳዳሪ ባይገኝላትም፣ በተለያዩ ጊዜያት ሊወሯት የመጡትን በሙሉ አሳፍራ በመመለስ ብትታወቅም፣ ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት የሆነችና ለፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መፈጠር መነሻ ምክንያት መሆኗ ቢታወቅም፣ ይህንን የተከበረና ኩሩ ሕዝብ አንገት ሲያስደፋ የኖረው ድህነት ግን የጨለመ ገጽታዋ ማሳያ ነው፡፡ ድህነት ብሔራዊ ክብርንና ማንነትን ያዋረደ የዘመናት ጠላት ከመሆኑም በላይ፣ አሁንም አገሪቱን እየተፈታተናት ያለ ክፉ ደዌ ነው፡፡ ድህነትን የማስወገድ ትልም የኢትዮጵያን ሕዝብ ትብብር ካላገኘ ችግሩ እየከፋ መሄዱ አይቀርም፡፡ ይህም አስመራሪ በሆነው ስደት እየታየ ነው፡፡ ድህነት የሚባለው አገራዊ ውርደት በፈጣን ዕድገት ታሪክ ለማድረግ፣ በአገር ጉዳዮች እኩል ተሳትፎ የግድ መኖር አለበት፡፡ ብሔርንና እምነትን መሠረት ያደረጉ መጠቃቀምና አግላይነት መወገድ አለባቸው፡፡ ሥልጣንን መከታ በማድረግ የሚፈልጉትን መጥቀም፣ የማይፈልጉትን መከልከል በአንድ አገር ውስጥ ሁለት ዓይነት ዜግነት ይፈጥራል፡፡ እኩልነት ካልሰፈነ ሰላም አይኖርም፡፡ 

- Advertisement -

የንግዱ ማኀበረሰብ ለአገሩ የሚያደርገው አስተዋጽኦ የበለጠ ጎልቶ የሚታየው በሥነ ምግባር ሥራውን ሲያከናውን ነው፡፡ ከሥነ ምግባር አፈንግጠውና የኅብረተሰቡን ባህላዊ እሴቶች ንደው በሕዝብ ላይ አደጋ የደቀኑ ወገኖችን የማረቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሕዝባቸውን በቅንነት ለማገልገል የሚለፉ ያሉትን ያህል፣ ከመጠን በላይ በሆነ ራስ ወዳድነት ውስጥ የተዘፈቁ ሞልተዋል፡፡ የግብይት ሥርዓቱን መላቅጡን የሚያጠፉትንና ጤናማ ውድድር እንዳይኖር የሚያደርጉትን፣ የንግዱ ማኅበረሰብ በንግድ ማኅበራትም ሆነ በንግድ ምክር ቤቶች አማካይነት ሊታገላቸው ይገባል፡፡ ምርት በመደበቅ፣ የግብይት ሰንሰለቱን በማዛባት፣ ሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት በመፍጠርና የሕዝቡን ሕይወት በማናጋት ላይ የሚገኙት እነዚህ ኃላፊነት የማይሰማቸው ወገኖች በሕግ መባል አለባቸው፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናትንና በየደረጃው የሚገኙ ሹማምንትን በሌብነት በመበከል የግብይት ሥርዓቱን እያጠፉት ስለሆነ፣ ለአገር የሚያስቡ የንግድ ማኅበረሰብ አባላት ይታገሏቸው፡፡ በዚህም ሕዝባዊ ወገንተኝነታቸውን ያሳዩ፡፡ ጤናማ፣ ፉክክር ያለበትና ለሁሉም የተመቻቸ ፍትሐዊ የውድድር ሜዳ እንዲፈጠር የበኩላቸውን ይወጡ፡፡ ይህንን በስኬት ከተወጡ ለመላው የአገሪቱ ሕዝብ ትልቅ ስጦታ እንደሰጡ ይቆጠራል፡፡ የመስጠትና የማካፈል በጎ ተግባር ተባባሪ ይሆናሉ፡፡ 

የኑሮ ውድነቱን እያባባሱ ካሉት ተጠቃሽ ችግሮች መካከል አንዱ ገበያው በጥቂቶች ቁጥጥር ሥር መዋሉ ነው፡፡ ዋጋ በአድማ እየተወሰነና የምርቶች ሥርጭት ሥልታዊ በሆነ መንገድ እየተስተጓጎለ ስለፍትሐዊ ግብይት ፈጽሞ መነጋገር አይቻልም፡፡ ከአምራች ወይም ከአስመጪ እስከ ችርቻሮ ንግድ ድረስ ያለው መጠኑ የበዛ ሰንሰለት፣ በፍላጎትና በአቅርቦት ሚዛናዊ መስተጋብር መወሰን ያለበትን ግብይት ጤና እያሳጣው ነው፡፡ ጥቂቶች ገበያውን እንደፈለጉ በሚያሾሩበት አገር ውስጥ የኑሮ ውድነቱ ሕዝቡን እያንገፈገፈው ነው፡፡ በሌላ በኩል ሕዝቡን ከአልጠግብ ባዮች ይታደጋሉ የተባሉ የሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ እንዲሁም የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ሚና ፋይዳ ሊታወቅ አልቻለም፡፡ እነዚህ ዋጋን በማረጋጋት የምርቶችንና የሸቀጦችን ሥርጭት ፍትሐዊ ያደርጋሉ የተባሉ ተቋማት፣ ሸማቾችን ከአስደንጋጩ የዋጋ ንረት ሊከላከሉ አልቻሉም፡፡ ብዙዎቹ የተቋቋሙበትን ዓላማ እየሳቱ በአልጠግብ ባዮች መጠለፋቸው የታወቀ ነው፡፡ ሕዝቡን አስመራሪ ከሆነው የኑሮ ውድነት ሊታደጉት ካልቻሉ የእነሱ ህልውና ምን ይጠቅማል? ወይ በአግባቡ ሥራቸውን እንዲሠሩ ማድረግ፣ ካልሆነም ዘግቶ መገላገል ይበጃል፡፡

የሲቪል ማኅበራት፣ የትምህርትና የጤና ተቋማት፣ የግልና የመንግሥት ሠራተኞች፣ ወዘተ በየተሰማሩበት መስክ ለአገር ጠቃሚ የሆኑ ተግባራትን ያከናውኑ፡፡ ፍትሕ እንዳይጓደል፣ መልካም አስተዳደር እንዳይመክን፣ ሌብነትና ዝርፊያ አገርን እንዳያጠፋ፣ ብልሹ አሠራሮች እንዳይሰፍኑ፣ የአገልጋይነት መንፈስ እንዳይጠፋና የአገርና የሕዝብ ጥቅም ቀዳሚ እንዲሆን ይትጉ፡፡ የመደጋገፍና የመተሳሰብ ግንባር ቀደም ተዋናይ ይሁኑ፡፡  እያንዳንዱ ዜጋ ከራሱ ቤት ጀምሮ በየተሰማራበት መስክ የበኩሉን ከተወጣ አገር ከድህነት መንጋጋ ትላቀቃለች፡፡ ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ሥራቸውን ሲያከናውኑ፣ መብታቸውንና ግዴታቸውን ለይተው ሲያውቁ ለሕገወጦች ቀዳዳ አይከፈትም፡፡ ማንም አምባገነን እየተነሳ ልርገጣችሁ ማለት አይችልም፡፡ ሁሉም ዜጋ ለአገሩና ለወገኑ ከልቡ ከሠራ ካለው ላይ እንደሰጠና እንዳከፈለ ይቆጠራል፡፡ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ ፍትሕ በእኩልነት ተደራሽ እንዲሆን፣ የአገርና የሕዝብ ጠንቅ የሆነው ሌብነት እንዲጠፋ፣ ፀረ ዴሞክራሲያዊና አምባገነናዊ አስተሳሰቦች ቦታ እንዳይኖራቸው ከእያንዳንዱ ዜጋ እስከ ልሂቃን ድረስ የመተሳሰብና የመደጋገፍ መንፈስ ሊያድርባቸው ይገባል፡፡ የመተሳሰብና የመደጋገፍ አኩሪ የጋራ እሴቶች የሚጎለብቱት እኩይ ድርጊቶች ሲወገዱ ነው፡፡ የሕዝባችን ዘመን ተሻጋሪ የጋራ እሴቶች ይጠናከሩ! መልካም በዓል!

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...