ዕውቅና ከሌላቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመረቀው በሥራ ላይ የሚገኙና በመማር ላይ ያሉ ተለይተው ማስረጃቸው ይሰረዝ ወይስ ይቀጥል በሚለው ላይ ውሳኔ እንደሚሰጥ፣ የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን አስታወቀ።
በተለያዩ ጊዜያት በርካታ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዕውቅና ሳይኖራቸው ተማሪዎችን አሠልጥነው ማስመረቃቸውንና በአሁኑ ወቅትም እስከ ከፍተኛ ኃላፊነት የደረሱ ሰዎች መኖራቸውን፣ የትምህርና ሥልጠና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አንዷለም አድማሴ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ገልጸዋል።
ፈቃድ ሳይኖራቸው ሲሠሩ ከነበሩ ተቋማት በተጨማሪ የከፍተኛ ትምህርት ፈቃድ ኖሯቸው፣ ዕውቅና ባልተሰጣቸው የትምህርት መስኮች አስተምረው ያስመረቁ መኖራቸውን አክለዋል። በ2014 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ብቻ 13 የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ዕርምጃ የተወሰደ መሆኑን፣ ከእነዚህም ውስጥ ሁለቱ ሙሉ ለሙሉ ዕውቅና የሌላቸው መሆናቸውን አቶ አንዷለም አስረድተዋል።
በ2012 እና በ2013 ዓ.ም. ደግሞ በአጠቃላይ በ25 የትምህርት ተቋማት ላይ ዕርምጃ መወሰዱን ገልጸው፣ በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት በርካታ ተማሪዎች ተምረው መመረቃቸውንና በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ የደረሱ መኖራቸውን ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት ፈቃድ በሌላቸው የትምህርት ተቋማት የተማሩትን በመለየት የትምህርት ማስረጃቸው ሕጋዊ ሆኖ ይቀጥል ወይስ ይሰረዝ በሚለው ላይ ውሳኔ ለመስጠት፣ ከሁሉም የትምህርት ባለድርሻ አካላት ተውጣጥቶ ጥናት እንዲደረግና መንግሥት ውሳኔ እንዲሰጥበት ለማድረግ እየሠራ ነው ብለዋል።
ያለ ፈቃድ ሲያስተምሩ ተገኝተው በተዘጉና ዕውቅና ያላገኙባቸውን የትምህርት መስኮች ሲያስተምሩ በነበሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመማር ላይ የነበሩ ተማሪዎች ደግሞ፣ ወደ ሌሎች የትምህርት ተቋማት መዘዋወር የሚችሉት እንዲዘዋወሩ ተደርጓል ብለዋል። ወደ ሌሎች ተቋማት መዘዋወር ያልቻሉት በጊዜና በገንዘብ የደረሰባቸውን ኪሳራ ካሳ “የተማሩባቸውን ተቋማት” ሊጠይቁ ይችላሉ ብለዋል። ነገር ግን ሲማሩ የቆዩበት ጊዜ ፈቃድ በሌለውና መሥፈርቱን ባላሟላ ተቋምና የትምህርት ዘርፍ ከሆነ የተማሩት ጊዜ ታሳቢ አይደረግም ሲሉ ገልጸዋል።
የከፍተኛ ትምህርት የመግቢያ መሥፈርት ሳያሟሉና የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ሳይኖራቸው ሲማሩ የነበሩ መኖራቸውን ገልጸው፣ እነዚህ ወደ ሌሎች ኮሌጆች የማዘዋወርም ሆነ ሌሎች ድጋፎች አይደረግላቸውም ብለዋል።
በኢትዮጵያ በአጠቃላይ የርቀት ትምህርት ማስተባበሪያዎችን ጨምሮ ዕውቅና የተሰጣቸው 328 የግል የትምህርት ተቋማት ሲኖሩ፣ 2500 ካምፓሶች አሏቸው። ዕውቅና በተሰጣቸው የትምህርት ዘርፎችም 1.1 ሚሊየን ተማሪዎች በእዚሁ ተቋማት እንደሚማሩ አንዷለም (ዶ/ር) አስረድተዋል።