ኢትዮጵያውያን ካሏቸው ቱባ ባህሎች ‹‹አኾላሌ›› የተሰኘው በተውኔት የታጀበ የልጃገረዶችና የወጣት ወንዶች ባህላዊ ጭፈራ አንዱ ነወ፡፡
ይህ በወሎ በተለይም በገጠራማው አካባቢ የተለመደው ባህላዊ ጭፈራ በክርስትናም ሆነ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የበዓላትን ወቅት ተከትሎ የሚከናወን ነው፡፡
በክርስትናና በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ እንደየእምነታቸው የሚከበሩትን ገና፣ ጥምቀት፣ አስተርዮ ማርያም፣ ጥር ሚካኤል፣ ዓረፋና አሹራ በዓላትን ተከትሎም ይጨፈራል፡፡
በልጃገረዶች ጭፈራ የሚደምቀውና በወንዶች የሚታጀበው የአኾላሌ ጭፈራ፣ በተውኔት፣ በስንኝ ድርደራና በግጥም ምልልስ የታጀበ ነው፡፡ የባህሉ ተሳታፊ ልጃገረዶች፡-
‹‹እራሷን ተሠርታ ወለባ ስጋለች፣
እንሶስላ ሙቃ ሎሚ ጨብጣለች፣
ያች ያገሬ ልጅ እሷው ትሆናለች፤›› እያሉ ሙዚቃዊ ግጥም የሚደረድሩለት አኾላሌ ባህላዊ ጭፈራ ምንድነው? ስንል በወሎ ዩኒቨርሲቲ የፎክሎርና ሥነ ጽሑፍ መምህርና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ብርሃኑ አሰፋ (ዶ/ር) አነጋግረናቸዋል፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ የአኾላሌ ሥነ ሥርዓትን ከክርስትና እምነት ጋር የሚያያይዙት አሉ፡፡ አኾላሌ ‹እልል ተወለደልን› ማለት ነው፣ ከክርስቶስ መወለድና ደስታ፣ ሰብ አሰገል ወርቅ ከርቤና ዕጣን ከማቅረባቸው ጋር የሚያያዝ፣ በወቅቱ ደስታውን ያበሰሩት ያላገቡ ልጃገረዶችና ወንዶች በመሆናቸው ከዚህ ጋር ተያይዞ የመጣ ባህል ነው የሚሉ አሉ፡፡
አንዳንዶች ደግሞ ቃሉን ለሁለት ሰንጥቀው የተለያየ ትርጉም ይሰጡታል ‹‹አኾ›› ኅብረት ላሌ ‹‹ደስታ፣ ጨዋታ›› አኾላሌ በኅብረት መጫወት መደሰት ነው ይላሉ፡፡
በብርሃኑ (ዶ/ር) ጥናት መሠረት ደግሞ፣ አኾላሌ ማለት ጨዋታው የራሱ ዘፈን ስላለው የዘፈኑ ዜማ መጠሪያ፣ አዝማች ነው፡፡ ግጥም ገጥመው በዜማ ይሉትና በየመሀሉ ‹‹ሆ፣ ኾላሌ ነሆላሌ›› ይላሉና፡፡
ይህ ባህላዊ ጭፈራ ትልልቅ ዓመታዊ በዓላትን አስመልክቶ ይከናወናል፡፡ ነገር ግን ባህላዊ ጨዋታው እየቀነሰ ስለመጣ መልሶ እንዲያንሰራራ በፌስቲቫል ደረጃ በዓመት አንድ ቀን ይከበራል፡፡ ዘንድሮም ለሦስተኛ ጊዜ በደሴ ከተማ ተከናውኗል፡፡
ከገና፣ ጥምቀት፣ አስተርዕዮ ማርያም፣ ከዓረፋና አሹራ በተጨማሪ በሠርግ ወቅት ጎልቶ ሙሉ ትዕይንቱ ባይታይም እንጨት ለቀማ ላይ ይዘፍኑታል፣ ይጨፍሩታል፡፡
የአኾላሌ ጨዋታ በዓላትን ተንተርሶ ይከወን እንጂ ግጥሞቹ ሃይማኖትን ወይም በዓላትን የሚገልጹ አይደሉም፡፡ ይልቁንም ፍቅር የሚገለጽባቸው ናቸው፡፡
ከልጃገረዶች፣ ከወጣት ወንዶች አለባበስ፣ ጀግንነት፣ ውበት፣ ፈሪነት ጋር የተያያዘና ለሴቷ ጀግና የከንፈር ወዳጅ ከመያዝ ጋር የተገናኘ ነው፡፡
ጨዋታው ሴቶች ክብ ሠርተውና ወንዶች በዙሪያቸው ከበው የሚከናወን ነው፡፡ አለባበሳቸውም ለየት ያለ ነው፡፡ ጨዋታው በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ለጎፈሬና ለጥርስ ውበት ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋሉ፡፡
ወንዶቹ ለጎፈሬና ለጥርሳቸው የሚያደርጉትን ጥንቃቄ ያህል ሴቶች ለሹሩባቸውና ለጥርሳቸው ውበት ይጠበባሉ፡፡ ለምሳሌ ሴቶችም ወንዶችም የላይኛውን አራት የፊት ጥርሳቸው ሹል ያደርጋሉ፡፡ ጥርሳቸው ሾሎ መታየቱ ‹ውበት ነው› ይላሉ የጭፈራው ተሳታፊዎች፡፡
ወንዶች ጎፈሬያቸውን አበጥረው ማበጠሪያ ሰክተው፣ ቅቤ ተቀብተው፣ ቅቤው ወደ አንገት እንዳይወርድ በሻሽ ገድበው፣ ነጠላ ጋቢያቸውን ትከሻ ላይ ጥለው፣ ቁምጣ ይለብሳሉ፡፡ ከላይ የሚለብሱት ሰርድያ የሚባል ልብስ ነው፡፡
ሴቶች ሙሉ በጥልፍ የተጌጠ ፈትል ቀሚስ ይለብሳሉ፡፡ የልብሳቸው ስም ደረት፣ በአንገት ዙሪያ የሚዘመዘመው ከብር የተሠራ ጌጥ ደግሞ መልጎም ይባላል፡፡ ላይ ቢያገቡም ባያገቡም እጃቸው የብር አምባር ያደርጋሉ፡፡ ቅቤ በአደስ መቀባትና ጥርስን እየፋቁ መሄድም የባህሉ አካል ናቸው፡፡
እንደ ብርሃኑ (ዶ/ር)፣ የሃይማኖት በዓላት ተከብረው ሳያልቁ የአኾላሌ ባህላዊ ጨዋታ አይጀመርም፡፡ ለምሳሌ ታቦት የሚገባ ከሆነ፣ ታቦት ገብቶ የንግሥ በዓሉ ሲያበቃ የአኾላሌ ጨዋታ ይጀመራል፡፡
በአኾላሌ ጨዋታ ዋናዎቹ ተዋናዮች ሴቶች ናቸው፡፡ ሴቶች ክብ ሠርተውና እጃቸውን ወደ ኋላ አድርገው በሚጫወቱት ጨዋታ አንዷ ስታቀነቅን ሌሎች ይቀበላሉ፡፡ ወንዶች ደግሞ በሴቶቹ ዙሪያ ክብ ሠርተው ይታደማሉ፡፡ አኾላሌ ከዘፈንና ጨዋታው ጋር ልጃገረዶች የከንፈር ወዳጅ የሚመርጡበትም ነው፡፡
የከንፈር ወዳጅ መምረጥ የፈለገች ልጃገረድ ከበው ከሚጨፍሩት ልጃገረዶች መሀል ገብታ ታዜማለች፡፡ ለጨዋታው የመጡ በሙሉ ለምለም አሪቲና ያልተላጠ ንፁህ ሎሚ ይዘው የሚመጡ ሲሆን፣ አርቲና ሎሚያቸውን እያሸተቱ ከንፈር ወዳጅ መረጣ ዙሪያቸውን ወደ ከበቡዋቸው ወጣት ወንዶች ያማትራሉ፡፡ ቀልባቸው ላረፈበት ወንድ ሎሚውን ይሰጣሉ፡፡
ሎሚና አሪቲ እንዲሰጣቸው የሚለምኑ ወንዶችም በርካታ ናቸው፡፡ ልመናቸውንም፡-
እባክሽ አየሁሽ
በላሁሽ
ከንፋስ የፈጠነ
ከውኃ የቀጠነ ፍቅር ይዞኛል
እቴ ጎንበስ አልኩልሽ፣ ቀጥ አድርጊኝ
በጀግና ሞት ነይ ውሰጅኝ ባክሽ
ክንዴም አልጠና
በጓያ ስንቅ ነው የመጣሁት
በሰንበሌጥ ምርኩስ ነኝ… አንሽኝ እያሉ ይለምናሉ፡፡
ብርሃኑ (ዶ/ር)፣ እንደሚሉት፣ ይህ ከፍተኛው ልመና ነው፡፡ ነገር ግን ሴቷ ቀልቧ ካላረፈበት እሺ አትለውም፣ ሎሚ አትሰጠውም፡፡
ሴቷ ያገባም ያላገባም ሰው ባለበት ሁኔታ መሀል ገብታ የከንፈር ወዳጇን በነፃነት በምትመርጥበት ባህላዊ ጭፈራ፣ እሷ የመረጠችው የከንፈር ወዳጅ እያለ፣ ሌላ እሷን የሚወድ ቢኖር ‹ወድጃታለሁ ከዚች ልጅ ጋር ማንም እንዳይጫወት› ይላል፡፡ በዚህ ጊዜ ቀድማ እሷ የመረጠችው ወንድ ‹ና ውረድ› ብሎ እወዳታለሁ ካለ ፍልሚያ እንዲገጥመው ይደረጋል፡፡ ተፋላሚው ነጠላው በበትር አድርጎ ይዞ ለመፋለም ባላንጣውን ይጋብዛል፡፡
ፍልሚያው የሚከናወነው አባ ሃጋ፣ አባ ሃይጤ የሚሏቸው ሽማግሌዎች ባሉበት ይከናወናል፡፡ ከፍልሚያው በፊት ግን ሽማግሌዎቹ ወንዶቹ ወጣቶች በንግግር እንደተማመኑ ዕድል ይሰጣሉ፡፡
ፍልሚያው ምንም ዓይነት ዱላ፣ ስለት ወይም ሌላ የሚጎዳ ነገር በሌበት በትግል ብቻ የሚከናወን ሲሆን፣ ቀድሞ መሬት የጣለ ወንድ ልጃገረዷን የከንፈር ወዳጅ ያደርጋል፡፡
ፍልሚያው ሲካሄድ ልጃገረዶች ከበው የሚመለከቱ ሲሆን፣ የከንፈር ወዳጅ የመረጠችው ደግሞ በሷ ምክንያት ወንዶች ትግል መግጠማቸውን ዓይታ ትኩራራለች፡፡ ይህ ለሷ ትልቅ ድል ነው፡፡ ጓደኞቿ ደግሞ
‹‹የቃልቻ ልጅ ናት ብላችሁ ስትሉ
ያረፋና የዒድ አስገደለች አሉ›› ብለው ያወድሷታል፡፡
አሸናፊው በሚወደስበት፣ ተሸናፊው በሚወቀስበት ትግል፣ ለአሸናፊው ልጃገረዶች፡-
አባቱ ሙቶ ያደገው በእናት
ድብ አዘልሎ ይወጋል በአናት
የሰማም ያውራ ያየም ይናገር
ሸከርካራ ነው እንደ ባድ ማገር እያሉ ያሞግሱታል፡፡
ለተሸናፊው ደግሞ፡-
‹‹አንተ ዝብጥብጥ ወግድ ከፊቴ
አቅረሸረሽከኝ መጣ ጥፋቴ
አዙሮ ይነፋል ወንፊት
ምን ያዘልቅሃል ከጀግኖቹ ፊት›› እያሉ ዝቅ ያደርጉታል፡፡
ልጃገረዷ የመጠረችው የከንፈር ወዳጅ ከተሸነፈ ምርጫዋ ትክክል እንዳልነበር ለመግለጽም
‹‹ያንችማ ወዳጅ የኮራሽበት
ወድቆ ቀረልሽ እንደ በሬ እበት
የበሬ እበት ያገለግላል ቢያፋፍሙበት እሳት ያውላል››
ብለው ለከንፈር ወዳጅነት የመረጠችው ከምንም የማይገባ እንደሆነ በዘፈን ይነግሯታል፡፡
አንድን ልጃገረድ ከምርጫዋ ውጭ በትግል ስላሸነፈ ብቻ መውሰድ አይቻልም፡፡ ተሸናፊው በምትሄድበት እየሄደ ተደጋጋሚ ሙከራ ያደርጋል፡፡ መንገድ ይጠብቃታል፡፡ ብትር ከፊቷ አጋድሞም በግጥም፡-
‹‹እንዳንቺ ያለ ልጅ እንዳንቺ የሚያምር
እንኳን እዚህና የለም በጎንደር
አይቆጡኝ እንደው አብሬሽ ልብረር›› ይላታል፡፡
ልጃገረዷ ከፈለገችው ብትሩን አንስታ ትሰጠዋለች፡፡ ይህ ማለት የከንፈር ወዳጅ እንዲሆን ፈቅዳለች፣ በትግል አሸንፎ የነበረውን ትታዋለች ማለት ነው፡፡ ካልፈለገችው ብትሩን ተራምዳ ትሄዳለች፡፡ በዚህ ጊዜ
እንዳተ ያለ ልጅ እንዳንተ የሚያምር
እንኳን ጎንደርና ሞልቶ በሀገር
ሌላ መች አጥቼ ካንተ ጋር ልብረር
ብላ እንደማትፈልገውም ትገጥምለታለች፡፡
ብርሃኑ (ዶ/ር) በአኾላሌ ዙሪያ ጥናት ሲያደርጉ ‹‹ፍችር›› የሚባል ግጥም እንዳለም አውቀዋል፡፡ ፍችር አስሮ የሚይዝ ግጥም ቢሆንም፣ መልስ የሚፈልግ ነው፡፡ በዚህ ግጥም የምትጠየቀውን ጥያቄ እሷ ካላወቀች፣ የመረጠችው የከንፈር ወዳጅም ለግጥሙ ምላሽ ካልሰጠ ይቀማል፡፡ ለምሳሌ
አራት መሬት ነካሽ
አንድ መነሳንስ
ሁለት ሰማይ ጠቀስ
ይህንን ካልፈታሽ
ባይንሽ አይመላለስ
ይላል የሚፈልጋት ወጣት የዚህን ትርጉም መፍታት ከቻለች ትፈታለች፣ ካልቻለች ለመረጠችው ከንፈር ወዳጅ ትሰጣለች፡፡
አራት መሬት ነካሽ – የበሬ እግር ነው
አንድ መነሳንስ – ጅራቱ
ሁለት ሰማይ ጠቀስ – ቀንዱ ነው፡፡ ይህንን መመለስ ከቻለች ወደምትፈልገው ወጣት ትሄዳለች፡፡ እሷ ካቃተት የከንፈር ወዳጇ ይሞክራል ሁለቱም ካቃታቸው እወድሻለሁ ወዳላት ወጣት ትሄዳለች፡፡
ልጃገረዷም የመጠየቅ መብት አላት፡፡ እሷ ጠይቃ የሚፈልጋት ወንድ ካልመለሰ ወደ ከንፈር ወዳጇ መሄድ ትችላለች፡፡
በአኾላሌ ባህላዊ ጨዋታ ላይ ልጃገረዷ የመረጠችው የከንፈር ወዳጅ ወይም እሷ የመረጠችውን በትግል አሸንፎ የሷ የከንፈር ወዳጅ የሆነ ወጣት ከከንፈር ወዳጅነት የዘለለ ግንኙነት ውስጥ እንዲገባ አይፈቀድለትም፡፡ የከንፈር ወዳጅነቱ የሚዘልቀውም እስከ ጋብቻ ድረስ ነው፡፡
ልጃገረዷ በአካባቢው ሕግ ደንብና ባህል መሠረት በትዳት ወይም ወንዱ ሲያገባ የከንፈር ወዳጅነታቸው ያከትማል፡፡ እነሱ በከንፈር ወዳጅነታቸው ጊዜ ከተፈቃቀዱና አብረው ለመኖር ከወሰኑ ደግሞ በደንቡ መሠረት ሽምግልና ተልኮ እንዲጋቡ ይደረጋል፡፡
ልጃገረዷ ከከንፈር ወዳጇ ጋር ቆይታ ሌላ ወንድ ስታገባም ልጃገረድ ሆና መገኘት አለባት፡፡ ሌላ ስታገባ ክብረ ንፅህናዋ ባይገኝ የከንፈር ወዳጇ ተጠያቂ ነው፡፡ በመሆኑም እንጨት ስትለቅምና ከብት ስታግድ እንዳትደፈር በቅርብ ርቀት እየጠበቃት ይኖራል፡፡ ዕድሜዋ ደርሶ ሌላ ሰው ብታገባም አይጣላም፣ አይረብሽም፡፡ ይህ የአኾላሌ ተውኔታዊ ጭፈራ መገለጫ ነው፡፡ ማኅበረሰቡም የኖረበትና ያደገበት ስለሆነ የከንፈር ወዳጅዋን በግድ ማግባት አለባት አይልም፡፡
አኾላሌ ከሐይቅ ከተማ ከ10 እስከ 17 ኪሎ ሜትር ላይ ባሉ ሰግለን፣ ቀቢሳና ጎድጓዲት በተባሉ ሦስት ቀበሌዎች በዋናነት ይከበራል፡፡ ባህሉ እስከ ወረባቦና ውጫሌ በተለይ ከሐይቅ ከተማ አፋር ድንበር ያለው ቆላማ አካባቢ ላይ በስፋት እንደሚከናወን ብርሃኑ (ዶ/ር) ነግረውናል፡፡
ይህን ባህል በስፋት ለማስተዋወቅ ደግሞ የዞኑ ባህልና ቱሪዝም፣ የወረዳው ባህልና ቱሪዝምና ወሎ ዩኒቨርሲቲ አንድ ላይ ሆነው የአኾላሌ ፌስቲቫልን በደሴ ከተማ ለሦስተኛ ጊዜ ማዘጋጀታቸውንም አክለዋል፡፡