Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአፍሪካ የሚቲዎሮሎጂ ቦርድ የአምስት ዓመታት ዕቅዱን ሊያቀርብ ነው

የአፍሪካ የሚቲዎሮሎጂ ቦርድ የአምስት ዓመታት ዕቅዱን ሊያቀርብ ነው

ቀን:

በኢትዮጵያ የሚገኘው የአፍሪካ የሚቲዎሮሎጂ ሥራ አመራር ቦርድ የሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ዕቅዱን ቀርጾ ለዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ሊያቀርብ መሆኑን አስታወቀ።

ከሦስት ዓመታት በፊት መቀመጫውን ኢትዮጵያ ያደረገው የአፍሪካ የሚቲዎሮሎጂ ሥራ አመራር ቦርድ ለሁለት ቀናት የቆየ ውይይት በአዲስ አበባ ያደረገ ሲሆን በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚኖሩትን ዕቅዶች በመቅረጽ ለዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት እንደሚያቀርብ የአፍሪካ ቀጣና ቢሮ ዳይሬክተር አሞስ ማካራው (ዶ/ር) ገልጸዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ቦርዱ በአጭር ጊዜና በረዥም ጊዜ በመክፈል ከፈረንጆቹ 2022 እስከ 2027 የሚኖሩትን ዕቅዶች ለዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት በማቅረብ ለአኅጉሪቱ አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎችን ይጠይቃል።

በሚቲዎሮሎጂ ዘርፍ የሚደረገውን ድጋፍ የተሻለ ለማድረግ ይቻል ዘንድ ከሁሉም አባል አገሮች መረጃዎችን በመሰብሰብ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። በሚቀርበው ዕቅድ መሠረትም ለሚቲዎሮሎጂ መረጃ መሰብሰብና መተንተን የሚረዱ መሣሪያዎችን ጨምሮ የተለያዩ የቴክኒክ ድጋፎችን ለማግኘት ያስችላል ብለዋል።  አፍሪካ እስካሁን ከዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት 110 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማግኘቷን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በበኩላቸው አፍሪካ 27 አገሮች ከተወከሉበት የዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ውስጥ ዘጠኝ መቀመጫ እንዳላት ገልጸው ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ የአፍሪካ የሥራ አመራር ቦርድ ቢሮ ኢትዮጵያ እንዲሆን መወሰኑ የአኅጉሪቱን ተሰሚነት ከፍ አድርጎታል ብለዋል። በተለይም የአፍሪካን የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የሚያስችል ድጋፍ ለማግኘት አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል። በጤና፣ አቬሽን፣ ግብርናና ሌሎችም ዘርፎች የሚያስፈልጉ የመረጃ መሰብሰብ፣ የጣቢያዎች ግንባታ፣ የመሠረተ ልማትና የመሣሪያ ድጋፍ ለማግኘት የአፍሪካ ድምፅ በአንድነት መሰማቱ ጠቃሚ ነውም ብለዋል። ከዚህ በፊት የአፍሪካ ቀጣና ቢሮ ጄኔቫ እንደነበር ገልጸው በተፈለገው ጊዜ ውይይት ለማድረግም ይሁን ውሳኔዎችን ለማሳለፍ አስቸጋሪ ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል።

በአኅጉሪቱ በሚቲዎሮሎጂ ዘርፍ ያሉ ፈተናዎችን በመለየትና በሚቀጥሉት ጊዜያት የሚሠሩ ሥራዎችን ለመለየት የመረጃ መሰብሰብ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸው በሚቀጥለው የድርጅቱ ስብሰባ እንደሚቀርብ አቶ ፈጠነ ገልጸዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...