Friday, December 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በቴሌ ብር አነስተኛ ብድሮችን ለማቅረብ ለብሔራዊ ባንክ ጥያቄ ቀረበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት ላይ ካዋለው አንድ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ቀናት በቀሩት የቴሌ ብር ሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት አነስተኛ ብድሮችን ለማቅረብ፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥያቄ እንዳቀረበ ተገለጸ፡፡

ኩባንያው በፋይናስ አገልግሎት ተደራሽ ያልሆነውን ኅብረተሰብ ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ ያስታወቁት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ፣ በቴሌ ብር በመደበኛነት እየቀረቡ ከሚገኙት አገልግሎቶች ባሻገር፣ አነስተኛ የብድርና ቁጠባ አገልግሎት ለመጀመር የብሔራዊ ባንክን ፈቃድ ተጠይቆ ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ለአገርና ለሕዝብ የሚያስገኘውን ፋይዳ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ተደርጎ መቅረቡን ያስታወቁት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣  በቴሌ ብር አማካይነት የሚሰጠውን የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ለማስፋት ለብሔራዊ ባንክ የቀረበው የፈቃድ ጥያቄ በቅርብ ጊዜ ምላሽ ያገኛል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በቴሌ ብር የሚያቀርበው አዲስ አገልግሎት ጥቃቅን ክፍያዎችን መፈጸም ብቻ ሳይሆን፣ ደንበኞች አነስተኛ ብድር ማግኘት ወይም መቆጠብ እንዲችሉ የሚያደርግ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም በመደበኛ የባንክ አገልግሎት ተደራሽ ያልሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለማገልገል እንደሚያግዝ ተነግሯል፡፡

ቴሌ ብር ይፋ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ 17.5 ሚሊዮን የሚደርሱ ደንበኞችን እንዳፈራ፣ 56.7 ሚሊዮን የሚደርሱ የገንዘብ ዝውውሮች ተፈጽመውበት 12.8 ቢሊዮን ብር እስከ ተጠናቀቀው ሳምንት አጋማሽ እንደተንቀሳቀሰበት ተጠቁሟል፡፡

በአገልግሎቱ የተመዘገበው አበረታች ውጤት የተለያየ ውጣ ውረዶችን በመቋቋም የተገኘ እንደሆነ የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ ከዚህም ውስጥ በአገሪቱ ውስጥ ከዓመት በላይ የቆየው ጦርነት አንደኛው ነው ብለዋል፡፡ በጦርነቱ ሳቢያ ብሔራዊ ባንክ በቀን ውስጥ የሚደረገውን የዲጂታል የገንዘብ ማስተላለፊ ገደብ ማውጣቱን ያስታወሱት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ በዚህም በአገልግሎቱ ሲዘዋወር የቆየው ገንዘብ በጣም ዝቅተኛ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ የገንዘብ ዝውውር ገደቡ እንደተነሳ አስታውሰው፣ ይህንን መሠረት በማድረግ ኩባንያው ከአንጋፋው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር  በቴሌ ብር አማካይነት የአየር ትኬት ለሽያጭ እንዲቀርብ የሚያስችል ስምምነት ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

በተጠናቀቀው ሳምንት አጋማሽ አገልግሎቱን መስጠት የሚያስችላቸውን ስምምነት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቺፍ ኮሜርሻል ኦፊሰር አቶ ለማ ያዴቻና የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት በተገኙበት በስካይላይት ሆቴል ተፈራርመዋል፡፡

አቶ ለማ በስምምነቱ ወቅት እንደተናገሩት፣ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የተደረገው የስምምነት አገልግሎት የአየር መንገዱ የአገር ውስጥ ደንበኞችን የክፍያ አማራጭ እንዲሰፋ የሚያደርግ ነው፡፡

የአገር ውስጥ በረራ አገልግሎት ደንበኞች ትኬታቸውን በዲጂታል መንገድ እንደሚቆርጡ የተናገሩት አቶ ለማ፣ ኢትዮ ቴሌኮም ወደ ሥራ ያስገባው የቴሌ ብር አገልግሎት ቀልጣፋና አስተማማኝነት ያለው በመሆኑ በተለይም የአገር ውስጥ ደንበኞችን ፍላጎት እንደሚያሟላ ገልጸዋል፡፡

እስከ 30 ሺሕ ብር የሚያወጣ የአየር ትኬት በቀጥታ በቴሌ ብር መግዛት እንደሚቻል የተገለጸ ሲሆን፣ ይህ የገንዘብ መጠን አየር መንገድ ወደ ዱባይ፣ ሳዑዲ ዓረቢያና የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ትኬት ሊሸጥ የሚችልበት ዋጋ ድረስ መቁረጥ የሚያስችል ነው፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአገር ውስጥ በአራቱም አቅጣጫዎች 22  መዳረሻዎች እንዳሉት የተገለጸ ሲሆን፣ በቀን 6,900 እንዲሁም በዓመት ከ2.5 ሚሊዮን በላይ የአገር ውስጥ መንገደኞች እንደሚያጓጉዝ ተነግሯል፡፡ በቴሌ ብር የሚቀርበው አገልግሎት እነዚህ ደንበኞች በቀላሉ የሞባይል ስልካቸውን በመጠቀም ትኬት መቁረጥ  የሚያስችላቸው እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

ለአብነትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሙከራ ደረጃ በቴሌ ብር የአገር ውስጥ ትኬት ክፍያን ከጀመረበት ከየካቲት 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ፣ 6.67 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የአገር ውስጥ የበረራ ትኬቶችን በቴሌ ብር አማካይነት መሸጥ እንዳስቻለው አስታውሷል፡፡

የቴሌ ብር አገልግሎት የትራፊክ ደንብ መተላለፍ ቅጣትን ጨምሮ ከ52 በላይ የቀጥታ ግብይትን (Online Merchandise) ከሚያከናውኑ፣ ወርኃዊ የአገልግሎት ክፍያን በቴሌ ብር ከሚቀበሉና ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን ከሚሰጡ አጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ እየሠራ ይገኛል፡፡ በቅርቡም ከሃያ በላይ ከሚሆኑ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር የአገልግሎት ክፍያን በቴሌ ብር መፈጸም የሚያስችል ስምምነት ለማድረግ ኩባንያው በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች