Friday, September 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ እሳት የሆነ ኑሮ ውድነት ሲገጥመን፣ በሐሳብ ወደ ኋላ እየሄድን ሕይወታችንን በወፍ በረር እንቃኘዋለን፡፡ የበዓል ሰሞን ነውና በተለይ ከፋሲካ በዓል ጋር የተያያዘ ገጠመኜን ልንገራችሁ፡፡ የዛሬ 12 ዓመት ከጓደኛዬ ጋር ቢሮ ውስጥ ስለበዓሉ ወጪዎቻችን እየተነጋገርን ነበር፡፡ ከጓደኛዬ ጋር ላነሳነው ወሬ ምክንያት የሆነን በተደጋጋሚ በሞባይል ስልኩ ላይ እየተደወለለት ፋታ ማጣቱ ነው፡፡ ለካ ጓደኛዬ በመኖሪያ አካባቢው የበሬ ዕርድ መዋጮ ገንዘብ ሰብሳቢ ነው፡፡ እሱ እንደነገረኝ ሁለት በሬዎች ለማረድ 16 ሰዎች መዝግቦ ጨርሷል፡፡ ነገር ግን በወቅቱ ያልተመዘገቡ ሰዎች ነበሩና በየደቂቃው ልዩነት እየደወሉ ያስቸግሩታል፡፡

እሱ በዚያን ወቅት አንድ በሬ ለስምንት ሰዎች ለማካፈል ይመዘግብ የነበረው በነፍስ ወከፍ 800 ብር እየተቀበለ ነበር፡፡ ልብ በሉ፡፡ እሱ እንደሚለው ከሁለት ዓመት በፊት ለአንድ ሰው ምዝገባ የሚያስፈልገው 500 ብር ብቻ ነበር፡፡ በመዋጮና በቅርጫ የረጂም ዓመታት ልምድ ያለው ይኼው ጓደኛዬ፣ ‹‹በደህናው ጊዜማ 200 ብር አዋጥተን ምን የመሰለ በሬ አርደን ተካፍለናል…›› ያለኝ አይረሳኝም፡፡

እኔ ከነበርኩበት መሥሪያ ቤት ለቅቄ የራሴን ሥራ በመጀመሬ ምክንያት እንደ በፊቱ ከጓደኛዬ ጋር በየቀኑ ባንገናኝም፣ አሁንም ድረስ በጣም ስለምንቀራረብ በሳምንት አንዴ እንገናኛለን፡፡ በቀደም ዕለት ተገናኝተን ቢራችንን እየጠጣን ስናወራ የሞባይል ስልኩ ጮኸ፡፡ አንስቶ መነጋገር ሲጀምር ያው የተለመደው የዕርድ መዋጮ ነው፡፡ ‹‹አዎን ምዝገባ ተጀምሯል፡፡ ፈጠን ካላልክ ለሌላ ሰው ዕድሉ ይሰጣል፡፡ ስለዚህ ሰባት ሺሕ ብር ይዘህ ነገ ወይም ተነገ ወዲያ እንድትመጣ…›› ሲል የዛሬ 12 ዓመቱ ወጋችን ትዝ አለኝ፡፡

‹‹እንዴ ብላችሁ ብላችሁ የበሬ መዋጮ ሰባት ሺሕ ብር አስገባችሁ እንዴ?›› ስለው እያሾፍኩ፣ ‹‹ኧረ ተወኝ እባክህ፣ ይኼም ለመነሻ ያህል ነው እንጂ ሊያስጨምር ይችላል…›› ሲለኝ ገረመኝ፡፡ እርግጥ ነው በአገሪቱ ውስጥ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ እንኳን ከዓመታት በፊት ከቀናት በፊት የነበረ የገበያ ሁኔታ ባለበት እንደማይገኝ እንግባባለን፡፡ ነገር ግን ኑሮን በተመለከተ ብዙዎቻችን የትናንቱን ከዛሬው ጋር ማነፃፀራችን የተለመደ ነው፡፡ አንዳንዴ ከመጠን ያለፈ ግነት የምናይባቸው ምርቶችና አገልግሎቶች ግን ከማሳሰብ አልፈው ናላችንን ያዞሩታል፡፡ በሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት ምክንያት ብቻ ትናንትን እንድንናፍቅ የሚያደርጉ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡

ለምሳሌ በጣም የምትቀርቧቸውን የምግብ ቤት ባለቤቶችን ስለሚያገኙት ጥቅም ስታነጋግሯቸው፣ እንደ ምግብ የሚያዋጣ ቢዝነስ እንደሌለ ትረዳላችሁ፡፡ አንድ የማውቀው ባለምግብ ቤት እንደነገረኝ በአሁኑ ወቅት ጣጣውን ጨርሶ በ200 ብር የሚሸጥ የፆም በየዓይነቱ ምግብ ወጪው 65 ብር ብቻ ነው፡፡ ይህ የምግብ ግብዓቶችን፣ ማገዶን፣ የሰው ጉልበትና ሌሎች ተዛማጅ ወጪዎችን ችሎ ነው፡፡ በ600 ብር የሚሸጥ ክትፎ ጠቅላላ ወጪው ከ100 ብር አይበልጥም፡፡ ከአንድ ምግብ በትንሹ ከእጥፍ በላይ፣ ከፍ ሲልም ከሦስትና ከአራት እጥፍ በላይ የተጣራ ትርፍ እየተገኘ በአርቲፊሻል የዋጋ ንረት እንመታለን፡፡

ወደ በዓሉ ወግ ልመልሳችሁና፣ ‹‹እኔ ድሮ ልጅ ሆኜ ትልቅ የበግ ሙክት በሦስት ብር ተገዝቶ ቆዳው በሁለት ብር ሲሸጥ፣ በአንድ ብር ሙሉ ቤተሰብ በሙክት ሥጋ በዓሉን ተንደላቆ ያሳልፍ ነበር…›› ብለው የነገሩኝ አንድ ጎረቤቴ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ አሥር ዓመት ሞልቶአቸዋል፡፡ እሳቸው ይህንን የነገሩኝ አንድ እኔ ነኝ ያለ ሙክት 800 ብር አውጥቷል መባሉን ሰምተው ነበር፡፡ ‹‹ወይ ጊዜ! እኔ የማዝነው ለዚህ ትውልድ ነው…›› እያሉ የተመረሩት አይረሳኝም፡፡ አፈር መስኮት የለውም እንጂ የዘመኑ ሰው ያውም ደልቀቅ ያለው ከአሥር ሺሕ ብር በላይ አውጥቶ የፍየል ሙክት ሲገዛ ቢያዩ ምን ይሉ ነበር? አንድ ኪሎ ጥሬ ሥጋ አንድ ሺሕ ብር የሚሸጥበት ዘመን ላይ መድረሳችንን ቢያዩ ምንኛ ይደነቁ ነበር?

ወደ ጓደኛዬ ልመልሳችሁ፣ ‹‹ለመሆኑ አሁንም ሁለት በሬ ነው የምታርዱት?›› ብዬ የድሮውን እያስታወስኩ ጥያቄ ሳቀርብለት፣ ‹‹ኧረ አሁንማ አራት በሬ ደርሰናል…›› አለኝ፡፡ ‹‹አንድ መደብ ሰባት ሺሕ ብር እያወጣ ሰው እንዴት ይችላል?›› ስለው የሚያስገርም መልስ ሰጠኝ፡፡ ‹‹እሱማ ልክ ነህ ይከብዳል፡፡ ነገር ግን አንዱን መደብ እኮ ብዙዎቹ ለአራት ነው የሚካፈሉት…›› ሲለኝ፣ ‹‹ተመሥገን›› ከማለት ውጪ የምለው አልነበረኝም፡፡ ይህንንም በምሬት አንድ መደብ እንዴት ለአራት ሰዎች ተካፍሎ በዓል ይዋላል ብለን ብናጉረመርም ጥቅም የለውም፡፡ ምክንያቱም ‹‹ከነገ ዛሬ ይሻላል›› አይደል የሚባለው? አሁንም ተመሥገን እንበል፡፡ ምክንያቱም ከዛሬ ትናንት፣ ከነገ ደግሞ ዛሬ እየተሻለ ነውና፡፡

(ማስረሻ ድንቁ፣ ከአየር ጤና)  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...