Thursday, May 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የዋጋ ንረቱ በቁጥርም በተግባርም እየኖረብን ነው

እንደተለመደው የማዕከላዊ ስታትስቲክ አገልግሎት የመጋቢት 2014 ዓ.ም. የዋጋ ንረት ደረሰበት ያለውን መረጃ ይፋ አድርጓል፡፡ ገበያውን ተመልክቶ ደምሮና ቀንሶ የመጋቢት ወር የምግብ ነክ ምርቶች የዋጋ ንረት ከቀደመው ዓመት ተመሳሳይ ወቅትጋር ሲነፃፀር በ43.4 በመቶ ዕድገት አሳይቷል ብሏል፡፡

ካለፈው ወር አንፃር ደግሞ በ1.5 በመቶ አካባቢ ከፍ ማለቱን እወቁልኝ የሚል መረጃ ሰጥቷል፡፡ እንዲህ ያለውን በአኃዝ የተደገፈ የዋጋ ንረት መስማት ከጀመርን ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ለነገሩ ልብ በሉ የምግብ ዋጋ ግሽበት በዚህን ያህል ቀነሰ የሚል መረጃ የሰማንበትን ጊዜ ማስታወስ አንችልም፣ ጨመረ እንጂ ቀነሳ የሚል ዜና ብርቃችን ሆኗል፡፡ ሥራው ሆኖ መረጃውን ወር እየጠበቀ ይንገረን እንጂ፣ ከእነርሱ በላይ እኛ ከዋጋ ንረቱ ጋር አብረን እየኖርን ያለነው ሸማቾች በደንብ እናውቀዋለን፡፡

ኤጀንሲው ከሚነግረን በላይ የዋጋ ንረቱ እንዴት እያጎበጠን እንደሆነና እርሱ በቁጥር እኛ በተግባር እየኖርነው ነው፡፡ እንዲያውም ኤጀንሲው የኑሯችንን ክብደት በቁጥር ከሚያስቀምጠው በላይ ሆኖብናል፡፡፡ እርሱ የሚነግረን የዋጋ ንረቱን የአንዱን ወር ከአንዱ እያመዛዘነ በመቶኛ ሲሰላ ጭማሪው ይህንን ያህል ሆነ የሚለውን መረጃ ነው፡፡ ነገር ግን እንዲህ በቁጥር የሚገለጹ ትንታኔዎች ክፋት ባይኖራችም፣ አሁን ላይ ያለንበት ሁኔታ ድርጅቱ በአኃዝ ካስቀመጠው በላይ መሆኑን ግን እንደ ሸማች መግለጽ ይኖርብናል፡፡

የኢትዮጵያ የዋጋ ንረት በዓለም ላይ ከፍተኛ ከሚባሉ መካከል አንዱ መሆን ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በየጊዜው ያለ ማቋረጥ እየጨመረ የመጣው የኑሮ ውድነት በየወሩ በአኃዝ ከሚገለጸው በላይ ነው ለማለት የሚያስደፍረንም ከ15 እና ከ20 ዓመት በላይ ያለማቋረጥ ዋጋ ሲጫንብን በመቆየቱ ነው፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያ በዋጋ ንረት ስትነረት ከመቆየቷ አንፃር የምግብ ዋጋ ንረቱ 43 በመቶ ደረሰ ተብሎ የሚገለጽ ብቻ አይደለም፡፡

የመጋቢት ኑሮህ ከቀዳሚ ወር አንፃር ሲታሰብ 1.5 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ‹‹ዋጋ ጨመረብህ›› የሚባል ሸማች መረጃውን እንደ ቀልድ ቢመለከት አይፈረድበትም፡፡ ምክንያቱም አሁን በገበያ ውስጥ የምናየው የሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ ጠዋት ተጠይቆ ከሰዓት አጀብ የሚያስብል ጭማሪ እየታየበት በመሆኑ ነው፡፡ ሁላችንም በሚገባን መልኩ የዋጋ ንረቱን አስከፊነት ለመገንዘብ ደግሞ በአንድ ዓመት ወይም በወራት መካከል የታየውን ጭማሪ ብቻ በመግለጽ የምንለካው አይደለም፡፡ ችግሩ ሥር የሰደደ ለዓመታት ሳይገታ የቀጠለ በመሆኑ ዛሬ የደረስንበትን የዋጋ ንረት ከአምስት ወይም ከአሥር ዓመታት በፊት ከነበረው ጋር ካመዛዘንነው ከሁለት ዲጂት አልፎ ወደ ሦስት ዲጂት የተሻገረውን የዋጋ ንረት የተሸከምን መሆናችን በግልጽ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

 የአምስት ሊትር የዘይት ዋጋ ከአንድ ሁለት ዓመታት በፊት ካለው ጋር ብናነፃፅር የዋጋ ንረቱ በትንሹ አምስት እጥፍ ደርሷል፡፡ ሌሎች ገበያ ውስጥ ያሉ መሠረታዊ የሚባሉ ሸቀጣ ሸቀጦች አሁን ላይ በትንሹ በሦስትና በአራት እጅ ጨምረዋል፡፡ ስለዚህ የዋጋ ንረቱ በ43 በመቶ ብቻ አደገ ብሎ መግለጽ ከኢኮኖሚያዊ ትንታኔ አንፃር ልክ ሊሆን ቢችልም፣ ገቢው ምንም ካልጨመረ ለሸማቹ አንፃር መረጃው አይገልጸውም፡፡ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት የታየው የዋጋ ዕድገት ምናልባትም በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ያልታየ ከመሆኑ አንፃር ሸማቾች ወይም ደመወዝተኛው በአስማት እየኖሩ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

ወቅታዊውን የዋጋ ንረት ከሌላው ጊዜ የተለየ የሚያደርገው ደግሞ ቀድሞ የዋጋ ንረት የሚታይባቸው ምርቶች የተወሰኑ መሆናቸውና አሁን ላይ ሁሉንም ማካተቱ ነው፡፡ አሁን ላይ ከውጭም መጣ በአገር ውስጥም ተመረተ የሸቀጦች ዋጋ ሳያቋርጥ እየጨመረ ነው፡፡ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ሥር በሰደደባት አገር ውስጥ ነንና በምንም ሁኔታ ዋጋ ጭማሪ ሊመለከታቸው የማይችሉ ወይም ዋጋቸው ይጨምር ቢባል እንኳን አነስተኛ መሆን የነበረባቸው ምርቶች ሁሉ ከሌሎች ጋር እንዲመሳሰሉ ዋጋቸው ይሰቀላል፡፡

ስለዚህ ለተከታታይ ዓመታት ያየነው የዋጋ ንረት በአኃዝ ከሚገጸው በላይ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ሕዝብ የተጠራቀመውን የዋጋ ንረት ሊቋቋም ያልቻለው ደግሞ፣ በተለይ ደመወዝተኛ ገቢው ባለበት ቆሞ የሸቀጦች ዋጋ በርቀት እየቀደሙት በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ሳያንስ በግብይት ውስጥ ያለው ሸፍጥ ችግሩን አብሶበታል፡፡ ልክ የሌለው ትርፍ የለመዱ ነጋዴዎች ከሕግ በላይ ሆነው እንዳሻቸው ሲሆኑ ሃይ አለመባለቸው ሸማቹን እያደማ ነው፡፡ የባንኮች የብድር ወለድ መጠን እንደፈለገው ሲለጠጥ ሸማች ላይ ሊያኖር የሚችለው ጉዳት የትየለሌ ነው፡፡ ይህንን አለመረዳት የችግሩ አካል መሆኑ ነው፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ የዚህ አገር ትልቅ ችግር ሆኖ የሚገለጸው አሁን ላለው የዋጋ ንረትና መረን የለቀቀ የገበያ ሥርዓት መንሠራፋት ሕጋዊ ዕርምጃ ሽባ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ያላግባብ ዋጋቸውን የሚጨምሩ ምርቶች ገበያውን ይዘው ሸማቹንና ተጠቃሚውን እያማረሩ እንዲቀጥሉ አድርጓል፡፡ ለዚህ አንድ ምሳሌ ላንሳ ሰሞኑን ሲሚንቶ እንደገና ዋጋው ተሰቀለ፡፡ አንድ ኩንታል ሲሚንቶ ከአንድ ሺሕ ብር በላይ መሸጥ ተጀመረ፡፡ ከሲሚንቶ አምራቾች አንዱ የሆነው ደረባ ሲሚንቶ ምርታችሁ አንድ ሺሕ ብር እየተሸጠ ነው ተብሎ ሲጠየቅ፣ ‹‹እኔ 24 ብር ብቻ ጨምሬያለሁ፣ የፋብሪካ ዋጋዬም 400 ብር ነው፤›› ብሎ ተናገረ፡፡ በፋብሪካ ዋጋውና በችርቻሮ መሸጫ ዋጋው መካከል 600 ብር ልዩነት ታየ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ለምን ሆነ የሚል መንግሥት አለመኖሩ እየጎዳን ነው፡፡  

ስለዚህ እንዲህ ያሉ ክፍተቶችን ከሥር ከሥር እያረምንና እያስተካከልን ባለመሄዳችን እነሆ ግልጽ ዘርፉ እንዲንሠራፋ ምክንያት ሊሆን ችሏል፡፡ የዋጋ ንረቱ ነገ ከነገ ወዲያም ላለመቀጠሉ እርግጠኛ መሆን አንችልም የምንለው ለዚህ ነው፡፡ ጭራሹን የዋጋ ንረቱን ሊያብሱ የሚችሉ ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ኖረው፣ እንዲሁም በሰበብ አስባቡ ያልተገባ ዋጋ ጭማሪ የሚወደውን ገበያ የበለጠ አጋግሎታል፡፡ አንዴ የተሰቀለው ዋጋ ሲወርድ አይታይም ከሚለው ምልከታ አንፃር ደግሞ ሰሞኑን በበዓል ሰበብ የሚደረግ ጭማሪ ከበዓሉም በኋላ ይዞብን የሚመጣውን ጣጣ ሳስብ ደግሞ በዚህች አገር የገበያ ሥርዓት፣ እንዲሁም ሸማቹን ለመታደግ ባልቻለው መንግሥት የበለጠ እንድናዝን ያደርገናል፡፡ መልካም በዓል!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት