Monday, March 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የመንግሥት ተቋማት በግል ባንኮች የከፈቷቸውን ሒሳቦች እንዲዘጉ መታዘዛቸው የፈጠረው ቅሬታ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመንግሥት ባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች በግል ባንኮች የከፈቷቸውን አካውንቶች እንዲዘጉ ገንዘብ ሚኒስቴር ትዕዛዝ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ አካውንት ለመክፈት ያሰቡ ሌሎች የመንግሥት ተቋማት ካሉም ከዚህ አድራጎታቸው እንዲቆጠቡ አሳስቧል፡፡ በገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የተጻፈው ይህ ደብዳቤ፣ በግል ባንኮች አካውንት የከፈቱ የመንግሥት ባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች አካውንቶቹን ተዘግተው በአስቸኳይ ሪፖርት እንዲያደርጉ፣ ይህንን ካላደረጉ ግን ሚኒስቴሩ ዕርምጃ እንደሚወስድ አሳስበዋል። 

ሚኒስቴሩ ይህንን ዕርምጃ የወሰደው በመንግሥት የፋይናንስ አስተዳደር ሕግና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ መሠረት ብሔራዊ ባንክ ከሚወክለው ባንክ ውጪ የመንግሥት ገንዘብ የሚንቀሳቀስበት አካውንት መክፈት የተከለከተ ተግባር መሆኑን በመግለጽ ጭምር ነው፡፡ ይህ የገንዘብ ሚኒስቴር ትዕዛዝ ግን በግል ባንኮች አካባቢ ቅሬታን ፈጥሯል። የመርህ ጥያቄ እያስነሳም ይገኛል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የገንዘብ ሚኒስቴር ሰሞናዊ ዕርምጃ ተገቢ አይደለም በሚል፣ ሁሉንም ባንኮች በአባልነት በያዘው በኢትዮጵያ በባንኮች ማኅበር በኩል አጀንዳ ተይዞ እንዲመከርበት ያስገደደ ጉዳይ ጭምር እስከመሆን ደርሷል፡፡  

ከኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ያገኘነው መረጃም ይህንኑ የሚያመለክት ሲሆን፣ ባንኮች በዚህ የገንዘብ ሚኒስቴር ውሳኔ ላይ አቋም በመያዝ በጉዳዩ ላይ የደረሱበትን ውሳኔ ለማሳወቅ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው ዓለሙ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባለ በጀት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በግል ባንኮች ያላቸውን አካውንት እንዲዘጉ የገንዘብ ሚኒስቴር ያስተላለፈው ትዕዛዝ በባንኮች ማኅበር አባላት ዘንድ ጥያቄ በመፍጠሩ ማኅበሩ በጉዳዩ ላይ አጀንዳ ይዞ ተወያይቶበታል፡፡ በተላለፈው ትዕዛዝ ላይ ማኅበሩ የያዘውን አቋም ለማሳወቅና ለገንዘብ ሚኒስቴር አቤት ለማለት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹በዚህ አጀንዳ ላይ በመወያየት በአቋም ደረጃ የመርህ ጉዳይን አስቀድመናል፡፡ ይህም በመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን ደረጃ የመንግሥት ተቋማት በግል ባንኮች ያላቸውን ሒሳብ እንዲዘጉ መግለጫ ሲወጣ በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚፈጥረው ስሜት የተዛባ ሊሆን ስለሚችል ይህ ሁኔታ እንዲስተካከል እንፈልጋለን፤›› ሲሉ አቶ አስፋው ገልጸዋል፡፡ 

ከዚህም ሌላ የግል ባንኮች ለዚህ አገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ከመሆኑ አንፃር ከመንግሥት በኩል እነዚህን ባንኮች የሚመለከት ውሳኔ ሲተላለፍና መግለጫ ሲወጣ በተሳሳተ መንገድ ትርጉም እንዳይሰጥ ጥንቃቄ መውሰድ እንዳለበት በውይይቱ አቋም የተያዘበት ሌላው ነጥብ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሰሞኑን በገንዘብ ሚኒስቴር የተላለፈውን ትዕዛዝ የተገለጸበት መንገድ የተሳሳተ ትርጉም የሚሰጥ መሆኑን የገለጹት አቶ አስፋው፣ ይህ ዓይነቱ አካሄድ መታረም እንደሚገባው በባንኮች ማኅበር አባላት መግባባት ላይ መድረሱን አመልክተዋል፡፡ 

‹‹የመንግሥት ባለ በጀት ተቋማት የሚገለው አገላለጽ በመንግሥት በጀት የምትተዳደሩ የሚል የተሳሳተ ትርጓሜን የሚፈጥር በመሆኑ፣ ትዕዛዙ የማይመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት በሙሉ በግል ባንኮች የከፈቷቸውን አካውንቶች ማዞር አለብን ወደሚል ዕሳቤ የሚከት ስለሚሆን ለገንዘብ ሚኒስቴር ተገቢውን ምላሽ መስጠት ይኖርብናል የሚል ስምምነት ላይ ደርሰናል፤›› ብለዋል።

የተጣሰ መመርያና ሕግ እንኳን ቢኖር ሚኒስቴሩ እንዲህ ያለውን ደብዳቤ ማውጣቱ ተገቢ አይደለም የሚል አቋም በባንኳች ማኅበር መያዙን የገለጹት አቶ አስፋው፣ እንዲህ ዓይነት አካሄዶች ወደፊት ጉዳት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ በመግባባት በዚሁ ዕሳቤ መሠረት ለገንዘብ ሚኒስቴር አቤቱታቸውን እንደሚያስገቡ አመልክተዋል፡፡ 

የባንኮች ማኅበር አጀንዳ አድርጎ በመከረበት በዚህ አጀንዳ ላይ የማኅበሩ አባል የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አለመገኘቱን ሪፖርተር ለማወቅ ችሏል።

‹‹የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋነኛ የመንግሥት አበዳሪ እኔ ሆኜ ሳለ፣ ሒሳባቸውን በባንኩ የሚያስቀምጡ የመንግሥት ድርጅቶች ግን የተወሰኑ ናቸው። ይህ ደግሞ ተገቢ አይደለም። ካልሆነ ግን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የወደቀውን ለመንግሥት ብድር የማቅረብ ሸክም የግል ባንኮችም ሊጋሩት ይገባል፤›› የሚል አቋም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል እየተራመደ መሆኑን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል።

ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ባንኮች በበኩላቸው፣ ‹‹ከግል ባንክ ያለህን ሒሳብ ዘግተህ ወደ እዚህ አምጣ›› የሚለው የንግድ ባንክም ሆነ የመንግሥት አስተሳሰብ ተገቢ አለመሆኑን ይገልጻሉ።

የተሳሳተ ነገር ቢገኝ እንኳን እንዲህ ባለው መንገድ መገለጽ ባንኮችን የሚጎዳ እንደሆነ የሚገልጹት አቶ አስፋው፣ አግላይነት ያለው አሠራር ተገቢ ባለመሆኑ፣ ሰሞኑን የተፈጠረውን ሁኔታ መነሻ በማድረግ ተጨማሪ ጥያቄዎችንም አያይዘው ለመንግሥት እንደሚያቀርቡ ጠቁመዋል። ሰሞኑን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተላለፈው መመርያ ብዥታ ያለው በመሆኑም ይህ እንዲጣራ ፍላጎት እንዳላቸውም አቶ አስፋው አስረድተዋል፡፡  

የመንግሥት ባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች ገንዘባቸውን ማንቀሳቀስ የሚችሉት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወይም በብሔራዊ ባንክ ውክልና በተሰጠው ባንክ ብቻ እንደሆነ የመንግሥት የፋይናንስ አስተዳደር ሕጉ ይደነግጋል፡፡ ሕጉ ይህን ቢልም ሰሞኑን የወጣው መመርያ ግን ‹የትኛው አካውንት ነው የሚዘጋው› የሚለውን በግልጽ አለማስቀመጡ ትልቁ ችግር መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ አቶ አስፋውም፣ ‹‹ምን ዓይነት ሒሳብ ነው የሚዘጋው የሚለው ያልተለየ በመሆኑ፣ ገንዘብ ሚኒስቴር ያስተላለፈው ትዕዛዝ ብዥታን የሚፈጥር ነው። ስለሆነም መጥራት አለበት፤›› ብለዋል።

እንደ ምሳሌ የጠቀሱትም ዩኒቨርሲቲዎችን ነው፡፡ ‹‹ዩኒቨርሲቲዎች ከመንግሥት የሚሰጣቸው በጀት አለ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በራሳቸው ሪሰርች ፈንድ ብለው አፈላልገው የሚያመጡት አለ፡፡ አንዳንዴ ደግሞ አንዳንድ የመንግሥት ድርጅቶች በራሳቸው እንቅስቃሴ የሚያመጧቸውን ፈንዶችም ስላሉ እንዲህ ባለ መንገድ የተከፈቱ አካውንቶችን ይመለከታል ወይስ አይመለከትም የሚለውን አልለየም፡፡ ስለዚህ ይህም ማብራሪያ የሚፈልግ በመሆኑ የጥያቄያችን አንድ አካል ሆኖ ይቀርባል፤›› ብለዋል።

ጉዳዩን የመርህ ጉዳይ አድርገው የተነሱበት ሌላው ነጥብ፣ አንዳንዴ ለመንግሥት ሥራ የሚከፈቱ አካውንቶች በመኖራቸው የገንዘብ ሚኒስቴር ትዕዛዝ እንዲህ ያሉ አካውንቶችን እንዴት መስተናገድ አለባቸው የሚለውን ጥያቄ የሚያስነሳ ጭምር በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ የገንዘብ ሚኒስቴር ያስተላለፈው ትዕዛዝ ግልጽ እንዲሆን የባንኮች ማኅበር ይፈልጋል ተብሏል፡፡  

በገንዘብ ሚኒስቴር የወጣው ትዕዛዝ አሻሚ ትርጉም ይዞ እንዲወጣ ተፈልጎ እንዳልነበር ሌሎች የሪፖርተር ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ የነበረው ሐሳብ በጀት ከመንግሥት የሚያገኙ የመንግሥት ተቋማት ገንዘባቸውን በግል ባንክ የሚያስቀምጡ ከሆነ ትክክል አይደለም የሚል እንደነበር ምንጮቹ ይገልጻሉ። ምክንያቱ ደግሞ መንግሥት በጀት ሲይዝ የአገር ውስጥ ብድርን ታሳቢ አድርጎ እንደሆነ፣ ይህ ብድር የሚገኘውም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመሆኑ ከዚህ ባንክ የሚገኝ ብድር በበጀት መልክ ለመንግሥት ባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች ተላልፎ መሥሪያ ቤቶቹ ሒሳባቸውን በግል ባንኮች መክፈታቸው ትክልል አይደለም ነው።

ነገር ግን ባለ በጀት ያልሆነ የመንግሥት ድርጅት አካውንት ከከፈተበት ከየትኛውም ባንክ ብድር ማግኘት የሚችል እስከሆነና ባንኩም ብድር የሚሰጥ እስከሆነ ድረስ አካውንት ዝጉ ማለቱ ትክክል እንደማይሆን አስተያየት ሰጪዎች ይገልጻሉ፡፡

አቶ አስፋውም በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ። ‹‹ገንዘብ ከዚህ ወስደው ሌላ ቦታ እያስቀመጡ እንደገና ደግሞ ንግድ ባንክ አነስተኛ የብድር ወለድ ስላለው እርሱ እንዲያበድራቸው መፈለግ አግባብ ላይሆን ይችላል፡፡ አንድ የመንግሥት ተቋም እኔ የምሠራው ከግል ባንክ ጋር ነው፡፡ ብሬን በግል ባንክ ባስቀምጥ የተሻለ ወለድ ስለሚከፍለኝ አድቫንቴጅ አለኝ፣ ወይም ለሠራተኞቼ የተሻለ የብድር ፋሲሊቲ ያመቻችልኛል ብሎ ካሰበ ግን የከፈተው አካውንት ሊዘጋ አይገባም፤›› ብለዋል።

የባንኮች ማኅበር ለገንዘብ ሚኒስቴር ያቀርባል ተብሎ ከለያቸው ነጥቦች መካከል አንዱ ይህ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ነጥቦች ይቀርቡበታል የተባለው የባንኮቹ አቤቱታ መቋጫ ግን፣ ከመንግሥት ፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ ጋር ተያይዞ በተለይ የመንግሥት ተቋማት ገንዘባቸውን በየትኛው ባንክ ማንቀሳቀስ አለባቸው የሚለው ድንጋጌ እንዲሻሻል የሚጠይቅ ጭምር እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

በተጨማሪም የግልና የመንግሥት የሚል አገላለጽ በገበያ ላይ ፍትሐዊ ውድድር እንዳይኖር የሚያደርግ በመሆኑ፣ ይህንን ጨምሮ መሰል አሠራሮችም ከዚሁ ጋር እንዲታዩ ፍላጎት መኖሩ ተገልጿል፡፡ ‹‹በተለያዩ አሠራሮች  ንግድ ባንክ ብቻ የሚለው አተረጓጎም ችግር እያመጣ ነው፤›› ያሉት አቶ አስፋው፣ ስለዚህ እስካሁን የነበረው አሠራር ሊሻሻል እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ አንዳንድ የባንክ ሥራዎችን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ የሚሠራ አድርጎ የመመልከት ችግር እንዳለ  የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ ለዚህም ምሳሌዎችን ጠቅሰዋል፡፡ 

‹‹ለምሳሌ ከዚህ ቀደም በአንዳንድ ክልሎች የኮንዶሚኒየም ቁጠባን ለማሰባሰብ ሲፈልጉ ‹‹ባንክ›› የሚለውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ እያሉ ተርጉመው ቁጠባውን እሱ ብቻ ማድረግ ይታሰብ ነበር፡፡ እንዲህ ያለው ችግር በአንድ ወቅት በአማራ ክልል ተከስቶ አይተነዋል፡፡ ባንክ ማለት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብሎ፣ ቆጥብ የሚባለው ደግሞ ኅብረተሰቡ ነው፡፡ ለመቆጠብ ደግሞ አንድ ባንክ ብቻ መለየት የለበትም፡፡ ስለዚህ ይህ መነሻ ሆኖ፣ አጠቃላይ እንዲህ ያለ አተረጓጎም ያላቸው ሕጎች ይስተካከሉ ነው የምንለው፤›› ሲሉ አቶ አስፋው ተናግረዋል፡፡ 

በአጠቃላይ እንዲህ ያሉ ጭብጦችን ሁሉ በዚህ ደብዳቤ ይገልጻሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 

የግል ባንኮች አሁን ባሉበት ደረጃና አቅም ከመንግሥት የሚቀርብ የብድር ጥያቄ ማስተናገድ እንደሚችሉ አቶ አስፋው ጠቁመዋል፡፡ ብድር ለማግኘት መሥፈርቱ ከተሟላ የማይሰጥበት ምክንያት እንደሌለም ይጠቁማሉ፡፡ ተበዳሪው ማስያዣ ካለው የተሟላ ከሆነ ብድር የሚጠይቅበት ፕሮጀክት አዋጭ መሆኑ ከታወቀ የግል ባንኮች ብድር ማቅረብ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

እንደ ምንጮች ገለጻ በንግድ ባንክ በኩል የመንግሥት ተቋማት በግል ባንክ ገንዘባቸውን ካስቀመጡ ብድርም ይስጡ የሚል አመለካከት ይንፀባርቃል፡፡ አቶ አስፋው ደግሞ እንዲህ ያለው ሐሳብ ትክክል ነው ብለው አያምኑም፡፡ ‹‹በትዕዛዝ የሚሰጥ ብድርና አዋጭነቱን ታይቶ የሚሰጥ ብድር ይለያያል፣ በትዕዛዝ የሚሰጥ ብድር አደጋ ይኖረዋል፡፡ ይህ መለየት አለበት እንጂ የግል ባንኮች ለመንግሥት ብድር የማይሰጡበት ምክንያት የለም፤›› ብለዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለመንግሥት ተቋማት ብድር የሚያቀርብ ሆኖ ሳለ፣ ተቋማት ግን ገንዘባቸውን በግል ባንክ ማስቀመጣቸው ተገቢ አለመሆኑን የሚሞግቱ ወገኖች ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሕግ የተሰጠውን ኃላፊነት ያላግባብ እየተንሸራሸረበት ነው ይላሉ፡፡ ገንዘብ ሚኒስቴርም የተሰጠውን ሥልጣን በአግባቡ አልተጠቀመም በማለት፣ የመንግሥት ተቋማት በግል ባንክ ገንዘባቸውን ሲያንቀሳቅሱ እስካሁን የት ነበር ብለው ይጠይቃሉ፡፡   

በርካታ የመንግሥት ባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች የመንግሥትን ገንዘብ ለማንቀሳቀስ በግል ባንኮች፣ የባንክ ሒሳብ ቁጥር በመክፈት ላይ የሚገኙ መሆኑን የገለጸው ገንዘብ ሚኒስቴር፣ ይህ ሕገወጥ በመሆኑ የከፈቱትን አካውንት በአስቸኳይ እንዲዘጉ ያስተላለፈው ውሳኔ አግባብ እንደሆነም እኚሁ ወገኖች ያምናሉ፡፡ ሆኖም ይህ ትዕዛዝ የመጣው ዘግይቶ በመሆኑ መንግሥት ወይም የገንዘብ ሚኒስቴር ችግሩን በመፍጠር ረገድ ተሳትፎ አድርጓል በማለትም ይገልጻሉ፡፡ 

የመንግሥት የፋይናንስ አስተዳደር አዋጅን መሠረት አድርጎ የወጣ መመርያ እንደሚያመለክተው፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሒሳብ አከፋፈትና አስተዳደርን በተመለከተ በመመርያው ክፍል ሦስት አንቀጽ ሰባት ላይ፣ ማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ከሚኒስትሩ በጽሑፉ ሳይፈቀድለት የባንክ ሒሳብ መክፈት አይችልም፡፡ በተጨማሪም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የባንክ ሒሳብ የሚከፈተው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወይም እሱ በራሱ በሚሰይመው ወይም በሚወክለው ባንክ እንደሚሆን ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም ገንዘብ ሚኒስቴር ከሰሞኑ ያስተላለፈው ትዕዛዝ ይህንን ሕግ ተከትሎ እንደሆነና ይህንን ማድረጉም ተገቢነት እንዳለው የሚከራከሩ አሉ፡፡

አቶ አስፋው ግን በወቅቱ የወጣው ሕግ እንዲህ የሚል ቢሆንም፣ በመርህ ደረጃ ሲታይ ግን ይህ አሠራር ወቅቱን ያገናዘበ ባለመሆኑ ሊሻሻል ይገባል የሚል አቋም አላቸው፡፡ ገንዘብ ሚኒስቴር ያስተላለፈው ትዕዛዝ ሕግን የተከተለ መሆኑን የሚጠቁሙ ወገኖች ደግሞ፣ ስህተት ከተባለ እንደ ስህተት የሚታየው ጥቂት የማይባሉ የመንግሥት ተቋማት በግል ባንኮች ሒሳባቸውን ማንቀሳቀስ ከጀመሩ በኋላ መመርያው በመውጣቱ ራሱን የቻለ ችግር ሊፈጥር የሚችል መሆኑን ነው፡፡    

ተቋማቱ አካውንት ሲከፍቱ ሕግን ተከትለው ይሁን አይሁን ባታወቅም፣ መመርያው ላይ፣ ‹‹ሚኒስቴሩ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ስም የተከፈቱ የባንክ ሒሳቦችን በበቂና በአሳማኝ ምክንያት ሊዘጋ ይችላል፤›› የሚል ድንጋጌ ተቀሞጧል፡፡ በተጨማሪም፣ ማንኛውም የመንግሥት ተቋማት አካውንት ሲከፍት ለሚኒስቴሩ ማሳወቅ እንዳለበት የሚደነግግ በመሆኑ፣ ተቋማቱ በግል ባንኮች አካውንት ሲከፍቱ ለገንዘብ ሚኒስቴር ማሳወቅ አለማሳወቃቸው በራሱ ጥያቄ የሚያስነሳ እንደሆነ የሚገልጹ አሉ፡፡ 

የማኅበሩ አቋም ግን የግል ባንኮች ለአገር ልማትና ተያያዥ ጉዳዮች ጥሪ ሲደርሳቸው ተገቢውን እንደሚያደርጉ፣ በልማት ባንክ በኩል ለብድር የሚውለው ገንዘብም ከግል ባንኮች የመነጨ መሆኑን ነው። ስለዚህ ይህ ሁሉ አስተዋጽኦ እያለ ለአንድ ወገን የሚያደላ መመርያ ይዞ መጓዙ ተገቢ እንዳልሆነ ይከራከራሉ፡፡ 

‹‹እዚህ አገር ያልጠራ ነገር ያለው የግልና የመንግሥት ባንክ የሚለው ነገር ነው፤›› የሚሉት አቶ አስፋው፣ ‹‹ብዙ ጊዜ ወደታች ወርዶ ሲታይ ጉምሩክን ጨምሮ የመንግሥት ተቋማት ሁሉንም ተገልጋይ ‹ሲፒኦ› ክፈቱ የሚባለው ከመንግሥት ባንክ መሆኑን በምሳሌነት አንስተዋል፡፡ ይህ አስተሳሰብ መለወጥ አለበት፡፡ ተወዳድሮ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ይህም የገንዘብ ሚኒስቴር ትዕዛዝ ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው፤›› ሲሉ ይጠቅሳሉ፡፡ 

በጥቅሉ አሁን ገንዘብ ሚኒስቴር ባስተላለፈው መልዕክት ላይ ብቻ የተንጠለጠለ አይደለም፡፡ እዚህ አገር ላይ ሊጠፋ ያልቻለው የመንግሥትና የግል ባንክ እየተባለ የሚለየውን መስመር ማስተካከል ጭምር ያለመ በመሆኑ፣ መንግሥት እንዲህ ያለውን አካሄድ እንዲያስተካከል ሁሉ የሚፈልጉ ስለመሆኑ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ 

የመንግሥት ባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች በግል ባንኮች በከፈተቱ አካውንት ምን ያህል ይሆናል? የሚለው ለጊዜው የተገለጸ መጠን የለም፡፡ አቶ አስፋውም፣ ‹‹አሁን ይህንን ያህል ነው ብሎ ለመናገር ለጊዜው ቁጥሩን አልያዝንም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹እኛ አሁን ወደ መጠኑ መግባት አልፈለግንም፡፡ ምክንያቱም የመርሁን ጉዳይ ነው ማስቀደምና ማንሳት የፈለግነው፤›› በማለት ጥያቄያቸውን አድሏዊ የሚመስሉ ሕጎች ሁሉ እንዲስተካከሉ ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በየዓመቱ ለመንግሥት እያበደረ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ ለአዲስ አበባ አስተዳደር የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ብቻ ካበደረው ውስጥ እስካሁን ያልተመለሰለት 54 ቢሊዮን ብር ስለመኖሩ መረጃዎች ያመለክታሉ። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን፣ የስኳር ኮርፖሬሽንና የባቡር ኮርፖሬሽንን ጨምሮ በጥቅሉ ሰባት ለሚሆኑ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አበድሮ ያልተመለሰለት ከ700 ቢሊዮን ብር በላይ ስለመኖሩ መረጃዎች ያመለክታሉ።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች