በዚህ በዘመናችን በጣም ከሚያስፈልጉት መጻሕፍት አንዳንዱ ታሪክ ነውና የታሪክ ድርሰት ያለው ሰው እንዳለ በደስታ እንቀበላለን። ታሪክ ትልቅ ነገር ነውና ከፍ ባለ ሐሳብ መጻፍ ያስፈልጋል። ታሪኩን የሚጽፉ ሰዎች ሁሉ በእውነተኛነትና በትክክለኛነት፣ አድልኦ ሳያደርጉ መጻፍ ያስፈልጋቸዋል። በሐቅ ካልተጻፈ ግን የታሪክ ድርሰት ዋጋውን ያጣና ታሪክ መሆኑ ይቀራል። ስለዚህ ታሪክ ጸሐፊዎች ሁሉ ትክክለኛውን መንገድ እየተመለከቱ እውነቱን ብቻ የሚገልጸውን ትርጉም ሊሰጡት ይገባቸዋል።
በእውነት ላይ መጨመር፣ ወይም ከእውነቱ ማጉደል፣ አድልኦም ማድረግ ለታሪክ ጸሐፊዎች የተገባ ነገር አለመሆኑን ባለማወቅ አንድ አንድ ታሪክ ጸሐፊዎች በጠባብ ሐሳብ የአንዱን ሕዝብ አኗኗርና አስተያየት ብቻ ተከትለው የጻፉ አሉ። ሌሎች ግን የዓለምን ሕዝብ ሁሉ ሐሳብና አኗኗር ተመልክተው ትርጉሙን አስፋፍተው ይጽፋሉ።
ዛሬ የዓለምን የፖለቲካ የኢኮኖሚክና የሕዝብ አኗኗርን ስንመለከት ጸሐፊዎችን በጠባብ አስተያየት ታሪክ እንዲጽፉ አንመክራቸውም። ለሕዝብ ከሌላው ዓለም ሁሉ ተለይታችሁ ለብቻችሁ የምትኖሩ ናችሁ ብሎ መስበክ ስህተት ያመጣል። የዓለም ሕዝብ ሁሉ ዛሬ በሥራቸውም በትዳራቸውም እየተጋገዙና እየተባበሩ ነው የሚኖሩት።
- (ይልማ ዼሬሳ – ሰኔ 1933)