Saturday, July 13, 2024

የውጭ ምንዛሪ ድርቅ ሰበቦችና መፍትሔ አልባ ጥረቶች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ወጣቱ አትሌት ሰለሞን ባረጋ ባለፈው ክረምት ተካሂዶ በነበረው የቶኪዮ ኦሎምፒክ፣ ኢትዮጵያ የለመደችው ወርቅ እንዳይቀርባት በ10 ሺሕ ሜትር አሸናፊ በመሆን ለአገሩ ወርቅ አስገኘ፡፡ በወቅቱ ከፍተኛ አድናቆት ጎረፈለት፣ የመኪናና የመሬት ሽልማትም ተበረከተለት፡፡ ሆኖም ከስምንት ወራት በላይ ሽልማቱ እጁ ሳይገባ መቆየቱ ከሰሞኑ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች መነጋገሪያ ነበር የሆነው፡፡ ለሰለሞን የመኪና ሽልማት መዘግየት ምክንያት ነው ተብሎ የቀረበው ደግሞ፣ መኪናውን ማስመጫ የውጭ ምንዛሪ እጥረት መሆኑ ተሰምቷል፡፡ ኢትዮጵያ ወርቅ ላመጣላት ብቸኛ አትሌት መኪና የምትሸልምበት ዶላር አጣች መባሉ ግርምት ቢፈጥርም፣ ሆኖም ያልተጠበቀ ችግር አለመሆኑን ነው ብዙዎች የሚስማሙበት፡፡ ለአትሌት ሰለሞን ሽልማት መዘግየት ምክንያት የሆነው የውጭ ምንዛሪ ችግር አትሌቶችን ብቻ ሳይሆን፣ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚፈትንና በሁሉም ዘርፍ የገባ ቀውስ መሆኑ በገሃድ የሚታይ ነው የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡

ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ አንድ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች አስመጪ፣ ‹‹ከአንድ የግል ባንክ ዕቃ ለማስመጣት እ.ኤ.አ. በ2016 የጠየቅኩትን ዶላር ከሰሞኑ ነው የሰጡኝ፡፡ እኔ ስለመዘገብኩት እንጂ ብዙዎች ወረፋው መቼ እንደሚደርሳቸው ያስታውሳሉ ብዬ አልገምትም፡፡ ኢምፖርት ላይ የሚሠሩ ሰዎች ይታወቃሉ፡፡ ወረፋው እንዴት ነው የደረሳቸው? ዶላሩን በምን አገኙት? የሚለው ለእኔ ግራ ነው የሚገባኝ፡፡ ብዙ ነጋዴዎች ባንኮች ዘንድ ወረፋ መሠለፍና ደጅ መጥናት ነው ሥራችን፤›› በማለት በየዕለቱ በሥራው ውስጥ እያጋጠመው ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ፈተና ይናገራል፡፡

በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ጉዳይ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጥያቄ ነው፡፡ አስመጪው፣ ላኪው፣ አገልግሎት ሰጪውም ሆነ አምራቹ የምንዛሪ እጥረት ዋና እንቅፋቱ እንደሆነ ያወሳል፡፡ በምንዛሪ  አቅርቦት እጥረት የተነሳ ፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃ መግዣ ተቸግረው ሊዘጉ ነው የሚል ዜና መስማት አዲስ አይደለም፡፡ የምንዛሪ  አቅርቦት ችግሩ በአገሪቱ ለሚታየው የዋጋ ንረትና ለገበያ አለመረጋጋት ችግሮች ትልቁ ምንጭ መሆኑን ነው ብዙዎች የሚስማሙበት፡፡ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን በተመለከተ አስተያየት ሰጪው ‹‹ነጋዴው የመግዣ ዋጋ ይጨምርበታል እንጂ ማትረፉን አይተውም፤›› ሲል እንደተናገረው ሁሉ፣ የኢትዮጵያ ገበያ በምንዛሪ  እጥረትና በምንዛሪ  ንረት በሚፈጠር የዋጋ ግሽበት መረጋጋት ተስኖት እያዘገመ መሆኑን የዘርፉ አንቀሳቃሾች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ 

በቅርቡ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ክፍተት የሚያስከትለውን የገበያ አለመረጋጋት ችግር ለመፍታት በመንግሥት በኩል ከተወሰዱ አማራጮች አንዱ፣ በፍራንኮ ቫሉታ ሸቀጦች ከቀረጥ ነፃ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ የሚል ውሳኔ ይገኝበታል፡፡ በአንዳንድ ሸቀጦች ላይ ብቻ ተወስኖ ሲተገበር የቆየው ይህ የቀረጥ ነፃ ንግድ የራሱ ሕግ ወጥቶለት ለረዥም ጊዜ ሲሠራበት የቆየ መሆኑ ይገለጻል፡፡ ባለፈው ዓመት በተለይ በመሠረታዊ ሸቀጦች ላይ ፈቃዱ ሰፍቶ መተግበር የጀመረው ፍራንኮ ቫሉታ፣ አሁን ደግሞ የገንዘቡ ጣሪያ ከ250 ሺሕ ዶላር በታች በሆነ ገንዘብም እንዲተገበር ተፈቅዷል፡፡ በቅርብ ጊዜያት ወደ አገር ውስጥ ከገቡ ምርቶች 44 በመቶው የተሸፈነው በፍራንኮ ቫሉታ በገቡ ምርቶች ነው ተብሎ በብሔራዊ ባንክ ሪፖርት ተመልክቷል፡፡ በዚህ መንገድ በአጠቃላይ ባለፈው ዓመት 1.8 ቢሊዮን ዶላር ሸቀጥ ገብቷል የሚለው ሪፖርቱ፣ ይህም 77.8 በመቶ ከዓምናው ብልጫ እንዳለው ነው የሚያስረዳው፡፡

ሆኖም በዚህ አሠራር የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ  አቅርቦትም ሆነ የሸቀጦች ዋጋ ንረትን መቅረፍ ይቻላል የሚለውን የመንግሥት ዕቅድ የተጠራጠሩና የደገፉ ወገኖች፣ በተለያየ ጎራ ተሠልፈው ሲከራከሩ ነው የሚታየው፡፡ መንግሥት ብቻውን በሚያደርገው ድጎማ ከውጭ በሚገቡ እንደ ዘይት፣ ስኳር፣ ስንዴና የሕፃናት ወተት የመሳሰሉ ሸቀጦች የሕዝቡን ፍላጎት ማሟላት አለመቻሉ ስለታመነበት በውጭ አገሮች ምንዛሪ  ያላቸው ግለሰቦች በፍራንኮ ቫሉታ ሸቀጦችን እንዲያስገቡ መፈቀዱ ገበያን ያረጋጋል የሚለው ለአንዳንዶች ተስፋ ሰጪ ሆኖ ቢታይም፣ ለሌሎች ግን የሚዋጥ ሐሳብ አለመሆኑን በማኅበራዊ የትስስር ገጾች የሐሳብ ልውውጦች ላይ ተስተጋብቷል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ስበው ከነበሩ ክርክሮች ደግሞ ፖለቲከኛውና የፋይናንስ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሙሼ ሰሙና ፖለቲከኛው አቶ ግርማ ሰይፉ፣ በየግል ፌስቡክ ገጾቻቸው ያሰፈሩት ሐሳብ ይገኝበታል፡፡

ፍራንኮ ቫሉታ የምንዛሪ  አቅርቦት ችግርን በመቅረፍ ገበያን ያረጋጋል የሚለው ሐሳብ ያልተዋጠላቸው አቶ ሙሼ፣ ‹‹በየቀኑ ግሽበት ባለበት አገር ውስጥ ዶላሩን በዕቃ እየለወጠ በፍራንኮ ቫሉታ ለማስገባት የሚፈልግ ወገን አይኖርም፡፡ ፍራንኮ ቫሉታን መፍቀድ ድሮም ያበደውን የዶላር ጥቁር ገበያን የበለጠ ያባብሰዋል፡፡ ከብዛትም ሆነ ከአቅርቦት አኳያ ገበያን አያረጋጋም፡፡ ዘላቂና ትልቅ የውጭ ምንዛሪ  አቅም ያለው ሸቀጦችን ማስገባት የሚፈልግ ዳያስፖራ ኢትዮጵያ የላትም፡፡ መሠረታዊ ችግርን ካለመፍታት የሚመነጭ የመፍትሔ አማራጭ ነው፤›› የሚል ይዘት ያለው ሐሳብ ነው ያጋሩት፡፡

ለአቶ ሙሼ በቀጥታ የመልስ ጽሑፍ ያሰፈሩት አቶ ግርማ ሰይፉ በበኩላቸው፣ ‹‹በፍራንኮ ቫሉታ የሚመጣ ሸቀጥ ትንሽም ሆነ ብዙ በልዋጩ ጥሬ ዕቃ ወደ ውጭ መላክን አይጠይቅም፡፡ የግለሰቦች የምንዛሪ አቅም ውስን ቢሆንም ብዙ ሲሆኑ ግን አቅማቸው ያድጋል፡፡ ፍራንኮ ቫሉታ ዶላርን በጥቁር ገበያ ከመላክ በቁስ ወደ አገር ቤት በሕጋዊ መንገድ መላክን ያበረታታል፡፡ በፍራንኮ ቫሉታ ሸቀጦችን ያለ ቀረጥ ማስገባት ጥሬ ዕቃ ወይም ማምረቻ ለመግዛት ምንዛሪ አጥተው ሥራ ያቆሙና ሊዘጉ ያሉ ተቋማትንም ይታደጋል፤›› የሚል ይዘት ያለው ተቃራኒ ሐሳብ አጋርተዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የሚደረገው የሐሳብ ክርክር ሲሆን፣ ምናልባትም በኢትዮጵያ ያለው የምንዛሪ አቅርቦት ችግር እስከቀጠለና የዋጋ አለመረጋጋቱ እስካልተፈታ ድረስ ክርክሩ እንደሚቀጥል ነው ብዙዎች የሚገምቱት፡፡ አቶ ሙሼም ሆነ አቶ ግርማ ፍራንኮ ቫሉታ ጊዜያዊ የውጭ ምንዛሪ  አቅርቦት መፍቻና የሸቀጦች ዋጋ ማረጋጊያ ዕርምጃ ነው በሚለው ሐሳብ ላይ ልዩነት ባይኖራቸውም፣ ነገር ግን አማራጩ ሊፈታ ይችላል ብለው በሚያምኗቸው ዝርዝር ሐሳቦች ላይ ፍፁም ሲቃረኑ ነው የታየው፡፡

ይህንኑ በተመለከተ ሐሳባቸውን ለሪፖርተር  ያጋሩ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የብሔራዊ ባንክ የቀድሞ ከፍተኛ ባለሙያ፣ ‹‹ለካንሰር አስፕሪን እንደ መዋጥ ያለ መፍትሔ›› ሲሉ ነው ሰሞነኛውን የፍራንኮ ቫሉታ መፍትሔ ያስቀመጡት፡፡

እንደ ባለሙያው ገለጻ፣ ‹‹ፍራንኮ ቫሉታ በአገሪቱ ያለውን የሸቀጦች ከፍተኛ ፍላጎት ለማስታገስ ይረዳ ይሆናል እንጂ፣ ለአጠቃላይ ችግራችን መፍትሔ አይሆንም፡፡ ፍራንኮ ቫሉታ በተፈቀደ ጥቁር የገበያና የኢኮኖሚ መዛባትን እየጨመረ ነው ያለው፡፡ ሕገወጥ ገንዘብ ዝውውርን ይጨምራል፡፡ ፍራንኮ ቫሉታ አይደለም የችግሩ መፍትሔ፤›› በማለት አገሪቱ በመሠረታዊነት ችግሩን ለመፍታት ልትከተል ይገባል የሚሉትን መፍትሔ ሰንዝረዋል፡፡ 

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የምጣኔ ሀብት ምሁርና ኢንቨስትመንት አማካሪ አቶ ያሬድ ኃይለ መስቀል በበኩላቸው፣ ‹‹የፍራንኮ ቫሉታ ግብይት መከፈቱ ጥሩ ነው፣ የተወሰነ ነገር ይቀንሳል፡፡ ገበያው ፈጽሞ መዘጋት የለበትም፣ የበለጠ መከፈት ነው ያለበት፡፡ የዘይትና የስኳር ዓይነት ምርቶችን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ወደ አገር ውስጥ መግባት የሚኖርባቸው አስፈላጊ ነገሮችን በሙሉ ማስገባትም ሊፈቀድ ይገባል፡፡ ይህ ገበያውን ያረጋጋል፣ ችግራችንን በመጠኑም ያቃልላል፤›› በማለት ነው ወቅታዊውን የመፍትሔ አማራጭ የደገፉት፡፡

ዕርምጃው የትይዩ ገበያን ወይም ጥቁር ገበያን ያስፋፋል የሚለውን መላምት የነቀፉት አቶ ያሬድ፣ ‹‹ብላክ ማርኬት እኮ ሁሌም ዝግ በሆኑና ቁጥጥር በሚበዛባቸው አገሮች አለ፡፡ ፍራንኮ ቫሉታው አይደለም ያመጣው፡፡ አሁን እኮ ከመደበኛው ገበያ ጭራሽ ወደ 20 ብር ልዩነቱ እየሰፋ ነው ያለው፡፡ ጥቁር ገበያ የቁጥጥር ውጤት ነው፡፡ ለምን ሶማሌላንድ፣ ጂቡቲ ወይም ኬንያ የለም?›› በማለትም የሌሎች አገሮች ተሞክሮን አቶ ያሬድ በማነፃፀሪያነት አቅርበዋል፡፡

የችግሩ ፖለቲካዊ  ምክንያቶች

በኢትዮጵያ አስመጪና ላኪው ነጋዴ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የገበያ ተዋረድ ባሉ የንግድ ሰዎች የውጭ ምንዛሪ  እጥረት ከባድ ፈተና እንደሆነ ተደጋግሞ ይጠቀሳል፡፡ አገሪቱ የውጭ ምንዛሪ  ግኝትን ለማስፋትና ለማሳደግ ብዙ ጥረቶችን ማድረጓ ቢነገርም፣ ነገር ግን ይህ ችግር በቀላሉ መፈታት አልቻለም፡፡ ወደ ውጪ የሚላከው ሸቀጥ (ኤክስፖርት) በዓይነትም ሆነ በመጠን መጨመሩን ይፋዊ መረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡ ወደ ውጭ ምርትና አገልግሎት ተልኮ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ  ማደጉም በኢኮኖሚ ሪፖርቶች ተደጋግሞ ይጠቀሳል፡፡ ከውጭ አገሮችና ተቋማት ጋር አገሪቱ ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስሮሽ በማስፋቷ በዕርዳታም ሆነ በብድር የሚመጣው ገቢ በእጅጉ እንዲሻሻል አስተዋጽኦ እንዳለው ተደጋግሞ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ሆኖም ይህ ሁሉ ሆነ ተብሎም በተጨባጭ የውጭ ምንዛሪ  እጥረቱ አልተቀረፈም  ይላሉ ብዙዎች፡፡

ስሜ አይጠቀስ ያሉት ከፍተኛ የቀድሞ የብሔራዊ ባንክ ባለሙያ፣ ‹‹የውጭ ምንዛሪ  ግኝታችንን ለማስፋት ምንጫችንን ማሳደግ መቻል አለብን፡፡ ሁለተኛው የተገኘውን የውጭ ምንዛሪ  ደግሞ አጠቃቀሙ ላይ ብክነትን መቀነስ አለብን፡፡ አጠቃቀማችን በአግባቡ ቢሆን ሦስተኛው ደግሞ ገበያ መር የሆነ የምንዛሪ  ግብይትን መከተል አንዱ የመፍትሔ አካል ነው፤›› በማለት የመፍትሔ አማራጮችን ካሉት ሐሳብ ጋር ደምረው ችግሩን አስቀምጠዋል፡፡

ከዚህ በመጠኑ በተለየ ሁኔታ የችግሩን ምንጭ ለማስቀመጥ የሞከሩት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ያሬድ በበኩላቸው፣ የውጭ ምንዛሪ  ገበያን ክፍትና ተወዳዳሪ የማድረግ ዕርምጃን ነው በትኩረት የሚያነሱት፡፡ ‹‹የገንዘቤ ምንጭ ሕጋዊ እስከሆነ በድረስ እንግሊዝ ብነግድበት ወይም ኬንያ ይዤው ብሄድ ምን ችግር አለው? የኛ አገር የውጭ ምንዛሪ ግብይት ዝግ ስለሆነ እንጂ፤›› ሲሉ ነው በአጠቃላይ የገንዘብ ዝውውርን ፖሊሲ ግትርነት አጥብቀው የሚተቹት፡፡   

‹‹እኛ ከሶሻሊዝም አስተሳሰብ መውጣት ስላልቻልን ነው ቁጥጥር የምናበዛው፡፡ በአገሪቱ  ያለው ዶላር በሙሉ የእኔ ነው የሚል መንግሥት ነው ያለን፡፡ ይህ ዓይነት ሕግ የወጣው ደግሞ በደርግ ዘመን በ1969 እና 1970 ዓ.ም. ነው፡፡ ዓለም ተቀይሮም እኛ ጋ ይሠራበታል፡፡ 

‹‹አንድ ሰው ቢታመምና ታይላንድ ሄዶ ለመታከም ባንክ ዶላር አልሰጥም ቢለው፣ ወደ ጥቁር ገበያ ከመሄድ ውጪ ምርጫ የለውም፡፡ በኪሱ 50 ዶላር ያለው ሰው ዕቃ ገዝቶ ቢያስገባ ምንድነው ኃጥያቱ? ከውጭ አገር አንድ ሰው ኢትዮጵያ ሲመጣ ገና እግርህ እንደረገጠ የታክሲ ሾፌሩ ነው ዶላር ልመንዝርልህ የሚልህ፡፡ ኬንያ ታክሲ ሾፌሩ ይህን ላድርግ ቢል ከመደበኛው ምንዛሪ የተለየ ትርፍ አያገኝበትም፡፡ እንደገናም አገልግሎቱን ለሰጠበት ለመንግሥት ለመክፈል ይገደዳል፡፡ ስለዚህ አይፈልግም፡፡ እዚህ አገር ግን ጥቁር ገበያ ከፍተኛ ልዩነት ስላለው ሁሉም ይሻማበታል፡፡ የእኛ አገር ከአስተሳሰብ ነው ችግሩ የሚጀምረው፡፡ የምንዛሪ  እጥረት አለብን፡፡ ቁጠባና አጠቃቀሙን አናውቅበትም፡፡ ዛሬ እኮ ሆስፒታል ተሂዶ ክትባት ማግኘትም እያስቸገረ ነው፤›› ሲሉ ነው የችግሩ መሠረታዊና መነሻ ምንጭ ከፖሊሲ እንደሚጀምር የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ያብራሩት፡፡

በኢትዮጵያ ባለፉት አሥርት ዓመታት በውጭ ካሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚላከው የሐዋላ ገቢ፣ ለአገሪቱ ዋነኛ የዶላር ምንጭ እየሆነ ነው ሲባል ቆይቷል፡፡ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ስለማደጉ፣ እንዲሁም የቱሪዝም ገቢ መጨመሩ ሲነገር መስማትም አዲስ አይደለም፡፡ ይህ ሁሉ የኢኮኖሚ ዕድገት አመላካች እየተባለ የሚቀርብ መረጃ በተጨባጭ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ችግር መቅረፉን የሚጠራጠሩ ግን በርካታ ናቸው፡፡ በየጊዜው የውጭ ምንዛሪ ገቢያችን ጨመረ  ሲባል ቢቆይም፣ ነገር ግን ከዚህ በሚቃረን ሁኔታ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ  ችግር መባባሱን የሚያመላክቱ መረጃዎችን መስማት በኢትዮጵያ አዲስ አለመሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡

ይህ ተቃርኖ የተፈጠረው ደግሞ በውጭ ምንዛሪ  አቅርቦቱና ፍላጎቱ መካከል አለመጣጣም በመኖሩ ነው የሚለው ቀዳሚው ምክንያት ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ አንዳንዶች ችግሩን ከኢኮኖሚ ሕጎችና ፖሊሲዎች መዛባትና አተገባበር ችግር ጋር አገናኝተው ያቀርቡታል፡፡ በመንግሥት በኩል የኮቪድ ወረርሽኝ መስፋፋት፣ የዓለም ሸቀጦች ዋጋ መዛባት፣ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ማጋጠም፣ ወዘተ እየተባለ ወቅቱን የተከተሉ አመክንዮዎች ለችግሩ በምክንያትነት ይቀርባሉ፡፡ መንግሥት መሠረታዊ ሸቀጦችን ከመደጎም ጀምሮ ቅድሚያ ለሚሰጣቸውና አንገብጋቢ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ለሚያስፈልጋቸው የኢኮኖሚ መስኮች መንቀሳቀሻ እንዲሆን፣ ውስኑን የአገሪቱን ምንዛሪ  ግኝት በፍትኃዊነት እያከፋፈለ መሆኑን ከመናገር ተቆጥቦ አያውቅም፡፡ ነገር ግን መንግሥት የችግሩን መነሻና መሠረታዊ ምክንያቶች እንደ መፍታት ጊዜያዊ፣ የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ላይ ብቻ ያተኩራል የሚሉ በርካታ ናቸው፡፡ በዚህ የተነሳ የውጭ ምንዛሪ  እጥረት ቀውስ ሳይፈታ ለረዥም ጊዜ አገሪቱን ተጭኗት ቆይቷልም ይላሉ፡፡

የቀድሞው ብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ ባለሙያ፣ ‹‹ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦች ዋጋ መጨመርም ሌላ ራሱን የቻለ የምንዛሪ እጥረቱን ያባባሰ ችግር ነው፡፡ ማዳበሪያ፣ ነዳጅ፣ ዘይትና ምግቡ ሳይቀር ጨምሯል፡፡ ዘንድሮ ለኢምፖርቱ ከበፊቱ በእጅጉ የበዛ የምንዛሪ  አቅርቦት ያስፈልገናል ማለት ነው፤›› ሲሉ ዘርፉ በየወቅቱ የተለያዩ ፈተናዎች እየገጠመው ይገኛል የሚለውን ሐሳብ አጠናክረዋል፡፡  

አቶ ያሬድ በበኩላቸው፣ ‹‹ዶላር የሌለው አገር ሆነን እንደገና ዶላር ካልከፈልናችሁ ዕቃ አትስጡን የሚል ሕግ በራሳችን ላይ መደንገጋችን ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ሌላው አገር የሚሠራበት ሸጠህ ክፈለኝ በሚል ሕግ ነው፡፡ የእኛ አገር የወጪ ንግድ ግን ያለችንን ውስን ዶላርም አሟጦ ከአገር የሚያሰድድ የንግድ ሥርዓት ነው ያለን፤›› በማለት ነው ከንግድ አሠራር ጀምሮ የውጭ ምንዛሪ  አጠቃቀም ድረስ ትልቅ  ችግር ያለበት መሆኑን ያስረዱት፡፡

‹‹በሌሎች አገሮች ምርት ያላቸው ኩባንያዎች አገርህ ወስደህ ሽጥና ክፈለኝ በማለት በጊዜ ገደብ ምርቶቻቸውን ይሰጣሉ፡፡ በዚህ ዋጋ ነው የሚሸጠው፣ ሲሸጥ ክፈለኝ ተብሎ ነው ንግድ የሚካሄደው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሱፐርማርኬቶቻችን ላይ የተደረደሩ ምርቶችም እኮ ከአምራቾች በዱቤ የሚረከቧቸው ናቸው፡፡ የወጪና የገቢ ንግዳችን ላይ ግን ይህ አይሠራም፡፡ የአንዲት ካልሲ ወይ ጫማ ልዩነት ከመጣ ኮንቴይነሩ ላይገባ ይችላል፡፡ ሁሌም በጥሬ ዶላር ተገዝቶ ካልገባ ማለት የአገራችንን የውጭ ምንዛሪ  ክምችት ያደርቃል፡፡ ይህ የሚመጣው በመንግሥት የመቆጣጠር አባዜ ነው፡፡ መንግሥት ሁሉን አዋቂና የአገር ጠባቂ ነው ተብሎ ስለሚታመን፣ ከሕዝብ በላይ ለአገር ተቆርቋሪም መንግሥት ነው ተብሎ ይቀርባል፤›› ሲሉ የተናገሩት አቶ ያሬድ፣ የምንዛሪ  ግብይትና አጠቃቀም ላይ ያለው ክፍተት የፖሊሲ ምንጭ እንዳለው ነው ያብራሩት፡፡

የውጭ ምንዛሪ  እጥረት ችግር በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ መነሻ አለው ብለው የሚሞግቱ ወገኖች፣ በተለይ አገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንድታጠናክር ያሳስባሉ፡፡ ከዕርዳታ፣ በብድርና ከኢንቨስትመንት አገሪቱ የበለጠ ተጠቃሚ መሆን ትችላለች ብለው የሚያስቡ ብዙዎች ናቸው፡፡ በዕርዳታ፣ በብድር፣ በኢንቨስትመንትም ሆነ በፕሮጀክት ፈንዶች የሚፈሰው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ለደሃዋ አገር ለኢትዮጵያ ብዙ የበጀት ቀዳዳዎችን መሸፈኛነት እንደሚውል የሚጠቅሱ ወገኖች፣ በዚህ በኩል ዶላር የሚገኝበትን ቀዳዳ ሁሉ አነፍንፋ  እድትጠቀም ያሳስባሉ፡፡  

ኢትዮጵያ ባለፉት 30 ዓመታት በዚህ በኩል ስኬታማ እንደነበረች ይነገራል፡፡ በተለይ የምዕራባውያን የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሁነኛ አጋር ስለመሆኗ የሚነገርላት ኢትዮጵያ እንደ ቻይና ካሉ ሌሎች አጋሮች ጋርም ጥብቅ ግንኙነት በመፍጠር እንደማትታማ ተደጋግሞ ይወሳል፡፡ አሁን በተለይ ከኮቪድ ወረርሽኝ፣ እንዲሁም ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መስፋፋት ጋር በተያያዘ የብድር፣ የዕርዳታና የኢንቨስትመንት ምንጮቿ እየደረቁ ነው ቢባልም ነገር ግን በዚህ ረገድ ብዙ የመጠቀም ዕድል እንዳላት ነው የሚነገረው፡፡

የውጭ ልማት አጋሮች እጃቸውን መሰብሰባቸው በቀጥታ የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር እንደሚፈትነው የሚናገሩት የቀድሞው ብሔራዊ ባንክ ባለሙያ፣ ‹‹አገሮችና ድርጅቶች በጀት መቀነሳቸው ትልቅ ችግር ነው፡፡ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መቀነሱም የዚሁ ችግር አካል ነው፡፡ የዓለም ገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የሚሰጡን ዕርዳታና ብድር የውጭ ምንዛሪ ክምችታችንን ከ25 እስከ 30 በመቶ ይሸፍናል፡፡ ይህ እንደኛ ላለ የውጭ ምንዛሪ ማግኛ ምንጭ እጥረት ላለበት አገር ትልቅ ጉድለት የሚሸፍን ነው፡፡ በተለያየ መንገድ ከዕርዳታ ድርጅቶችና አበዳሪዎች የሚመጣው ዶላር መቀነሱ ችግራችንን በደንብ አባብሶታል፤›› ይላሉ፡፡

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ያሬድ፣ ፈረንጆቹ እጃቸው ማጠሩ በውጭ ምንዛሪ  አቅርቦት ላይ ተፅዕኖ አለው የሚለውን መላምት በተለያዩ አቅጣጫዎች መፈተሽን ነው የሚመርጡት፡፡  ‹‹ኢትዮጵያ ለ27 ዓመታት በየዓመቱ በአማካይ ወደ 3.5 ቢሊዮን ዶላር ዕርዳታ ታገኝ ነበር፡፡ ሲደማመር በ27 ዓመታት ወደ 94 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል፡፡ ይህ ሁሉ ዶላር ተገኝቶም በውጭ ምንዛሪ  አቅርቦት እጥረት እንቸገር ነበር፡፡ ሕወሓት ይህን ሁሉ አግበስብሶ ትግራይ ውስጥ የውኃ ጉድጓድ እንኳን በበቂ አልቆፈረበትም፡፡ ይህ ሁሉ ገንዘብ ወዴት ገባ? ምንስ ተሠራበት? እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ለዕርዳታ ይጠቅማል አይጠቅምም? የሚል መሠረታዊ ጥያቄ የሚያስነሱ ናቸው፡፡

‹‹እኛ ጋ የሚገባው ዕርዳታ በዕርዳታነት መታየት የሚችል ነው ወይ? የሚል ጥያቄም ማንሳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ በዩክሬን እንደምናየው እነ አሜሪካ ሰምተነው የማናውቀውን መጠን ረዱ ሲባል ታዝበናል፡፡ ዩክሬን ተጠቃች ባሉ ቀን ወደ 1.4 ቢሊዮን ዶላር ነው የመደቡት፡፡ አለን ብዬ መመፃደቅ አልፈልግም፣ የውጭ ድጋፍ ያስፈልገናል፡፡ ሆኖም እኛ ጋ የ200 እና 300 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ ወይም ፕሮጀክትና የቀለብ ስንዴ መምጣቱ መሠረታዊ ችግራችንን የሚፈታና ከድህነት የሚያላቅቅ ነው ብዬ አላምንም፤›› በማለት ነው አቶ ያሬድ የምዕራባውያኑን ዕርዳታና ብድር መቅረት ብዙ ችግር እየፈጠረ ነው የሚሉት፡፡   

በፖለቲካ አለመረጋጋትና ግጭት ሳቢያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ  ምንጭ የነበሩ ዕርዳታዎችና ብድር ምንጮች ደርቀዋል የሚለው አስተያየት እየጎላ መጥቷል፡፡ በሰሜኑ ጦርነት የተነሳ አገሪቱ ለማዕቀብ የምትዳረግ ከሆነ ሊገጥማት የሚችለው አደጋ ከእስካሁኑ የከፋ መሆኑም ይነገራል፡፡ ከሰሞኑ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አመራሮች የተደረገው የውጭ አገር ጉዞም ዋና ዓላማው፣ ይህን የምዕራባውያንና የኢትዮጵያን ግንኙነት በማለዘብ ወደ ቀደመ መልካም ሁኔታው መመለስን ያለመ ነው ተብሎ ተገምቷል፡፡ ስለጉዞውም ሆነ ባለሥልጣናቱ ስላሳኩት ጉዳይ የተብራራ መረጃ ባይወጣም፣ ነገር ግን ሁኔታው አገሪቱ የውጭ የልማት አጋሮችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ማጣት የማትፈልግበት ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ ማመላከቻ ሆኖ ነው የቀረበው፡፡  

የቀድሞው ብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ ባለሙያ በዚህ ጉዳይ ላይ መፍትሔና መደረግ አለበት የሚሉት፣ ‹‹ያለውን የፖለቲካ ችግር በሰላማዊ መንገድ መጨረስና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን ማሻሻል ይገባል፡፡ አሁን በአገሪቱ ሪፎርሞች ተጀምረዋል፡፡ የምንዛሪ  ግብይቱን ወደ ገበያ መር ለማሸጋገር ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡ ይህ በሒደት ለረዥም ጊዜ ተብሎ ደረጃ በደረጃ የሚሠራ የመፍትሔ ዕርምጃ ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡  

አቶ ያሬድ በበኩላቸው መፍትሔ የሚሉትን ሲያስቀምጡ የሚከተለውን ይናገራሉ፡፡ ‹‹የፈረንጆቹ ዕርዳታ ማቋረጥ ዞሮ ዞሮ በዶላር ስለሚመጣ ያለብንን የውጭ ምንዛሪ  ችግር ማባባሱ አይቀርም፡፡ አሁን ደግሞ ኤችአር በሚባለው ሕግ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባውን የሃዋላ ገቢም ለመዝጋት መነሳሳታቸው አገሪቱን ይጎዳል፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ አንድ ምክንያት እንጂ የችግሩ ምንጭ ነው ተብሎ ሊቀመጥ የሚችል አይደለም፤›› ሲሉ ችግሩ ዘርፈ ብዙ መፍትሔ እንደሚሻ የጠቆሙት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -