Friday, July 19, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የአንጐል ነገር

በመምህር ሳህሉ ባዬ ዓለሙ

ከአኩሪ አተር የተሠራ እርጐ (Tofu) የመሰለ፣ ከበድ ያለ፣ ሸካራ፣ ግራጫና ነጭ ቀለም ያለው ስሪተ-አካል ነው።  ሦስት ኪሎ ግራም የሚመዝነው አንጐል በክብደት ከሚታወቁት አካላዊ ክፍሎች መካከል ኦክስጅን በጣም ፈላጊው አካል ነው።  እስከ 30 በመቶ የሚሆነውን የሰውነት የግሉኮስ አቅርቦት ለሥራ ይጠቀማል። 

እንድናስብ፣ አካባቢያችንን እንድንገነዘብ፣ በዓላማ እንድንቀሳቀስ፣ ስሜት እንዲሰማን፣ ስሜታችን ተረድተን እንድንተረጉም፣ በአጠቃላይ የዕለት ተዕለት ተግባራትን (በማወቅም ሆነ ባለማወቅ) በሥርዓት እንድናከናውን የሚያስችል አካል ነው።  ባህሪያትን፣ ልምዶችን፣ ተሞክሮዎችን በማቀናጀት ማንነትን መፍጠር የሚያስችል አካል ነው።  

የአንጐል ውቅር፦ 

 አንጐል በሎቦች (የአንጐል ክፍሎች) የተከፋፈለ አካል ነው።  በአንጐላችን ውስጥ በትንሹ 100 ትሪሊዮን የነርቭ ግንኙነቶች ወይም ሲናፕሶች ይከናወናሉ። ይህ አሃዝ በእኛ ጋላክሲ ውስጥ ካሉት የከዋክብት ብዛት ቢያንስ 1,000 ጊዜ እጥፍ ነው።   በሰዓት 268 ማይል ፍጥነት መልዕክቶች በአከርካሪ (ስፓይናል ኮርድ) ውስጥ በሚገኘው የአልፋ ሞተር ነርቭ በኩል ይጓዛሉ። ይህ ጉዞ በሰው አካል ውስጥ በጣም ፈጣኑ ጉዞ ነው።  

በቆዳ ውስጥ የሚገኙ የስሜት ህዋሳት ማይሊን ሼት የተባለ ፍጥነት አሳላጭ ኢንሱሌን ስለሚያጥራቸው በሰዓት አንድ ማይል በመጓዝ በጣም ቀርፋፋ ከሚባሉ ነርቮች መካከል ይመደባሉ።  

በሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ (UCLA) ውስጥ ያሉ የነርቭ ሳይንቲስቶች እንደዘገቡት፣ አንድ የ20 ዓመት ወጣት በአማካይ 100,000 ማይል በማይሊን የተሸፈኑ የነርቭ ክሮች በአንጎሉ ውስጥ አሉት። ከ 23 እስከ 80 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ በተገኙ የጎልማሶች አንጐልና ስለ ማይሊን ያጠኑ እነዚህ ምሁራን የማይሊን ሽፋንና የሞተር ችሎታ በ39 ዓመት አካባቢ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደሚደርስ ጠቁመዋል። 

የብሪታንያ ተመራማሪዎች በታኅሣሥ ወር እንደዘገቡት በሲናፕስ አሠራር ውስጥ የተካተቱት የቤተሰብ ዘር ግንድ ጂኖች 17 በመቶውን የኛን ጂኖም ይይዛሉ። 

ከሁለት ቢሊዮን በላይ ያህል የሚሆኑት አብዛኞቹ የነርቭ መጋጠሚያዎች በቆዳችን የላይኛው ክፍል ላይ የሚሰማንን የሕመም ስሜት ይከታተላሉ። በቁጥር አናሳዎቹ ደግሞ እስከ 0.01 ዲግሪ ፋራናይት ድረስ ያለውን ዝቅተኛ የሙቀት ልዩነት ማወቅ ያስችሉናል። 

በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ሳይንቲስቶች እየተሠራ ያለው የአንጐል ካርታ ለአእምሮ ሕመም፣ ለማስታወስ እና የሰብዕና ባህሪያት ፍንጭ ሊሰጥ ይችላል ተብሎ ተገምቷል።  ለማንኛውም ትክክለኛው የሰው አንጎል 100 ቢሊዮን ያህል የነርቭ ሴሎችን እንደሚይዝ ተመራማሪዎች አስምረውበታል። ስለዚህ ሳይንቲስቶች ቢያንስ ጥሬ ቁጥሮችን እየጠጉ ነው። 

አንጐል የዶክተሮችንና ተመራማሪዎችን ከፍተኛ ትኩረት ያገኘ አካል ነው። የዩኤስ አሜሪካ ኮንግረስ እ.ኤ.አ.1990ዎቹን ‹‹የአንጎል አሥር ዓመታት›› በማለት ሰይሟቸው ነበር። 

ስለዚህ እያንዳንዱ የአንጐል ክፍል ሥራውን በተገቢው ሒደትና ፍጥነት ካላከናወነ ምን ዓይነት ሕመም ሊከሰት እንደሚችል በመገንዘብ ለልጆቻችን ምቹና ሰላማዊ አካባቢ ለመፍጠር እንጣር።

አንጎል ለምን አይሠራም?

በቅድሚያ የፊትለፊት (ፍሮንታል) ሎብ ወይም የኮርቴክስ ስሪት እና እክሎች እንመልከት፦

     እኛ ማለት አንጎላችን ነን። አንጐል ማንነትን ይወስናል። በስሜት ህዋሳት በኩል የሚደርስ መረጃ ይገነዘባል፣ ይመዘግባል። ደስታን፣ ስሜትን፣ አስተሳሰብን፣ በአጠቃላይ ሰብዕናን ይቆጣጠራል። ዋናው ውጫዊ የአንጎል የፈትለፊት ክፍል ፍሮንታል ሎብ (ኮርቴክስ) በመባል ይታወቃል። ሰብዕናችን የተሠራው በአብዛኛው በዚህ የአንጎል ክፍል ምከንያት ነው። 

የፊትለፊት (ፍሮንታል ሎብ) ወይም ኮርቴክስ ከግንባርና ዓይን ጀርባ በጐን በኩል ከአገጭ አጥንት ከፍ ብሎ ከጆሮ ፊትለፊት ተዘርግቶ የሚገኝ ውጫዊ አካል ነው። ሰዎችን ከእንስሳት የሚለየንም ይህ የአንጐላችን ክፍል ነው። 

በፍሮንታል ሎብ (ኮርቴክስ) ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰ የሰው ሰብዕና ሙሉ ለሙሉ ይለወጣል። የጉዳት ተጠቂ ሰው ወደ ተሟላ ጤንነቱ መመለስ እጅግ ይከብደዋል። ለምሳሌ ብስክሌትና ሞቶር ብስክሌት ከመጠቀማችን በፊት አደጋ መከላከያ ቆብ ወይም በጦር ሜዳ የብረት ሔልሜት በጭንቀላታችን ላይ ማድረግ እንዳለብን የምንመከረው ወይም የምንገደደው  በዚህ የአንጎል ክፍል ላይ ሊከሰት የሚችልን ማንኛውንም አደጋ ቀድሞ ለመከላከል ሲባል ነው፡፡

በፊት ለፊት (ፍሮንታል ሎብ) ወይም ኮርቴክስ ላይ የደረሰ ጉዳትን ተከትለው የሚከሰቱ እክሎች ምንድን ናቸው? 

  1. ደካማ ማኅበራዊ ተግባቦት፣ የተዛባ የማመዛዘን ችሎታና ፍርድ አሰጣጥ፣የፊት ለፊት (ፍሮንታል) ሎብ ወይም ኮርቴክስ ስሜትን በምክንያት መዝነንና ተቆጣጥረን በህብረተሰቡ ውስጥ የተሰጠንን ኃላፊነት በሥርዓት መወጣት የሚያስችለን የአንጎል ክፍል ነው። ለምሳሌ ድንገት ስንናደድ በሰው ላይ ከመጮህና ለመደባደብ ከመጋበዝ እንቆጠባለን። ሙሉ ለሙሉ መግታት ባይቻልም በጥቃት ዝንባሌ ከንቱ ስሜት ተገፋፍተን ጾታዊ ፍላጎት በኃይል ለማርካት እንዳንሞክርና ተቀባይነት የሌላቸውን አጉል ጠባያት እንዳንፈፅም ራሳችንን እንጠብቃለን።
  2. የስሜታዊነት ግፊት፣

      በፊትለፊት (ፍሮንታል) ሎብ ወይም ኮርቴክስ ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ስሜታዊ ግፊታቸውን መቆጣጠር ስለሚሳናቸው መናገር የማይገቧቸውን ነገሮች ሁሉ ያወራሉ። የወሲብ ፍላጐታቸውን አይደብቁም። በፍቅር ግንኙነት ወቅት የትዳር አጋሮቻቸውን ወይም ጓደኞቻቸውን ያጭበረብራሉ። በንግድ ሽርክና እና በግል ሕይወታቸው የሚሰነዝሯቸው ሀሳቦችና እቅዶች ተግባረዊ አይሆኑም። 

  1. የተቀናጀ ፕሮጀክት አተገባበር ችግር፣

የፊት ለፊት ኮርቴክስ ስሜትን፣ ተነሳሽነትን እና ዕቅድ ማውጣትን ስለሚያስተዳድርና ስለሚቆጣጠር በዚህ አካላችን ላይ የሚደርስ ጉደት የፕሮጀክት እቅድን፣ ተግባራትን እና ግብን ተከታትለን፣ ገምግመን፣ ተቆጣጥረንና መዝነን እንድናስፈፅም እንቅፋት ይሆናል። አንድ ተጎጂ ሰው ፍላጐት ቢኖረውም እንኳ በገባው ቃል መሰረት እቅዱን ማስፈፀም አይችልም። በዚህ ችግር ምክንያት ሰነፍ፣ ፍላጐት አልባና የድብርት ሰለባ ሊሆን ይችላል። 

      አንጐል ለምን አይሠራም? ፍሮንታል ሎብ / ኮርቴክስ ሲጐዳ፣ በፊት ለፊት (ፍሮንታል) ሎብ/ ኮርቴክስ ላይ ጉዳት የደረሰበት ሰው፦ 

  1. ለድብርት ተጋላጭ ይሆናል። በኒውሮሳይንስ (የነርቭ ሳይንስ) መስክ ድብርት እንደ ኮርቴክስ እክል ይቆጠራል።  የፊት ለፊት ኮርቴክስ ጡንቻዎችን የማነቃቃት ሥራ ያከናውናል። በዚህ አካል ላይ ጉዳት ሲደርስ የጡንቻ ጥንካሬ፣ ኃይልና ፍጥነቱን ይቀንሳል። ለምሳሌ በጣም በዝግታ ይራመዳል፣ ሲራመድ ክንዶቹን አያወዛውዝም፣ ቀሰስተኛ ይሆናል፣ ለውዝዋዜ፣ ዳንስና ስፖርት ፍላጎት አይኖረውም፣…።  ይህ የአንጎል ክፍል የተወሰኑ የዓይን ጡንቻዎችንና ሚዛን ነክ ሥራዎችን የሚያከናውኑ አካላትን ስለሚመራ በዚህ አካል ላይ ጉዳት የደረሰበት ሰው አካላዊ ሚዛኑ ይዛባል። 
  2. የእጅ ጽሑፍ ደካማ ይሆናል።

  ኮርቴክስ የእጅ ጽሑፍ፣ ጥልፍ ሥራ፣ ወዘተ ሥራ የሚሠሩ ረቂቅ ሞተር ነርቮችን ያስተባብራል። ይህ ክፍል ሲበላሽ የእጅ ጽሑፍ ደካማ ይሆናል።  የእጅ ጽሑፍ ጥራት በመከታተል ስለ ነርቭ ተግባር መድከም መረዳት ይቻላል። የአንድ ሰው እጅ ጽሑፍ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ጐን እየዘመመ፣ እየቀጨጨ፣ እየተንቀጠቀጠና ጥራቱ በፍጥነት እየቀነሰ ከመጣ (ማይክሮግራፊያ) ነርቮቹ መድከም፣ መበላሸት ወይም መበስበስ ስለመጀመራቸው የሚያረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ምልክት ነው። ስለዚህ ይህን ችግር በራሱ ላይ ያስተዋለ ሰው ስለ ኮርቴክሱ ጤንነት ማሰብ መጀመር እንዳለበት ይመከራል። 

  1. ሕጻናት ለኤዲኤችዲ (ADHD) ሕመም ይጋለጣሉ።

የኮርቴክስ ዕድገት መዘግየት ተጠቂ የሆነ ሕጻን ለትኩረት ማጣትና ቅብጥብጥነት ሕመም (ADHD) ተጋላጭ ይሆናል።  ፍላጎትንና ስሜታዊ ግፊትን መግታት ይሳነዋል።  የስንፍናና አእምሮ ዝግመት ችግር ይገጥመዋል።  የትምህርት አቀባበል አቅም ችግር ይገጥመዋል።  በሒሳብ፣ በቋንቋ፣ በፍልስፍና ትምህርቶች፣ በእቅድ አወጣጥ ችሎታ… እውቀት ማዳበር ይከብደዋል። 

መፍትሔው ምንድን ነው? የተጐዳ የፊት ለፊት የአንጐል ክፍል /ኮርቴክስ እንዴት ይጠገን? 

ስትሮክ፣ ኢንፌክሽን፣ የነርቭ መበስበስ፣ ዕጢና ሌሎች በአንጐል ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች የአንጐልን የፊት ለፊት ክፍል ያጠቃሉ።  የፊት ለፊት ሎብ/ኮርቴክስ ሲጐዳ እውቀት፣ የጡንቻ እንቅስቃሴና ነርቮች ይዳከማሉ። የስሜት፣ የባህርይና የሰብዕና ለውጦች ይከሰታሉ። እንደ እድል ሆኖ የበርካታ ሰዎች አንጐል ሊያገግምና ሊሻሻል ይችላል። ባለሞያዎች አጋዥ ያሏቸውን ምክሮች እንደሚከተለው አስቀምጠዋል። 

ኃይል ጨማሪ ምግቦች መመገብ – ባቄላ፣ አረንጓዴ አትክልት፣ ቲማቲም፣ ሳልሞን፣ ቡና፣ ሻይ፣ ጥቁር ቸኮሌት፣… ኮርቴክስን እንደሚያሻሽሉ ታምኗል። 

ሙዚቃ የፊት ለፊት የአንግል ክፍልን ያነቃቃል – በኔዘርላንድስ የዩትሬሽት ዩኒቨርሲቲ የተመራማሪዎች ቡድን ባደረገው ፍተሻና በኒውሮሳይኮሎጂ መጽሔት ባሳተመው ሰነድ መሠረት ሙዚቃ የመስማት ችሎታን ያሻሽላል።  ከምግቦች በተጨማሪ ዐረፍተ ነገሮች፣ ጥቅሶችና ምሕፃረ ቃላትን ያስታውሱ፤ እንቆቅልሾችን ይፍቱ፣ ጨዋታ ይጫወቱ፤ ምግቦች ያዘጋጁ፤ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያድርጉ፤ አዘውትረው ያሰላስሉ፤ የእንቅልፍ መርሐ ግብር ይኑርዎ፣ አዲስ ነገር/ አዲስ ቋንቋ ይማሩ፣ ለማኅበረሰብዎ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይስጡ። ችግሩ ከቀጠለ የንግግር/የቋንቋ፣ የእውቀት (ኮግኒቲቭ)፣ የሥነልቦና፣ የቀዶ ሕክምና፣… ሕክምናዎች ያግኙ። 

ሕጻናትን በተመለከተ በሕክምናው ዘርፍ ያለው ሁኔታ ችግሩን መርዳት በሚያስችሉ ስልቶች ላይ ከማተኮር ይልቅ ለተጠቂ ሕጻናት አነቃቂ መድኃኒቶችን በማዘዝ ሥራ ላይ ተጠምዷል። እነዚህ መድኃኒቶች የፊትለፊት አንጎል በተሻለ ሁኔታ እንዲሠራ ቢያግዙም የአንጎልን እድገት ሊያሻሽሉ ግን እንደማይችሉ ታውቋል። 

ይህ አመዛዛኝ የአንጎል ክፍል ካልዳበረ የባህርይ ለውጥ ማምጣት የማይታሰብ ነው። ይህ የአንጐል ክፍል እንዲሻሻል የወላጆችና መምህራን ድርሻም ከፍተኛ ነው። በሥልጠና ታግዘው ሕጻናትን መርዳት ይችላሉ። አሳዛኙ ጉዳይ የሕጻናትን ችግር ባለመረዳት አካላዊ ቅጣትን እንደመፍትሔ መጠቀማቸው ነው። 

      መልካም፣ መልካሙን ለሕጻናት!                                                         ከአዘጋጁ፡ መምህር ሳህሉ ባዬ ዓለሙ፣ የሕፃናት አስተዳደግ ስፔሻሊስትና ፕሮጀክት ማናጀር ሲሆኑ፣ በትምህርት ዝግጅታቸው፣ ‹‹MA in Chid Development, BA in Psychology, MBA & IDPM in Project Management›› አግኝተዋል፡፡  ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] and/or [email protected]/ www.enrichmentcenters.org  ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles