በአቅም ማጣት ምክንያት በራቸውን ዘግተው የሚሰቃዩ የኩላሊት ሕሙማንን ለመታደግና ዘርፉ ላይ እየታየ ያለውን ችግር ለመቅረፍ በአንድ ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፍ ማዕከል ሊገነባ መሆኑን የኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት አስታወቀ፡፡
ድርጅቱ ይህንን ያስታወቀው ረቡዕ ሚያዝያ 12 ቀን 2014 ዓ.ም. ለማዕከሉ ግንባታ የሚውል 1,410 ካሬ ሜትር የቦታ ይዞታ ከመንግሥት በኩል መረከቡን ባስታወቀበት ወቅት ነው፡፡
ግንባታው ከሚያርፍበት ውጪ ያለው 410 ካሬ ሜትር ቦታ ለአረንጓዴ ልማት እንደሚውል በወቅቱ ተገልጿል፡፡
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰሎሞን አሰፋ እንደገለጹት፣ ማዕከሉን ለመገንባት አምስት ዓመታት ይፈጃል፡፡ እስከዚያው ግን ጊዜያዊ የሆነ ማዕከል በመገንባት የዲያሊሲስ (የኩላሊት እጥበት) አገልግሎት ለመስጠት ቅድሚያ ዝግጅት ተጠናቋል፡፡
የማዕከሉ ግንባታ ከጠናቀቀ በኋላ የሚከራዩ ሱቆች ይኖሩታል ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ከሱቆቹ የሚገኘው ገቢ ለኩላሊት ሕሙማን ድጋፍ ለማድረግ የሚውል መሆኑን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
ማዕከሉን ለመገንባት ከባንኮች በኩል ድጋፍ እንደሚደረግላቸው፣ አንድ ወለልም ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚጠይቅና ይህንንም ለማሳካት አብዛኛው ባንኮች ፈቃደኛ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ ሦስት ወለል ለየዲያሊሲስ ማዕከል እንደሚሆን፣ የተቀሩት ደግሞ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና መስጫና የሚከራዩ ሱቆች መሆናቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡
በማዕከሉ አገልግሎት የሚያገኙ ሕሙማን ልየታ በተመለከተም ከሆስፒታሎች ጋር ቅንጅት በመፍጠር የሚሠራ መሆኑን፣ ከፍተኛ ችግር ያጋጠማቸው ሕሙማን ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡
የሚገነባው ሕንፃ ከ17 እስከ 20 ወለል ይኖረዋል ተብሎ እንደሚታሰብ የተናገሩት አቶ ሰለሞን፣ ግንባታውን በአፋጣኝ ለመጨረስ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡
የኩላሊት ሕሙማንን ችግር ለመቅረፍ የሚሆኑ ማሽኖችን በምኒልክ ሆስፒታል በማስገባት አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ላይ መሆናቸውን፣ ይህም 120 የሚሆኑ ሕሙማችንን ችግር ያቃልላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡
የኩላሊት ሕሙማንን ችግር ለመቅረፍ ባንኮች ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው፣ እያንዳንዱ ባንክም አንድ፣ አንድ ወለል በማስገንባት ለኩላሊት ሕሙማን ተብሎ የሚከናወነውን የመንገድ ላይ ልመና ማስቀረት እንደሚቻል አክለዋል፡፡
የኩላሊት ንቅለ ተከላ ለማካሄድ አብዛኛው ሕሙማን እንደሚቸገሩ፣ ችግሩን ለመቅረፍ እንደ ዓይን ባንክ፤ ከሞተ ኩላሊት ይወሰድ የሚለውን ለማሳካት ማኅበሩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሚገነባው ማዕከል ከተጠናቀቀ በኋላ በርካታ የኩላሊት ሕሙማን ችግር ይቀረፋል የሚሉት አቶ ሰለሞን፣ በተለያዩ ክልሎች በበሽታው እየተሰቃዩ የሚገኙ ሕሙማን የገንዘብና የተለያዩ ድጋፎች ለማድረግ ምቹ አማራጭ ነው ብለዋል፡፡
ድርጅታቸውን በአሁኑ ወቅት በቋሚነት በየወሩ የሚደግፉ ባንኮች እንዳሉ፣ በሌሎች ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች የበኩላቸውን በመወጣት ብዙ ሕሙማንን ከሞት እንዲታደጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡