የእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ (ተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት) የሥነ ጥበብና የሙዚቃ ትምህርት ክፍል 335,000 ብር የሚያወጡ ልዩ ልዩ ዓይነት የሙዚቃ መሣሪያዎች ከእማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ የሙዚቃ ፋውንዴሽን ተበረከተለት፡፡
የኮሌጁን የሥነ ጥበብና የሙዚቃ ትምህርት ክፍል በማጠናከር ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሎ የታመነበትን ዕርዳታ የእማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ የሙዚቃ ፋውንዴሽን ማበርከቱን አስመልክቶ፣ የኮሌጁ የሆቴልና የቱሪዝም ዲፓርትመንት መምህር አቶ ይታየው ንጉሤ እንደገለጹት፣ በዕርዳታ ከተለገሱት የሙዚቃ መሣሪያዎች መካከል ቴነርና አልቶ የሚባሉ ሁለት ሳክስፎኖችና ድራም ፓድና ድራም ስቲክ፣ ሚክሰርና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
ኮሌጁ ዕርዳታውን ሊያገኝ የቻለው በኮሌጁ የቀድሞ ተማሪዎች ማኅበር አማካይነት ሲሆን፣ የዕርዳታው ርክክብ የተከናወነው የኮሌጁ ኃላፊዎች፣ አርቲስት ደበበ እሸቱን ጨምሮ የቀድሞ የኮሌጁ ተማሪዎችና የፋውንዴሽኑ ተወካዮች በተገኙበት ሥነ ሥርዓት ላይ ነው፡፡
ኮሌጁ በድምፅና በመሣሪያ (ቮካልና በኢንስትሩመንት) የታገዘ የሙዚቃ ትምህርት ለሦስት ዓመታት በደረጃ አራት አሠልጥኖ በዲፕሎማ እንደሚያስመርቅ፣ ወጣቶቹም እንደተመረቁ የሥራ ዕድል እንደሚያገኙ አንዳንዴም ከመመረቃቸው አስቀድሞ የሥራ ዕድል እንደሚመጣላቸው አቶ ይታየው ተናግረዋል፡፡
የእማሆይ ጽጌ ማርያም የሙዚቃ ፋውንዴሽን እ.ኤ.አ. በ2007 በቤተሰቦቻቸው የተመሠረተ ሲሆን፣ የልጆች የሙዚቃ ትምህርት ዕድል፣ የካምፕና ሌሎች አገልግሎቶች ይሰጣል፡፡