ኅብረተሰቡ በትንሣዔና በኢድ አልፈጥር በዓል ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል
አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ግምታቸው 6,588,139 ብር ወይም 176,517.39 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ ምግቦች ብልሽት የተገኘባቸው መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ፣ መድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
ነባር የምግብ ማምረቻ፣ ማከፋፈያ፣ አገልግሎት መስጫና የችርቻሮ ንግድ ሹቆች ላይ አሰሳ ያደረገ መሆኑን የገለጸው ባለሥልጣኑ፣ ቁጥጥር ከተደረገባቸው 26,843 ተቋማት ውስጥ 3,600 ላይ ዕርምጃ እንደተወሰደ ሚያዝያ 12 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡
ዕርምጃ ከተወሰደባቸው ውስጥ 3,291 የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ 195 የብቃት ማረጋገጫ ዕገዳ፣ ስድስት በሕግ የተጠየቁና 133 በገንዘብ የተቀጡ መሆናቸውን፣ በባለሥልጣኑ የምግብና መጠጥ ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግሥት በዳዳ ተናግረዋል፡፡
ብልሽት ከተገኘባቸው ምግቦች በተጨማሪ ግምታቸው 1,060,609 ብር የሆኑ ወይም 9,054 ብልሽት የነበራቸው የመጠጥ ዓይነቶች እንደተወገዱ ምክትል ዳይሬክተሯ አስረድተዋል፡፡
በተደረገው የውኃ፣ የምግብና የመጠጥ ናሙና ፍተሻ መሠረት ስምንት የምግብና አንድ የውኃ ድርጅቶች ላይ ችግር እንደተገኘባቸው የገለጹጹት ወ/ሮ ትዕግሥት፣ ዕርምጃ እንደተወሰደባቸው አክለዋል፡፡
ባለሥልጣኑ በበዓላት ሰሞን በሠራው አሰሳ መሠረት፣ ሕገወጥ እርድና ምንጫቸው ያልታወቁ ምርቶች ማግኘቱን፣ ብልሽት አምራቾች ያለባቸው ምግቦች አምርተው መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ታደሰ አጥላባቸው በበኩላቸው፣ በትንሳዔና በኢድ አልፈጥር በዓላት ወቅት ማኅበረሰቡ የምግብና መጠጥ ምርቶችን በጥንቃቄ መግዛት አለበት ብለዋል፡፡
በዚህም ኅብረተሰቡ ሕገወጥ ንግድና መሰል ያልተገባ ድርጊቶችን መከላከል እንዳለበት የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ሕግ ተላልፈው የሚገኙ ነጋዴዎችን በ8864 ነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዘርፉ ባሉ ሕገወጥ ድርጊቶች ተጎጂ የሚሆነው ማኅበረሰቡ መሆኑን የገለጹት አቶ ታደሰ፣ ማኅበረሰቡ አጥፊዎችን ማጋለጥ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡