Thursday, June 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርከዘመቻ ይልቅ አብዮት የሚሻው የከተማ ግብርና በአዲስ አበባ

ከዘመቻ ይልቅ አብዮት የሚሻው የከተማ ግብርና በአዲስ አበባ

ቀን:

በቶፊቅ ተማም

የከተማ ግብርና ጠባብና ውስን በሆነ ቦታ ላይ ዘመናዊ የአሠራር ዘዴ ቴክኖሎጂን በመጠቀም፣ በግልና በተደራጀ መንገድ በመሥራት የግብርና ምርትና ምርታማነት በመጠንና በጥራት ማሳደግ ነው፡፡ በሌላ በኩል በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወጣቶች ሴቶችና አዛውንቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ የሚያደርግ የሥራ ዘርፍ ነው፡፡ በአገራችን ኢትዮጵያ የከተሞች ዕድገትና ልማት ከአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ልማታዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ፈጥረው በከፍተኛ የለውጥ ሒደት ውስጥና  ልማት ላይ ካሉ ከተሞች መካከል ደግሞ አዲስ አበባ ተጠቃሽ ነች፡፡ የከተማ ግብርናን በማስፋፋትና በማጠናከር የከተማዋ ነዋሪዎች የራሳቸውን ፍጆታ እንዲሸፍኑና ገቢያቸውን እንዲያሻሽሉ በማድረግ፣ ጤንነቱና ደኅንነቱ የተጠበቀ የግብርና ምርት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻልና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይጨምራል፡፡

ከእዚሁ ጋር በተያያዘ የአገራችን ከተሞች በፈጣን ዕድገት ላይ የሚገኙ ከመሆናቸውም በላይ፣ የነዋሪውም ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ፍጥነት በመጨመር ላይ ነው፡፡ በከተሞች ያለው የመሠረተ ልማትና የኢንዱስትሪ መስፋፋት ሰፊ ሰው ኃይል ስለሚፈለግ፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጓል፡፡ ለዚህም መፍትሔ ለዜጎች የሥራ ዕድል ከሚፈጥርባቸው መስኮች መካከል አንዱ የከተማ ግብርና ነው፡፡ ይህን በመጠቀም የነዋሪውን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ማድረግ ካልተቻለ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል፡፡ በነገራችን ላይ የከተማ ግብርና ሲባል የብዙ የግብርና መስኮች ጥቅል ሲሆን፣ በዋነኛነት የሰብል ልማት (በተለይ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ)፣ የእንስሳት ዕርባታ፣ የንብ ማነብ፣ የዶሮ ዕርባታና የመሳሰሉት ሲያጠቃልል የእዚህ ጽሑፍ ዓላማ በተለይም የሰብል ልማት፣ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ላይ ያተኩራል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አብዛኞቹ ነዋሪዎች ይነስም ይብዛ ለከተማ ግብርና የሚሆን ቦታ ይዘው እንደሚገኙ ሲታወቅ፣ ይህን ሀብት በአግባቡ ለከተማ ግብርና መጠቀም አልተቻለም፡፡ ለዚህም በዋነኛነት የከተማ ግብርናን ከሰፋፊ መሬትና ከገጠር ጋር አያይዞ የማየት አመለካከት ሲሆን፣ ይህ አመለካከት በሒደት ከተቀየረና የከተማ ግብርናና እንደ ቢዝነስ ማሰብ ከተቻለና በግብርና እበለፅጋለሁ የሚል ትውልድ ከተፈጠረ፣ ከራስ አልፎ ለሌሎች መትረፍ እንደሚቻል ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ከተሞች ተሞክሮ መቅሰም ይቻላል፡፡ ከእነዚህም መካከል በምሥራቅ አፍሪካ የሚገኙት ኬንያና ኡጋንዳን ማንሳት ይቻላል፡

በተለይ ለከተማ ግብርና እንደ ዋነኛ ችግር ተደርጎ የሚወሰደው የመሬት ጉዳይ ቢሆንም፣ ዋናው የቁርጠኝነት ጉዳይ እንጂ ሰፋፊ መሬት ካላቸው ነዋሪዎች ጀምሮ የተለያዩ ቦታ ቆጣቢ የግብርና ዘዴዎችን ማለትም እንደ ሽቅብ እርሻ (Vertical Farming) በመጠቀም፣ በተለይ ለዕለት ፍጆታ የሚውሉ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ለማምረት ጥረት ማድረግ ያሻል፡፡ ከግለሰብ በዘለለ በተለይ የእምነት ቦታዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ አልፎ አልፎ አንዳንድ የመንግሥትና የግል ተቋማት ሰፋፊ ሊባል የሚችል ቦታ ይዘዋል፡፡ እነዚህን ለከተማ ግብርና ማስፋፊያነት በአግባቡ በመጠቀም በምግብ እህል ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ያግዛል፡፡ የከተማ ግብርናን በአግባቡ ተግብሮ ውጤታማ ለመሆን በተለይ የመጀመሪያ ደረጃና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ላይ መሥራት የሚያሻ ሲሆን፣ እንደ ሌሎች አገሮች የግብርና ትምህርት በትምህርት ካሪኩለም ውስጥ አካቶ መስጠት ባይቻል እንኳ፣ በአዲስ አበባ በሚገኙ ከ2,000 በላይ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በትምህርት ቤቶቻቸው ባሉ ክፍት ቦታዎች የጓሮ አትክልት እንዲያለሙ ሁኔታዎችን በማመቻቸት፣ ግብዓት በማቅረብ፣ በቂ ባለሙያ በመመደብ፣ ለከተማ ግብርና የተሻለ አተያይ እንዲኖራቸው በማድረግ የግብርና ክህሎት እንዲያሳድጉ ማድረግ ይቻላል፡፡ ከዚህ ባለፈም የከተማ ግብርና በትምህርት ቤት መተግበሩ ተማሪዎች በቤታቸው የጓሮ አትክልት መትከልና ማልማት ይለማመዳሉ፡፡ ትምህርት ቤቶች የከተማ የግብርና መረጃ የሚለዋወጡበት መድረክ ይሆናሉ፡፡ ትምህርት ቤቶች አሁን እንደሚታየው በጋራ በመሆን የፅዳት ሥራ፣ የጥያቄና የመልስ ውድድር፣ እንዲሁም የሥነ ጽሑፍና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ላይ  እንደሚሳተፉት ሁሉ በከተማ ግብርና እርስ በርስ የሚወዳደሩበት ዕድል ሲፈጠር ተማሪዎችም በከተማ ግብርና ዙሪያ ልምድ ይለዋወጡበታል፡፡

የከተማ ግብርና በአግባቡ ለማስከወን ሌላው አመቺ ሁኔታ በከተማው ያሉ ያለ ሥራ ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎች ሲሆኑ፣ የከተማ አስተዳደሩ ከዓመት ገደማ በፊት ታጥረው የቆዩ መሬቶች ለከተማ ግብርና ይውላሉ ቢልም ይህ ተግባራዊ ሳይሆን ቆይቷል፡፡ በእነዚህ ቦታዎች ላይ የከተማ ግብርና በተለይ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ቢተገበር እጅግ ውድ የሆነውን መሬት ፆም ከማደር ተርፎ፣ ብዙ ፆም የሚያድሩ የከተማዋ ነዋሪዎችን ከመመገብ በመለስ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ሊያስገኝ ይችላል፡፡ በእነዚህ ክፍት ቦታዎች የሚተገበር የከተማ ግብርና የከተማው ነዋሪ ስለከተማ ግብርና በቃል ከሚነገረው ባለፈ፣ በተግባር ተመልክቶ የተሻለ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ያስችለዋል፡፡

ይህን በማድረግም የአርሶ አደሩን ጫና መቀነስ ከቻልን አርሶ አደሩ ከጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ይልቅ፣ ሌሎች በከተማ የማይመረቱትን ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎና ሌሎች ሰብሎች ላይ ሙሉ ኃይሉን እንዲያውል ያስችለዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ሠርቶ ከተማውን ይመግብ የነበረው አርሶ አደር፣  አሁን ግን በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ፣ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ለግብርና የሚውሉ የቴክኖሎጂና ግብዓቶች ለማሟላት እጅ አጥሮታል፡፡ ከእዚህ ባለፈም አገራችን በአፈር መሸርሸርና መከላት፣ በደን ምንጠራ፣ በዝናብ እጥረትና በሌሎች እንቅስቃሴዎች ሳቢያ የአፈር ነባር ይዘት፣ ለምነትና ምርታማነት እያሽቆለቆለ ይገኛል፡፡ አርሶ አደሩም የአፈር ማዳበሪያ ላይ ጥገኛ ከሆነ በርካታ ዓመታት አልፈዋል፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት የማዳበሪያ ዋጋ ከሁለት እጥፍ በላይ መጨመሩ እየተጠቀሰ ሲሆን፣ የእዚህም ምክንያቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የማዳበሪያ ዋጋ መጨመሩ ነው፡፡ አርሶ አደሩ ለሌላው ሊተርፍ ቀርቶ ለራሱም ማዳበሪያ ገዝቶ መጠቀም ፈተና ሆኖበታል፡፡ ይህም በአገሪቱ የእህል ምርት መጠን ሲቀንስ ሸማች ማኅበረሰብ የምግብ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ለእዚህም ነው ከተሜው በከተማ ግብርና በሰፊው በመሰማራት የአርሶ አደሩን ጫና በማቃለል ሊያግዘው ይገባል የሚባለው፡፡

በግብርናው ዘርፍ ከተጋረጡ ችግሮች ለመውጣት አንዱ መፍትሔ የግብርና ባንክ ማቋቋም እንደሆነ የወሰነው መንግሥት፣ የግብርና ባንክ ለማቋቋም የቀረበውን ሐሳብ አፅድቋል፡፡ ባንኩ ሲቋቋም የብድር አገልግሎት በግብናው ዘርፍ ለተሰማሩ ዜጎች የሚሰጥ እንደሚሆን፣ አገልግሎቶችም ለዘር ብድር መስጠት፣ ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ ለዶሮ ዕርባታ፣ ለንብ ማነብ፣ ለከብት ዕርባታና ሌሎችም የከተማ ግብርና ዘርፎች መስጠት ብሎም የመድን ሽፋን መስጠት ነው፡፡ ከእዚህ ባለፈም የሚፈጥረው የሥራ ዕድል ቀላል የማይባል አዎንታዊ ሚና ይጫወታል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ የግብርና ባንክን በተመለከተ ለአብነት ያህል የጥቂት አገሮችን ተሞክሮ ብንመለከት፣ በሰሜን አሜሪካ የግብርና ባንኮች ከ80 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ሲፈጥሩ፣ የግብርና ሥራን የሚያቀላጥፉ ከ1,500 በላይ ባንኮችም አሏቸው፡፡ እነዚህ ባንኮች ትርፋማ መሆናቸውን መረጃዎች ሲያሳዩ፣ እነዚህ ባንኮች የአሜሪካ ገበሬዎች በተለያዩ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ችግሮች ምክንያት አደጋ ለሚጋለጡ ገበሬዎች ጥላና ከለላ መሆን ችለዋል፡፡

ጎረቤታችን ኬንያን ስንመለከት በግብርና ለተሰማሩ ዜጎቿ የተለያዩ የብድር አቅርቦት አማራጮችን ያቀረበች ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ በእንስሳት ዕርባታ ለተሰማሩ የሚሆን የፋይናንስ አቅርቦት (Livestock Loan)፣ ሌላኛው የብድር ዓይነት የሥራ ማስኬጃ ብድር (Working Capital Loan) ሲሆን የግብርና ውጤቶችን ለሚያቀነባብሩ (Agro Processors)፣ እንዲሁም የግብርናና የእንስሳት ሕክምና  መድኃኒት፣ መሣሪያዎች፣ ዘሮች፣ እንዲሁም የተለያዩ የላብራቶሪ ኬሚካሎች በማከፋፈል ላይ ለተሰማሩ (Agro Vets) ይሰጣሉ፡፡ ሌላው የሚሰጡት የሰብል ብድር (Crop Loan) ነው፡፡ ይህም ለሰብል ብዜትና ለአበባ ምርት ሲሆን፣ ከእዚህ በተጨማሪም ለግብርና ማስፋፊያ መሬት መግዣ፣ እንዲሁም የግብርና ማሽነሪዎች ለመግዛት የሚሰጥ የግብርና ልማት ብድር (Farm Development Loan) በዋናነት ሲጠቀስ፣ በኬንያ በጥቅሉ ከ30 በላይ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትና ባንኮች ከአርሶ አደሩ ጋር አብረው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሌላው የምናየው ተሞክሮ የህንድ ነው፡፡ በዓለማችን በሕዝብ ቁጥር ብዛት በሁለተኝነት ስትገኝ፣ የኢኮኖሚዋ የጀርባ አጥንት ለሆነው ግብርና በአገሪቱ ያሉ የፋይናንስ ተቋማት የገንዘብ ድጋፍና ብድር ይሰጣሉ፡፡ አገሪቱም ለግብርና ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የህንድ የግብርናና የገጠር ልማት ባንክ (National Bank of Agriculture and Rular Development) አቋቁማለች፡፡ ይህም የአገሪቱ በግብርና የተሰማሩ ዜጎች ለዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው፣ ለእርሻ ማሽነሪዎች፣ እንዲሁም ለመሬት ግዥ ለመግዛት ብሎም ለመጋዘን፣ ለእርሻ ማስፋፊያና ምርትን ወደ ገበያ ለማውጣት ብድር የሚያቀርቡ ሲሆን፣ ከዚህ ባፈም የአገሪቱ ገበሬዎች ከሚደርስባቸው መደበኛ ባልሆነ የብድር አገልገሎት ከሚፈጠረው ቀውስ ይታደጋሉ፡፡ ህንድ በርከት ያለ የግብርና ብድር ለመስጠትና ከገበሬው ጎን በመሠለፍ አብረው የሚሠሩ ባንኮች አሏት፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለይ በአሁኑ ወቅት ለከተማ ግብርና ትኩረት በመስጠት ባቋቋመው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን አማካይነት፣ የከተማ ግብርናን በማስፋፋትና በማጠናከር ነዋሪዎች ምግብ ከመሸመት ይልቅ የራሳቸውን ፍጆታ እንዲሸፍኑና ገቢያቸውን እንዲያሻሽሉ ይረዳል፡፡ ጤንነቱና ደኅንነቱ የተጠበቀ የግብርና ምርት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል፣ ብሎም በከተማው ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ሥራ እየሠራ ሲሆን፣ የከተማ አስተዳደሩ የበለጠ ለከተማ ግብርና ትኩረት እንዲሰጥ ያስገደደው ጉዳይ በዋነኛነት የከተማው ነዋሪ ቁጥር ከዕለት ዕለት መጨመር ነው፡፡ በእህል ፍላጎትና አቅርቦት ላይ በተፈጠረ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ሳቢያ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እጅግ ፈታኝ ሲሆን፣ ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን መረዳት እንደሚቻለው፣ በተለይ ባለፉት ዓመታት የምግብ ዋጋ ግሽበት ከሁለት አኃዝ በላይ ነው፡፡ በቅርብ ይፋ በተደረገ ጥናት ምግብ ነክ ያልሆኑና የምግብ ዋጋ ግሽበት እንዳጋጠመ ይታወቃል፡፡ ለአብነትም በሐረር የምግብ ዋጋ ግሽበት 49.9 በመቶ፣ በጋምቤላ 48.3 በመቶ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ 47.7 በመቶ፣ በአዲስ አባባ 35.9 በመቶ ግሽበት አሳይቷል፡፡ ለእዚህም የብሔራዊ ባንክ መረጃ እንደሚያሳየው  የብር የመግዛት አቅም በ28 በመቶ ገደማ ባለፉት አምስት ዓመታት መድከም (Devaluate) ማድረግ፣ አነስተኛ የእህል ምርት (Poor Yeild)፣ ብሎም በአገሪቱ ያለው የሰላም ዕጦት፣ የመንግሥት ድጎማ መቀነስና በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ መጨመር በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡

የከተማ ግብርናን በተመለከተ የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ወደኋላ የቀረችበት ሌላው ጉዳይ ቢኖር፣ የከተማ ግብርና ዕውቀትን በተለይ ለወጣቶች በአግባቡ በማስረፅ የግብርና ቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ማዕከል አለመኖር በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ ከአገሪቱ የሕዝብ ቁጥር ከፍተኛ ድርሻ ያለውን ወጣት በከተማ ግብርና ዙሪያ በቂ ዕውቀት ክህሎትና ዕውቀት እንዲኖረው ለቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ መሥራት ያሻል፡፡ በተለይም በከተማ አካባቢ ግብርና በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ዘርፍ ብዙ ትኩረት ያልተሰጠውና ወጣቶች የማይሳቡበት ሆኖ ይታያል፡፡ ይህን የአመለካከት ችግር ለመቅረፍ  ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የግብርና ቴክኒክና ሙያ ወጣቶች የሚሳቡበት እንዲሆን ከፍተኛ ሥራዎች ሊሠሩ ይገባል፡፡ ይህንን የከተማ ግብርና ጉዳይ የመንግሥት ብቻ ተደርጎ መወሰድ የሌለበት ሲሆን፣ በተለይ የግሉ ዘርፍ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ በኢትዮጵያ ካሉ ከ1,600 በላይ የቴክኒክና የሙያ ማሠልጠኛ ተቋማት መካከል 50 በመቶ የሚሆኑት የግል ናቸው፡፡ በግል የቴክኒክና የሙያ ሥልጠና ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ፊታቸውን ወደ ከተማ ግብርና በማዞር፣ በዘርፉ የሠለጠነ ባለሙያ በማፍራት የበኩላቸውን አገራዊ ሚና ሊወጡ ይገባል፡፡ ሌሎች በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች በከተማ ግብርና የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ለሚወስዱ ሠልጣኞች በግል ባለሀብቶች በተቋቋሙ የግብርና ማቀነባበሪያ እንዲሁም በግሉ ዘርፍ በለሙ ማሳዎች፣ የከብትና የዶሮ ዕርባታዎች በቂ የተግባር ልምምድ (Apparenteciep) ማዘጋጀት፣ ብሎም ከሥልጠና በኋላ የሥራ ዕድል የማመቻቸት አገራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡

ሌላው ካለፉት ዓመታት ወዲህ በመንግሥት ደረጃ ለቴክኒክና ሙያ ሰፊ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ሲሆን፣ በተለይ ከአጠቃላይ የትምህርት ዘርፍ  በጀት አሥር በመቶ እንዲመደብ ቢደረግም ለግብርና ቴክኒክና ሙያ የተሰጠው ድጋፍ እጅግ አነሳ (Under Funding of ATVET) ነው፡፡ ይህም ሊቀረፍ ሲገባ ከበጀት ባለፈ የግብርና ቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ኮሌጆች ቁጥር መጨመር ያሻል፡፡ ለእዚህም ማሳያ አዲስ አበባ ውስጥ ካሉ በርካታ የመንግሥት የቴክኒክና የሙያ ማሠልጠኛ ኮሌጆች ውስጥ ሦስቱ ብቻ የከተማ ግብርናን ለመስጠት እንቅስቃሴ እያደረጉ ሲሆን፣ በከተማው ረዘም ያለ ዕድሜ ያላቸውና በተለያዩ መስኮች ብዙ ምሩቃንን ያፈሩ እንደ ተግባረ ዕድ፣ ጄኔራል ዊንጌትና ንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ በመሳሰሉት ኮሌጆች የከተማ ግብርና አለመሰጠቱ ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን መገንዘብ ያስችለናል፡፡ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት በቀጣይ በሙያው በቂ ልምድና ያላቸውን መምህራን መመደብና አቅም ማጎልበት ተግባራት በማከናወን፣ ሥራ  ላይ ላሉና ወደፊት ለሚከፈቱ የግብርና ቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋማትን በአቅም ማጠናከር ይገባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአብዛኛው በግብርናም ሆነ በከተማ ግብርና ዙሪያ የሚሠሩ ጥናቶች ከዩኒቨርሲቲዎች የሚወጡ ሲሆን፣ ይህንን በማሻሻል የቴክኒክና የሙያ ማሠልጠኛ ማዕከላትን የጥናትና የምርምር ማዕከል በማድረግ ችግር ፈቺ የምርምር ውጤቶች በከተማ ግብርና ዙሪያ መውጣት ይኖርባቸዋል፡፡

ከላይ በመጠኑም ቢሆን ያነሳናቸውን የከተማ ግብርናን የተመለከቱ ሐሳቦች ግባቸውን ይመቱ ዘንድ፣ እንዲሁም የከተማ ግብርናን በኅብረተሰቡ ውስጥ ባህል ሆኖ እንዲሰርፅ፣ በተጨማሪም የግብርና ዕውቀት ሽግግር ተግባራዊ እንዲሆን የላቀ ሚና የሚጫወቱ የመገናኛ ብዙኃን መሆናቸው አሌ የማይባል እውነት ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ በዋነኛነት የግብርና መረጃን ማሠራጨት፣ ብሎም ክትትልና ድጋፍ ማድረግ የግብርና ባለሙያ በተለይም በግብርና ኤክስቴንሽን ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች ላይ ቢሆንም፣ ከከተማ ሕዝብ ቁጥር ብዛትና ከተጠቃሚነት አንፃር በግብርና ኤክስቴንሽን ብቻ ሊሸፈን እንደማይችል ይታመናል፡፡ በዚህም ሳቢያ የመገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም በግብርናም ሆነ በከተማ ግብርና ዙሪያ መረጃዎች በአግባቡ ማሠራጨት የሚገባ ሲሆን፣ በአገራችን ታላላቅ ግብርናን የተመለከቱ ጉዳዮች ብቻ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን አውታሮች የዜና ሽፋን ከመስጠት ባሻገር፣ እንዲሁም እጅግ ጥቂት በሆኑ ሚዲያዎች ብቻ ግብርና ላይ አተኩሮ የሚሠራ ሚዲያዎች ከመኖር ባለፈ፣ ግብርናው ላይ በጥልቀት የሚሠራ ሚዲያ እንደ አገር የለም፡፡ ይህንንም ክፍተት ለመሙላት እንደ ሌሎች አገሮች በተሌቪዥን ግብርናና ግብርና ነክ ፕሮግራሞችን በስፋት አየር ላይ አውሎ እንዴት በከተማ ግብርና የበለጠ ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል በተግባር የተደገፈና የተሻለ ልምድ ካላቸው ልምድ የሚቀሰምበት፣ ወቅታዊና ሳይንሳዊ መረጃዎች ያካተተ ፕሮግራም፣ እንዲሁም ከተመልካቾች ለሚመጡ ግብርና ነክ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥበት ፕሮግራም መሥራት ያሻል፡፡

ሌሎች የከተማ ግብርና የመረጃ ማሠራጫ ዜዴ የሚሆኑት ጋዜጣና መጽሔት ሲሆኑ፣ እንደ ሌሎች አገሮች የከተማ ግብርናውን በተመለከተ የራሱ የሆነ መጽሔት ማዘጋጀት ቢቻል ጥቅሙ የጎላ ነው፡፡ ለዚህም እንደ አብነት የኬንያውን (The Organic Farmer) መሰል መጽሔቶች በማዘጋጀት እንዴት አድርገን በከተማ ግብርና ተጠቀሚ መሆን እንደምንችል፣ በገበያ ውስጥ ስላሉ አዳዲስ የከተማ ግብርና ቴክኖሎጂዎች፣ እንዴት ጤናማ የሆነ ምርት ማምረት እንደሚቻል፣ በእንስሳትና በሰብሎች ላይ ስለሚከሰቱ በሽታዎችና መድኃኒታቸው፣ ስለግብርና ሥራ ፈጠራ  (Agriprenuership) መረጃ የሚሰጥበትና የግብርና ተግባቦት የሚጨምርበት ማድረግ ይቻላል፡፡ የአገራችን የፕሬስ ኢንዱስትሪ ባጣር ላይ ቢሆንም ልክ እንደ መጽሔቱ ሁሉ በእርግጥ በጋዜጣም ቢሆን በተወሰነ ደረጃ የከተማ ግብርናን አስመልክቶ ቋሚ የሆነ ዓምድ አዘጋጅቶ በከተማ ግብርና ዙሪያ የተለያዩ ሥራዎች ቢሠሩ፣ የራሱ የሆነ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡ ለእዚህም የኬንያውን ዘ ስታንዳርድ፣ ዴይሊ ኔሽንና የኡጋንዳውን ደይሊ ሞኒተር መመልከት ይቻላል፡፡

ከጋዜጣና መጽሔት በዘለለ የወቅቱን የመረጃ ማስተላለፊያ መሣሪያ የሆነውን ማኅበራዊ ሚዲያን ስንመለከት፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይ ወጣቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ እየሆነ ከመምጣቱ አንፃር አሁን አሁን እየተሠሩ ካሉ ኢኮኖሚያዊም ሆኑ ማኅበራዊ ፋይዳቸው አናሳ ከሆኑ መዝናኛው ዓለም ላይ ብቻ ከተንጠለጠሉ ዝግጅቶች ወጣ ማለት ያስፈልጋል፡፡ የከተማ ግብርናን አስመልክቶ በተለይ ከግብርና ባለሙያዎች ጋር በመሆን ስለከተማ ግብርና በተግባር የተደገፈ ዝግጅት በማዘጋጀትና በማቅረብ ለወጣቱ ተደራሽ ማድረግ፣ ወጣቱን ወደ ከተማ ግብርና ለመሳብ ላቅ ያለ ሚና እንደሚጫወት ዕሙን ነው፡፡ ይህንንም ለማሳካት በተለይ በግብርና ዙሪያ የሚሠሩ ተቋማት ትኩረት ሰጥተው የከተማ ግብርናን በደንብ በማኅበራዊ ሚዲያው ሊያስተዋውቁ፣ ብሎም በከተማ ግብርና ዙሪያ በተለይ ወጣቱን ሊያነቁት ይገባል፡፡ ይህም የከተማ ግብርና ያለውን ዕምቅ አቅም ተገንዝቦ የሥራ ዕድል የሚያገኝበትን፣ ስለግብርና ግብዓቶች፣ ስለውጤታማ የሰብል አያያዝና አመራረት፣ ውጤታማ የእንስሳት ርቢ፣ ወቅታዊ የግብርና የገበያ መረጃ፣ በግብርና ውጤቶች ላይ እሴት ስለመጨመር፣ እንዲሁም ለግብርናው ዘርፍ ስለሚሰጡ የፋይናንስ አገልግሎቶችን በተመለከተ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ ያስችለዋል፡፡

ከእዚሁ ከማኅበራዊ ሚዲያ ጋር በተያያዘ በአሁኑ ጊዜ እጅግ ቀላል የማይባል ቁጥር ያለው በተለይ በከተሞች የዘመኑ የቴክኖሎጂ በረከት የሆነውን ኢንትርኔት ተጠቃሚ ቢሆንም፣ በተለይ ወጣቱ በመዝናኛውና ረብ የለሽ በሆኑ ፕሮግራሞች ላይ ወድ የሆነውን ጊዜ እያባከነ ነው፡፡ ወጣቱ ቆም ብሎ በማሰብ ዘመኑ የሰጠውን ዕድል በአግባቡ በመጠቀም ስለከተማ ግብርና ያለውን ዕውቀትና አተያይ በማሻሻል ራሱን ተጠቃሚ ሊያደርግ ይገባል፡፡ የከተማ ግብርናን አስመልክቶ በጣም ጥቂት ወጣቶች ያላቸውን ልምድ ለማካፈል ጥረት እያደረጉ ቢገኝም፣ የሠሯቸውን ቪዲዮዎች ከአንድ ሺሕ በላይ ዕይታ ያላቸውን ፕሮግራሞች ፈልጎ ማግኘት አዳጋች ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ወጣቶች ሥራቸውን በማየት ‹‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ›› እንዲሉ እነሱንም እያበረታቱ ስለከተማ ግብርና በቂ ዕውቀት ማገኘት ይቻላል፡፡ ከእዚሁ ከማኅበራዊ ሚዲያ ሳንወጣ ከወራት በፊት በግብርና ሚኒስቴርና በዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን የተዘጋጀ እጅግ ጥሩ አስተማሪ ‹‹የከተማ ግብርና በእጅ ያለ ወርቅ›› የተሰኘ ዶክመንተሪ፣ በጥር 2014 ዓ.ም. በዋልታ ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ገጽ ቢለቀቅም እስከ ሚያዝያ አጋማሽ ድረስ የነበረው ተመልካች ከአንድ ሺሕ አልዘለለም፡፡ ለዚህም ነው የከተማ ግብርና እውነትም በእጅ ያለ ወርቅ እንድንል የሚያስገድደን፡፡

ማጠቃለያ

በከተማ ግብርና ዙሪያ በዋነኛነት ሊሠራ የሚገባው ጉዳይ ቢኖር፣ የከተማ ግብርና ከሰፊ መሬትና ከገጠር ጋር የተያዘውን አስተሳሰብ መግራት ነው፡፡ ይህንን ለማድረግም ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ሲያሻ፣ ከከተማ ግብርና ትምህርት ቤቶች ባለፈ በተለይ በመንግሥት ተቋማት የሠርቶ ማሳያ ቦታዎች በማዘጋጀት፣ ለአብነትም እንደ ፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት ድርጅት የተጀመሩ ጅምሮች ወደ ሌሎች ተቋማት ማስፋት፣ በሠራተኛው ዘንድ የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት ጥሩ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ ሌላው የከተማ አስተዳደሩ ሊሠራ የሚገባ ጉዳይ ሰፋፊ መሬቶች አጥሮ ከማስቀመጥ ይልቅ፣ አስቸኳይ ውሳኔ ሰጥቶ ወደ ከተማ ግብርና ልማት ማስገባት ይጠበቅበታል፡፡ በአገሪቱ በአብዛኛው ዝግና አካታች ያልሆነውን የከተማ ግብርናን አካታች ወደሆነ የፋይናንስ ሥርዓት እንዲዘረጋ ማድረግ፣ የከተማ ግብርና በተለይ በወጣቱ እንደ ሌሎች ሙያዎች ወዶና ፈቅዶ እንዲገባ የግብርና ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ማስፋፋትና መደገፍ፣ በፌዴራል ደረጃ በአሥር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ውስጥ በአግባቡ ያልተካተተውን የከተማ ግብርና በአግባቡ አጢኖ በልዩ ሁኔታ ለከተማ ግብርና የራሱ የሆነ ዕቅድ ማዘጋጀት፣ የከተማ ግብርና ተግባቦትን በተመለከተም አሁን ከሚታየው ጭላንጭል የሚዲያ ሽፋን በዘለለ ሚዲያው በአግባቡ አጀንዳ አድርጎ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩም ለከተማው ግብርና ፈታኝ የሆኑ የግብርና ግብዓቶች፣ የመሥሪያ ቦታ፣ የመሬትና የውኃ እጥረት፣ በተለይ በእንስሳት አርቢ ለተሰማሩ ዜጎች ማነቆ የሆነውን የመኖ ዋጋ መናር የሚያመጣውን ጫና ለመቀነስ የድጎማ ሥርዓት ማበጀት፣ የቅንጅት ሥርዓት ውሱንነትና ሌሎች ማነቆዎችን ለመፍታት በቁርጠኝነት መሥራት ከከተማ አስተዳደሩ ይጠበቃል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...

ማን ይቻለን?

በጠዋት የተሳፈርንበት ታክሲ ውስጥ በተከፈተው ሬዲዮ፣ ‹‹ይኼኛው ተራራ ያን...