Friday, September 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መሪና ተመሪ!

እነሆ መንገድ! ከቄራ ወደ ሜክሲኮ ልንጓዝ ነው። ከፊሉ በተንቧቸንበት ጎዳና ላይ ሲሮጥ፣ ከፊሉ ጉልበት ሳይከዳው ኑሮ ከብልኃቱ አልገናኝ ብሎት በጉብዝናው ወራት እያዘገመ ይጓዛል። ሩቅ ማሰብ፣ ነገን ማብሰልሰል፣ የዛሬን ሰላምና እርጋታ ያውካል። መንገድ ነውና ሰው መሆን በዘመናት ሒደት ሊፈታ ያልቻለ ታላቅ ሚስጥር ነውና ሕፃን አዋቂው ‘የዛሬ መንገዴ የት ያደርሰኝ ይሆን?’ ብሎ ሲርበተበት ገጹ ላይ ይነበባል። በመኖር ብዙ ያስተዋሉ፣ ያሳለፉ፣ ክፉና ደግ ዕይታቸውን የለጠጠው አዛውንቶችና ጎልማሶች ጭንቀትና ሐሳብ የሚያጠወልጋቸውን ወጣቶች እያዩ ትናንትናቸው ውስጥ የተልከሰከሱ ሀቆችን በመገረም እያሰሉ ወዲያ ወዲህ ይላሉ። ያለፉበትን ጎዳና ሌላ ትውልድ፣ ሌላ አዲስ ፍጥረት በገዛ ራሱ ተሞክሮ እየዳሰሰ ሲያጣጥመው ሲያዩ፣ የሕይወት እንቆቅልሽ በዕድሜ ብዛት ጭምር የማይፈታ መሆኑን የሚገነዘቡ ይመስላሉ። መጪ ሂያጁን፣ መተላለፊያ ሰርጡን ሳይቀር ላጠና የሚመዘው ዕውቀት አያጣም። ከሚስተዋለው ትዕይንት በስተጀርባ የሚዘውረን ኃይል ሊሰጠን ያልሳሳው ነገር ቢኖር፣ በትዝብት የሚሰባሰብ የመረጃ ዕውቀት ሳይሆን አይቀርም። ጎዳናው በተመላላሹ የሐሳብ መጉላላት ተደበላልቋል። ይህ የሰው ልጅ መባዘን መስከኛው መቼ ይሆን? መልሱ የማይገደውን መጠየቅ ይቻላል!

‹‹ምንድነው? ቶሎ ቶሎ ግቡ እንጂ! የቡፌ ሠልፍ አስመሰላችሁት እኮ! ሰዓት የለንም!›› ሾፌራችን ይንጨረጨራል። ‹‹ስንቸኩል ስድብ! ስንሰክን ተረብ! ምን እንሁን እሺ!›› አንዲት መለሎ ለወዳጇ ሾፌሩን ታማለታለች። ሁላችንም እንድንሰማት ድምጿን ታጎላለች። ‹‹ኧረ ቀስ በይ እባክሽ አንቺ ሴት። ዓይን ውስጥ መግባት ስትወጂ?›› ትላለች ወዳጅዋ ተሳቃ። ‹‹አይ አንቺ ይኼ ሁሉ ሰው ዓይን ስላለው ብቻ የሚያይ ይመስልሻል? እንደዚያማ ቢሆን ምነው በአደባባይ ቀማኛውና ጉቦኛው ሲበዛ የሚጮህ ሰው የጠፋ?›› ትላትና ጥርሷን ትነክሳለች። ‹‹ቢሆንም ዝምታን የመሰለ ነገር የለም። እግዜር ከሚሰጠን ይልቅ ዝምታ የሚሰጠን ዕድሜ ነው ተሽሎ የተገኘው፤›› ወዳጇ ትመልሳለች። ‹‹እኮ ዝምታ? ምነው ለእኔ ነፈገኝ ታዲያ? አንድም ሲያደኸየኝና ሲያመኝ ኖረ። ባል ተብዬው ከቀን ቀን ይሻለዋል እያልኩ ዝም ብዬ ብኖር ይኼው በላዬ ላይ ቤቴን በዕዳ አሸጠው። ይኼን ያህል ዘመን ተለጉሜ ዛሬ መሳቂያ ሆንኩ። ተይኝ እስኪ! ሰው ዕድሜ ልኩን ሰው ሳይሆን ይኖራል?›› አለቻትና ወዲያው መሀል መቀመጫ ላይ ገብተው አጠገብ ላጠገብ ተቀመጡ።

‹‹ጉድ ነው ዘንድሮ! አሁን ይህች ሴት አዕምሮዋ ጤነኛ ነው ትላለህ? በቁሙ የሚሞተውና በጤናው የሚያብደው እኮ በዛ፤›› ብሎ ደግሞ አንድ ጋዜጣ የያዘ ወጣት ዞሮ ያናግረኛል። ወዲያ ወያላው ‹‹ተንቀራፈፋችሁ…›› እያለ ሾፌሩን ተከትሎ ይወርድብናል። ‹‹ደርሰው የጊዜ ጠበቃ ሲመስሉ እውነት አይመስልም? አስመሳይ ሁላ . . .›› ይላል የጋቢናውን በር የሚከፍት ጎልማሳ። ‹‹መተው ነው እንጂ በስንቱ ተቃጥለን እንችለዋለን? የፖለቲከኛውን፣ የአክቲቪስት ተብዬውን፣ የአገልግሎት ሰጪውን፣ የአላፊ አግዳሚውን የታይታ አመል ከቆጠርንማ ማበዳችን ነው፤›› ስትል ደግሞ ጎልማሳውን አስቀድማ ጋቢና የምትንጠላጠል ወይዘሮ ትናገራለች። ያም ያም የመሰለውን እየተናገረ ይሳፈራል። በተለያየ ዕቅድና ጉዳይ አንድ አቅጣጫ ያገናኘን መንገደኞች፣ ባገኘናት ዕድል ሁሉ ለመተንፈስ እንሽቀዳደማለን። የእሽቅድምድም ዓለም! 

ጉዟችን ተጀምሯል። ከሾፌሩ ጀርባ አሁንም አሁንም ከንፈሩን የሚነክስ ጎልማሳና ሻሽ ያሰረች የቤት እመቤት ተሰይመዋል። ሦስተኛው መቀመጫ ላይ ከተሠለፉ ጀምረው ስልካቸው ላይ የተተከሉ ወጣቶች ተቀምጠዋል። መጨረሻ ወንበር እኔን ጨምሮ ጋዜጣ ይዞ የነበረው ወጣት ጋዜጣውን በትኖ እያነበበ፣ ከሴት ልጃቸው ጋር ከጣራው በላይ የሚስቁ ተጫዋች አዛውንት በስተቀኝ ተቀምጠው መንገዱ ሲወዘውዘን እየተወዘወዝን፣ ሲያነጥረን እየነጠርን እንጓዛለን። ወያላው፣ ‹‹ሒሳብ ወጣ! ወጣ! በቅድሚያ ግን በዶላርና በዩሮ የማንቀበል መሆናችንን እናስታውቃለን፤›› ይላል። ‹‹ፈርሞ መሄድስ ይቻላል?›› ትለዋለች ቤቴ በዕዳ ተሸጠ ብላ ነገር ዓለሙን ንቃ በነፃነት ያሻትን የምትናገረው ሴት። ‹‹መፈረምና ማፅደቅ የአገር መሪዎች ተግባር እንጂ፣ መቼም ቢሆን የሒሳብ አሰባሰባችን ሥልት ሆኖ አያውቅም። ጨዋታው በ‘ካሽ’ ብቻ ነው፤›› ይላል ወያላው እየሳቀ። ‹‹ሥልጣን ቢኖረኝ ኖሮ አንተን ነበር የፖለቲከኞች መሰብሰቢያ አዳራሽ ንግግር እንድታደርግ የምጋብዝህ፤›› ስትለው ወያላው እየሳቀ አንገቱን ያቀረቅራል። ስንቱ አንገቱን ማቀርቀር እንደጀመረ ግን አለመጠየቅ ይሻላል፡፡

አጠገቤ የተሰየሙት አዛውንት ጣልቃ ገቡ። ‹‹መሪዎቹ ራሳቸው መቼ ተናግረው አበቁና ነው ተመሪዎቹ የሚናገሩት? አገር በትምህርትና በዕውቀት እንጂ በንግግር የምትነቃ ይመስል ቢሉት አይታክታቸውም። የታከታቸውም ዓለም እየታዘባቸው እንቅልፋቸውን ይቀጫሉ። ዕድሜ ልካችንን አንድ ዓይነት መልክና አቋም እያየን ዴሞክራሲያዊት አፍሪካን ዕውን እናደርጋለን ይሉናል። እኛ ተውን እንጂ አድርጉልን አላልን። ፈረደብን እኮ!›› እያሉ ሳለ ከበድ ያለ ሳል ንግግራቸውን አቋረጣቸው። ወዲያ ደግሞ ሻሽ ያሰረችው የቤት እመቤት ጎልማሳውን ጠጋ ብላ፣ ‹‹እኔንስ ገላግለውኛል። ይኼው ሦስት ረባሽ ልጆቼን አደብ የማስገዛቸው በፖለቲካ መሪዎችና በተወካዮች ምክር ቤት አፍዛዥ ስብሰባ ነው፤›› አለችው። ጎልማሳው ግራ ገብቶት ‹‹አልገባኝም?›› ሲላት፣ ‹‹አንድ ጥፋት ሲያጠፉ ሦስቱንም ቴሌቪዥን ፊት አስቀምጥና ቀድቼ የማስቀምጣቸውን የፖለቲከኞችን ወይም የተመራጮችን ስብሰባ መክፈት ነው። አምስት ደቂቃ ሳይቆዩ በያሉበት ሲፈነገሉ የእኔ ሥራ ጋቢ መደረብ ብቻ ይሆናል። አልዘየድኩም ታዲያ?›› ትለዋለች። አምርሬያለሁ ብሎ ከሚያሾፍብን በላይ አሾፍኩ ብሎ የሚያመረው ባሰ እንዴ?

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ጥቂት ቀደም ብሎ ሦስተኛው ረድፍ ላይ ማውራት የማይቦዝኑ ወጣቶችን ወያላው ተክቷል። የቀደምነው ተሰለቻችተን ነው መሰል ዝምታችን ያስፈራል። ሁለቱ በስሜት የሚጫወቱትን እናዳምጣለን። ‹‹እኔ እኮ የሰላምና የዴሞክራሲ ቱርፋት ነው የሚባለው ለሐሳብ የበላይነት ለምን እንደማንጥር ነው የማይገባኝ። ‘አገር ምድሩ ለሐሳብ የበላይነት ቅድሚያ በመስጠት በነፃነት መነጋገር አለበት በተባለ ማግሥት፣ እርስ በርስ ተከባብረን በሠለጠነ መንገድ መነጋገር ሲገባን የተለመደው ጉልበተኝነትና ማስፈራራት፣ ዛቻና ድንፋታ ነው የሚሰማው። ዕድገቱም የጋራ ውድቀቱም የጋራ’ የሚለን እኮ ነው የናፈቀን። ሁሉም ነፃ አውጪ ነኝ እያለ በመታበይ አገር ማመስ እንጂ ለአገር የሚጠቅም መቼ ሲያበረክት ይታወቃል?›› ሲል ጥግ ላይ የተቀመጠው ደግሞ፣ ‹‹መቼ ነውን’ አሁን ደውዬ በ ‘ኤፍ ኤም’ እጋብዝሃለሁ። መቼም ሐሳብ ከማዋጣት ዘፈን መጋበዝ የሚቀልበት አገር ሆኗል፤›› ይለዋል። አገር የመደዴዎች መጫወቻ ስትሆን ግን ያስቆጫል፡፡

‹‹ታዲያስ ገንዘባችን ብቻ መሰለህ መቅኖ ያጣው? እኛም ጭምር ነን እኮ፤›› ይላል ጥግ ያለው መልሶ። ‹‹ኧረ ተረጋጉ መብራት እንዳትጥሱ!›› ሲሉ ደግሞ አዛውንቱ አጠገቤ የተቀመጠው ወጣት፣ ‹‹ሰው ተገኘ እያለ ይኼን የተወጋ መጠጥ ይልፍ ይልፍና ማታ በሞቅታ የጀመረውን ፈንጂ መርገጥ ቀንም ይቀጥለዋል። እንዲያው ምን ይሻላል?›› ይለኛል። ወዲያው ታክሲያችን ጥጓን ያዘችና ቆመች። ወያላው ‹‹መጨረሻ›› ብሎ በሩን በረገደው። ተራችንን እየጠበቅን ሁላችንም እስክንወርድ አላስችል ያለው ወያላ፣ ‹‹ዛሬ ሰው ምን ሆኗል? ሥራ ያለን ሰዎች እኮ ነን አፍጥኑት እንጂ!›› ብሎ ሲያበቃ፣ ‹‹እዚህ እዚያ ተፍ ተፍ ብለን ባኖርናችሁ ደግሞ ትጀነኑብናላችሁ?›› አለን በግልምጫ። እኛም ወደ ቀጣይ ጉዟችን ተበታተንን። ግራ ተጋብተው ግራ የሚያጋቡን ሲበዙ ምን ይባላል? ከመሪ እስከ ተመሪ ግራ ከገባን እኮ ያሠጋል፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት