Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 143 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ሰበሰበ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት ከዕቅዱ በላይ ውጤት በማስመዝገብ 143 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ የቻለ ቢሆንም፣ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ ለማሰባሰብ ያቀደው ተቀማጭ ገንዘብ ግን የዕቅዱን ያህል እንዳልሆነ ተመለከተ፡፡ 

ባንኩ የ2014 ዓ.ም. የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸሙን አስመልክቶ ይፋ ባደረገው መረጃ እንደሚጠቁመው፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ 135.2 ቢሊዮን ብር እሰበስባለሁ ብሎ አቅዶ ነበር፡፡ በተጨባጭ ማሰባሰብ የቻለው ግን ከዕቅዱ በላይ 143.8 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም የዕቅዱን 132 በመቶ ማሳካት መቻሉን የባንኩ ሪፖርት አመላክቷል፡፡ ሆኖም በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ማሰባሰብ እችላለሁ ብሎ አቅዶት ከነበረው 16.6 ቢሊዮን ብር ውስጥ ማሳካት የቻለው 12.7 ቢሊዮን ብር በመሆኑ ከዕቅዱ ወደ አራት ቢሊዮን ብር ያነሰ አፈጻጸም ያስመዘገበበት ሆኗል፡፡ 

ባንኩ ካሰባሰበው ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለውን ተቀማጭ ገንዘብ ያገኘው ከግለሰብ ቆጣቢዎች ነው፡፡ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከግለሰብ ቆጣቢዎች 87.1 ቢሊዮን ብር ማሰባሰብ ችሏል፡፡ ከሕዝባዊና መንግሥታዊ ተቋማት ማሰባሰብ የቻለው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ደግሞ 58.5 ቢሊዮን ብር መሆኑን የሚጠቅሰው የባንኩ መረጃ፣ ከወለድ ነፃ ባንክ (ሲቢኢ ኑር) ቁጠባ ደግሞ 12.7 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም ከኅብረት ሥራ ማኅበራት አንድ ቢሊዮን ብር አዲስ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰቡን አመልክቷል፡፡

ባንኩ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከፍተኛ አፈጻጸም ካሳየባቸው ክንውኖች መካከል በገቢ ደረጃ ያስመዘገበው ውጤት ነው፡፡ በባንኩ መረጃ መሠረት በዘጠኝ ወራት ውስጥ አገኛለሁ ብሎ ያቀደው 64.8 ቢሊዮን ብር ገቢ ሲሆን፣ አፈጻጸሙ ግን 86.01 ቢሊዮን ብር ሆኗል፡፡ ይህም አቅዶት ከነበረው ገቢ ከ22 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው ነው፡፡ በዘጠኝ ወራት ያገኘው ገቢ ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም የ54 በመቶ ብልጫ እንዳለው ይኼው የባንኩ መረጃ ያስረዳል፡፡ 

በአንፃሩ ግን የባንኩ ወጪም እየጨመረ ስለመምጣቱ ከሪፖርቱ መገንዘብ የተቻለ ሲሆን፣ በባንኩ መረጃ መሠረት ባለፉት በዘጠኝ ወራት ውስጥ ያወጣው ወጪ 67.9 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህም በዘጠኝ ወራት አወጣዋለሁ ብሎ ካቀደው 140 በመቶ ነው፡፡ ይህ ወጪ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ የ60 በመቶ ብልጫ እንዳለው መረጃው ያመለክታል፡፡ 

ባንኩ በዘጠኝ ወራት ካስመዘገበው የሥራ ውጤትም ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት 18.07 ቢሊዮን ብር ማትረፉን አስታውቋል፡፡ ባንኩ በ2014 የሒሳብ ዓመት ያስመዘገበው የትርፍ መጠን ከቀዳሚው ዓመት የ35 በመቶ ብልጫ ያለው ሲሆን፣ ከዕቅዱ አንፃር ደግሞ ከ1.37 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው፡፡ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ዘጠኝ ወራት አተርፋለሁ ብሎ ያቀደው 16.7 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች