Wednesday, September 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኢትዮ ኢንጂነሪንግ የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ሠራተኞች የደመወዝ ጥያቄ አልተመለሰልንም አሉ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ሠራተኞች ሥራ አቁመው እንደነበር ይናገራሉ

የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ሠራተኞች ላቀረቡት የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄ በአጭር ጊዜ ምላሽ ይሰጣችኋል ተብለው የነበረ ቢሆንም እስካሁን እየጠበቁ መሆኑን ገለጹ፡፡

ከሦስት ሳምንታት በፊት ሠራተኞች ለአራት ቀናት አካባቢ ሥራ ካቆሙ በኋላ፣ የበላይ አካላት መጥተው ጥያቄያቸውን እንደተቀበሉ ሠራተኞቹ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የቀድሞው ሜቴክ የአሁኑ ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው የተሾሙት ምስጋኑ አረጋ (አምባሳደር) ከሳምንታት በፊት በቦታው ተገኝተው ሠራተኞቹን ማነጋገራቸውን፣ የደመወዝ ጥያቄውን ለመመለስ አዲስ አደረጃጀት እንደሚደረግም ቃል ገብተው እንደነበረ ተገልጿል፡፡

የኢትዮ ኢንጂነሪንግ የሕዝብ ግንኙነት ሞላልኝ ከሰተብርሃን ‹‹ሠራተኞች እንደ ማንኛውም ሰው የደመወዝ ጭማሪ አቅርበዋል፣ የሥራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን ግን አላውቅም፤›› ብለዋል፡፡

ቢሾፍቱ ኢንጂነሪንግ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶችን የሚገጣጥም ሲሆን በአሁኑ ጊዜ 40 አውቶቡሶች እየተጠናቀቁ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ፋብሪካው ከሦስት ሺሕ በላይ ሠራተኞች የነበሩት ሲሆን፣ ከዓመት በፊት ግማሾቹን ቀንሶ አሁን 1,500 ገደማ ሠራተኞች እንዳሉት ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ባደረገው አዲስ አደረጃጀት ደመወዝ አስተካክሎ የነበረ ሲሆን፣ የተጨመረላቸውም የተቀነሰባቸውም አሉ፡፡ በ2007 ዓ.ም. በፋብሪካው ተቀጥራ ለሰባት ዓመት የሠራችው ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገች ሠራተኛ 3,500 የተጣራ ደመወዝና 400 ብር የምግብ ክፍያ ማግኘቷን ትናገራለች፡፡

ፋብሪካው ከአንድ እስከ 16 የደረጃ ደመወዝ ዕርከኖች ሲኖሩት፣ ‹‹ያኔ የተደረገው ማስተካከያ በቂ አይደለም፡፡ ቦነስና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችም አግኝተን አናውቅም፤›› ብላለች፡፡

ፋብሪካው የልማት ድርጅት በመሆኑ የደመወዝ ጭማሪና ጥቅማ ጥቅም የሚያደርገው ትርፍ ሲያስመዘግብ ብቻ መሆኑን፣ ይህም ማለት ቢሾፍቱ ኢንጂነሪንግ ብቻ ሳይሆን ዘጠኙም በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ሥር ያሉት ፋብሪካዎች ትርፍ ሲያስመዘግቡ እንደሚሰጡ ነው የሚነገረው፡፡

በተያዘው ዓመት የመጀመርያ መንፈቅ ኪሳራ ካስመዘገቡት አራት የልማት ድርጅቶች ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ አንዱ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች