Thursday, November 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኤክስፖርት ቡና ሰውረዋል የተባሉ አሽከርካሪዎች ምርመራ እየተደረገባቸው ነውበኤልያስ ተገኝ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከቡና የሽኝት ጣቢያዎች የወሰዱትን ቡና ወደ ኤክስፖርት ማዘጋጃና ማከማቻ ሳያደርሱ ተሰውረዋል የተባሉ አሽከርካሪዎች ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነ ተገለጸ፡፡ የኤክስፖርት ቡናው ተጭነውባቸው የነበሩ 18 ተሽከርካሪዎችም ተይዘዋል፡፡

በጉዳዩ የተጠረጠሩ ግለሰቦች በፌዴራል ፖሊስ በቁጥጥር ሥር እንደሚገኙ የተነገረ ሲሆን፣ ስድስት ተሽከርካሪዎች ደግሞ ከ77 ቶን በላይ የሚደርስ የኤክስፖርት ቡና ጭነው የነበሩ ተሽከርካሪዎች መያዛቸው ታውቋል፡፡

በግለሰቦቹ የተሰወረው ቡና ትክክለኛ መጠን 77.7 ቶን ቡና እንደሆነ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን፣ ግምታዊ ዋጋው 311,080 ሺሕ ዶላር ወይም ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ አገሪቱ በትክክለኛው መንገድ ቡና ወደ ውጪ ልካ ልታገኝ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ የሚያሰናክሉ መሆናቸውን ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡

የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ያበለፀገውን ሶፍትዌር ሥራ ካስጀመረ በኋላ በተደረገ የማመሳከር ሥራ፣ ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ 18 ተሽከርካሪዎች የቡና መሰወር ድርጊት እንደተፈጸመባቸው ተገልጿል፡፡

በሶፍትዌሩ የተሰወረውን የኤክስፖርት ቡና የመለየት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፣ እያንዳንዱ ተሽከርካሪ ቡናውን ከወሰደበት ወደ የሚፈለገው ሥራ ማድረስ አለማድረሱን ይለያል ተብሏል፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው የላላ የቁጥጥር ሥርዓት ሳቢያ በአብዛኛው ተሽከርካሪዎች በትክክል የት እንደደረሱ እንደማይታወቅ፣ ይህም በዋናነት ከኮንትሮባንድ ጋር ከሚፈጸም ድርጊት ጋር የሚያያዝ እንደሆነ የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች ሰኞ ግንቦት 8 ቀን 2014 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

ሶፍትዌሩ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ኤክስፖርት መዳረሻ ድረስ እያንዳንዱ ቡና በተለይም ከባለሥልጣኑ የሽኝት ጣቢያ ማዕከላት ጀምሮ እስከ የኤክስፖርት ማዘጋጃና ማከማቻ ድረስ ምን አለ? የሚለውን ነገር በደንብ ተከታትሎ (Tracking) የሚመዘግብ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የሾፌር ስም፣ የተሽከርካሪ የሰሌዳ ቁጥር፣ ቡናው ወደ የትኛው ማዘጋጃ እንደሚሸኝ፣ የአቅራቢና የተቀባይ እያንዳንዱን መረጃ በዝርዝር የሚያመላክት ሲስተም እንደሆነ ባለሥልጣኑ ገልጿል፡፡

በኬላ ላይ ብቻ ሳይሆን በጉምሩክ ኮሚሽን የሚተገበር እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ እያንዳንዱ ተመዝግቦ የወጣ ቡና የኤክስፖርት ማዘጋጃና መከማቻ ደርሷል ወይስ አልደረሰም የሚለውን መረጃ ከኮሚሽኑ በመውሰድ የማመሳከር ሥራ (ባላንስ) እንደሚሠራ ተነግሯል፡፡

ባለፉት ሦስት ወራት የነበረው ማመሳከር እንደታየ የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህም ቡና አምጥተው ግን ወደ ማዘጋጃና ማከማቻ ያላስገቡ (መርካቶ ያስገቡ) አካላት ለሕግ እንዲቀርቡ መደረጉን፣ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን የገበያ ልማትና ቁጥጥር ዘርፍ ምክትል ዳይሬክትር አቶ ሻፊ ዑመር አስታውቀዋል፡፡

ድርጊት ፈጻሚዎቹ (ኮንትሮባንዲስቶቹ) ያሉበት አካባቢ የተለያየ እንደሆነ ተገልጾ፣ በተለይም በምዕራብ የአገሪቱ ክፍል ቴፒና ቦንጋ አካባቢ የሚገኙ የሽኝት ጣቢያዎች ላይ እንደሚበዙ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡ ድርጊቱ በሌሎች አካባቢዎች ቢበዛም በምዕራብ አካባቢዎች በስፋት የሚስተዋል እንደሆነ ተነግሯል፡፡

በሌላ በኩል ባለፉት አሥር ወራት ውስጥ በባለሥልጣኑ ከተከናወኑ ሥራዎች አገራዊ የግብረ ኃይልን የማጠናከር ሥራ አንዱ እንደሆነ ተጠቁሞ፣ ደራሽ ቁጥጥር በማድረግ ቡና እንዳይባክን ማድረግ ሌላው እንደሆነ አቶ ሻፊ አስረድተዋል፡፡

ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከጉምሩክ ኮሚሽን፣ ከአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ፣ ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ፣ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና ከሲዳማ ክልሎች ጋር የተቀናጀ ኮሚቴ በማዋቀር ቁጥጥር መከናወኑ ተመላክቷል፡፡

በቁጥጥሩም ከአራት ክልሎች 60 ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱ የተገለጸ ሲሆን፣ የቡናና ሻይ ባለሥልጣንን የግብይት መመርያ ከተላለፉ አካላት ከሚተላለፈው የሁለት በመቶና የአምስት በመቶ ቅጣት ዓይነቶች 23 ሚሊዮን ብር በአጠቃላይ 83 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል ተብሏል፡፡ የተገኘው ገቢ በዝርዝር ሲታይ ከኦሮሚያ 31 ሚሊዮን ብር፣ ከደቡብ ክልል 14 ሚሊዮን ብር፣ ከሲዳማ ክልል ሦስት ሚሊዮን ብር፣ ከደቡብ ምዕራብ 11 ሚሊዮን ብር ለመንግሥት ገቢ መደረጉ ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ በአሥር ወራት ብቻ 231 ሺሕ ቶን ቡና ልካ 1.014 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ገልጸው፣ በቀሪዎቹ ሁለት ወራት ይህንን ገቢ ወደ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

ለዘርፉ ዕድገት ማነቆ የነበሩትን በግብይቱና ልማቱ ላይ ያሉ ችግሮች ነቅሶ በማውጣት በአሥር ወራት ውስጥ ከፍተኛ ገቢ ተገኝቷል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በዓመቱ መጨረሻም 300 ሺሕ ቶን የሚደርስ ቡና ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ እንደምታቀርብ አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች