Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለሥራ ፈጣሪዎች ከዋስትና ውጪ ብድር መስጠት የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

አዋሽ ባንክ የፈጠራ ባለቤቶች ቢዝነሳቸውን ከግብ ለማድረስ የፋይናንስ ድጋፍና ከዋስትና ውጪ እስከ አምስት ሚሊዮን ብር የሚደርስ ብድር ለመስጠት የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ አደረገ፡፡

ከትናንት በስቲያ በሸራተን አዲስ ፕሮጀክቱ ይፋ በተደረገበት ወቅት የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው እንደገለጹት፣ ይህ አዳዲስ የሥራ ፈጠራ ባለቤቶችን ለማበረታታት በባንኩ የተቀረፀው የሥራ ፈጠራ ውድድር ፕሮጀክትም ‹ታታሪዎቹ› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ውድድሩም አዳዲስ የሥራ ፈጠራ ክህሎት ኖሯቸው፣ በፋይናንስ እጥረት ምክንያት ተግባራዊ ማድረግ ያልቻሉ በርካታ ሥራ ፈጣሪዎችን እንደሚያነሳሳም አመልክተዋል፡፡

‹ታታሪዎቹ› የሥራ ፈጠራ ውድድር መርሐ ግብር በዋነኛነት ሦስት የሥራ ፈጣሪዎችን ተግዳሮቶች ማለትም የክህሎት፣ የሥራ መነሻ ካፒታልና የዘላቂ ብድር አቅርቦት ችግሮችን ለመቅረፍ ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ ነውም ብለዋል፡፡  

በዚህ የሥራ ፈጠራ ውድድር ላይ አዳዲስና ችግር ፈቺ የሆኑ የሥራ ሐሳቦች ያላቸው ሁሉም የአገራችን ዜጎች የሚሳተፉበት ሲሆን፣ የሥራ ፈጠራ ሐሳባቸውንም፣ በእንግሊዝኛና በአማርኛ ወይም በአፋን ኦሮሞ ማቅረብ በውድድሩ የሚሳተፉ እንደሚሆን ባንኩ አስታውቋል፡፡

የፕሮጀክቱ ተግባራትን በተመለከተ ከተሰጠ ተጨማሪ መረጃ መረዳት እንደሚቻለው፣ በዚህ ውድድር በመጀመርያው ዙር አንድ ሺሕ ተወዳዳሪዎች ይመረጣሉ፡፡ ከዚያም እነዚህ ዕጩ ተወዳዳሪዎች በሁሉም ክልሎች በተመረጡ የሥልጠና ማዕከላት፣ እንዲሁም በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች የክህሎት ሥልጠና በመውሰድ ለቀጣይ ውድድሮች እንደሚቀርቡ ይደረጋል፡፡

ከእነዚህ መካከል ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፉት 100 ተወዳዳሪዎች ተጨማሪ ሥልጠናዎች ተሰጥቷቸው የሥራ ፈጠራ ሐሳባቸውን አሻሽለው እንዲያቀርቡ ከተደረገ በኋላ የፕሮጀክት ሐሳባቸው ለዚሁ ሥራ በተመረጡ ዳኞች እንዲገመገም ይደረጋል ተብሏል፡፡  በዳኞች ውሳኔ መሠረት ምርጥ አሥር ተወዳዳሪዎች ለቀጣዩ ዙር የሚያልፉ ሲሆን፣ የተቀሩት ደግሞ ገንዘብና ሰርተፍኬት ይሰጣቸዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ለቀጣዩ ዙር ካለፉት አሥር ምርጥ ተወዳዳሪዎች ውስጥ የተሻለ  የፕሮጀክት ሐሳብ የሚያቀርቡ አምስት ተወዳዳሪዎች ለቀጣይ የመጨረሻው ዙር ውድድር ሲያልፉ፣ የተቀሩት አምስቱ ደግሞ የገንዘብ ድጋፍና ሰርተፍኬት ይሰጣቸዋል ተብሏል፡፡

እንደ ባንኩ መረጃ በመጨረሻው ዙር ከአንደኛ እስከ አምስተኛ የሚወጡት ተወዳዳሪዎች የሚያገኙትን ድጋፍ በተመለከተ እንደተገለጸው፣ አንደኛ የወጣ ተወዳዳሪ ፕሮጀክቱን ተግባራዊ የሚያደርግበት የአንድ ሚሊዮን ብር የገንዘብ ሽልማትና ቢዝነሱን የሚያስቀጥልበት እስከ አምስት ሚሊዮን ብር ከዋስትና ውጪ የብድር አገልግሎት ይሰጠዋል ተብሏል፡፡ ‹‹በተመሳሳይ ሁኔታ በውድድሩ ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ የሚወጡት ተወዳዳሪዎችም ጠቀም ያለ የገንዘብ ሽልማትና የቢዝነስ ሐሳባቸውን ተግባራዊ የሚያደርጉበት ከዋስትና ውጪ የብድር አገልግሎት የሚመቻችላቸው ይሆናል፤›› ብሏል፡፡

በዚህ ፕሮጀክት የማስጀመርያ ፕሮግራም ላይ የተገኙት የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ ባንኩ ስትራቴጂካል የሆነ ያልተቋረጠ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ጭምር ያግዘዋል ያሉትን ይህንን ፕሮጀክት አድንቀው፣ ሌሎች የፋይናንስ ተቋማትም በተመሳሳይ መንገድ ቢቀጥሉ ብዙዎችን መድረስ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ሐሳብ ማስያዣ መሆን የሚችበት አገር እንዲሆን እፈልጋለሁ፤›› ያሉት ሚኒስትሯ፣ የሥራ ፈጠራና ሐሳብ ወደ ተግባር እንዲለወጥ የፋይናንስ ተቋማት በዚህ መንገድ ይጓዙ ዘንድም ተመኝተዋል፡፡ እንዲህ ባለው ሐሳብ የበለጠ ትርጉም የሚኖረው ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ታክለው ብዙ ኢንተርፕረነሮችን ማፍራት እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች