የሶማሊያ ምርጫ በሰላም ተጠናቋል፡፡ ጥብቅ ጥበቃ በሚካሄድበት የአውሮፕላን ማረፊያ አዳራሽ/መጋዘን ውስጥ በተደረገው የእሑዱ ምርጫ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ በከፍተኛ አብላጫ ድምፅ ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድን (ፎርማጆ) ማሸነፋቸው ተረጋግጧል፡፡ የ66 ዓመቱ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ በመጨረሻው ሦስተኛ ዙር የመለያ ምርጫ 214 ለ110 ነበር ተቀናቃኛቸውን ያሸነፉት፡፡ ሰውየው ከዚህ ቀደምም እ.ኤ.አ. በ2017 ከፎርማጆ ጋር ተፎካክረው በመሸነፍ ሥልጣን መልቀቃቸው የሚታወስ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. ከ2012 እስከ 2017 ድረስ የመሯትን ሶማሊያን ዳግም ለመምራት የአሁኑ ድል መንገዱን ጠርጎላቸዋል፡፡
የሶማሊያ ምርጫ ሒደት እሑድ ዕለት እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ በቴሌቪዥን ቀጥታ ሥርጭት ሲተላለፍ ነበር፡፡ ለምርጫው ሒደት ሰላማዊነት ሲባል የእንቅስቃሴ ገደብ በመታወጁ፣ ሁሉም ሶማሊያዊያን በየቤታቸው ሆነው ነበር የምርጫውን ውጤት የተጠባበቁት፡፡ በሞቃዲሾ ከተማ በዕለቱ መጠነኛ ፍንዳታ ተከሰተ ቢባልም፣ ከተማይቱ ሰላማዊ ሆና ነበር የዋለችው፡፡ የምርጫው ውጤት እኩለ ሌሊት ሲታወጅ ግን በደስታ የፈነጠዙ የሀሰን ሼክ መሐመድ ደጋፊዎች የሞቃዲሾን ጎዳና አጥለቀለቋት፡፡ ፕሬዚዳንት ፎርማጆ አምባገነን ሆነዋል ሲሉና ሲቃወሟቸው የነበሩ ሁሉ ደስታቸውን አብረው ገለጹ፡፡ አንዳንዶች ምርጫውን ‹‹ፕሬዚዳንታዊ ሳልቫጅ ነው›› ቢሉትም፣ ብዙዎች ግን በሀሰን ሼክ መሐመድ እንደገና ወደ ሥልጣን መመለስ አዲስ ተስፋና አዲስ ምኞት መሰነቃቸው አልቀረም፡፡
የእሳቸውን መመረጥ አንዳንድ ሶማሊያዊያን ‹‹ከበጣም መጥፎ መጥፎውን እንደ መምረጥ ነው›› ብለው ጨለምተኛ በሆነ መንገድ ቢገልጹትም፣ ነገር ግን ብዙዎች በተስፋና በደስታ ነው የተቀበሉት፡፡ ሀሰን ሼክ እንደተመረጡ ባሰሙት ንግግርም፣ ‹‹የዛሬ አምስት ዓመት ለተቀናቃኜ ሥልጣን ባስረከብኩበት በዚህ አዳራሽ እንደገና ስለተመረጥኩ ደስ ብሎኛል፡፡ አገራችንን የተረጋጋች ሆና ወደ ዕድገት ጎዳና እንድትገባ ሁላችንም ተባብረን መሥራት ይኖርብናል፤›› ሲሉ ነበር አንድነትን የሚጋብዝ መንፈስ ያለው መልዕክት ያስተላለፉት፡፡ ሀሰን ሼክ እንዳሉት ሶማሊያ በእሳቸው ዘመን ወደ መረጋጋትና ወደ ልማት ትመጣለች ወይ? የሚለው ብዙ ያነጋግራል፡፡ ሰውየው ከአገራቸው አልፈው በቀጣናው ላይ የሚፈጥሩት የጂኦፖለቲካ ተፅዕኖም ቢሆን ከወዲሁ እያነጋገረ ነው የሚገኘው፡፡
ይህን በሚመለከት ለሪፖርተር አስተያየት የሰጡ የሶማሊያን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉ ባለሙያዎች የተለያየ ሐሳብ ነው የሰነዘሩት፡፡ ባለፈው ቅዳሜ በአንድ የጥናት መድረክ ላይ ‹‹በፈተና የተሞላው የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት አማራጮች›› የሚል ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረበውና የምሥራቅ አፍሪካን ጉዳይ ሲከታተል የቆየው ጋዜጠኛ ፍትሕ አወቅ የወንድወሰን፣ የፋርማጆ መሸነፍና የሀሰን ሼክ መመረጥ የተለየ ጂኦፖለቲካዊ ለውጥ እንደማያመጣ ይናገራል፡፡
‹‹የሀሰን ሼክ መሐመድ መመረጥ በአንዴ ቀጣናዊ የጂኦፖለቲካ ሁኔታ ላይ የተለየ ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ምናልባት ከኬንያ ጋር ያለው የሶማሊያ ግንኙነት በብዙ መንገድ ይለወጥ ይሆናል እንጂ፣ ከኢትዮጵያ ጋር የተለየ ግንኙነት አይከሰትም፡፡ በሶማሊያ ማንም ወደ ሥልጣን ሲመጣ የሚጠብቀው ፈተና ይታወቃል፡፡ ሶማሊያ ልክ እንደ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የተለያዩ ግዛቶችን አሰባስባ አገር የመሆን ባህሪ የሚታይባት አገር ናት፡፡ ዋናው የፌዴራል መንግሥት አቅሙ በሞቃዲሾ አካባቢ የተወሰነና የግዛት መንግሥታት ጠንካራ ገቢና ጉልበት ያላቸው ናቸው፡፡ ሰውየው ክልሎችን አስተባብሮ በአንድነት አግባብቶ መምራት የመቻል ከባድ ኃላፊነት ይጠብቃቸዋል፡፡ እንደ ማዶቤ ዓይነት ጠንካራ አመራሮች ያላቸው ኃይለኛ ግዛቶች በምርጫው መራዘም፣ እንዲሁም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተፈጠረው ውዝግብ የተለየ አሠላለፍ የያዙበት ሁኔታ አለ፡፡ እነዚህን አንድ ማድረግና ከምዕራባዊያን ጋር የተፈጠረውን የግንኙነት መላላት ማጠናከር ከሰውየው የሚጠበቅ ነው፤›› ሲል የገለጸው ጋዜጠኛው፣ ከዚህ በተለየ ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖር የግንኙነት ለውጥ አለመኖሩን ያብራራል፣
‹‹የሶማሊያን የቅርብ ጊዜ ታሪክ ካየን በተግባር የሶማሊያ መሪዎች ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ግንኙነት ነው የነበራቸው፡፡ ፎርማጆም ሆነ ሀሰን ሼክ ብቻ ሳይሆኑ ከእነሱ በፊት የነበረው ሼክ ሸሪፍ ሼክ አህመድ የሚባለው የኢስላማዊ ፍርድ ቤት የሚባለው ቡድን አባል ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ግንኙነት መመሥረት አስፈላጊ መሆኑን በተግባር አሳይተዋል፤›› ሲል የሚያክለው ጋዜጠኛው፣ ማንም በሞቃዲሾ ቤተ መንግሥት ቢሰየም የኢትዮጵያ ተፅዕኖም ሆነ አገሪቱ ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖራት ግንኙነት በቀላሉ እንደማይቀየር ነው ግምቱን ያስቀመጠው፡፡
ከእሱ ሐሳብ ጋር በመጠኑ የሚቃረን ሐሳብ የሚያነሳው በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆነው ኡስማን መሐመድ አህመድ በበኩሉ፣ በሶማሊያ አዲስ ፕሬዚዳንት መመረጡ ለኢትዮጵያም ሆነ ለምሥራቅ አፍሪካ ብዙ ለውጥ እንደሚያመጣና የተሻለ ነገር እንደሚፈጠር እምነት እንዳለው ያስረዳል፡፡
‹‹አንደኛ የፎርማጆ የውጭ ግንኙነት ልዝብ አልነበረም፡፡ ሁለተኛ በኢኮኖሚ መስክ ደግሞ የዓለም ንግድ ድርጅት ሳይቀር ብዙ ተቃውሞ የሚያነሳበት የንግድ ግንኙነት ነው የነበራቸው፡፡ የሀሰን ሼክ መሐመድ መመረጥ ምናልባት በፀጥታና በደኅንነት ላይ በጎ ሁኔታን ባይፈጥርም፣ ነገር ግን በቀጣናዊና በአገራዊ ፖለቲካም ሆነ በንግድ ላይ የተሻለ ተፅዕኖ ይፈጥራል ብዬ ነው የምገምተው፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት የሶማሊያ መንግሥት (የፎርማጆ አስተዳደር) ከኢትዮጵያና ከኤርትራ ጋር ጠንካራ ግንኙነት ቢፈጥርም፣ ነገር ግን ከሌሎች ጋር ሁለንተናዊ ግንኙነት በመፍጠር ረገድ ብዙ ድክመት ነበረበት፡፡ በአንድ በኩል ደግሞ በፀጥታ አያያዝ ረገድ ፎርማጆ የተሻለ ውጤታማነት ነው ያሳየው፡፡ ይህን የፎርማጆን ውጤታማነት ሀሰን ሼክ ይማርበታል የሚል ግምት ያለኝ ሲሆን፣ ደካማ በሆነባቸው ጉዳዮች ደግሞ ማሻሻያዎችን ያደርጋል ብዬ እጠብቃለሁ፤›› ሲሉ የፖለቲካ መምህሩ ኡስማን ይናገራል፡፡
ሁለቱን የሚቃረን ሐሳብ ያለው በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህሩና በማኅበራዊ ሚዲያ ዓምደኝነቱ የሚታወቀው ሙክታር ኡስማን በበኩሉ፣ የአዲሱ ፕሬዚዳንት ወደ ሥልጣን መምጣት ትልቅ ጂኦፖለቲካዊ ተፅዕኖ አለው ይላል፡፡
‹‹ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ኢሳያስ አፈወርቂና ፎርማጆ በፈጠሩት ጥምረት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን መግባባትና ስምምነት አሜሪካኖቹ ስላልወደዱት ፎርማጆን ጠምደው በመያዝ ከሥልጣን ለማስወገድ ሲሠሩ ነበር፣ ይህም ተሳክቶላቸዋል፡፡ የፎርማጆ በምርጫ መሸነፍና ሀሰን ሼክ መሐመድ ወደ ሥልጣን መምጣታቸው ይህን የሦስትዮሽ ወዳጅነት የሚያደናቅፍ ነው፡፡ ሀሰን ሼክ መሐመድ ወዴት እንደሚሄዱ አይታወቅም፡፡ ነገር ግን ሰውየው ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ከነበረው ሕወሓት መራሽ መንግሥት ጋር ጠንካራ ግንኙነት የነበራቸው ሰው መሆናቸው መረሳት የለበትም፡፡ ከዚህ ውጪ እኔም ሆንኩ ሌሎች ጉዳዩን በቅርበት መከታተልና መመርመር ይኖርብናል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው የሰውየውን ፖለቲካዊ ዝንባሌ በትክክል ማስቀመጥ የሚቻለው፤›› በማለት ነው ሙክታር ኡስማን ሐሳቡን ያጠቃለለው፡፡
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህመት የሶማሊያ ምርጫን በስኬት መጠናቀቅ በማድነቅ ለተመራጩ ፕሬዚዳንት የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ተሰናባቹን ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆንም ላሳዩት ጠንካራ አመራርና ለዴሞክራሲ ላላቸው ቁርጠኝነት አድናቆት በመቸር፣ የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ የሽግግር ሰላም አስከባሪ ጦር ለአገሪቱ መረጋጋት ያልተቆጠበ ድጋፍ እንደሚያደርግ በማረጋገጥ ሊቀመንበሩ በመግለጫቸው አጋርነትን አሳይተዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሶማሊያ ወኪል ጀምስ ስዋን የምርጫውን ሒደት በተመለከተ ባወጡት መግለጫ፣ ‹‹ፉክክር የታየበትን ምርጫ እንደግፋለን፤›› ብለዋል፡፡ በምርጫው ሒደት አሸናፊ ለሆኑት ሀሰን ሼክ መሐመድ ብቻ ሳይሆን፣ ሽንፈታቸውን በፀጋ ተቀብለው ለተመራጩ ድጋፋቸውን ላሳዩት ለተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ለፎርማጆም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ አድናቆት እንዳለው ነው ተወካዩ በመግለጫቸው ይፋ ያደረጉት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በጎ ምኞታቸውን ለተመራጩ ፕሬዚዳንት ባስተላለፉበት አጭር መልዕክት፣ ከአዲሱ ፕሬዚዳንት ጋር በሁለትዮሽና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ተባብሮ ለመሥራት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ ይህንኑ የኢትዮጵያን በጎ ምኞትና ተቀራርቦ የመሥራት ፍላጎት ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በይፋ ባወጣው መግለጫ ደግሞ አስተጋብቶታል፡፡ ከኢትዮጵያ ውጪ በቀጣናው ያሉ ሶማሊያን የሚጎራበቱ አገሮችም ሆነ በቅርብም ሆኑ በሩቅ ያሉ በቀጣናው ልዩ የጂኦፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው አገሮችና ወገኖች በየፊናቸው መልካም ምኞትና ተባብሮ የመሥራት ፍላጎታቸውን ለተመራጩ መሪ እያስተላለፉ ነው፡፡ ሆኖም ቀጣናውን በቅርበት የሚከታተሉ አንዳንድ ወገኖች አዲሱ ፕሬዚዳንት ወዴት ያዘነበለና የማንን ፍላጎት ያስቀደመ ፖሊሲ እንደሚከተሉ ግልጽ አለመሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡
ጋዜጠኛ ፍትሕ አወቅ፣ ‹‹አዲሱ ፕሬዚዳንት በዓለም አቀፍ ተቋማት የሠሩና በሰብዓዊ መብት ተሟጋችነታቸው የሚጠቀሱ ሰው ናቸው፤›› ይላል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ እንዲሁም በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም ደሳለኝ የሥልጣን ዘመን ለንደን የሶማሊያ ጉዳይን ባስተናገደ ጉባዔ ላይ ለዘገባ መካፈሉን፣ ከአዲስ አበባ ወደ ለንደን ሁለት ጊዜ ከሀሰን ሼክ መሐመድ ጋር መጓዙን ጋዜጠኛ ያስታውሳል፡፡ በእነዚህ መድረኮች ላይ የሰውየው ምሁራዊ ምልከታም ሆነ ግንኙነት የመፍጠር ሁኔታ የሚደነቅ ሆኖ እንዳገኘውም ይናገራል፡፡
‹‹መጀመርያ ላይ ሰውየው ቁጥብ ቢሆኑም፣ ነገር ግን በሒደት ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ያላትን ጉልህ አስተዋጽኦ ተረድተው አመለካከታቸውን ለውጠዋል፡፡ ኢትዮጵያ ሶማሊያን ለማጠናከር ስትተጋ ኬንያዊያን በኪስማዩ ወደብ የተከማቸ ከሰል ሲሸጡ ነበር፡፡ አንዳንዶች የሀሰን ሼክ መሐመድን መመረጥ ለራሳቸው የሚጠቅም ሊያስመስሉት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የሶማሊያ መሪዎች የኢትዮጵያ መንግሥት አሁንም ድረስ ጠንካራ ዕገዛ ለአገራቸው እያደረገ መሆኑን ይረሳሉ ማለት መሳሳት ነው፡፡ ሶማሊያዊያን ከሶማሌ ክልል ጋር ጠንካራ ግንኙነት ለመመሥረት አሁን መልካም አጋጣሚ እንዳላቸውም አንርሳ፤›› በማለት የሚናገረው ጋዜጠኛው፣ የአሁኑ መሪም ቀጣናውን በተለይ ኢትዮጵያን ያስቀደመ ፖሊሲ ይከተላሉ የሚል ግምት እንዳለው ይናገራል፡፡
የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ኡስማን መሐመድም በተመሳሳይ ሰውየው ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነታቸውን ያጠናክራሉ ይላል፡፡ ‹‹ሀሰን ሼክ መሐመድ ከዚህ በፊትም ቢሆን ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት ለመፍጠር አልተቸገሩም፡፡ ሰውየው እንደ ኢትዮጵያ ሶማሌ የሚያስቡና ለኢትዮጵያ ቀና አመለካከት ያላቸው መሆናቸውን ነው የምረዳው፡፡ አሁንም ምርጫ ለማሸነፍ የበቁበት የቅስቀሳ መርሐቸው እርስ በርስ የተስማማች ሶማሊያን፣ እንዲሁም ከጎረቤት አገሮች ጋር የተስማማች ሶማሊያን መፍጠር የሚል መፈክር ያነገበ ነው፡፡ ሀሰን ሼክ መሐመድ የፖለቲካ ስትራቴጂያቸው የተለሳለሰና ልዝብ ነው፡፡ በሥልጣን ዘመናቸው ብዙ ስምምነቶችን ከተለያዩ አገሮች ጋር ሲፈራረሙ ቆይተዋል፡፡
‹‹እርግጥ ነው በፀጥታና ደኅንነት ረገድ ፎርማጆ አገሪቱን ብዙ ለውጠዋል፡፡ አሁን በአገሪቱ የሚከሰት የሽብር ጥቃትና ሁከት ገወደ 12/20 በመቶ ወርዷል፡፡ ፎርማጆ ጥብቅ የጸጥታ አጠባበቅ ዕርምጃ መውሰዱ ለዚህ ትልቅ ዕገዛ ነበረው፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ ያሠጋ የነበረ የፀጥታ ችግር በፎርማጆ ዘመን ተለውጧል፡፡ በሐሰን ሼክ መሐመድ ዘመን ግን ከፀጥታው ይልቅ ውጭ ግንኙነቱ ነበር ጠንካራ ቦታን የያዘው፤›› በማለት በምርጫው ውጤት ሊከተል ይችላል ያለውን ተፅዕኖ ተናግሯል፡፡
እሑድ ምሽት የሶማሊያን የምርጫ ሒደት ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መዲና ጅግጅጋ እስከ ጅቡቲና ሐርጌሳ ድረስ ብዙዎች በቀጥታ ሲከታተሉ አምሽተዋል፡፡ የሶማሊያ ጉዳይ ቅርባቸው የሆኑ ወገኖች ውጤቱን በቴሌቪዥን መስኮት ሲጠባበቁ አመሹ፡፡ ሶማሊያ የኢትዮጵያ፣ የጂቡቲና እንዲሁም የራሷ አካል የሆነችው የሶማሌላንድ ጎረቤት በመሆኗ ብቻ ሳይሆን ከነዚህ አገሮች ጋር በዘር፣ በሃይማኖት፣ በባህልና በቋንቋ የሚዛመድ ሕዝብ ያላት በመሆኑ ብዙ ሰዎች ጅግጅጋ ኢስታንቡል ሆቴል በረንዳ ላይ ሆነው የምርጫውን ሒደት ሲከታተሉ ነበር፡፡ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ሙስጠፌ መሐመድ ኡመር፣ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ወዳጅነትንና ጉርብትናን በሚያንፀባርቁ ቃላት ለተመራጩ ፕሬዚዳንት የደስታ መልዕክት ፈጥነው ማስተላለፋቸው፣ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ያላትን ቅርበት የሚያሳይ ነበር፡፡
ከዚህ ሁሉ አልፎ ግን የሶማሊያ ምርጫን በተመለከተ የትግራይ ፖለቲካ ልሂቃንና የሕወሓት ደጋፊዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ያሳዩት ስሜትና ግብረ መልስ ብዙ ያነጋገረ መሆኑን ታዛቢዎች ይገልጻሉ፡፡ የኢትዮጵያን፣ የሶማሊያንና ኤርትራን መንግሥታት የሚቃወሙ ኃይሎች ምርጫውን በተመለከተ ያሳዩት ስሜታዊ ግብረ መልስ ያመሳሰላቸው ነበርም ሲሉ ያስቀምጧቸዋል፡፡ ብዙዎቹ የዓብይ፣ የኢሳያስና የፎርማጆ ቀጣናዊ ጥምረት መፍረሱን ሲናገሩ ነበር፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የኢትዮጵያ አጋሮች አንድ በአንድ ከሥልጣን መወገዳቸውን በመጥቀስ፣ ከዓብይ አስተዳደር በፊት የነበረው ቀጣናዊ ጂኦፖለቲካዊ ሁኔታ እንደሚመለስ ተስፋ በሚያደርግ ስሜት ሐሳባቸውን አስተጋብተዋል፡፡
ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ለአዲሱ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ለሀሰን ሼክ መሐመድ ለማስተላለፍ ቀድመው ታይተዋል፡፡ አንዳንዶች የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮችና የጦር መሪዎች ከሀሰን ሼክ መሐመድ ጋር የተነሱትን ፎቶግራፍ በመለጠፍ ስሜታቸውን አስተጋብተዋል፡፡ ብዙዎቹ በአዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት መመረጥ ቀጣናዊ ጂኦፖለቲካ፣ በተለይ የኢትዮጵያ ሁኔታ እንደሚለወጥ ተስፋ የሚያደርግ ስሜት የተንፀባረቀባቸውም ነበሩ ይላሉ ሁኔታውን የተከታተሉ ታዛቢዎች፡፡
የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ኡስማን መሐመድ አህመድ፣ ሕወሓትና አንዳንድ ወገኖች የሀሰን ሼክ መሐመድን መመረጥ የደገፉበትን ምክንያት ሰፋ በማድረግ አብራርቷል፡፡
‹‹ብዙ የሶማሊያ ተኮር ሚዲያዎች የሀሰን ሼክ መሐመድ መምጣት ብዙ አላስደሰታቸውም፡፡ ሀሰን ሼክ ሥልጣን ዘመናቸው ከአብዲ ኢሌና ከአብዲ ኢሌ ጀርባ ከተሠለፉት ከሕወሓቶች ጋር ጠንካራ ግንኙነት ነበራቸው፡፡ ሰውየው በሥልጣን ዘመናቸው አስተዳደራቸው በሙስናና በምዝበራም የሚታማ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ሁለቱን ወገኖች ማለትም የሀሰን ሼክ አስተዳደርና የሕወሓት መንግሥትን የሚያዛምድ ነበር፡፡ ለምሳሌ ያክል በሀሰን ሼክ ሥልጣን ዘመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከፕሬዚዳንቱ ቢሮ ጋር ተጎራብቶ ነበር የተቋቋመው፡፡ ፎርማጆ ሲመጣ ግን ዓለም አቀፍ መርሆችን ባከበረ መንገድ፣ ሁለቱ አገሮች ተስማምተው ኤምባሲው ለብቻው ራሱን የቻለ ጽሕፈት ቤት እንዲኖረው ነበር የተደረገው፡፡ በሀሰን ሼክ ሥልጣን ዘመን የተደረገውን ነገር ለሚረዳ አሁንም እሳቸው ወደ ፕሬዚዳንትነት በመምጣታቸው፣ ሁለቱ አገሮች የሚኖራቸው ግንኙነት ሊቀየር ይችላል ብሎ ቢሠጋ ትክክለኛ ሥጋት ነው፡፡ በሶማሌ ክልል ያሉ የአብዲ ኢሌ ደጋፊዎች ጭምር ልክ እንደ ሕወሓት አመራሮች ሁሉ ሀሰን ሼክ መሐመድን ደግፈዋል፡፡ ካሁን በፊት የነበረው ሁኔታ ይመጣል ብለው በመመኘት የተፈጠረ ስሜት ነው፡፡ በኬንያዊያን በኩልም ቢሆን ተመሳሳይ የደስታ ስሜት እየተስተጋባ ነው፡፡ ይህ ከኬንያም ሆነ ከኢትዮጵያ እውነተኛ ጥቅሞች ጋር የተገናኘ ሳይሆን ከተወሰኑ ኃይሎች በጋር በተሳሰረ የጥቅም ግንኙነት የመጣ ስሜት ነው፡፡ በፎርማጆ ዘመን የውጭ ምንዛሪ ግብይቱና ንግዱ ዓለም አቀፍ መርሆዎችን በተከተለ ሁኔታ እንዲካሄድ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ አሁን አንዳንድ ኬንያውያን በሀሰን ሼክ መሐመድ መመረጥ የጨፈሩት ግን የኢትዮጵያ የጫት ንግድ ከሶማሊያ ገለል ተደርጎ፣ የእኛ በቦታው ይተካል በሚል መንፈስ ጭምር ነው፡፡ ሀሰን ሼክ በነበሩ ዘመን የኬንያ ጫት ነበር የሞቃዲሾን ገበያ የተቆጣጠረው፡፡ ፎርማጆ ይህን ለውጠውት ነበር፤›› ይላል፡፡
በመቀጠልም፣ ‹‹ኢትዮጵያ የጫት ንግዷ እንዳይቋረጥ ብቻ ሳይሆን፣ ከሶማሊያ የምትፈልገውን የውጭ ግንኙነት ጥቅም ለማስተበቅ ጠንካራ የግንኙነት ማጠናከር ሥራ መሥራት ይኖርባታል፡፡ አሁን ግንኙነትን በማጠናከር በኩል ድክመት ይታያል፡፡ ይህ ሊሆን የማይገባው ነው፡፡ ሌሎች ኃይሎች የሚጨፍሩት ከራሳቸው ጥቅም ተነስተው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ የፖለቲካ ሽግግር ለመጠቀም መሥራት ነው ያለባት፤›› በማለት የተናገረው የፖለቲካ ምሁሩ ኡስማን፣ ከሀሰን ሼክ መሐመድ መመረጥና ከፎርማጆ መሸነፍ በስተጀርባ ያለውን ቀጣናዊ፣ ጂኦፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት ሰፊ ተቃርኖ ያለው መሆኑን በሰፊው ተንትኖታል፡፡
ጋዜጠኛ ፍትሕ አወቅ በበኩሉ፣ ‹‹ፎርማጆ ከኢትዮጵያና ከኤርትራ ጋር ልዩ የሦስትዮሽ ግንኙነት በመፍጠር ሲወነጀሉ ነው የቆዩት፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ ኃያል ጥምረትን እንፈጥራለን ብለው ተንቀሳቀሱ ተብለው ተወንጅለዋል፡፡ ጦራቸውን በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ አሰማሩ የሚል ውንጀላም ቀርቦባቸዋል፡፡ ሰውየው ከኢትዮጵያ ጋር መወዳጀታቸው አልተወደደም፣ ተቃውሞ ነው ያስከተለባቸው፡፡ አሁን እንደገና የተመረጡት ሀሰን ሼክ መሐመድም ቢሆኑ ከኢትዮጵያ ጋር ጥብቅ ግንኙነት መመሥረት ያለውን ጠቀሜታ ያጡታል ብዬ አልገምትም፡፡ ልክ እንደ ፎርማጆ በአንዴ ከምዕራባዊያኑ ጋር ግንኙነትን ወደ ማሻከርና ከእነ ቱርክ ጋር መወገን ላይታይባቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን ደግሞ በእሳቸው የቀደመ የሥልጣን ዘመን የቱርክ ኤምባሲ መከፈቱን አንርሳ፤›› በማለት ነው አዲሱ የሶማሊያ መሪ በተፃራሪ ኃይሎች ፍላጎት መካከል ሚዛን ጠብቆ ለመጓዝ የሚገጥማቸውን ፈተና ያስቀመጠው፡፡
ሶማሊያ 16 ሚሊዮን ያህል ሕዝብ አላት፡፡ ሆኖም ምርጫ የሚካፈለው ከ30 ሺሕ የማይበልጥ መሆኑ ይነገራል፡፡ ቀጥተኛ ባልሆነው በሶማሊያ ምርጫ የጎሳ መሪዎች 275 የፓርላማ ተወካዮችን ይመርጣሉ፡፡ እነዚህ የምክር ቤት ተመራጮች ደግሞ ለፕሬዚዳንትነት የሚፎካከሩ ዕጩዎችን በቀጥታ ድምፅ አሰጣጥ ይመርጣሉ፡፡ በዚህ መሀል የወጣቶችና የሴቶች ድምፅ አይወከልም የሚል ቅሬታ ይሰማል፡፡ በሌላ በኩል በውጭ ኃይሎች ጭምር የፓርላማ አባላት ድምፅ በገንዘብ ይገዛል እየተባለ የምርጫው ሒደት በሙስና ይታማል፡፡ በሶማሊያ ጎሳ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ አገሪቱ ዲጊል፣ ዳሮድ፣ ሀዊያና ዲር የተባሉ አራት ዋና ዋና ጎሳዎችን ጨምሮ ሌሎች አናሳ ጎሳዎችና በርካታ ንዑስ ጎሳዎች ይኖራሉ፡፡ የእነዚህ ጎሳዎች ፉክክር፣ ግንኙነት ወይም ዝምድና በምርጫውም ሆነ በአጠቃላይ በሶማሊያ ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያሳድር መሆኑ ይታወቃል፡፡
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የምሥራቅ አፍሪካ በተለይም የሶማሊያን ፀጥታ ሁኔታ በቅርበት የሚከታተሉ አንድ የደኅንነት ባለሙያ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የፋርማጆ በምርጫ መሸነፍ የሚጠበቅ ነበር ብለውታል፡፡
‹‹በሶማሊያ ሀዊያ ትልቅና ተፅዕኖ ፈጣሪ ጎሳ ነው፡፡ ፎርማጆ ከዳሮድ ጎሳ መሆኑና ተፅዕኖ ፈጣሪነቱ መጉላቱ በሀዊያዎች መካከል አልተወከልንም የሚል ቅሬታ ፈጥሮባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሶማሊያ አሥር ጊዜ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ስታደርግ በእነዚህ ጊዜያት ሁለተኛ የሥልጣን ዘመን ያገኘ ሰው አልነበረም፡፡ የሀሰን ሼክ መሐመድ እንደገና ወደ ሥልጣን መመለስ ታሪካዊ ነው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ በሌላም በኩል ሀሰን ሼክና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉበት የተቃዋሚዎች ጥምረት በአንድነት ኃይሉን አስተባብሮ ነበር የፎርማጆን ሥልጣን የነቀነቀው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም የውጭ ኃይሎች ግፊትም ከባድ ነበር፡፡ ራሱ ፋርማጆም ከግዛት አስተዳደሮችና ከጠንካራ የጎሳ አለቆች ጋር መጋጨት ማብዛቱ ብዙ አልተወደደለትም፡፡ ይህ ሁሉ የፎርማጆን ወዳቂነት አይቀሬ አድርጎት ቆይቷል፤›› በማለትም የደኅንነት ባለሙያው ምልከታቸውን አጋርተዋል፡፡
ሶማሊያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብዙ ለውጦችን አምጥታለች፡፡ በአገሪቱ ያለው የሰላም ሁኔታ ከእነ ሥጋቱ አንፃራዊ መሻሻል በማሳየቱ ብዙ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ለውጦች በአገሪቱ እየመጣ ይገኛል፡፡ ለአብነት ያክል በዳያስፖራ የሚኖሩ ሶማሊያዊያን ሀብትና ዕውቀታቸውን ይዘው በወደ አገር ቤት መግባት መጀመራቸው እንደ ትልቅ እመርታ ይታያል፡፡ አሁንም ቢሆን ዳያስፖራው የሚልከው የሃዋላ ገንዘብ ለሶማሊያ ጥቅል ኢኮኖሚ ዕድገት 40 በመቶውን የሚሸፍን ነው ይባላል፡፡
በአገሪቱ የፋይናንስና የሃዋላ አገልግሎቶች ከመስፋፋታቸው በተጨማሪ፣ የቴሌኮም ዘርፍና ቱሪዝምም አዳዲስ ዕድሎችን መፍጠር ጀምረዋል ነው የሚባለው፡፡ ሆኖም ሶማሊያ አሁንም ቢሆን ብዙ ፈተናዎች ያለባት አገር ናት፡፡ አልሸባብ አልከሰመም፡፡ እንዲያውም ኃይሉ እየተጠናከረ ይገኛል፡፡ የሽብር ቡድኑ በእነ አሜሪካ ለሞቃዲሾ ቤተ መንግሥት ታጭቷል ሲባል መቆየቱ እንደ ቀላል የሚታይ ሥጋት አለመሆኑን ተንታኞች ይናገራሉ፡፡
ሆኖም በምርጫው ማግሥት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በሰጡት ትዕዛዝ ይህን ግምት ፉርሽ አድርገውታል፡፡ ባይደን አሜሪካ ወደ ሶማሊያ እግረኛ ጦር እንድትልክ ጥብቅ ትዕዛዝ ለወታደራዊ መኮንኖቻቸው አስተላልፈዋል ተብሏል፡፡ ኒውዮርክ ታይምስን ጠቅሰው በርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሆነ፣ አሜሪካ አልሸባብን ለመደምሰስ ነው እግረኛ ጦር ወደ ሶማሊያ የምትልከው ተብሏል፡፡ አሜሪካ ልክ እንደ አፍጋኒስታኑ ታሊባን ለቤተ መንግሥት ልታበቃው ነው ሲባል የቆየውን አልሸባብን ለመውጋት መዘጋጀቷ፣ በምርጫው ማግሥት የተሰማ አስገራሚ ዜናም ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል ሶማሊያ በአሁኑ ወቅት ሌሎች ሥጋቶች እንደተጫኑባት ይነገራል፡፡ ከ650 ሺሕ በላይ ዜጎቿ በጎረቤት አገሮች ስደተኛ ሆነው ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ አገሪቱ ዘንድሮም ቢሆን በከባድ ድርቅ የተጠቃች ሲሆን፣ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿ የረሃብ ጥላ አጥልቶባቸዋል ነው የሚባለው፡፡ ይህ ሁሉ ቀውስ እያለባት ሰላማዊ የፖለቲካ ሥልጣን ሽግግር ማድረግ መቻሏ ትልቅ ዕፎይታን የፈጠረ ጉዳይ ቢሆንም፣ ነገር ግን አዲሱ የሀሰን ሼክ መሐመድ አስተዳደር ቀጣይ ዕርምጃዎች በአገር ቤትም ሆነ በቀጣናው የሚፈጥሩት ተፅዕኖ ከወዲሁ የሚጠበቅና ሁሉም በትኩረት የሚከታተሉት ሆኗል፡፡