Monday, July 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ለ13 ተቋማት ዕውቅና ሰጠ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ዓለም አቀፍና ብሔራዊ መሥፈርት ላሟሉ ለስድስት የሕክምና፣ ለሁለት የፍተሻ ላብራቶሪ፣ ለሦስት የኢንስፔክሽንና ለአንድ የሰርተፊኬሽን በአጠቃላይ ለ13 ተቋማት የአክሪዲቴሽን አገልግሎት መስጠቱን አስታወቀ፡፡

እነዚህ ዕውቅና ያገኙ ተቋማት ቀደም ሲል ለኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ማመልከቻ አስገብተው ሰነዳቸው የተገመገመና የመስክ ግምገማ የተሠራላቸው መሆናቸውን፣ በአክሪዲቴሽን አፅዳቂ ኮሚቴ ዕውቅና ያላቸው (አክሪዲትድ) እንዲሆኑ የተወሰነላቸው መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ተቋማቱን የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ለውጭ ንግድ መቀላጠፍ፣ የተጠቃሚዎችን አመኔታ ለመፍጠርና ወደ አገር የሚገቡ ምርቶች ደረጃና ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍሰሐ አርዓያ ተናግረዋል፡፡

ዕውቅና ከተሰጣቸው ድርጅቶች መካከል የመንግሥት ልማት ድርጅት የሆነው የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት አንዱ ሲሆን፣ ድርጅቱ ለሦስት ማለትም ለላቦራቶሪ ፍተሻ፣ ለኢንስፔክሽን (ጥራት)፣ ለምርትና ለአሠራር ሥርዓት ሰርተፊኬሽን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለውን ዕውቅና የሚሰጥ ነው፡፡

ድርጅቱ ከአክሪዲቴሽን አገልግሎት በ120 ፓራሜትሮች ዕውቅና ማግኘቱን የገለጹት የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሻለ በልሁ፣ ይህን ዕውቅና ለማግኘት ለአንድ ዓመት የሚቆይ ከፍተኛ ሥራ ይጠይቃል ብለዋል፡፡

ለአራት ተቋማት ከአምስት ዓመታት በፊት ከተመደበ 50 ሚሊዮን ዶላር ከፍተኛውን መጠን የወሰደው የተስማሚነት ድርጀት የምግብ ጥራት ፍተሻ ላቦራቶሪ፣ የቆዳ ፍተሻ ላቦራቶሪና የጨርቃ ጨርቅ ፍተሻ ላቦራቶሪ ከ200 ሺሕ እስከ 300 ሺሕ ዶላር ለአንድ መሣሪያ ወጪ በማድረግ ወደ ሥራ በማስገባት፣ የተቀላጠፈ አገልግሎት እየሰጠ ያለ ተቋም ነው ሲሉ አቶ ተሻለ ተናግረዋል፡፡

እነዚህ ላቦራቶሪዎች መኖራቸው ለፍተሻ ወደ ውጭ ለሚላኩ ምርቶች የሚወጣውን ወጪ በአገር ውስጥ ፍተሻ በማድረግ መሥራት ተችሏል ብለዋል፡፡ የአክሪዲቴሽን አገልግሎት ዕውቅና የሰጠው በአራት ዘርፎች ነው፡፡

በሕክምና ላብራቶሪ ዘርፍ ዕውቅና የተሰጣቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ የደብረ ማርቆስ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ የቢሾፍቱ ሆስፒታል፣ የእንጅባራ አጠቃላይ ሆስፒታል፣ የዳንግላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፣ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ናቸው፡፡

የቀድሞ የፍተሻ ላብራቶሪያቸውን በማስፋት የእንስሳት ጤና ኢንስቲትዩትና  የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት የሚጠቀሱ ሲሆን፣ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲና የኢትዮጵያ የቴክስታይልና ፋሽን ኢንስቲትዩት በፊዚካልና በኬሚካል የፍተሻ ወሰን አክሪዲቴሽን ተሰጥቷቸዋል፡፡

በግብርና ምርቶች ኢንስፔክሽን ዘርፍ ደግሞ ኮንትሮል ዩኒየን ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ አፍሮ ስታር ኢንተርናሽናል ኮሜርሻል ኤጀንሲ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ኤዋይ ኖብል ኢንስፔክሽንና ሰርቪላንስ የአክሪዲቴሽን አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

የአለርት ኢትዮጵያ ማኔጅመንት ሰርተፊኬሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በማኔጅመንት ሲስተም ሰርተፊኬሽን ዘርፍ አግኝቷል፡፡

የአክሪዲቴሽን አገልግሎት ለሕክምና ላብራቶሪዎች፣ ለፍተሻ ላብራቶሪ፣ በኢንስፔክሽን፣ በፐርሶኔል ሰርተፊኬሽን፣ በምርት ሰርተፊኬሽን፣ በአመራር ሥርዓት ሰርተፊኬሽን፣ እንዲሁም በካሊቢሬሽን ዘርፍ ዕውቅና በመስጠት ለ11 ዓመታት የቆየ ተቋም ነው፡፡

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎትን በዋና ዳይሬክተርነት ለ11 ዓመታት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ፍሰሐ አርዓያ ከሦስት ወራት በፊት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ያስገቡት የመልቀቂያ ደብዳቤ ተቀባይነት አግኝቶ ከኃላፊነታቸው ሊለቁ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

ተቋሙ ከመጀመሪያ ጀምሮ ሲመሩ የቆዩት አቶ ፍሰሐ በፍተሻና በሕክምና ላብራቶሪ፣ በኢንስፔክሽን፣ እንዲሁም በሰርተፊኬሽን ሥርዓት ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና እንዲኖረው ማድረጋቸው ይነገራል፡፡

የአፍሪካ አክሪዲቴሽን ኮርፖሬሽንን በሊቀመንበርነት፣ እንዲሁም አፍሪካን በመወከል ለስድስት ዓመታት የዓለም አቀፍ ላብራቶሪ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን አገልግለዋል፡፡

ተቋሙ ሲያከናውናቸው ከነበረው ተግባራት በላይ ማከናወን ይጠበቅበት የነበረ ሲሆን ከአገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም፣ ከነበሩ ባህላዊ አሠራሮች፣ የተቆጣጣሪ ባለሥልጣናት ለተቋሙ ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ መሆን እንደ ችግር ይጠቀሳሉ ሲሉ አቶ አርዓያ ተናግረዋል፡፡

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኬሚስትሪ፣ በኬሚካል ኢንጂነሪንግ ደግሞ ማስተርስ ያላቸው አቶ አርዓያ ከመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ በኬሚካል ኢንጂነሪንግ መምህር ሆነው ሲያገለግሉ በቆዩበት ወቅት ከመጀመሪያ ዓመት እስከ ማስተርስ ፕሮግራም በመቅረፅ የተደራጀ ዲፓርትመንት እንዲኖር ማድረግ መቻላቸው ይነገራል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች