የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለከተማው ‹‹የተዘበራረቀ›› የሕንፃዎች ቀለም ወጥ የሆነ ስታንዳርድ ለማውጣት ባደረገው ጥናት፣ ሁሉም ሕንፃዎች ቀለማቸው ግራጫ (ግሬይ) እንዲሆን መወሰኑን አስታወቀ፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ውሳኔውን አስመልክቶ የሕንፃ ባለቤት ከሆኑ የከተማዋ ባለሀብቶች ጋር ውይይት የጀመረ ሲሆን፣ ከሁለት እስከ ሦስት ወራት ባለ ጊዜ ውስጥ የውሳኔው ማሳያ የሚሆን ሞዴል አካባቢ ለማዘጋጀት አቅዷል፡፡
በከተማው ለሚገኙ ሕንፃዎች ቀለማቸው ወጥ የሆነ ስታንዳርድ ለማዘጋጀት ላለፈው አንድ ወር ጥናት ሲደረግ መቆየቱን ለሪፖርተር የተናገሩት የከተማዋ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ቢሮ ኃላፊ አቶ ስጦታው አካለ (ኢንጂነር)፣ በጥናቱ አብዛኞቹ ሕንፃዎች ቀለማቸው ምን ዓይነት እንደሆነ የመለየት ሥራ እንደተከናወነ ገልጸዋል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ የከተማዋ ሕንፃዎች ተቆጥረው ቀለማቸው የተለየበት ጥናት አብዛኞቹ ሕንፃዎች ግራጫ ቀለም ያላቸው መሆኑን አመላክቷል፡፡ ቂርቆስ ክፍለ ከተማን ለማሳያነት የጠቀሱት ኃላፊው፣ በቂርቆስ ከ100 ሕንፃዎች ውስጥ ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆኑት ሕንፃዎች ቀለም ግራጫ ነው ብለዋል፡፡ ከእዚህ ውጪ ያሉት ቀለሞች አነስተኛ ቁጥር ያላቸውና የተለያዩ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
‹‹መሬት ላይ የሌለ አዲስ ቀለም ብናስቀምጥ የተሠሩት ሁሉም ሕንፃዎች እንደ ገና [ቀለም] ሊቀይሩ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ዋነኛው የትኛው ቀለም ነው የሚለውን ወስደን ቀሪዎቹ ሕንፃዎችና ወደፊትም የሚሠሩት በተመሳሳይ ግራጫ እንዲሆኑ ወስነናል፤›› ሲሉ ለከተማዋ ሕንፃዎች ግራጫ የተመረጠበትን ምክንያት አስረድተዋል፡፡
ግራጫ ቀለም ሲወሰን ሁሉም ሕንፃዎች ሙሉ ለሙሉ ተመሳሳይ ቀለም ይኖራቸዋል ማለት እንዳልሆነ የሚናገሩት ኃላፊው፣ እስከ 30 የሚደርሱ በኮድ የሚለያዩ የግራጫ ቀለም ዓይነቶች እንዳሉና የሕንፃ ባለቤቶች ከእነዚህ ውስጥ መምረጥ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ከግራጫ ቀለም ዓይነቶች ውስጥ የማይካተት ቀለም የተቀቡ ሕንፃዎች በሙሉ፣ ቀለማቸውን በግራጫ ቀለም አማራጮች እንደሚቀይሩ አስረድተዋል፡፡
ኃላፊው እንደሚናገሩት በከተማ ውስጥ ያሉት ሕንፃዎች ቀለም የተዘበራረቀ፣ እርስ በርስ የሚጋጭና ጎን ለጎን ባሉ ሕንፃዎች መካከል እንኳን ተቀራራቢነት የሌለው ነው፡፡ ከእዚህ በላይ ‹‹ለዓይን ዕይታና ለጤና ጉዳት ያላቸው›› መስታወቶችንና አልሙኒየሞችን የሚገጥሙ ባለ ሕንፃዎች መኖራቸውን አስታውቀዋል፡፡
ይህ ዓይነቱ አሠራር መቅረትና ወጥ በሆነ ስታንዳርድ መመራት እንዳለበት የሚገልጹት ስጦታው (ኢንጂነር)፣ አሁን ያለው አሠራር የከተማዋን የአፍሪካ መዲናነትንም ሆነ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ከተማነት የማይመጥን መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሕንፃዎቻቸው የቀለም ስታንዳርድ ያበጁ ከተሞች እንዳሉ ጠቅሰው፣ የከተማ አስተዳደሩም ይህንን ልምድ በአዲስ አበባ ለመተግበር ማሰቡን አስረድተዋል፡፡
በፌዴራል ደረጃ የወጣው የሕንፃ አዋጅም ሆነ የከተማዋ የሕንፃ መመርያ የቀለም ስታንዳርድን ስለማያስቀምጡ፣ የከተማ አስተዳደሩ በ2010 ዓ.ም. የወጣውን የሕንፃ መመርያ ቁጥር 2/2010 በማሻሻል ረቂቁን ለከተማዋ ዓቃቤ ሕግ መላኩን ገልጸዋል፡፡ የሕንፃና የቀለም ስታንዳርድ መመርያው ላይ የተካተቱ አዲስ ሐሳቦች መሆናቸውን የተናገሩት ስጦታው (ኢንጂነር)፣ በየአንቀጾቹ ሌሎች ማሻሻያዎች መደረጋቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ረቂቅ መመርያው ከፀደቀ በኋላ ቢሮው የሕንፃዎችን ቀለም መቆጣጠር ኃላፊነት እንደሚኖርበት፣ አዲስ ሕንፃ ገንቢዎችም ካሉት የግራጫ ቀለም አማራጮች ውስጥ የመረጡት ቀለም በቢሮው ፈቃድ ሳያገኝ መቀባት እንደማይችሉ አብራርተዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ለሕንፃዎች የወሰነውን የቀለም ስታንዳርድ በተመለከተ ካለፈው ሳምንት አንስቶ ትልልቅ ሕንፃዎች ካሏቸው ባለሀብቶች ጋር ውይይት ማድረግ የጀመረ ሲሆን፣ እስካሁን በቂርቆስና በልደታ ክፍላተ ከተሞች ውይይት ተደርጓል፡፡ እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ በተደረጉት ውይይቶች የሕንፃ ባለቤቶች ውሳኔውን በመደገፍ ለመተግበር ተስማምተዋል፡፡ በየአካባቢው ከሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪዎች ማኅበራት ጋርም ምክክር መጀመሩን፣ የሕንፃዎቹንና የጣርያዎቹን ቀለም ወደ የሚፈለገው ስታንዳርድ ለማምጣት ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡ ይህ ውይይት በሁሉም ክፍላተ ከተሞችና ወረዳዎች እንደሚቀጥልም አክለዋል፡፡
የከተማዋን ሕንፃዎች ቀለም ወደ ግራጫ ለመቀየር ከአንድ ዓመት በላይ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ያስረዱት ኃላፊው፣ እስካሁን ድረስ የሕንፃዎችን ቀለም ለመቀየር የተቀመጠ የጊዜ ገደብ አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ታሳቢ እናደርጋለን፣ እስከ መቼ ድረስ ሊጨርሱ ይችላሉ የሚለውን አስበንና ጊዜ ሰጥተናቸው እንወስናለን፤›› ብለዋል፡፡
በመጪው ሁለትና ሦስት ወራት ግን በአንድ የተመረጠ አካባቢ የሚገኙ ሕንፃዎችን ቀለም ሙሉ ለሙሉ ወደ ግራጫ በመቀየር ሞዴል አካባቢ የማሳየት ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡ ሞዴል አካባቢው ሌሎች ክፍላተ ከተሞች ጭምር ያምራል አያምርም የሚለውን መጥተው ልምድ የሚወስዱበት፣ ይሳካል አይሳካም የሚለውንም የሚመለከቱበት እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡
ይሁንና በከተማው ውስጥ የሚገኙ ስማቸው መለያ (ብራንድ) የሆኑ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ሕንፃቸውን በግራጫ ቀለም ለመቀየር እንደማይገደዱ ስጦታው (ኢንጂነር) ገልጸዋል፡፡ የተለየ ቀለም ያለው መስታወት ወይም አልሙኒየም የተገጠመላቸው ሕንፃዎችን በተመለከተ፣ ‹‹እንዴት እናርመው የሚለውን ተወያይተን መፍትሔ እንፈልጋለን፤›› ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ለከተማዋ ሕንፃዎች የቀለም ስታንዳርድ ተግባራዊ የማድረግን ሐሳብ ከሳምንታት በፊት በተደረገው የከተማ አስተዳደሩ የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ላይ አንስተው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለከተማ ካቢኔ አባላት መመርያ ካስተላለፉባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ስለሆነው የሕንፃዎች ቀለም ጉዳይ ሲናገሩ፣ የከተማዋ ሕንፃዎች ቀለም ወጥነት የሚጎድለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዓብይ (ዶ/ር)፣ ‹‹እያንዳንዱ ሕንፃ በተፈቀደለት የቀለም ዓይነት ነው እንጂ የሚቀባው፣ የእኔ ስለሆነ ቀለም ስላማረኝ ብሎ ሁላችንም የምናየውን ቀለም እንደፈለገ መቀባት አይችልም፤›› ካሉ በኋላ፣ የካቢኔ አባላት ሊመለከቱት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ተናግረው ነበር፡፡