Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹ሱዳን የወረረችው የኢትዮጵያ መሬት በየትኛውም መመዘኛ ግዛታችን ስለሆነ ይመለሳል›› አቶ ደመቀ መኮንን፣...

‹‹ሱዳን የወረረችው የኢትዮጵያ መሬት በየትኛውም መመዘኛ ግዛታችን ስለሆነ ይመለሳል›› አቶ ደመቀ መኮንን፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

ቀን:

ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በሚያዋስናት ድንበር በኃይል አልፋ የወረረችው መሬት በየትኛውም መመዘኛ የኢትዮጵያ ግዛት ስለሆነ ይመለሳል ሲሉ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አስታወቁ፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን ይህን የተናገሩት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ማክሰኞ ግንቦት 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 7ኛ መደበኛ ጉባዔ ባቀረቡበት ወቅት ነው፡፡

ምንም እንኳ ከሱዳን ሕዝብ ጋር ያለው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በእጅጉ በኢኮኖሚ የተሳሰረ ቢሆንም፣ ሁለቱ አገሮች በሚጋሩት ድንበር ባለ የረዥም ጊዜ የይገባኛል ጥያቄ ችግሩን ለመፍታት የተዘረጋ መንገድ ቢኖርም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር በተያያዘ ፊቱን ወደ እዚህ ጦርነት ባዞረበት ወቅት ሁለቱ አገሮች ዘላቂ መፍትሔ እስኪመጣ አክብረውት የቆዩትን መንገድ በመጣስ ወራራ ማካሄዷን ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

በዚህ ሒደት ሱዳን የኢትዮጵያን ሕዝብ ያስቆጣ፣ የአካባቢው ነዋሪዎችን በከፍተኛ ሁኔታ የጎዳ፣ ከፍተኛ መፈናቀልና የሀብት ንብረት ውድመትና ዝርፊያ፣ እንዲሁም ብዙ ጫናዎች ያስከተለ ወረራ ማካሄዷን ገልጸዋል፡፡

ሱዳኖች በወረራ ቦታውን መያዝ ብቻ ሳይሆን የአካባቢውን ዲሞግራፊ ለመቀየር የተለያዩ የመሠረተ ልማቶች ግንባታ እያካሄዱ እንደሆነ በመግለጽ፣ ጉዳዩን እንዲያጤኑት በማሳሰብ፣ ኢትዮጵያ ችግሩን ለመፍታት ሰለማዊ መንገድን እንደመረጠች አቶ ደመቀ አስታውቀዋል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ አልበቃ ብሎ በስደተኛ ስም የገቡና በተለያዩ ቦታ የተሰባሰቡ የአሸባሪው የሕወሓት ኃይሎች ሱዳንን መቀመጫቸው አድርገው ወደ ኢትዮጵያ ጥቃት እየሰነዘሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ሱዳን ለአሸባሪ ኃይል ድጋፍ ማድረጓና መቀመጫ መሆኗ ኢትዮጵያን የመውጋት ያህል በመሆኑ ሊታረም እንደሚገባ፣ ለሱዳን መንግሥት እንደተነገረው አቶ ደመቀ ገልጸዋል፡፡

የሱዳንን ወረራ አስመልክቶ የዓለም አቀፍ ማኅረሰቡ ምላሽ ምንም እንኳ ጉዳዩ ወደ ግጭት እንዳይገባ የማድረግ ሁኔታ ቢታይበትም፣ ሱዳን በኢትዮጵያ መሬት ላይ ያላግባብ ወረራ ማካሄዷን ግልጽ አቋምና ውግዘት ማሳየት ላይ ከፍተኛ የሆነ ልግመት እየታየ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም ዓለም አቀፉ ማኅረሰብ የመፍትሔ አካል የሚሆን ከሆነ፣ ይህንን ወረራና ፀብ አጫሪነት የሚያርም እንቅስቃሴ ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ችግሩን በሰላማዊ አካሄድ ለመፍታት የተጀመሩ መንገዶች እያሉ ይህ ወረራ አደገኛ ውጤት ሊያሰከትል የሚችል በመሆኑ፣ አሁንም ኢትዮጵያ ለሰላማዊ መንገድ በር ከፍታ እየጠበቀች መሆኑን ለሁሉም አካላት መገለጹን አብራተዋል፡፡

በዚህ ሒደት የሱዳን መንግሥት የዓለም አቀፍ ሕግና የሁለትዮሽ ስምምነቶችን በመጣስ በጋራ ድንበር አካባቢ ኢትዮጵያን በመውረር ይዞታውን ለማጠናከርና ነባራዊ ሁኔታውን ለመቀየር በመሬት ላይ እያካሄደችው ያለውን የግጭት ቀስቃሽ ድርጊቶች በሚመለከት፣ ኢትዮጵያ ያላትን ፅኑ ተቃውሞና ችግሩን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ፍላጎቷን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ለአፍሪካ ኅብረት ለማሳወቅ እንደተሠራ አቶ ደመቀ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡

አቶ ደመቀ በሌላ በኩል የወደብ ተጠቃሚነትን ለማስፋት ከጎረቤት አገሮች ያለውን ግንኙነት በማሻሻል በፍጥነት እያደገ ያለውን የሕዝብ ቁጥር፣ ከወደብ አማራጭነትና ትብብር ውጪ ሊመለስ የሚችል ሌላ መንገድ እንደማይኖር አስታውቀዋል፡፡

በቀይ ባህርና በባህረ ሰላጤው አካባቢ ኢትዮጵያ ተመልካች ሆና መቀጠል እንደማይገባት በመጠቆም፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደ አንድ መሪ ሐሳብ በመያዝ በዓመታዊ ዕቅድና በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ስተራቴጅክ ዕቅዶች ላይ በትኩረት እየሠራበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ለአብነትም የቀይ ባህር ፎረም ሲደራጅ ኢትዮጵያን ወደ ጎን የገፋ ስምምነት በዓለም አደባባይ በየትኛውም ቦታ ተገቢነት የሌለው አሠራር በመሆኑ ጥያቄ ቀርቦበት ክትትል እየተደረገበት መሆኑን፣ በዚህም አገሪቱ ተመልካች ሆና እንደማትቀጥል  አብራተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ባለው የቅርብ ርቀት ውስጥ ከተጠቃሚነትና ከተፅዕኖ ፈጣሪነት ውጪ የምትሆንበት ምክንያት ባለመኖሩ ሁኔታውን በመሠረታዊነት የሚቀይር ሚዛናዊ የሆነ ግንኙነትና ስትራቴጂ፣ በወዳጅነት ዘላቂ ጥቅምን ሊያስከበር የሚችል የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳ ሆኖ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ‹‹ቅርቦቹ ሩቅ ሆነን ልንቀጥል አንችልም፣ በሰላማዊ መንገድና በትብብር፣ በሚዛናዊነትና በፍትሕ የእኛ ተሳትፎና የተጠቃሚነት መንገድ ዕውን እየሆነ እንዲሄድ ማድረግ ቁልፍ አጀንዳችን ነው፤›› ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ዜና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፉት ወራት ባደረገው መዋቅራዊ ለውጥ በዋናው መሥሪያ ቤት በነባሩ መዋቅር ላይ በአመራር ደረጃ  የነበሩ ሦስት ሚኒስትር ደኤታዎች ወደ ሁለት፣ 28 የነበሩ ዳይሬክተር ጄኔራሎችና ጽሕፈት ቤቶች ወደ 17፣ በሚሲዮኖች በ47 ኤምባሲዎችና በ16 የቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች ላይ ለውጥ በማድረግ 25 መደበኛ ኤምባሲዎችና አምስት የቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች፣ 16 የላፕቶፕ ኤምባሲዎችና አምስት ጽሕፈት ቤታቸውን ዋና መሥሪያ ቤት ያደረጉ (Home Based) ኤምባሲዎች እንዲደራጁ መደረጉ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

ቀድሞ ከነበሩት በተጨማሪዎች በፓኪስታንና በቡሩንዲ ኤምባሲ ለመክፈት ስምምነት ላይ ተደርሶ የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በሪፖርቱ አሥር ኤርትራውያን አዲስ መኖሪያ ፈቃድ እንደተሰጣቸው፣ 21 ኤርትራውያን በኢትዮጵያ የነበራቸው ንብረት እንደተመለሰላቸው፣ እንዲሁም አራት ኤርትራውያን በባንክ የተቀመጠ ገንዘብ እንዲመለስላቸው ያቀረቡት ጥያቄ እንዲመለስ ሥራ መከናወኑን በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

ለአፍሪካ ኅብረት የ2022 በጀት ከተመደበው 651 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ፣ በመደበኛ በጀት ኢትዮጵያ ለኅብረቱ የምትከፍለው ድርሻ 8.1 ሚሊዮን ዶላር ገደማ መሆኑ በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...