እንደምን ጊዜ ጊዜ መስተዋቱ?
ገልጠህ የምታሳይ ሁሉን እንደ መልኩ፣
ሁሉን እንደ ልኩ፡፡
እንደምነህ ጊዜ?
ወደ ጽርሐ አርያም የከፍታው መውጫ፣
ወይም ወደ ጥልቁ ቁልቁል መፈጥፈጫ፡፡
- Advertisement -
እንደምነህ ጊዜ?
የሕይወት ምሕዋር ዑደት ማስቀጠያ፣
የመከፋት ድባብ የደስታው ገበያ፡፡
ጊዜ ሁሉን ዳሳሽ ጊዜ ሁሉን አወቅ፡፡
እውነተኛው ዳኛ ፍትሕ የማትሰርቅ፡፡
ዐይተን ነበር ያኔ፣
ጌቶች ሎሌ ሁነው ሎሌዎች ሲነግሡ፣
ጋጣ ሙሉ አጋንንት ቅድስቱን ሲሞሉ፣
በፃድቃን ምኩራብ ውሰጥ ለድሪያ ሲያልሉ፡፡
ዐይተን ነበር ያኔ፣
በጥንግ ድርቡ አጋንንት ሲያጌጡ፣
የኤልዛቤል ካህናት ጸጋን ሲሻሻጡ፡፡
ዐይተን ነበር ያኔ፣
ዲታዎች ሲጠግቡ ቁንጣን ሲይዛቸው፣
ብስናት ሲወራቸው፣
ዕብሪት ሲያንራቸው፣
ምስኪኖች ሲያነቡ ተስፋ እየራቃቸው፡፡
ይኼውና ዛሬ፣
ብያኔህ ሲቀና፣
ጽዋቸው ሲሞላ፣
ባንተ እየተሾሙ ባንተ እየተሻሩ፣
ሁሉም ሲሄዱ አየን ቦታ እየቀየሩ፡፡
- መዝገበቃል አየለ ገላጋይ፣ ‹‹ዶፍ አዘል ደመና›› (2013)
*****