Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

ገበያን ከዞን እስከ ከተማ በኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ለማስተሳሰር

በኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ በመታገዝ የተለያዩ ሥራዎችን መሥራት፣ በተለይም የኢንተርኔት ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ የገበያ ትስስርን መፍጠር እየተለመደ መጥቷል፡፡ በዚህ ውስጥ ደግሞ የቴክኖሎጂ አገልግሎት የሚያቀርቡ ማኅበራትና ድርጅቶች እየተበራከቱ ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል ከ57 በላይ ሠራተኞች ያሉትና በ2012 ዓ.ም. የተመሠረተው አሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ አክሲዮን ማኅበር አንዱ ነው፡፡ ማኅበሩ በ11 የቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ ለመሥራት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ አቶ ዳንኤል በቀለ የማኅበሩ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ የማኅበሩን ሥራዎች በተመለከተ ተመስገን ተጋፋው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ አክሲዮን ማኅበር እንዴት ተመሠረተ?

አቶ ዳንኤል፡- አሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ አክሲዮን ማኅበር ቁጭት የወለደው ተቋም ነው፡፡ ቴክኖሎጂው በኢትዮጵያ ብሎም ደግሞ በአፍሪካ የለም የሚባልበት ሁኔታ ላይ በመሆናችን ተቋሙን ለመመሥረት ተገደናል፡፡ በአሜሪካ፣ በቻይና፣ በእስያና በህንድ  ኢንተርኔትን ተጠቅመው የተለያዩ ነገሮችን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ይህንን ሥራ ወደ አፍሪካ በማምጣትና ከእነዚህ አገሮች ተሞክሮ በመውሰድ የኢንተርኔት አጠቃቀማችንን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጰያ ኢንተርኔትን በመጠቀም የተሻለና የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈታ በቴክኖሎጂ የታገዘ የለም ማለት ይቻላል፡፡ በአገሪቱ በዘርፉ ላይ ተሰማርተው የሚሠሩት አብዛኛዎቹ የውጭ አገሮች ተዋናዮች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ኢንተርኔትን ተጠቅሞ የተለያዩ አገልግሎቶችን ተደራሽ ማድረግ ላይ ብዙ ጥያቄዎች ሲነሱ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህንን ጥያቄ ለመፍታት ከብዙ ትግል በኋላ አሸዋ ቴክኖሎጂን ማቋቋም ችለናል፡፡ አሸዋ ቴክኖሎጂ ከተቋቋመ ሁለት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ አሜሪካን ስናስብ በጣም ብዙ አይስኒክ የሆኑ ካምፓኒዎች ኢንተርኔትን መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ካምፓኒ ብዙ የለም፡፡ በመሆኑም አሸዋ ቴክኖሎጂን አቋቁመናል፡፡ ብዙ ችግሮችን በቴክኖሎጂ ታግዘን ለመፍታት አሸዋ ቴክኖሎጂ በአፍሪካ ላይ ምሳሌ ለመሆን የተቀቋቋመ ካምፓኒ ነው፡፡ በዚህ ሥራ ቻይናን ስናስብ አሊባባን እንጠቅሳለን፡፡ ህንድን ስናስብ ደግሞ ፕሊንካርትን ማሰብ እንችላለን፡፡ አሜሪካን ደግሞ በምንመለከትበት ወቅት ፌስቡክ፣ ጎግልናና አማዞንን ማስታወስ እንችላለን ብዬ መናገር እችላለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- አገልግሎቱን በምን መልኩ እየሰጣችሁ ነው?

አቶ ዳንኤል፡- በአሁኑ ወቅት አገልግሎት እየሰጠን ያለው በአዲስ አበባ ከተማ ሲሆን፣ ኢንተርኔትን በመጠቀም ዓለም አቀፍ ግብይትን እየፈጠርን እንገኛለን፡፡ አሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን አክሲዮን ማኅበር የዓለም ምጣኔን ሀብት እያንቀሳቀሰ ባለው የዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፍ በመሰማራት በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልቅ አቅምን እየገነባ ያለ ሕዝባዊ ተቋም ነው፡፡ ድርጅቱም በዋናነት በአክሲዮን ሽያጭ ላይ የተሰማራ ነው፡፡ በቅርቡም የ160 ሚሊዮን ብር ኢንቨስት በማድረግ በኢትዮጵያ ትልቅና ሁሉንም አገልግሎት በአንድ ላይ የያዘ የመስመር ላይ የግብይት ቦታን መዘርጋት ችሏል፡፡ በአሁን ወቅትም በሺዎች የሚቆጠሩ ሻጮችና ከአምስት ሚሊዮን በላይ ጎብኚዎች አሉን፡፡ በኢትዮጵያ ገጠሩን ከከተማ በንግድ ለማስተሳሰር የሚደርግ አሠራር ዘርግቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ በሌላ መልኩም የተለያዩ የትምህርት ሥርዓቶችን ዘርግቶ በትምህርት ላይ እየሠራ ይገኛል፡፡ የኑሮ ውድነትን ሊፈታ፣ የገበያ መረጋጋትን ሊፈጥር፣ በቀላልና በአስተማማኝ መልኩ ገጠሩን ከከተማው በንግድ ለማስተሳሰር ዕቅዶችን ነድፈን እየሠራን ነው፡፡ ማኅበሩም በአሥር ዓመታት ውስጥ በርካታ ፕሮጀክቶችን ለማሳካት ዕቅድ መያዙን፣ በዚህም እ.ኤ.አ በ2030 ከአምስት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አልመናል፡፡ ማኅበሩም በይበልጥ የሚሠራው በአዲስ አበባ ከተማ ቢሆንም፣ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ምን ያህል ሸማችና ሻጭ አለ የሚለውን ለማወቅ ጥናት ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- በሥራችሁ ላይ ምን ዓይነት ተግዳሮቶች ገጥሟችኋል?

አቶ ዳንኤል፡- ኢንተርኔት ተጠቅሞ አገልግሎት ለመስጠት የሚደረጉ ነገሮች ብዙም ችግር አለባቸው ብዬ አላምንም፡፡ ይኼንን ያልኩበት ዋነኛ ምክንያት አብዛኛውን የአውሮፓ አገሮች ኢንተርኔት ተጠቅመው የተለያዩ አገልግሎት እየሠሩ በመሆኑ ነው፡፡ በእኛ በኩልም ከአቅም በላይ የሆነ ችግር አልገጠመንም፡፡ ኢትዮጵያ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ የራሷ የሕግ ማዕቀፍ ስላላት ብዙም ሥራችን ላይ እንቸገራለን ብዬ አላስብም፡፡ ከዚህ በፊት ዘርፉ የራሱ የሆነ መተዳደሪያ ደንብ ስለሌለው ከፍተኛ የሆነ ችግር እንደነበር ይታወሳል፡፡ አሁን ግን ይህ ሁሉ ነገር ተፈቷል ማለት ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያ ከ25 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች ኢንተርኔት ተጠቃሚ ናቸው፡፡ ይህም ኢንተርኔት ተጠቅሞ የተለያዩ ሥራዎች ለመሥራት ትልቅ ድልድይ ነው ብዬ መናገር እችላለሁ፡፡ በጣም ጥቃቅን የሚባሉ ችግሮች አሉ፡፡ ችግሮቹ ግን ኢንተርኔት ተጠቅሞ ለመሥራት እንቅፋት ይሆናሉ ብዬ አላስብም፡፡ በእርግጥ የተማረ የሰው ኃይል ማግኘት በጣም ፈታኝ በመሆኑ ዘርፉ በመጠኑም ቢሆን ሊጎዳ ይችላል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው የህንድና የአሜሪካ ዜጎችን እያሠራን እንገኛለን፡፡ ችግሩን በመፍታት በኢትዮጵያውያን ዜጎች ብቻ የሚሠራ ተቋም ለማድረግ የምንጥር ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያን የመሠረተ ልማት ችግሮች እንደ ችግር ልናየው እንችላለን፡፡ የኢንተርኔት ችግር ገጥሞን ነበር፡፡ አሁን ግን እየተፈታ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ተቋማችሁ እየሠራ ያለው በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ነው? ወይስ በክልሎችም ይሠራል? 

አቶ ዳንኤል፡- በቋሚነት እየሠራን ያለነው በአዲስ አበባ ነው፡፡ በከተማዋ በጥልቀት ሳንሠራ ወደ ተለያዩ ክልሎች መሄድ ትንሽ ይቸግራል፡፡ ይሁን እንጂ ወደ 720 ቅርንጫፎችን በመክፈት ክልሎች ላይ ለመሥራት ዕቅድ ይዘን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ 24 ዞኖች ውስጥ አገልግሎት ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት አጠናቀናል፡፡ ለዚህ በቂ የሆነ ዝግጅት ማድረግ ስለሚጠበቅብን በቅርቡ እንጀምራን ማለት ትንሽ ይቸግረናል፡፡ ያም ሆነ ይህ የተለያዩ አገልግሎቶችን ለመስጠት ተቋማችን እየሠራ ይገኛል፡፡     

ሪፖርተር፡- ከሌሎች ተቋማት ጋር በቅንጅት ለመሥራት ምን አስባችኋል?

አቶ ዳንኤል፡- ተቋማችን ከተለያዩ ተቋማት ጋር ለመሥራት በሩ ክፍት ነው፡፡ ሁሌም ቢሆን በአንድነት ከተሠራ ብዙ ነገሮችን መቀየር ይቻላል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በኢትዮጵያ በአንድነት የመሥራት ልማድ አልተለመደም፡፡ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ፣ ዕውቀት ያለው በዕውቀቱ በአንድነት ቢሠራ ኢትዮጵያ ካደጉት አገር ተርታ ልናገኛት እንችል ነበር፡፡ ነገር ግን እንደዚህ ዓይነት ሥራ ባለመሠራቱና ክፍተት በመኖሩ ኢትዮጵያ ወደፊት አንድ ዕርምጃ እንዳታድግ አድርጓታል፡፡ አሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ ከ30 በላይ ከሚሆኑ አጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ እየሠራ ይገኛል፡፡ መንግሥትም የተለያያዩ ድጋፎችን እያደረገልን ይገኛል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ብዙ የሚባሉ መንግሥታዊ ተቋማት ለሥራችን ስኬት በር ስናንኳኳ ክፍት ያደርጉልናል፡፡ ይህም ምን ያህል መንግሥት ለሥራችን በሩን ክፍት እያደረገልን መሆኑን ያሳያል፡፡ አሸዋ ቴክኖሎጂ እየፈታ ያለው ችግር የአገሪቱን በመሆኑ ሁሌም በሄድንበት በር ክፍት ከተደረገልን ተቋማችን በዘርፉ ላይ ያለውን ክፈተት በመቅረፍ የአንበሳውን ድርሻ ይወጣል ብዬ አስባለሁ፡፡   

ሪፖርተር፡- በቀጣይ ምን ለመሥራት አስባችኋል?

አቶ ዳንኤል፡- አሸዋ ቴክኖሎጂ በርካታ ዓላማዎችን አቅዶ በመነሳት ሥራዎች ይሠራል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢንተርኔት በመጠቀም የግብይት ሰንሰለታችንን እናሳድጋለን ብዬ አምናለሁ፡፡ ዘንድሮ ከ25 ሺሕ በላይ ደንበኞች ለማፍራት ዕቅድ ይዘናል፡፡ 45 ሚሊዮን ብር ለማትረፍና በሁሉም ክልሎች ላይ ለመገኘት ዕቅድ ይዘናል፡፡ ከ200 ሺሕ በላይ ፓኬጆችን ለመሸጥም እንቅስቃሴዎችን ጀምረናል፡፡ የመርካቶን ገበያ በመቆጣጠር የደንበኞቻችንን ፍላጎት ለማሟላት ጠንክረን የምንሠራ ይሆናል፡፡ ይኼንን ማድረግ ከቻልን በርካታ ደንበኞች ምንም ዓይነት መጉላላት ሳይደርስባቸው ግብይት ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡    

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

ግራ አጋቢው የኤሌክትሪክ መኪና ጉዳይ

በያዝነው ዓመት መጀመሪያ በወርኃ ጥቅምት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 39...

ጦርነቱና ሒደቱ

ሦስት ሳምንታት ያስቆጠረው ሦስተኛው ዙር የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አሁንም...

ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የአዲስ አበባን ንግድና ዘርፍ ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት በተደረገው ምርጫ አሸነፉ

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት፣...