Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርሸኔን የትሮይ ፈረስ አድርጎ የሥልጣን ኮርቻ መወጣጫ ለማድረግ የሚደረግ ከንቱ ሴራ

ሸኔን የትሮይ ፈረስ አድርጎ የሥልጣን ኮርቻ መወጣጫ ለማድረግ የሚደረግ ከንቱ ሴራ

ቀን:

በቶሌራ ጉደታ ጉርሜሳ

አንዳንድ የኦሮሞን ሕዝብ እንወክላለን ወይም ለኦሮሞ ሕዝብ እንታገላለን ብለው የፖለቲካ ፓርቲን እንደ ሽፋን ተጠቅመው የተቋቋሙ ፓርቲዎችና ሸኔ ግንኙነታቸው ላይ ላዩን ሲታይ እምብዛም ቢመስልም፣ በተለያዩ መስኮች የተሳሰረ መሆኑን እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል። ከዚህ አኳያ በተለያየ ደረጃ አብዛኛውን የኦሮሞን ሕዝብ እንደሚወክል እየደሰኮረ የሚገኘው ፓርቲና አመራሮቹ፣ ለሸኔ ታጣቂዎች በቀጥታ ድጋፍ የሚያደርጉ መሆናቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ። ከዚህ አኳያ የፓርቲው አባላትና አመራሮች በሰው ኃይል፣ በፋይናንስ፣ በሐሳብና በሞራል ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ ከቡድኑ ጋር በመቀላቀል ቡድኑን በማስተባበርና በመምራት ላይ ይገኛሉ።

በተለያዩ ጊዜያት የፖለቲካ ፓርቲን ሽፋን በማድረግ ከፍተኛ አመራሮች የነበሩ ግለሰቦች፣ በቀጥታ ከሸኔ ጋር ግንኙነት በመፍጠር ድጋፍ ሲያደርጉ በቁጥጥር ሥር የዋሉ በርካቶች መሆናቸውን የተለያዩ ማስረጃዎች አሉ። አንዳንዶቹ የፖለቲካ ድርጅቱን ሕጋዊ ፓርቲነት ሽፋን በመጠቀም ለሸኔ ታጣቂዎች ምልመላና የመረጃ ምንጭ ሆነው እያገለገሉ መሆናቸው በተጨባጭ ይታወቃል። ከዚህም አልፈው በቀጥታ ከፖለቲካ ድርጅቱ ወጥተው ሸኔን በመቀላቀል ታጣቂና አመራር ሆነው የሚንቀሳቀሱ እንዳሉም ይታወቃል፡፡

- Advertisement -

የፖለቲካ ድርጅቱ አባላት ገንዘብ በማሰባሰብ በቀጥታ ለሸኔ ታጣቂ እስከ መላክ የሚደርስ ሕገወጥ ተግባራት ላይ ሲሳተፉ መቆየታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። ከዚህም ባለፈ የፖለቲካ ድርጅቱ ሊቀመንበር የሆነው ግለሰብ ከዚህ በፊት በሰላማዊ ትግል ለውጥ ይመጣል በሚል ገጽታ ይታወቅ የነበረ ቢሆንም፣ በተጨባጭ ግን ለሸኔ ታጣቂ ፋይናንስ እንዲሰበሰብ አቅጣጫ የመስጠትና የመሪነት ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ በቅርበት ያሉ አካላት እየገለጹ ይገኛሉ። በተለይ በቅርቡ በአሜሪካ በነበረው ቆይታ፣ የሸኔ የሽብር ቡድን የሚያካሂደውን የሽብር ጥቃት አጠናክሮ እንዲቀጥል ለማስቻል በውጭ አገር የሚገኙ በፖለቲካ ድርጅቱ ደጋፊዎች አማካይነት ገንዘብ ተሰባስቦ ለሸኔ እንዲላክ ተስማምቶ ተመልሷል። ይህንን ሒደት እንዲመራ የፖለቲካ ድርጅቱ አመራር የሆነ ግለሰብ  በቀጥታ ኃላፊነት የተሰጠው ሲሆን፣ ጉዳዩ በፖለቲካ ድርጅቱ አባላት መካከል አለመተማመን ወደ መፍጠር እየተሸጋገረ ነው። ምክንያቱም በርካታ የፓርቲው አባላት ሸኔ እያደረሰ የሚገኘውን ጥቃት የሚያወግዙ በመሆናቸው ለሸኔ የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግ የቡድኑ ቀዳሚ የጥቃት ሰለባ የሆነው የኦሮሞ ሕዝብን ሥቃይና መከራ የሚያራዝም በመሆኑ፣ ‹‹የድርጅቱ ኃላፊ ምን ነካቸው?›› የሚል ጥያቄ እያነሱ ይገኛሉ።

በዚህም ምክንያት አንዳንዶቹ የፖለቲካ ድርጅቱ መሪ ከአመራርነት ቢነሱ ሳይሻል አይቀርም የሚል ሐሳብ ማንሸራሸር መጀመራቸውን፣ በውጭ አገር የሚገኝ የድርጅቱ አባላትና ውስጥ አዋቂዎች እየተናገሩ ነው። ጉዳዩን የሚያብሰው ከጥቂት ቀናተ በፊት በተካሄደው የፖለቲካ ድርጅቱ አመራሮች ምርጫ ላይ የኦሮሚያ ክልል በሚገባ አልተወከለም የሚል ቅሬታ የነበራቸው አካላት ውስጥ ለውስጥ ጎራ ለይተው እየተደራጁ በመሆናቸው፣ የፖለቲካ ድርጅቱ መሰንጠቅ እንዳያጋጥመው ሥጋት ፈጥሯል። 

የፖለቲካ ድርጅቱ በተለያዩ ጊዜያት በአገራችን የሚካሄዱ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን በመቃወም፣ የአፈንጋጭነት ባህሪ ሲያሳይ መቆየቱን በተጨባጭ ሐሳቦች አንስቶ ማሳየት ይቻላል። ይህ እንግዲህ በቀዳሚነት ከአመራሮቹ ባህሪ ሊመነጭ የሚችል ችግር መሆኑን በተጨባጭ ከሚታዩ ሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። ለምሳሌ የፓርቲው አመራሮች እውነት ለዴሞክራሲ ቆመዋል ወይ የሚል ጥያቄ ቢነሳ አሳማኝ ምላሽ መስጠት የሚችሉ አይመስለኝም። ለምን ቢባል የፖለቲካ ድርጅቱ ከተመሠረተ ምናልባትም አንዳንዶቹ ፖለቲካ ካወቁ ጀምሮ፣ የፖለቲካ ድርጅቱ መሪ ወይም ፕሬዚዳንት፣ መሪ ያልሆነበት ጊዜ ይኖር ይሆን? እሱም ይሁን፣ ሰውየው በአገራችን የተካሄዱ መልካም ለውጦችን መቼ ይሆን ዕውቅና ሰጥቶ የሚያውቀው? ለሃያ ሰባት ዓመታት ሲታገለው የነበረውን ሕወሓትን አሁን መልሶ ለመታደግ በሚመስል ሁኔታ በግልጽ መተቸት ለምን ተሳነው? ይልቁንም በድብቅ ውጭ አገር ሲሄድ ከሕወሓት ሰዎች ጋር አብሮ ለመሥራት እንደሚፈልግ ውይይት ሲያካሄድ መስተዋሉ፣ ዕውን አመራሩ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ማየት ይፈልጋል? ወይስ እንደ ወያኔ ዘርፎ አገሪቱን ለማራቆት ዕድል የሚፈጥርለትን ሁኔታ ለመፍጠር ነው የሚታገለው?

ለመሆኑ የፖለቲካ ድርጅቱ ምን ለማሳካት ነው የሚታገለው? ኅብረ ብሔራዊ አገር ለመፍጠር ነውን? ከሆነማ ለዚህ አስተዋጽኦ የሚኖራቸውን አገራዊ ሁኔታዎችን መደገፍ ለምን ይፈራል? አገራዊ ምርጫ ይካሄድ ሲባል እሺ ብሎ ተቀበለ፣ ትንሽ ቆይቶ ምርጫ ቦርድ እኔ እንደፈለግኩት አይደለም ስለዚህ አልሳተፍም አለ። የሚገርመው የምርጫ ቦርድ በመመሥረት ሒደት በአብዛኛው ላይ የፖለቲካ ድርጅቱ ራሱ ተሳትፎ ሐሳብ ሲሰጥ ነበር፡፡ እውነታውን ለማረጋገጥ ማኅበራዊ ሚዲያን መከለስ በቂ ማስረጃ ነው። የፖለቲካ ድርጅቱ ሩጫው ማራቶን ሲሆንበት አቋርጦ መውጣቱ የትናንት ትውስታ ነው። በኢሕአዴግ ወቅት ምርጫ ላይ የተሳተፈው የፖለቲካ ድርጅቱ አሁን ከኢሕአዴግ የበለጠ ጫና ስለተፈጠረበት ነው ከምርጫ የወጣው የሚል ጥያቄ ሲነሳም እንደነበረ ይታወሳል።

ከሸኔ የሞራል ድጋፍ አንፃር ስንመለከት አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የሸኔ ታጣቂዎችን ወደ ሰላማዊ መስመር ለማስገባት፣ በአገር ሽማግሌዎችና በአባ ገዳዎች ሲደረግ የነበረውን ጥረት እግር በእግር እየተከታተለ ሲያጠለሽና ሲያደናቅፍ የነበረ ፓርቲ መሆኑን ተጨባጭ ማስረጃዎች አሉ። በርካታ ሰዎችን የገደሉና የጨፈጨፉ የሸኔ ታጣቂዎች በሕግ እንዲጠየቁ ሲደረግ መጀመሪያ ወጥቶ የሚቃወም ይህ ፓርቲ ወይም የፖለቲካ ድርጅት ነው። በኢትዮጵያ መሆኑ ነው እንጂ በሌላው ዓለም የሽብር ቡድን ላይ የሚወሰድ ዕርምጃን መቃወም በራሱ ትልቅ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ነው። በእኛም አገር ቢሆን ተግባራዊ አለመደረጉ ነው እንጂ፣ በፀረ ሽብር ሕጉ ላይ የሽብር እንቅስቃሴዎችን በሞራል መደገፍ በግልጽ ተጠያቂነት እንደሚያስከትል ተቀምጧል።

ይባስ ብሎ የሽብር ቡድኑ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥትን በግልጽ በኃይል ከሥልጣን ለማስወገድ እንደሚፈልግ እየተናገረ፣ ይባስ ብሎ ከሕወሓት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ በሚዲያ ጭምር እያሳወቀ፣ መንግሥት በዚህ ቡድን ላይ ዕርምጃ መውሰድ ሲጀምር በግልጽ ተቃውሟል። በዚህም የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ሸኔ ላይ ዕርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ፖለቲካዊ ንግግር እንዲደረግ ጠይቋል። ለመሆኑ ነፍጥ አንስቶ ሕዝብ በጅምላ ከሚገድል ቡድን ጋር እንዴት የፖለቲካ ንግግር ማድረግ እንደሚቻል ካወቁት ምናለ በተግባር ቢያሳዩን? እውነት አሁን በተጨባጭ ሸኔ እያደረገ የሚገኘው እንቅስቃሴ ለፖለቲካ ንግግር ዕድል የሚሰጥ ነው ብሎ መጠየቅ ለምን ተሳናቸው?

በግልጽ እንደሚታየው የፖለቲካ ድርጅቱ፣ ሸኔን የትሮይ ፈረስ አድርጎ በመጠቀም ወደ ሥልጣን ኮርቻ መወጣጫ ማድረግ ይፈልጋል። ይሁን እንጂ የሁለቱ ቡድኖች ግንኙነት ዕድሜ እንደማይኖረው የሚያሳዩ ሽኩቻዎች እንዳሉ ለማወቅ ነብይነት አይጠይቅም። ከዚህም ውስጥ የፖለቲካ ድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ የሆነውና ተደማጭ ነኝ የሚለው የፖለቲካ አመራር፣ “ኦነግ ላይጠገን ፈርሷል” የሚል ዘመቻ ሲያካሂድ ቆይቶ፣ አሁን እንዴት ከእኛ ጋር ሊሠራ ይችላል የሚሉ ጥያቄዎች በሸኔ ከፍተኛ አመራሮች በስፋት ይነሳሉ። ከዚህም በላይ የፖለቲካ አመራሩ ከቀድሞ የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በነበረው ጥብቅ ጓደኝነት፣ ሸኔን ማዳከም ከቻለ በምላሹ ትልቅ ካሳ እንደሚኖረው በተገባለት ቃል መሠረት ቀላል የማይባሉ የሸኔ ታጣቂዎችን ለመንግሥት አሳልፎ እንደሰጠ እንደማይዘነጉት ይናገራሉ። የፖለቲካ ድርጅቱ ለአጭር ጊዜ ተጠቅሞባቸው እንደሚክዳቸው የቡድኑ አመራሮች ይገልጻሉ።

ሌላው የፖለቲካ ድርጅቱ መሪ አደገኛ አካሄድ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ፍላጎት በሚጎዳ መንገድ ለውጭ ኃይሎች የማሸርገድ ጉዳይ ነው። በግልጽ እንደሚታወቀው የፖለቲካ አመራሩ ወደ አሜሪካ ኤምባሲ ሲመላለስ ማየት የተመለደ መሆኑን በኢምባሲው አካባቢ ያሉ እማኞች ይናገራሉ። የፖለቲካ ድርጅቱ መሪ ሃያት ሬጀንሲ  ሲመላለስ መመልከት የተለመደ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ አንዱን የምዕራብ አገር ኤምባሲ ሠራተኛ እያገኘ መሆኑን እርግጠኛ መሆን ይቻላል። ለአብነትም እንናገር ከተባለ የምርጫው ሰሞን የአሜሪካን አምባሳደር ሃያት ሬጀንሲ አግኝቶ፣ አሜሪካ በአገራችን ምርጫ እንዳይካሄድ ጫና እንድታሳድር ሲለምናት እንደነበር የዓይን ዕማኞች ይገልጻሉ። ለመሆኑ የፖለቲካ ድርጅቱ መሪ በፖለቲካል ሳይንስ ሀ ሁ ውስጥ የአገር ሉዓላዊነትና ክብር ምን ማለት እንደሆነ አልተማረም? አላስተማረም? ለነገሩ ጠንቋይ ለራሱ አያውቅም ይባላል አይደል? አንድ የፖለቲካ ፓርቲ መሪ የውጭ ኃይል በአገሩ ላይ ምርጫ እንዳይካሄድ ጫና እንዲያሳድርለት ከመጠየቅም አልፎ ወደ ልመና ከገባ፣ እንዴትስ ነገ የሕዝብ ድምፅ ለማግኘት ይጠብቃል?  ቢያገኝስ ድምፁን ለውጭ ኃይሎች እንደማይሸጥ በምን እርግጠኛ መሆን ይቻላል? ከዚህም በላይ ይህ አልበቃ ብሎት በ2014 ዓ.ም. መጀመርያ አካባቢ በአሜሪካ ሸራቢነት የሽግግር መንግሥት እንመሠርታለን ብለው ከሚሠሩበት ከየሬስቶራንቱ ፈቃድ ለአንድ ቀን ወስደው ብቅ ያሉ ዘጠኝ ግለሰቦች ውስጥ፣ ይህ የፖለቲካ ድርጅት በግንባር ቀደም ተሳታፊ የነበረ ነው። ለመሆኑ ሊተገብሩት የነበረው የሽግግር መንግሥት የት ደረሰ? መቼ ነው እኛን ማስተዳደር የሚጀምረው? የሚገርመው በዚያ ሒደት ውስም እኮ ሸኔ ተሳታፊ መሆን አለበት የሚል ሐሳብ ሲያነሳ የነበረው ጓደኛው የእዚሁ ፖለቲካ ፓርቲ መሪ ነው።    

አሁን ደግሞ የፖለቲካ ድርጅቱ አመራሮች አመፅ ቀስቅሰን በኦሮሚያ ክልል ቢያንስ ሥልጣን ለመንጠቅ ዕድላችንን እንሞክር የሚል ሐሳብ እያነሱ ነው። ለዚህም ጉልበት እንዲሆናቸው ሸኔ ከጫካ እንዲገፋበት፣ ሕወሓት ደግሞ የአማራና የአፋር ክልሎችን እንዲረብሽላቸው እንደሚፈልጉ ውስጥ ለውስጥ ሲነጋገሩ ተደምጧል። ደግሞ ራሳቸው የተመካከሩትን ከውስጣቸው የሚያወራ ሰው መኖሩ ዕቅዳቸው ሳምንትም ሳይሞላው እንዲጋለጥ እያደረገ ነው። 

በዚህ የአፍራሽ ተግባር ውስጥ ያለው የፖለቲካ ፓርቲው ሸኔን ከመታደግም በላይ፣ አገር ለማፍረስ ዕድል ካገኘ ወደኋላ የማይመለስ መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት ታይቷል። የፖለቲካ ድርጅቱ አመራሮች ለሃያ ሰባት ዓመታት የኦሮሞን ሕዝብ ሲያሰቃይ የነበረን ሕወሓት ወዳጅ አድርገው ሲያሴሩ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ውጭ ባሉ ደጋፊዎቻቸው አማካይነት በጋራ ሆነው ሸኔን ለመደገፍና መንግሥትን በኃይል ከሥልጣን ለማስወገድ ያላቸውን ህልም ለማሳካት እንደሚሠሩ ቃል ተገባብተዋል። በዚህ ጉዳይ ምርጫ ቦርድና የሚመለከታቸው የፍትሕ አካላት መረጃ እንደሚኖራቸው እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል። ነገር ግን ተጠያቂ የማድረጉ ጉዳይ በዚህ ልክ እንዲዘገይ ለምን እንደተፈለገ ብዙዎች ጥያቄ ያነሳሉ። ይዘገያል እንጂ የራሳቸው ወጥመድ መልሶ በሕዝብ እጅ ላይ ይጥላቸዋል በሚል ተስፋ ያደረጉ ቀላል የማይባሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ናቸው።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...