Monday, May 20, 2024

የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት መግለጫና ግብረ መልሱ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ዓምና ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የአምስተኛው ዙር ስድስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን የሕዝብ ተወካዮችና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ሲከፍቱ፣ የማይረሳ የሚባል ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ የመንግሥትን የካቻምና ስኬቶች በመገምገም የ2013 በጀት ዓመትን ዓበይት የሥራ ዕቅዶች ባመለከቱበት በዚያ የመክፈቻ ንግግራቸው፣ ካቻምና (2012 ማለታቸው ነው) ‹‹ብዙ ስኬት የተመዘገበበት መረቅና ፍትፍት ዓመት›› ነበር ሲሉ የገለጹት፡፡ ‹‹መረቅና ፍትፍት›› ባሉት ዓመት በዲፕሎማሲውም ሆነ በፖለቲካውና በኢኮኖሚው መስክ ብዙ በጎ ለውጦች መምጣታቸውን ፕሬዚዳንቷ አመልክተው፣ ይህንን መነሻ በማድረግም ዓምና (2013) ከካቻምናው በእጅጉ የሚሻልና ብዙ ለውጦች የሚመዘገብበት ዓመት እንደሚሆን ከበጎ ምኞታቸው ጋር የመንግሥትን ዋና ዋና ዕቅድ አስረድተው ነበር፡፡

የፕሬዚዳንቷ የሁለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ ንግግር በጊዜው አገሪቱ የገጠማትን ሰላምና ፀጥታ የማስከበር ፈተና በሰፊው ያተተም ነበር፡፡ ይህ ችግር በ2013 ዓ.ም. መፍትሔ እንደሚያገኝና በመንግሥት በኩል ዋና የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም በንግግራቸው አመልክተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ፕሬዚዳንቷ የመንግሥት ዋና ዕቅድ ብለው ያቀረቡት ሰላምና ፀጥታን የማስከበር ጉዳይ፣ በ2013 ዓ.ም. ከቀደመው ዓመት በበለጠ በብርቱ ሲፈተን ነው የታየው፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ሁለቱን ምክር ቤቶች በከፈቱ በወሩ የትግራይ ጦርነት ፈነዳ፡፡ ሕወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ በከፈተው ጥቃት አገሪቱ ወደ ከባድ ጦርነት አመራች፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የታሰበው የሕግ ማስከበርና ሰላም የማስፈን ጥረት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሚፈጠሩ ግጭቶች ሳቢያ እስከ ዛሬ ሳይሳካ መቅረቱን፣ የአገሪቱን ሁኔታ በቅርበት የሚታዘቡ ሁሉ ይናገሩታል፡፡

መንግሥት ከሰሞኑ በወቅታዊ አገራዊ የደኅንነትና የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ያወጣው መግለጫ፣ በኢትዮጵያ ያለው የሕግ ማስከበርና ሰላም ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ያረጋግጣል፡፡ ቅዳሜ ሚያዝያ 15 ቀን 2014 ዓ.ም. የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ይፋ ባደረገው መግለጫ፣ መንግሥት የፀጥታና የሕግ ማስከበርን በተመለከተ ‹‹ትዕግሥቱ መሟጠጡን›› አስታውቋል፡፡ የመግለጫው ይዘት ከዚህ ቀደሞቹ የመንግሥት መግለጫዎች ሁሉ ጠንከርና ኮስተር ያሉ ሐሳቦችን በውስጡ ያጨቀ ነበር ይላሉ አንዳንድ ታዛቢዎች፡፡

ኢትዮጵያ ሦስት ዓይነት ጠላቶች አሏት ሲል የሚነሳው በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤቱ መግለጫ፣ የአገር ጠላቶች ሲል የበየናቸውን አካላት ይዘረዝራል፡፡ የመጀመርያዎቹን ኢትዮጵያ ከምድረ ገጽ እንድትጠፋ የሚተጉ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ናቸው ይላል፡፡ ሁለተኞቹ ደግሞ እንደ ይሁዳ አገራቸውን በሽርፍራፊ ሳንቲም የሚሸጡ አገር ሻጮች አሉ ሲልም ይበይናል፡፡ ከዚህ በመለስ ደግሞ በግዴለሽነት፣ በነሲብና ባለማወቅ ከአገር ጠላቶች ጋር የሚተባበሩ ወገኖች በሦስተኝነት የሚሠለፉ የኢትዮጵያ ጠላቶች መሆናቸውን ይኼው መግለጫ ይዘረዝራል፡፡

‹‹ኢትዮጵያዊያን ለኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ለአገራቸው ባላቸው የፀና ፍቅር የተነሳ፣ ጠላቶቻችን በፈለጉት መንገድ የጥፋት ግባቸውን ማሳካት አልቻሉም፤›› ሲል መግለጫው ሐተታውን ይቀጥላል፡፡ ‹‹ነገር ግን ጠላቶቻችን ተስፋችንን ለማጨለም ብዙ ፈትነውናል፡፡ በብዙ ጋሬጣዎች ውስጥ እንድናልፍም እያደረጉን ይገኛሉ፤›› በማለት ነው የአሪቱን ሁኔታ የሚያስቀምጠው፡፡ አሁን መንግሥት ሁኔታዎች ከሚታገሰው በላይ እንደሆኑበት በመጥቀስም፣ ጠላቶች ሲል በገለጻቸው አካላት ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ ነው የሚያሳስበው፡፡

ይህንኑ የመንግሥት መግለጫ በሚመለከት አንድምታው ምንድነው በሚለው ጉዳይ ሐሳብ የሰጡ ፖለቲከኞች ግን፣ የተለያየ ግብረ መልስ ነው ያንፀባረቁት፡፡ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ሙላቱ ገመቹ፣ ‹‹መንግሥት ሕግን ማስከበር እኮ መደበኛ ሥራው ነው፤›› በማለት ነው ሕግና ሥርዓት ለማስከበር የተለየ መግለጫ እንደማያስፈልግ የተናገሩት፡፡ ‹‹ሕግን እንዴት እንደሚያስከብር፣ በምን እንደሚያስከብርና ሥርዓት እንደሚያሰፍን በሕጎቻችን በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ስለዚህ በየጊዜው እየተነሱ እንዲህ እፈልጣለሁ ወይም እንዲህ እቆርጣለሁ ማለቱ አስፈላጊ አይደለም፤›› ሲሉ አቶ ሙላቱ የመንግሥትን ሰሞነኛ መግለጫ የተረዱበትን መንገድ ገልጸዋል፡፡

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የአደረጃጀት ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ቸኮል በበኩላቸው፣ በመግለጫው የፖለቲካ ምላሽ የሚያሻቸው ጥያቄዎች መነሳታቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ ሆኖም የመግለጫውን አንድምታ፣ ‹‹ዜጎችን ወይም የተለዩ ሐሳብ ያላቸውን ወገኖች የማስፈራራት መንፈስ ያለው ነው፡፡ በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ወገኖችን ለማጥቃት ከበስተጀርባው የተወጠነ ይመስላል፤›› በማለት ነው አቶ ስንታየሁ የመግለጫውን ጥቅል ይዘት ያስረዱት፡፡

የእናት ፓርቲ ዋና ጸሐፊ አቶ ጌትነት ወርቁ ስለዚሁ መግለጫ ይዘት ሲናገሩ፣ ‹‹እነሱ የሚታያቸው ለእኛ ግን የማይታይ አደጋ አገሪቱ ከገጠማት መግለጫው አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን አገሪቱ እየገጠማት ካለው የሆነ የተለየ ችግር ይፈጠራል ብለው በመረጃ ተንተርሰውና ገምተው ከሆነ መግለጫውን ያወጡት አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ዋናው የመንግሥት ሥራ ሕግና ሥርዓትን ማስፈን መሆኑ መረሳት የለበትም፤›› ሲሉ ነው የመግለጫውን ይዘት፣ ወቅታዊነትና አስፈላጊነት አቶ ጌትነት የሚያስረዱት፡፡

ሦስቱም አስተያየት ሰጪዎች መግለጫውን በሚመለከት አስፈላጊ ነው ወይ የሚለውን ጥያቄ በተመሳሳይ ያነሱ ሲሆን፣ ሕግ የማስከበር ሥራ የመንግሥት መደበኛ ኃላፊነት ነው የሚለውን ጉዳይም በተመሳሳይ ሁኔታ አውስተዋል፡፡

ለሪፖርተር በቀጥታ ሐሳባቸውን ያጋሩት ሦስቱ ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆኑ፣ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት መግለጫውን ይፋ ባደረገበት ኦፊሴላዊ የፌስቡክ ገጽ ግርጌ አስተያየታቸውን የሰጡ ዜጎችም በተደጋጋሚ አስተጋብተውታል፡፡ መግለጫው ይፋ በሆነበት በዚህ ፌስቡክ ገጽ የአስተያየት መስጫ ግርጌ የሰፈሩ የዜጎች አስተያየቶች በግብዓትነት ሊጠቀምባቸው ለፈለገ ሁሉ፣ ብዙ ትልልቅ ቁም ነገሮች ይዘው እንደሚያገኛቸው ይገመታል፡፡

ሶሬቲ ጅማ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ዛሬ በመሬት ዘረፋ የተሰማሩ አመራሮችና ሕገወጦች ዋና መከለያቸው አክቲቪስት በመግዛት ዝናቸውን መጠበቅ፣ በሌሎች ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ ማካሄድ ነው ሲሉ በአስተያየታቸው ጠቁመዋል፡፡

ማቲዎስ ገለቦ ለሚታ በበኩላቸው የእርስ በርስ ግጭት በመፍጠር የተጠመዱ ኃይሎች፣ የሕዝብ ስሜትን የሚኮረኩር አጀንዳ እየፈበረኩ በሐሰት ማሠራጨት ሥራቸው ሆኗል በማለት፣ ለሕግ ማስከበር ፈተና ያሉትን ችግር ተናግረዋል፡፡

ሰለሞን ወርቁ የተባሉ አስተያየት ሰጪ የሕግ የበላይነት ካልተከበረ አገር እንደ አገር አትቀጥልም በማለት ነው የጉዳዩን ክብደት ያስቀመጡት፡፡ በዚሁ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፌስቡክ ገጽ ላይ መግለጫውን በተመለከተ የተሰጡ አስተያየቶች እጅግ በርካታ ሲሆኑ፣ በአስተያየቶቹ ላይም ተጨማሪ ውይይቶች ሲካሄዱም ተስተውሏል፡፡ ኅብረተሰቡ በዚሁ አጋጣሚ ሕግ የማስከበር፣ እንዲሁም የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅ ሥራ የመንግሥት መሠረታዊና መደበኛ ሥራ መሆኑን በተደጋጋሚ ሐሳብ ሲሰጥበት ነው የተስተዋለው፡፡

ባለፈው ዓመት እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 24 ቀን 2021 የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ዘንድሮ እንዳደረገው ሁሉ፣ በወቅታዊ የደኅንነትና የፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ አውጥቶ ነበር፡፡ ልክ እንደ ዘንድሮው ሁሉ የዓምናው መግለጫም በሕግ ማስከበርና ሥርዓት ማስፈን ዘርፍ አገሪቱ ከባድ ፈተና እንደተጋፈጠች በሰፊው ያትታል፡፡

‹‹አገራችንን የተጫኗት ችግሮች በቀላሉ መወገድ ቢችሉ ጥሩ ነበር፡፡ ነገር ግን ተበታትነንና ተለያይተን ቀርቶ አንድ ላይ ሆነንም ልንፈታቸው ከባድ ሆነውብናል፤›› በማለት አገር እንዴት እንደሚፈርስ የቤት አፈራረስ ታሪክን ተምሳሌት በማድረግ ብዙ ሐሳቦችን  ይዘረዝራል፡፡ ለውጡ ሲጀምር ብዙ ተስፋ ያደረጉ ወገኖች ዛሬ መናደድ ካለባቸው በራሳቸው የተሳሳተ ግምት ላይ ነው መናደድ ያለባቸው ሲል ቃል በቃል ያስቀመጠው የዓምናው መግለጫ፣ በተለያየ መንገድ በሕዝቡ ዘንድ መነጋገሪያ ፈጥሮ ማለፉ አይዘነጋም፡፡  

የዓምናው መግለጫ አገሪቱ የተሸከመቻቸው በማለት ብዙ ችግሮችን የዘረዘረ ሲሆን፣ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ወሳኝ የመሠረት ድንጋይ የሚጥሉ ብሎ ካስቀመጣቸው የመፍትሔ ዕርምጃዎች አንዱ ደግሞ ያን ሰሞን ሊካሄድ በቀረበው ብሔራዊ ምርጫ በንቃት መሳተፍ የሚል ሐሳብን በጉልህ አንፀባርቆ ነበር፡፡  

የዘንድሮው መግለጫ ከዓምናውም ሆነ ከዚህ ቀደሞቹ ምን ለየው የሚል ጥያቄ እዚህ ላይ መነሳቱ አይቀርም፡፡ ስለሰሞነኛው የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት መግለጫ ምልከታቸውን ያጋሩ የፖለቲካ ሰዎችም ቢሆኑ፣ ልክ እንደ ዓምናውና ካቻምናው ሁሉ ከዘንድሮው መግለጫ ብዙ የተለየ ውጤት ይገኛል ብለው እንደማይጠብቁ ነው የተናገሩት፡፡ ፖለቲከኞቹ እንደሚናገሩት፣ የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤቱ ያወጣውን መግለጫ መንግሥት በተግባር ካልተረጎመው በስተቀር ለተዘረዘሩት ችግሮች መፍትሔ አይገኝም፡፡ በሌላ በኩል ለውጡ መጀመር ካለበት መንግሥት ሕዝቡ እንዲህ ያድርግ ከማለቱ በፊት፣ ራሱን መመልከትና ዕርምጃውን ከራሱ መጀመር አለበት የሚለውን ሐሳብም ፖለቲከኞቹ ይጋሩታል፡፡

የኦፊኮ ከፍተኛ አመራሩ አቶ ሙላቱ፣ ‹‹መንግሥት እኮ ሕዝብ ሰላሜን፣ ደኅንነቴን፣ ጥቅሜን ያስከብርልኛል ብሎ የሚቀጥረው የሕዝብ ተቀጣሪ አካል ነው፡፡ የሪፖርተር ሥራ በዝርዝር እንደሚታወቀው ሁሉ የመንግሥትም ሥራ በሕግ ተቀምጧል፣ በግልጽም ይታወቃል፡፡ እነዚህን ኃላፊነቶች በመደበኛነት በተግባር መተርጎም እንጂ የተለየ መግለጫ ማውጣት አይጠይቅም፡፡ ሕግ ጠዋት፣ ከሰዓት ጨለማ ሳይባል ሁል ጊዜ አለ፡፡ ኢትዮጵያም የምትተዳደረው በሕገ መንግሥትና በሕግ ነው፡፡ የመሬት ወረራን በማስቆም የሕዝብን ጥቅም እናስጠብቃለን ይላሉ፡፡ እኛ በ30 ዓመታት እንዳየነው ግን መሬት በኢትዮጵያ የኢሕአዴግና የብልፅግና ሲሆን እንጂ የሕዝብ ሆኖ አያውቅም፡፡ ስለዚህ ሕጉን ራሳቸው አክብረው ነው ማስከበር መጀመር ያለባቸው፡፡

‹‹መሬት የሚሸጥ የሚለውጠው ማነው? ሰው የሚያስረው ማነው? ሕዝብ የሚያፈናቅለው ማነው? እኛ ሠራዊትም ሆነ የታጠቀም ኃይል የለንም፡፡ ሱዳን በሰሜን ምዕራብ በኩል ድንበራችንን ጥሳ የኢትዮጵያን መሬት ወራለች፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ መሬትን የሚወረውና እንደፈለገ የሚሸጥ የሚለውጠው ከመንግሥት ውጪ ሌላ አካል የለም፤›› ሲሉ የተናገሩት አቶ ሙላቱ፣ የወቅቱ የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት መግለጫ በራሱ በመንግሥት ላይ ጭምር መተግበር እንደሚኖርበት አብራርተዋል፡፡

የባልደራሱ አቶ ስንታየሁ በበኩላቸው፣ መግለጫው በዋናነት ‹‹አርፋችሁ ትገዙ እንደሆነ ተገዙ›› የሚል ይዘት የተጫጫነው መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡ ‹‹በዋናነት ሦስት ዓይነት ዜጎች አሉ ይላል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም ተቃዋሚዎች አባሎቻችሁን ምከሩ ይላል፡፡ ሐሰተኛ መረጃ የሚያሠራጩና የሚሳደቡ ወገኖች በማለትም ይፈርጃል፡፡ እኔ እንደምታዘበው ከሆነ በብልፅግና ከፍተኛ አመራር ውስጥ ያሉ ሰዎች ናቸው የሚሳደቡትም ሆነ የተባለው ነገር የሚገልጻቸው፡፡ መንግሥት ውስጣዊ አንድነቱ ስለተፍረከረከና ስለተዳከመ እሱን ለመሸፋፈን ይመስላል የሰሞኑን መግለጫ ያወጣው፡፡ መንግሥት የራሱን ሥርዓት አልበኞች ቀጥቶ ዕርምጃውን ያሳይ፡፡ ከዚህ ውጪ ሕወሓት በመውደቂያው ሰዓት እንዳደረገው የመግለጫ ጩኸቶች ሁሉ፣ ይህም የተለየ ለውጥ አያመጣም፤›› በማለት ነው አቶ ስንታየሁ ሐሳባቸውን የሰጡት፡፡

የእናት ፓርቲው ዋና ጸሐፊ አቶ ጌትነት፣ ‹‹መንግሥት የተለየ ወይም እስካሁን ከገጠመን የሚከፋ የፀጥታ ችግር መኖሩን አረጋጋጦ ከሆነ፣ መግለጫውን ያወጣው ብዙም አያስገርምም፡፡ ነገር ግን ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ በሚል ፓርቲዎችን በደፈናው የሚፈርጅ የሚመስል አገላለጽ በመግለጫው ተጠቅሟል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የማያዳግም ዕርምጃ እንወስዳለን የሚል ጠንካራ ዛቻም ያሰማል፡፡ ኢመደበኛ በሚሉት ፋኖን በመሳሳለ ኃይል ላይ ለመዝመት የመከጀል ሐሳብ ያለውም ይመስላል፡፡ ዋናው ጥያቄ ግን በዚህ አገር የሕግ የበላይነት ወይም የሰላምና ፀጥታ ዋና ምንጭ የሆነው ማን ነው? የሚለው ነው፡፡ ራሱ መንግሥት፣ ትግራይ የመሸገው ኃይል፣ በኦሮሚያ የሚንቀሳቀሰው? ወይስ የዜጎች መሠረታዊ በሕይወት የመኖር መብት እንዲከበር የሚጠይቀው ነው የፀጥታ ሥጋት? የሚለው ጉዳይ ቢመለስ ይሻላል እላለሁ፡፡ የመሬት ወረራና የፀጥታ ሥጋት የሚል መግለጫ ከሚሰጡ ቦሌ ጎራ ቢሉ የችግሩን ምንጭ ያዩታል፣ መተከል ሄድ ቢሉ ችግሩን ያገኙታል፤›› ሲሉ ነው አቶ ጌትነት በትክክል የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት ተብሎ መግለጫው ስለመውጣቱ በጥያቄ የሚያነሱት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -