Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበኦሮሚያ ክልል ሁለት ተሽከርካሪዎች የጫኑት ማዳበሪያ በታጣቂዎች ተዘረፈ

በኦሮሚያ ክልል ሁለት ተሽከርካሪዎች የጫኑት ማዳበሪያ በታጣቂዎች ተዘረፈ

ቀን:

ሁሉም የደረቅ ጭነት ትራንስፖርት ማኅበራት ማዳበሪያ ለማጓጓዝ ተስማሙ

በኦሮሚያ ክልል የአፈር ማዳበሪያ ለማድረስ በነቀምት መስመር ላይ ሲጓዙ የነበሩ ሁለት የጭነት ተሽከርካሪዎች፣ በምዕራብ ሸዋ ዞን ከባኮ ከተማ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች መዘረፋቸው ተገለጸ፡፡

ተሽከርካሪዎቹ ከቀናት በኋላ ከእነ አሽከርካሪዎቻቸው ቢመለሱም ጭነውት የነበረው ማዳበሪያ ሙሉ ለሙሉ መዘረፉን፣ የተሽከርካሪዎቹ ባለቤት የሆነው ፈጣን ድንበር ተሻጋሪ የደረቅ ጭነት ማመላለሻ ባለንብረቶች ማኅበር አስታውቋል፡፡ በአካባቢው ማዳበሪያ ለማጓጓዝ አብዛኛውን ጨረታ ማሸነፋቸውን ለሪፖርተር የገለጹት የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ መርሻ ፀጋዬ፣ በመጋቢት ወር በታጣቂዎች ሁለቱ ተሽከርካሪዎች እያንዳንዳቸው ይዘውት የነበረው 435 ኩንታል ማዳበሪያ መዘረፉን አስታውቀዋል፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ ተሽከርካሪዎቹ በታጣቂዎች የተያዙት ከባኮ ከተማ አምስት ኪሎ ሜትር ወጣ ያለ አካባቢ ቢሆንም፣ ከዋናው መንገድ ወደ ውስጥ ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ እንዲጓዙ ተደርገዋል፡፡ ጭነታቸው በታጣቂዎች እንዲራገፍ ከተደረገ በኋላ አሽከርካሪዎች በሰላም ቢመለሱም በተሽከርካሪዎቹ ጎማ፣ መስታወትና ሌሎች አካላት ላይ ጉዳት መድረሱንም አስረድተዋል፡፡

አሽከርካሪዎቹ ማስፈራሪያ እንደ ደረሰባቸውና ለታጣቂዎቹ ወደ አካባቢው እንዳይሰማሩ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው የሚናገሩት አቶ መርሻ፣ በዚህም ምክንያት ማኅበሩ ወደ አካባቢው ተሽከርካሪዎችን ለመላክ ሥጋት እንዳደረበት ገልጸዋል፡፡ ሥራ አስኪያጁ የደረሰውን ዘረፋ ለኦሮሚያ ክልል ፀጥታ ቢሮ፣ ለግብርና ሚኒስቴርና ለሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ማስታወቁንና አሁን በመንግሥት ዕጀባ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አክለዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ፣ በተሽከርካሪዎቹ ላይ ስለደረሰው ዘረፋ መስማታቸውን ተናግረው፣ ዘረፋው የደረሰው በእጀባ መንቀሳቀስ ሲገባቸው ይኼንን ባላደረጉ ተሽከርካሪዎች ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የእርሻ ወቅት ከመድረሱ በፊት የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ለማከፋፈል እየሠራ ያለው መንግሥት፣ ለዘንድሮ የሰብል ዘመን ከገዛው 12.8 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ውስጥ፣ ከስድስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሚሆነው ጂቡቲ ወደብ ደርሷል፡፡ ከዚህ ውስጥም ከ4.7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሚሆነው በመሠራጨት ላይ ነው፡፡

መንግሥት የሰኔ ወር ከመጠናቀቁ በፊት ማዳበሪያውን ለማሠራጨት በማሰብ፣ ከወራት በፊት ከ17 የትራንስፖርት ማኅበራት ጋር ውል የገባ ቢሆንም፣ አሁን ሁሉም አገር አቋራጭ የደረቅ ጭነት ትራንስፖርት ማኅበራት በሚሰጣቸው ኮታ መሠረት 1.28 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያና ስንዴ እንዲያጓጉዙ ጠይቋል፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ከ72 ማኅበራት ጋር ባደረገው ውይይት፣ ማኅበራቱ ማዳበሪያውን ለሟጓጓዝ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውቋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የትራንስፖርት ማኅበራት እንደተናገሩት፣ በውይይት ላይ ከተነሱ ሥጋቶች መካከል አንዱ የፀጥታ ችግር ሲሆን፣ መንግሥት ለፀጥታ ችግር ኃላፊነት እንደሚወስድና ወለጋ አካባቢ ዕጀባ ለማድረግ መስማማቱን ተናግረዋል፡፡

ይሁንና ሁሉም ማኅበራት ማዳበሪያውን የሚያጓጉዙት ጨረታ አሸንፈው ውል የፈጸሙ ማኅበራት በተስማሙበት ታሪፍ በመሆኑ ያልተስማማቸው የትራንስፖርት ማኅበራት አሉ፡፡

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የአንድ አገር አቋራጭ የደረቅ ጭነት ትራንስፖርት ማኅበር ሥራ አስኪያጅ፣ ጨረታው በ2014 ዓ.ም. የመጀመሪያ ወራት ላይ ሲወጣ የነበረው የመኪና መለዋወጫ ዕቃዎች ዋጋና አሁን ካለው ዋጋ ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ጭማሪ ያለው በመሆኑ አዋጭ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

የሩሲያና የዩክሬይን ጦርነት ለመለዋወጫ ዕቃዎች ዋጋ መጨመር እንደ አንድ ምክንያት ያወሱት ሥራ አስኪያጁ፣ ‹‹ጨረታውን ያሸነፉት ማኅበራት የተስማሙት ዋጋ ሊያዋጣቸው ይችላል፣ ለእኛ ግን አይሆንም፤›› ብለዋል፡፡

ይሁንና መንግሥት የማዳበሪያ ዋጋ አሁን ባለበት ሁኔታ ከፍተኛ ጭማሪ በማሳየቱ፣ የትራንስፖርት ዋጋን ከፍ ማድረግ እንደማይችል መግለጹ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...