በሐረር ከተማ ሸንኮር ወረዳ፣ የሺ እመቤት ትምህርት ቤት አካባቢ በሚገኝ ዩዲ በተባለ ሆቴል ውስጥ ሲዝናኑ በነበሩ ሰዎች ላይ፣ በትንሳዔ በዓል ዕለት እሑድ ሚያዝያ 16 ቀን 2014 ዓ.ም. የትንሳዔ ዕለት በተወረወረ ቦንብ ስምንት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የሐረሪ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ከምሽቱ 2፡45 ላይ በሆቴሉ ወስጥ ተሰብስበው በነበሩ ሰዎች መሀል ቦምቡ መወርወሩን ለሪፖርተር የተናገሩት የሐረሪ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ነስሪ ዘከርያ፣ ግለሰቦቹ ለሕክምና መወሰዳቸውን አስረድተዋል፡፡ እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ ግለሰቦቹ የደረሰባቸው ጉዳት ቀላልና ለሕይወታቸው አሥጊ ያልሆነ ሲሆን፣ ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች ውስጥ አራቱ በማግሥቱ ሰኞ ሚያዝያ 17 ቀን 2014 ዓ.ም. ከሆስፒታል ወደ ቤታቸው ገብተዋል፡፡ ኮሚሽነር ነስሪ፣ ቀሪዎቹ አራት ግለሰቦች አሁንም በሕክምና ላይ መሆናቸውን ተናግረው፣ እግራቸው አካባቢ የደረሰባቸው የመቁሰል አደጋ ከባድ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡
ጉዳዩ በምርመራ ላይ በመሆኑ የጥቃት አድራሾቹን ማንነት መናገር ከባድ መሆኑን የተናገሩት ኮሚሽነሩ፣ ከጥቃቱ በተያያዘ የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታውቀዋል፡፡
ኮሚሽነር ነስሪ፣ ከዚህ አደጋ መከሰት በኋላ የተፈጠረ የሰላም መደፍረስ አለመኖሩን ተናግረው ‹‹ከሽብር ጋር ግንኙነት ይኑረው አይኑረው፣ መሬት ላይ በሌለና ባልተረጋገጠ ነገር መናገር ተገቢ አይደለም፡፡ በአንዳንድ ማኅበራዊ ሚድያዎች ደግሞ ዳግመኛ እንደተፈጠረ ሲናገሩ ነበር ሐሰትና ያልተረጋገጠ ነው፤›› ብለዋል፡፡