Sunday, June 16, 2024

የመንግሥት አሠራር የልምድ ሕክምና አይሁን!

የመንግሥት አሠራር በሥርዓት እንዳይመራ ከሚያደርጉ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ ለባለሙያዎች እዚህ ግባ የሚባል ትኩረት አለመሰጠቱ ነው፡፡ መንግሥት በተለያዩ ዘርፎች አዳዲስ አሠራሮችን ሲያስተዋውቅ ወይም ውሳኔዎች ላይ ሲደርስ፣ በአሠራሮቹ ምክንያት ሊተከተሉ የሚችሉ አዎንታዊና አሉታዊ ጎኖች ጥርት ብለው መታወቅ አለባቸው፡፡ ነገር ግን ብዙዎቹ አሠራሮችና ውሳኔዎች የባለሙያዎች ዕገዛ ስለማይደረግላቸው፣ በግርግርና በትርምስ የተሞሉ ዕርምጃዎች የሰዎችን ሕይወት እያቃወሱ ነው፡፡ ፖለቲካውን ሁሉንም ወገኖች በሚያግባባ ምኅዳር መምራት ባለመቻሉ፣ አገሪቱ የተቃርኖና የግጭት መናኸሪያ ሆና የንፁኃንን ደም መፍሰስ ማቆም አልተቻለም፡፡ የኑሮ ውድነቱ ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ ሕይወት ከሲኦል ባልተናነሰባት ኢትዮጵያ ውስጥ፣ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ማመንጨት አቅቶ ደመነፍሳዊ እንቅስቃሴዎች በዝተዋል፡፡ ሸማቹን ሕዝብ ከሕገወጥ የግብይት አሠራር እንዲከላከል በሕግ የተመሠረተ መንግሥታዊ ተቋም፣ እንኳንስ ሕዝቡን ሊታደግ ከእነ መኖሩም የተረሳ ይመስላል፡፡ የመንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነት የሕዝብን ደኅንነትና ሰላም መጠበቅ መሆኑ እየታወቀ፣ ሕግ ማስከበር ባለመቻሉ እየደረሰ ያለው ጥፋት ቀላል አይደለም፡፡ ደመነፍሳዊ አሠራሮችን በማስወገድ ኃላፊነትን መወጣት ሲገባ፣ ልማዳዊ አሠራሮች ሕዝቡን እያስመረሩ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በተለያዩ የዕውቀትና የሥራ መስኮች ከፍተኛ ልምድ ያዳበሩ በርካታ ልጆች አሏት፡፡ አገር በቀሉን ዕውቀት ከዘመናዊው ትምህርት ጋር አቀናጅተው ለዕድገት የሚጠቅሙ ውጤቶች ማስገኘት የሚችሉ ሞልተዋል፡፡ ከአገር ውስጥ ጀምሮ በመላው ዓለም ኢትዮጵያውያን በዲፕሎማሲ፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በትራንስፖርት፣ በፋይናንስ፣ በቱሪዝም፣ በማዕድናት፣ በቴክኖሎጂና በሌሎች በርካታ ዘርፎች ለፖሊሲና ለስትራቴጂ ዝግጅት አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችሉ በብዛት አሉ፡፡ አገራቸው በምትፈልጋቸው ጊዜ በነፃ ጭምር አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ያስታወቁ ቁጥራቸው ብዙ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አገራቸውን ለማዘመንና ሀብታም ለማድረግ የሚረዱ አዋጭ የፖሊሲና የስትራቴጂ ዝግጅቶችን በየዘርፉ ለመቅረፅ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚፈልጉም ይናገራሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት በጎ ተነሳሽነት ያላቸው በጣም ብዙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያሏት አገር ግን የታደለች አትመስልም፡፡ በየጊዜው የሚለዋወጡ መንግሥታት ለልማትና ለዕድገት መነሳታቸውን ቢደሰኩሩም፣ ለማስመሰል ነው እንጂ ለአገር ጠቃሚ የሆኑ ሰዎች አጠገባቸው እንዲገኙ አይፈልጉም፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያም ይህ ሁሉ ችግርና መከራ ተቆልሎ አገር የሚጠቅሙ ሰዎች ወደ ጎን ተገፍተዋል፡፡

አንድ ታዋቂ የንግድ ሰው በደረሰበት ኪሳራ ምክንያት በሚያስተዛዝኑት ሰዎች ኪሳራው እንዴት እንዳጋጠመው ሲጠየቅ፣ ‹‹ቀስ በቀስ እያለ፣ ነገር ግን በድንገት ነበር›› ብሎ ነበር የመለሰው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ቀስ በቀስ እየተለመዱ የመጡ ችግሮች ድንገት ከቁጥጥር የወጡ እንደሆነ፣ ግን ጠያቂና መላሽ ስለመኖራቸው የሚያጠራጥሩ በርካታ ምልክቶች አሉ፡፡ ኢኮኖሚው እየደረሰበት ያለው ጫና አገርን እያጎበጠ ባለበት በዚህ ጊዜ፣ በባለሙያዎች ዕገዛ የፖሊሲና የስትራቴጂ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ፣ ደመነፍሳዊ እንቅስቃሴዎች በስፋት ይስተዋላሉ፡፡ የኑሮ ውድነቱን በመግታት መረጋጋት ለመፍጠር ከመስኩ ባለሙያዎች ጋር ምክክር በማድረግ መፍትሔ ማግኘት ሲገባ፣ ለሰሚም ሆነ ለተመልካች አደናጋሪ የሆኑ ዕርምጃዎች እየተወሰዱ ከችግር አዙሪት ውስጥ መውጣት አልተቻለም፡፡ እዚህ ላይ በቅርቡ በፍራንኮ ቫሉታ ምርቶችን ከውጭ ለማስገባት የተደረሰበትን ውሳኔ ማጤን ተገቢ ነው፡፡ ለፖለቲካዊ ችግሮች የሚበጁ አገር በቀልና ከውጭ የሚገኙ ጠቃሚ ልምዶችን በጋራ ተቀምጦ ከመቀመር ይልቅ፣ ከዚህ በፊት ሕዝብና አገርን መከራ ውስጥ የከተቱ ፋይዳ ቢስ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ሥራዬ ተብሎ ቀጥሏል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም ጠፍቶ በየቦታው የግጭትና የውድመት ዜና መስማት ከተለመደ ሰነባብቷል፡፡ በመላ አገሪቱ የግጭት አወጋገድና የሽምግልና ሥርዓቶች ግን ሞልተዋል፡፡ በማኅበረሰቦች ውስጥ ችግሮች ሲያጋጥሙ በእምነት መሪዎችና በአዛውንቶች አማካይነት መፍትሔ መፈለግ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ በሰሜን፣ በምሥራቅ፣ በደቡብና በምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች በሽምግልና ጠብን አብርዶ ዕርቅ መፍጠር የተለመደ አኩሪ እሴት ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ በደም የሚፈላለጉ ሰዎችን አስታርቆ በጋብቻ ማስተሳሰርም የተለመደ አኩሪ ባህል ነው፡፡ ይህንን የመሰለ የጋራ አገር በቀል ዕውቀትን ከዘመናዊው ጋር በማቀናጀት ለዓለም መትረፍ ሲቻል፣ እርስ በርስ እየተጋደሉ ታሪክን ማበላሸት ነው ሥራዬ ተብሎ የተያዘው፡፡ በሌላ በኩል ኢኮኖሚው እየተፍረከረከና የኑሮ ውድነቱ መያዥ መጨበጫ ሲያጣ፣ አገር በቀሉን ከዘመናዊው ዕውቀት ጋር አዛምዶ መፍትሔ ለመፈለግ ሙከራ ሲደረግ አይታይም፡፡ በተለያዩ መስኮች ዕውቀቱና ልምዱ ያላችሁ ለመፍትሔ የሚበጁ ዕገዛ አድርጉ አይባልም፡፡ ‹‹ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲያ›› እንደሚባለው፣ ለኢኮኖሚውም ሆነ ለኑሮ ውድነቱ ከመንግሥት በኩል የሚቀርቡ መፍትሔዎች ግራ ያጋባሉ፡፡

በሰሞኑ የፍራንኮ ቫሉታ መፈቀድ ለኢኮኖሚው ያለው ፋይዳ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ፍራንኮ ቫሉታን መፍቀድ ማለት ሕገወጥ የውጭ ምንዛሪ ዝውውር ማበረታታት ነው ይላሉ፡፡ እንዲያውም ለጥቁር ገበያ ከለላ የመስጠት ያህል ነው የሚያዩት፡፡ በፍራንኮ ቫሉታ ገበያው ውስጥ እጥረት የተፈጠረባቸውን የተለያዩ ምርቶች ከውጭ በብዛት ለማስገባት አቅም ያላቸው ኢትዮጵያውያን ወይም ዳያስፖራዎች ካለመኖራቸውም በላይ፣ በሕጋዊውና በጥቁር ገበያው መካከል የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ተመን ያሰፋዋል ሲሉም ያስጠነቅቃሉ፡፡ በጥቁር ገበያ ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ፈላጊ ሲበዛና እጥረት ሲፈጠር፣ የኑሮ ውድነቱን የበለጠ ያጦዘዋል በማለትም ያሳስባሉ፡፡ መንግሥት በበኩሉ የዕርምጃውን ቅቡልነት የሚያሳይ አመክንዮ ካለው መልካም፣ ካልሆነ ግን ዘለቄታዊ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ የባለሙያዎችን ምክረ ሐሳብ ይስማ፡፡ ኤክስፖርተሮችን የሚያበረታታ አሠራር ከሌለ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ይዳከማል፡፡ ኤክስፖርተሮች ሲበረታቱ ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ በብዛት የምግብ ምርቶች ሊያስገቡ ይችላሉ፡፡ የአገሪቱን ውስን የውጭ ምንዛሪ ማድፋፋት መቆም አለበት፡፡ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደሩ በባለሙያዎች ዕገዛ ይደረግለት፡፡ አሁን የሚታየው አሠራር አገሪቱን የበለጠ ችግር ውስጥ ነው የሚከታት፡፡

መንግሥት ከእንዲህ ዓይነቱ አገርን ከሚያከስር አሠራር ውስጥ ለመውጣት ጥረት ማድረግ አለበት፡፡ ለአገር የሚጠቅሙ ባለሙያዎች በአገሪቱ ዙሪያ መለስ ችግሮች ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማበረታታት ተገቢ ነው፡፡ በፖለቲካው፣ በዲፕሎማሲው፣ በኢኮኖሚው፣ በማኅበራዊና በሌሎች ጉዳዮች የባለሙያዎች ዕገዛ ሲኖር ፖሊሲዎችም ሆኑ ስትራቴጂዎች ሲቀረፁ አዋጭነታቸው ላይ ስምምነት ይፈጠራል፡፡ ከአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚንቆረቆር ሐሳብም ሆነ የሥራ መዘርዝር የባለሙያዎች ምክረ ሐሳብ ከጎደለው፣ የሚከተለው ጭቅጭቅና ውዝግብ ከመሆኑም በላይ ውጤቱም ፋይዳ ቢስ ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምስክር መጥራት አስፈላጊ አይሆንም፡፡ በተለያዩ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ የሚስተዋለውን ተቃርኖ ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ ከዚህ ቀደምም ቢሆን ከቃላት አተካሮ አልፈው ደም አፋሳሽ ግጭትና ጦርነት ውስጥ የከተቱ ልዩነቶች፣ በብሔራዊ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ ለመመካከር ካለመፈለግ የመነጩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የመንግሥት አሠራር ለልብ ሕመም ወጌሻ የሚታዘዝበት የልምድ ሕክምና አይሁን!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...

ከውጭ በተላከ ገንዘብ ሀብት አፍርቶ የተላከበትን ደረሰኝ ያላቀረበ ንብረቱ እንዲወረስ የሚደነግግ አዋጅ ቀረበ

በጥፋተኝነት ላይ ያልተመሠረተ ንብረት የመውረስ ድንጋጌም በአዋጁ ተካቷል አዋጁ የሚፀድቅ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...

የዘመኑ ትውልድ ለአገሩ ያለውን ፋይዳ ይመርምር!

በዚህ በሠለጠነ ዘመን ኢትዮጵያን የሚያስፈልጓት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከብዙዎቹ በጣም ጥቂቱን አንስተን ብንነጋገርባቸው ይጠቅሙ ይሆናል እንጂ አይጎዱም፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ብዙኃኑ ሕዝቧ ያስፈልጓቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ...

ከግጭት አዙሪት ውስጥ የሚወጣው በሰጥቶ መቀበል መርህ ነው!

የኢትዮጵያን ሰላም፣ ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅሞች ማዕከል በማድረግ መነጋገር ሲቻል ለጠብ የሚጋብዙ ምክንያቶች አይኖሩም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሚደረጉ ክንውኖች በሙሉ ከጥፋት የዘለለ ፋይዳ አይኖራቸውም፡፡ በኢትዮጵያ ዘርፈ...