በመንገድ ግንባታ ለተሠማሩ ኮንትራክተሮች ከዋጋ ማካካሻ ጋር በተያያዘ ተጥሎባቸው የነበረው ገደብ ተነስቶ፣ በገበያ ዋጋ እንዲሠላላቸው መወሰኑ ተገለጸ፡፡
የሪፖርተር ምንጮች እንደለገጹት፣ በመንገድ ግንባታ ላይ ለተሰማሩ ኮንትራክተሮች ወቅታዊውን የዋጋ ንረት ያገናዘበ ማካካሻ እንዲሠላላቸውና እስካሁን የነበረውን አሠራር እንዲቀር ውሳኔ ያሳለፈው የገንዘብ ሚኒስቴር ነው፡፡
እስካሁን በነበረው አሠራር ኮንትራክተሮች ለሚገጥማቸው የዋጋ ንረት የሚፈቀድላቸው የዋጋ ማካካሻ፣ ከፕሮጀክቱ ጠቅላላ ገቢ ከ20 በመቶ በላይ መብለጥ እንደሌለበት የሚደነግግ ነበር፡፡ አሁን ግን ይህ ጣሪያ ተነስቶ በዓለም አቀፉ ዋጋ ማካካሻ አሠራር መሠረት ጥያቄያቸው እንዲስተናገድ፣ ለኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በደብዳቤ እንደተገለጸለት፣ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮች ለመረዳት ተችሏል፡፡ ማንኛውም ኮንትራክተር የሚያቀርበው የዋጋ ማካካሻ ከፕሮጀክቱ ጠቅላላ ወጪ ከ20 በመቶ መብለጥ የለበትም የሚለውን ድንጋጌ እንዲወጣ፣ ይህንንም ሲያስፈጽም የነበረው የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር እንደነበር ይታወቃል፡፡
እየታየ ያለው ከፍተኛ የዋጋ ንረት እየፈጠረ ያለውን ችግር በማየት፣ በሁሉም የኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ ያሉ ኩባንያዎች ወቅታዊው የዋጋ ንረት ያገናዘበ ማካካሻ የማይሰጥ ከሆነ፣ ግንባታዎቹን ጨርሶ ለማስከረብ የማይቻል መሆኑን በማሳወቃቸው፣ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት እንዲወሰን መደረጉንም ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በዚህ የዋጋ ንረት ምክንያት ሥራውን ለመቀጠል አለመቻላቸውን በመግለጽ፣ የዋጋ ማካካሻው እንዲሰጣቸው ለወራት ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ሲመክሩበት እንደቆዩ፣ በመጨረሻ ላይ ግን አዎንታዊ ምላሽ ማግኘታቸው ተሰምቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ዋጋ እስከ 300 የጨመረ በመሆኑ፣ ከዚህ ቀደም የመንገድ ግንባታዎቹ ይጠናቀቁበታል ተብለው ውል በተገባላቸው ዋጋ መሠረት ማጠናቀቅ እንደማይቻል በተደጋጋሚ ሲገለጽ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
አሁን በግንባታ ላይ ላሉ የመንገድ ፕሮጀክቶች የሚያቀርቡት የዋጋ ማካካሻ ዓለም አቀፍ ደረጃ፣ የዋጋ ማካካሻ ጥያቄ በሚስተናገድበት መንገድ ኮንትራክተሮች እንዲስተናገዱ የሚፈቅድ ቢሆንም፣ ይህ ውሳኔ መንግሥትን ለከፍተኛ ወጪ ይዳርጋል ተብሎ ተሠግቷል፡፡
የዋጋ ማካካሻ ጥያቄ በሕንፃ ግንባታ ላይ የተሰማሩ ኮንትራክተሮችም ያቀረቡ ቢሆንም፣ መንግሥት በመንገድ ግንበታ ላይ ለተሠማሩ ኮንትራክተሮች ቅድሚያ ሰጥቷል፡፡ በሕንፃና በሌሎች የግንባታ ዘርፎች ውስጥ የሚገኙ ኮንትራክተሮች ከዋጋ ማካካሻ ጋር ያቀረቡት ጥያቄ አሁንም እየታየላቸው መሆኑን ግን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይህ በገንዘብ ሚኒስቴር ተወስኖ ለኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የተላለፈው ውሳኔ የሚተገበረው፣ በግንባታ ላይ ለሚገኙና እንዲገነቡ የኮንትራት ውል ለተሠራላቸው ፕሮጀክቶች ብቻ ነው፡፡
በዚህ ውሳኔ ላይ ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የተገኘው መረጃ ደግሞ የዋጋ ማካካሻን በተመለከተ ሲሠራበት የነበረው የ20 በመቶ ገደብ መነሳቱን የሚያረጋግጥ ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት ግን ተቆጥቧል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአስተዳደሩ ባለቤትነት በመገንባት ላይ ያሉ ከ160 በላይ የመንገድ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች በ2014 ዓ.ም. ለአንድ ዓመት የተያዘላቸው በጀት ደግሞ ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡