Monday, September 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

  የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

  ቀን:

  በትንሳዔ በዓል ማግሥት ከቀኑ ስምንት ሰዓት ሲሆን ከምሳ በኋላ ቡና እየጠጣሁ ወጪ ወራጁን አያለሁ፡፡ ቡና እየጠጣሁበት ያለው ካፌ የሚገኘው ከቦሌ መድኃኔዓለም ወደ ብራስ ሆስፒታል በሚወስደው መንገድ ዳር ላይ ነው፡፡ በረንዳው ላይ ተቀምጬ ወጪ ወራጁን ሳማትር ከፊት ለፊቴ አንድ የአውሮፓ ገጽታ ያለው ፈረንጅ ባየው ነገር እየተደናገጠ በፍጥነት ይራመዳል፡፡ ምን ሆኖ ነው ብዬ እሱ እያየው ባለው አቅጣጫ ፊቴን ሳዞር፣ አንዲት የእኔ ቢጤ ከሦስት ልጆቿ ጋር ተቀምጣለች፡፡ እናትና ልጆች ለከተማው እንግዳ ይመስላሉ፡፡

  ይኼ ፊቱ በድንጋጤ ድርቅ ያለ ፈረንጅ እየተንደረደረ ሄዶ ሴትዮዋ አጠገብ ከደረሰ በኋላ ለማናገር ይሞክራል፡፡ የእኔ ቢጤዋ ፈረንጁ ምን እንደሚል ስላልገባት በመገረም ታየዋለች፡፡ እሱ ቁጣ በተቀላቀለበት ሁኔታ መናገር ሲጀምር በመንገዱ ላይ በመተላለፍ የነበሩ ሰዎች ከጉዞአቸው ተገተው ቆሙ፡፡ ፈረንጁ የእኔ ቢጤዋ አጠገብ ከተቀመጡት ልጆቿ መካከል አንዱ ላይ እያነጣጠረ፣ ‹‹ይኼን ልጅ ከየት አመጣሽው?›› በማለት ነበር ጥያቄ የሚያቀርበው፡፡

  ዓይኖቼን ወደ ልጆቹ ስመልስ አንደኛው ሕፃን ቁርጥ ፈረንጅ ይመስላል፡፡ ቆዳው ሙሉ በሙሉ የፈረንጅ ሆኖ ፀጉሩ የነጣና ሉጫ (ብሎንድ) የሆነውን ሕፃን ከእኔ ቢጤዋ ጋር ያገኘው ፈረንጅ፣ ከዚህ ቀደም የገዛ ልጁ የጠፋበት ወይም ዘመዱን ያጣ ይመስል ሕፃኑን እያየ፣ ‹‹ይህች ሴት ይህንን ሕፃን ከየት እንዳመጣችው ማወቅ እፈልጋለሁ…›› እያለ ሲወራጭ ዙሪያውን የከበቡት ሰዎች ዝም ብለው ያዳምጣሉ፡፡ ፈረንጁ እየተንቆራጠጠ ሲውረገረግ ሴትየዋን ደብድቦም ቢሆን ልጁን ከየት እንዳመጣችው ለማወቅ የሚፈልግ ይመስላል፡፡

  በፈረንጁ አኳኋን ግራ የተጋቡት ሕፃናትና እናታቸው ምን መዓት መጣብን ብለው ኩርምት ብለው ተቀምጠዋል፡፡ እኔ ሒሳቤን በቶሎ ከፍዬ ወደ ግርግሩ ቦታ በመሄድ ፈረንጁ ለምን ይህንን ጥያቄ እንደሚያቀርብ ለማወቅ ስጠጋ በችኮላ ከአካባቢው ፈትለክ ብሎ ሄደ፡፡ በዚህ መሀል እዚያ ከተሰባሰቡ ሰዎች አንዱ፣ ‹‹ይኼ የአንቺ ልጅ ነው?›› በማለት እናትየዋን ሲጠይቅ፣ ሦስቱም ልጆች ከአንድ አባት የተወለዱ መሆናቸውን ትነግረዋለች፡፡ አንዱ፣ ‹‹ፈረንጅ ይመስላል እኮ?›› ሲላት ሴትየዋ በተኮለታተፈ አማርኛ፣ ‹‹አባቱም እንደዚህ ሰው ቀይ ነው…›› እያለች ወደ አንዱ አመላከተች፡፡ ፈርጥጦ ሄዶ የነበረው ፈረንጅ ከአፍታ ቆይታ በኋላ አንድ የትራፊክ ፖሊስ ባልደረባ ይዞ መጣ፡፡

  የትራፊክ ፖሊሱ ሴትየዋንና ልጆቹን ወደ ሕግ በመውሰድ ሴትዮዋ ነጭ የሚመስለውን ሕፃን ከየት እንዳመጣች እድትጠየቅ እንዲያደርግ ፈረንጁ ትዕዛዝ መሰል ጥያቄ ሲያቀርብ፣ ውስጡ በዘረኝነት የተሞላ ይመስል ነበር፡፡ አንዲት አፍሪካዊት ለማኝ እንዴት የፈረንጅ ልጅ ይዛ መንገድ ላይ ትገኛለች የሚል ቁጭት ያለበት ይመስላል፡፡ ዓይኖቹም ያሳብቃሉ፡፡ በዚህ መሀል አንድ ሌላ ሞተረኛ የትራፊክ ፖሊስ ባልደረባ ደርሶ ለሴትየዋ ጥያቄ ማዥጎድጎድ ሲጀምር የተወሰኑ ሰዎች ማጉረምረም ጀመሩ፡፡ እስከዚያ ሰዓት ድረስ የሐበሻ ልጆች ፀጥ ብለው ድራማ የሚያዩ ይመስሉ ነበር፡፡ እኔ የትራፊክ ፖሊሶቹ አኳኋን ስላላማረኝ ጠጋ ብዬ ለመገሰፅ ስዘጋጅ አንድ ወጣት ተንደርድሮ መጣ፡፡

  ወጣቱ ንዴት ፊቱ ላይ እየተንቦገቦገ ፈረንጁን፣ ‹‹አንተ ማነህ?›› በማለት ጥያቄ አቀረበለት፡፡ ፈረንጁ፣ ‹‹ጋዜጠኛ ነኝ…›› አለው፡፡ ወጣቱ ተናዶ፣ ‹‹አትመስለኝም፡፡ ጋዜጠኛ እንዲህ አይደለም…›› ካለው በኋላ፣ ‹‹ከዚህ ልጅ ጋር የሚያገናኝህ ትውውቅ አለህ?›› ሲለው ፈረንጁ ትውውቅ እንደሌለው ተናገረ፡፡ ወጣቱ አበደ ማለት ይቻላል፡፡ ‹‹በማያገባህ ገብተህ ምን ትፈተፍታለህ? የማያገባህ ከሆነ ዘወር በል ከዚህ…›› ብሎ ወደ ትራፊክ ፖሊሶቹ ዞረ፡፡ ‹‹ይህች ደሃ ሴት በገዛ አገሯ ከእነ ልጆቿ በማታውቀው ፈረንጅ ስትዋከብ እንዴት ትተባበራላችሁ? ድህነቷ አልበቃ ብሎ ከእነ ልጆቿ እንደ አውሬ ስትከበብ እንዴት ዝም ትላላችሁ?›› ሲላቸው የብዙዎችን ድጋፍ አገኘ፡፡ የትራፊክ ፖሊሶቹ ምላሽ አጥጋቢ ባይሆንም ጉዳዩን ለማጣራት መምጣታቸውን ተናገሩ፡፡ ፈረንጁም ከአካባቢው ሹልክ ብሎ ጠፋ፡፡

  በእንዲህ ዓይነቱ አሳዛኝ አጋጣሚ እኔን ያስገረመኝ የእኛ ባህሪ ነው፡፡ ከወጣቱ በስተቀር የሌሎች ዝምታ፣ የትራፊክ ፖሊሶቹ ፈረንጁን ተከትለው መጥተው ሴትዮዋን እንድትበረግግ ማድረጋቸውና እንግዳ ተቀባይ የሚባለው ወገናችን ፈረንጅ በገዛ አገሩ ሲደነፋበት ችላ ባይነቱ አናዶኛል፡፡ በተለይ እኛ ከተሜ የምንባል ሰዎች በየማኪያቶና በየቢራ ጠረጴዛው ላይ ስንትና ስንት ጉዳዮችን እያነሳን ስንጥል እንደማንውልና እንደማናመሽ፣ በጠራራ ፀሐይ መሀል ቦሌ ላይ አንዲት ደሃ ወገናችን ከእነ ልጆቿ በፈረንጅ ስትዋከብ ዝም ብለን ተመልክተናል፡፡

  ያ ብልህና ቁጡ ወጣት ፀጥታችንን ሰብሮ ወሳኝ የሆነ ዕርምጃ ባይወስድ ኖሮ፣ እነዚያ ሕፃናትና ያቺ ደሃ እናት በዚያ ጠራራ ፀሐይ ይደርስባቸው የነበረው እንግልት ሲታሰበኝ አሁንም ድረስ ያበሳጨኛል፡፡ የእኛ ነገር ‹‹ባለቤቱ ያቀለለው አሞሌ…›› እየሆነ ነው እንጂ፣ ታሪካችንማ እንዲህ ዓይነቱን ወራሪ ፈረንጅ አባቶቻችንና እናቶቻችን ሲያርበደብዱት እንደነበር ይነግረናል፡፡ ለማይረባ ጉዳይ አሳራችንን ከምናይ ለአገራችንና ለወገናችን ጉዳይ እስቲ እንጨነቅ፡፡ በአያገባኝም ስሜት የተሞላውን መንፈሳችንን አስረነው እስከ መቼ እንዘልቃለን? ሕፃኑ ልጅ ፈረንጅ መስሎት የውጭ ዜጋ ሽንጡን ገትሮ ሲከራከር ብዙዎች ዝም ከማለት አልፈው፣ የጥቃት ስሜት እንኳ አይሰማቸውም ነበር፡፡ ‹‹አልቢኖ›› የሚባለው የቆዳ፣ የፀጉርና የዓይን ንጣት በበርካታ አገሮች እንደሚታወቅ እንኳ ለማስረዳት ከዚያ ወጣት በስተቀር የደፈረ አልነበረም፡፡ አንዳንዴ እኮ ነገራችን ሁሉ ግራ ያጋባል፡፡

  ግራ የተጋባ ፈረንጅ ‹‹አልቢኖ›› የሚባለው በዓለም የሚታወቅ የተፈጥሮ ክስተት እንዳለ ትንሽ እውቀት ሳይኖረው ግራ ሲያጋባንና ድሆቹን ሲረብሽ ማየት ቢገርምም፣ የእኛ አላዋቂነት ደግሞ ያናድዳል፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች ከባለሙያዎች በላይ ለመራቀቅ የምንፈልገው ከተሜዎች በማይም ፈረንጅ ስንዋከብ አያሳዝንም? ዋናው ዕውቀት ባይኖር እንኳ ጠቅላላ ዕወቀት እኮ አስፈላጊ ነው፡፡ ተግባባን? ያ ጀግና ወጣት፣ ‹‹ፈረንጁ ጋዜጠኛ ነኝ ሲል ሰማችሁት አይደል፣ እነሱ እኮ እኛን ጨምሮ ዓለምን ግራ የሚያጋቡት በውሸት ዜናቸውና በአደናጋሪ ምላሳቸው ነው፡፡ ዘረኝነቱ እንዳለ ሆኖ ውሸታቸው ሲታወቅባቸው እንዴት ሹልክ እንደሚሉ ማወቅ አለብን…›› ብሎን ከአላፊ አግዳሚው ጠቀም ያለ ገንዘብ አሰባስቦ እናትና ልጅን አፅናንቶ የሸኘበት ሁኔታ ልብ የሚነካ ነበር፡፡

  (ናኦድ ዓለማየሁ፣ ከኦሊምፒያ)       

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...