Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉጦርነትና ኢኮኖሚ - የማገገሚያ ፕሮግራም ዝግጅትና ትግበራ (ክፍል አንድ)

ጦርነትና ኢኮኖሚ – የማገገሚያ ፕሮግራም ዝግጅትና ትግበራ (ክፍል አንድ)

ቀን:

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር)

 1. መንደርደሪያ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አገሪቱ ባሳለፈቻቸው በሺሕ በሚቆጠሩ ዓመታት ውስጥ ለአንድ አሠርት ዓመት ያህል ለሚሆን ተከታታይ ጊዜ ከጦርነትና ከግጭት ያረፈበት ወቅት እንደሌለ በርካታ ጸሐፍት ጽፈውታል፡፡ በእኛ ዘመን ማለትም ከአፄ ኃይለ ሥላሴ አገዛዝ ጀምሮ ደግሞ ይኸው ቀጥሎ ያየነው ሲሆን፣ በዓይነትና በይዘት ግን ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ የታየው የውስጥ ግጭትና ጦርነት ለየት ያለ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ኢትዮጵያ ልትፈራርስ ነው የሚለው አባባል ወይም ዕሳቤ የዜናዎች ዘገባና የተለያዩ አካላት የክርክር ማጠንጠኛ ሆኖ የከረመበት የእርስ በርስ ጦርነት ነበር፡፡ በእርግጥ የውጭ ኃይሎች በእጅ አዙር የከፈቱብንና የተዋጋንበት ጦርነት ነው የሚልም ዕሳቤ አለ፡፡

በእኔ ዕውቀትና የመረዳት ደረጃ ኢትዮጵያ አትፈርስም ብዬ መግለጽና መሞገት የጀመርኩት በ2013 ዓ.ም. የጥቅምቱ ግጭት ማግሥት ቢሆንም፣ ነገሮች ከፍተው በ2013 ዓ.ም. ክረምት መግቢያ ጀምሮ በ2014 ዓ.ም. ማግሥት እስከ ነበረው ጊዜ ድረስ ግን የኢትዮጵያ አትፈርስም አቋሜ መሠረተ ቢስ እንደሆነ ሊያመላክቱኝ የሞከሩ በርካቶች ነበሩ፡፡ ዛሬም የኢትዮጵያ አትፈርስም አባባል አይዋጥልንም የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ዕድሜ ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት፣ በተለይ ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ የሚታገሉ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገሮች ያሉ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውን፣ ከእኛ ጋር የቆሙ የአፍሪካና የቀሪው ዓለም ሕዝቦችና መንግሥታት ሁሉ ተረባርበው ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ ሆና እንድትገኝ አድርገዋታል፡፡ ምንም እንኳ ዛሬ አገሪቱ በከባድና በተወሳሰቡ ብሔር ተኮር፣ የፖለቲካ ተቧዳኝነትና በውጭ ኃይሎች ደጋፊነት የሚመሩ ግጭቶች ቢኖሩም፣ በዚህና በተጓዳኝ ዓለም አቀፍ ክስተቶች ምክንያት ኢኮኖሚዋ በከባድ ችግር ውስጥ እንዲዘፈቅ ቢዳረግም፣ ኢትዮጵያ እንደ አገር ግን ዛሬም አለች፣ በእኔ እምነት ሳትፈርስም ትኖራለች፡፡ ስላለመፍረስ ዕሳቤ በዚሁ ጽሑፍ በክፍል ሁለት ተመልሼ እመጣበታለሁ፡፡ በክፍል ሁለት ‹‹የኢትዮጵያ አትፈርስም›› ዕሳቤን ከሰላም፣ ከደኅንነትና ከሀብት አጠቃቀም መርሆዎችና አስተምህሮዎች ጋር አጠር ያለ የዳሰሳ ማብራሪያ አቅርቤበታለሁ፡፡

የዚህ ጽሑፌ ዓላማ ዛሬ በተለያዩ አካባቢዎች በጦር መሣሪያ የታገዙ ግጭቶች ቢኖሩም፣ ጦርነት የሚባለው ክስተት ግን ረግቦ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወደ ልማቱ መስመር እንዲመለስ፣ ከመነሻው በጦርነቱ የተፈናቀሉትን ወደ ቀዬአቸው መልሶ፣ ከዚያም ረሃብ እንዳይከሰት በማድረግ፣ በመቀጠልም ከአጭር እስከ ረጅም ጊዜ ባለ የማገገሚያ ፕሮግራምና ዕቅድ ተመርቶ ወደ የሚፈለገው ልማታዊ አቅጣጫ  ይመለስ ዘንድ ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አንፃር ያስተዋልኳቸውን ክፍተቶች የመጠቆም፣ የማብራራትና በዚህ ረገድ ምን መሠራት እንዳለበት ምክረ ሐሳብ ማቅረብ ነው፡፡

በእኔ ምልከታ ዛሬ ኢትዮጵያ ከጦርነት ኢኮኖሚ ውስጥ ወጥታና አገግማ፣ ወደ ዘላቂ ልማትና ብልፅግና ጎዳናዋ ለመመለስ እንቅስቃሴ እያደረገች ነው፡፡ የእንቅስቃሴው ዋነኛ ተዋንያን መሆን ያለባቸው መንግሥትና ሕዝብ ናቸው፡፡ ሕዝብ የሚለው ቃል፣ ዜጎችና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች፣ በገንዘብም ሆነ በዕውቀትና በጉልበት በአገር ውስጥ ሆነው በአዎንታዊ ይዘት ለኢትዮጵያ ልማትና ብልፅግና የሚታትሩ ግለሰቦችን ያጠቃልላል፡፡

ምንም እንኳ ከጦርነት ማግሥት ለኢኮኖሚና ለማኅበራዊ የማገገሚያ ሥራዎች ቀዳሚ ተዋንያን ሕዝብና መንግሥት ቢሆኑም፣ ቀዳሚ ለመሆን የፈለጉ የውጭ ተዋንያንም አሉ፡፡ ለኢትዮጵያ ከጦርነት ማግሥት ኢኮኖሚ እንዴት ማገገም እንዳለበት አስጠንቼ አቀርብልሻለሁ ካሉ የውጭ ኃይሎች መሀል ፈረንሣይ ቀዳሚ ናት፡፡ ሌሎች አገሮችና ዓለም አቀፍ የብዝኃና የሁለትዮሽ የልማት አጋር ድርጅቶችም አሉ፡፡ ሆኖም አቀራረባቸው በጦርነቱ ወቅት እንዳደረጉት ግራ የሚያጋባ ይመስላል፡፡ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን መንግሥት የሦስት መቶ ሚሊዮን ዶላር የማገገሚያ ዕቅድ ማስፈጸሚያ የብድር ጥያቄ ተቀብዬዋለሁ ሲል፣ እነ ፈረንሣይና ጀርመን የሚያሾሩት የአውሮፓ ኅብረት ተቃውሞውን ሲያሰማ ጊዜ እንዳልፈጀበት ሪፖርተር ጋዜጣና ሌሎች የሚዲያ አካላት አሳውቀውናል፡፡ አሜሪካኖች በአንድ በኩል ለማገገሚያ በተለይ ለአፋጣኙ ሰብዓዊ ዕርዳታ ደራሽ ነን በማለት በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች ዕርዳታ ሰጠን እያሉ፣ በሌላ በኩል በሕግ አውጪ አካላቶቻቸው በኩል ኢትዮጵያ ከጦርነቱ እንዳታገግም ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚዋ እንዲሽመደመድ ኤችአር 6600 እና ኤስ 3199 የተባለ ሕግ አርቅቀው እያስፈራሩን ይገኛሉ፡፡

ከጦርነቱ በኋላ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ሥራዎችና ተቋማት የመልሶ ማቋቋሚያና ማገገሚያ እንቅስቃሴዎች ከፌዴራል መንግሥት በቂ ትኩረት አላገኙልንም የሚሉ፣ በጦርነቱ በግንባር ቀደም ተጠቂ ከሆኑ ክልሎች መሀል አንዳንዶቹ፣ ለምሳሌ የአማራ ክልል የራሱን የኢኮኖሚ ማገገሚያ ፕሮግራም ዝግጅት የጥናት ቡድን እንደ አቋቋመ፣ ሆኖም ለሚያስፈልገው የሰው ኃይል የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ዕገዛን እንደሚጠብቅ ገልጾልናል፡፡ አለፍ ሲል ደግሞ አንዳንድ አገር ወዳድ ግለሰቦችና ድርጅቶች ለመልሶ ግንባታው ሀብት አሰባስበን ልንቀሳቀስ ነው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ለምሳሌ ‹‹ኢትዮጵያን እንከላከል አየርላንድ›› አባላትና በሌሎችም በውጭ አገሮች በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተደራጁ አካለት እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፡፡

ከላይ የተገለጹት ኩነቶችና እንቀስቃሴዎች ሁሉ ግን የዚህን ጽሑፍ ጸሐፊ አሳስበውታል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ በተለያዩ ሚዲያዎች ቀርቤ ስለጦርነት ኢኮኖሚና ስለማገገሚያ ፕሮግራም ዝግጅትና አፈጻጸም ጉዳዮች ማብራሪያ፣ ምክረ ሐሳቦችና ማሳሰቢያ  ሰጥቻለሁ፡፡ እኔም ሆንኩ ሌሎች ኢትዮጵውያን ሙያተኞች የምንሰጣቸው ሙያዊ ማብራሪያዎች፣ ምክረ ሐሳቦችና ማሳሰቢያዎች በመንግሥት አካላት በኩል ወይ ሲተቹ ወይ ቅቡልነት ሲያገኙ አይስተዋልም፡፡ ኮምቦልቻ ከሕወሓት እጅ ተላቀቀች ሲባል በማግሥቱ በኢትዮጵያ ቴሊቪዥን የምሳ ሰዓት ዜና ፕሮግራም ላይ አጭር ማብራሪያ ስለጉዳዩ እንድሰጥ ተጠይቄ ኮምቦልቻም ሆነች ሌሎች በጦርነቱ የወደሙ ከተሞች፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ተቋማት፣ በተለይ የግብርና፣ የመፈብረኪያ ኢንዱስትሪና የአገልግሎት መስጫ መሠረተ ልማቶች የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ሥራ በአንድ ማዕከል በፕሮግራምና በዕቅድ መመራት እንዳለበት ምክረ ሐሳብ ሰጥቼ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ በኢቲቪም ሆነ በተለያዩ የኤሌክትሮኒክስና የኅትመት ሚዲያዎች ቀርቤ በጉዳዩ ላይ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቻለሁ፡፡ ጠቅለል ሲደረግ በተደጋጋሚ ያልኩት፣

 • በፌዴራል ደራጃ ክልሎችን ያካተተ አንድ የማገገሚያ ፕሮግራምና ዕቅድ ዝግጅትና ትግበራ አስተባባሪ አካል እንዲኖር፣
 • በክልሎች ደረጃ የሚቋቋምና ከፌዴራሉ አስተባባሪ አካል ጋር ተቀናጅቶ የሚሠራ የቴክኒክ ኮሚቴ በየክልሉ እንዲኖር፣
 • የዕቅድ ዝግጅቱም ሆነ ትግበራው መመራት ያለበት በኢትዮጵያውያን ሙያተኞችና ኤክስፐርቶች መሆን እንደሚገባው፣ ለዚህም በአገር ውስጥ ሆነ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በግልም ሆነ በሙያ ማኅበራቶቻቸው በኩል ተደራጅተው እንዲሠሩ ማድረግ፣
 • በቅድሚያ በሥፍራ፣ በዘርፍና/ሴክተር እንዲሁም በጊዜ፣ ማለትም የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ፣ በአፋጣኝ ደግሞ የሰብዓዊ ዕርዳታና የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ሥራዎችን መለየት፣
 • ልየታው በፕሮግራምና ዕቅድ ከተሰናዳ በኋላ ለዚሁ ማስፈጸሚያ የሀብት/ፋይናንስ ማሰባሰብ ሥራ መሥራት፣
 • የአስቸኳይ ጊዜ ሰብዓዊ ዕርዳታዎች፣ በተለይም ደግሞ ረሃብ እንዳይከሰት የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች በአፋጣኝ፣ በጊዜ ባልተገደበ፣ ባለ አቅም፣ የገንዘብና ሀብት ግኝት ላይ ተመርኩዞ እንዲተገበሩ፣ ለዚህም ቢሆን የፌዴራልና የክልል ተቋማት፣ ሕዝባዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተናበውና ተቀናጅተው እንዲሠሩ መደረግ እንዳለበት አሳውቄያለሁ፡፡

እኔም ሆንኩ ሌሎች ከላይ በተዘረዘሩት አቅጣጫዎች የመልሶ ማቋቋሙና ግንባታ ሥራው እንዲመራና እንዲሠራ የምናደርገው ጥረት ለፖለቲከኞች የተዋጣላቸው አይመስልም፡፡ በቅርቡ የሰማነው ከዓለም ባንክ የሦስት ሚሊዮን ዶላር ብድር ጥየቃ ጥናታዊ መሠረቱ ምን እንደሆነ ግልጽ ባይደረግም፣ በእኔ ግምት በአማራና በአፋር ክልሎች ለወደሙ ወደ ሦስት ሺሕ (3,000) ለሚጠጉ ትምህርት ቤቶች አስቸኳይ ጥገናና ትምህርት ማስጀመሪያ እንኳ የሚበቃ አይደለም፡፡ የሚገርመው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከራሱና ከባለሀብቶች አሰባስቦ ለፋሲካና ለረመዳን ከሁለት መቶ አርባ ሺሕ በላይ ነዋሪዎችን ለማዕድ ማጋራት አወጣሁት ያለው ወጪ እንኳ በገንዘብ ሲተመን ከዓለም ባንክ በጦርነት ለወደሙት ተቋማት፣ ከተሞች፣ መሠረተ ልማቶችና ተጓዳኝ ሥራዎች ተጠየቀ ከተባለው ብድር የማያንስ ነው፡፡ የብድሩ መጠየቂያ መሠረቱ አጠያያቂ መሆን ብቻ ሳይሆን፣ ከቁሳዊ መልሶ ግንባታው በተጨማሪ ከጦርነቱ ማግሥት በሥነ ልቦናዊና አስተሳሰባዊ ዕሴቶች ላይ የደረሰው ጥፋት እንዴት መዳሰስና መልሶ መገንባት እንዳለበት የተደረገ ጥናትና የተጠየቀ ፋይናንስ ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ፡፡

በአጠቃላይ በርካታ ከጦርነት ማግሥት የሚሠሩ ሥራዎች ለይስሙላና ለሚዲያ ዲስኩር የተመቻቹ ሲመስል፣ አንዳንዶች ለዚህ ምክንያቱ መንግሥት ገና በጦርነት ውስጥ ስላለና ጦርነትም እንበለው ግጭት፣ በአገሪቱ ዛሬም ተንሰራፍቶ ስለሚገኝ ነው ብለው ማስተዛዘኛ ሊያቀርቡ ሲዳዳቸው አስተውያለሁ፡፡ ይህ ከሆነ፣

 1. ለምን በችኮላ በመልሶ ግንባታ ስም የእነ ፈረንሣይ ዕገዛ፣ የእነ ዓለም ባንክ ብድር፣ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት ዕገዛ ተፈለገ?
 2. ለምንስ በቅድሚያ በኢትዮጵያውያን ሙያተኞች መሠራት የሚቻለው የፕሮግራምና ዕቅድ ዝግጅት ሥራ ሊሠራ አልተፈለገም?
 3. ለምንስ በጠዋቱ ውጭ ተመልካች፣ ለዶላር ሰጋጅ መሆን ተፈለገ?
 4. ለምንስ ጦርነቱን እንደ ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅሞ በጦርነቱ በተጎዱ አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን በመላ አገሪቱ ዘላቂ የሆነ፣ ሁለንተናዊ የቁሳዊና ሰብዓዊ፣ እንዲሁም ሥነ ልቦናዊ የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ሥራዎችን ለመሥራት ሕጋዊ ዕሳቤና የፖሊሲ፣ ስትራቴጂ፣ ፕሮግራምና ኢንስቲትዩሽኖች (ፖስፕኢ) ቀረፃና ትግበራ አልተፈለገም?
 5. ለምንስ መሠራት ያለባቸውን ሥራዎች አስቀድመን ለይተን፣ ከሀብት ምንጭና ፍሰት አንፃር በሚገባ ተናቦ ለማቀድና ለመፈጸም ዝግጁነት ጎደለን?

የሚሉ ጥያቄዎች እንደ አንድ ዜጋ ህሊናዬን ዕረፍት ስለነሱት በጉዳዩ ላይ ከዕሳቤ ጀምሬ ምን መደረግ እንዳለበት ለማስገንዘብ ይህን ጽሑፍ ጻፍኩ፡፡ ጽሑፉ በሚከተሉት ዓበይት ጉዳዮች ዙሪያ አጠንጥኖ ተዘጋጅቷል፡፡

 • በኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት ኖረም አልኖረ የኢኮኖሚው ሥርዓት መገንባት ያለበት በምን ዓይነት ዕሳቤዎችና መርህዎች ላይ መሆን እንዳለበት፣
 • ከጦርነት ማግሥት ማገገም ያለበት ኢኮኖሚ እንዲያገግም መሠራት ያለበት ዕቅድ ዝግጅትና አተገባበር፣ ከምሰሶዎችና መርሆዎች፣ ከተዋንያን ሚና፣ ከሥፍራና ከአመራር አንፃር ተብራርቶ ቀርቧል፡፡

ጽሑፉ በሰላሙም ጊዜ ሆነ ከጦርነት በኋላ በሚደረጉ የዕቅድ ዝግቶችና ትግበራቸው ዋነኛው መርህ ‹‹ባለን አቅም አቅደን ውጤታማ ሥራ እየሠራን፣ የሌለንን አቅም አቅደን እንገንባ›› የሚል መሆን እንደ አለበት ያስገነዝባል፡፡ 

ዕሳቤዎች፣ አስተምህሮዎችና፣ መርሆዎች

በዘመናት መለኪያ ወደኋላ ተመልሰን ለበርካታ ዓመታት ከዚያም የወቅቱን የአገራችን ኢኮኖሚ ጉዳይ ስናጠና፣ በተለይ ደግሞ በጦርነቱ ማግሥት ኢኮኖሚው አገግሞ ወደ የሚፈለግበት የዕድገትና ብልፅግና ጎዳና እንዲገባ ምን መደረግ አለበት ብለን ለምናዘጋጃቸው የአቅጣጫ ሰጪ ጭብጦች፣ የመፍትሔ ሐሳብና ድርጊቶች ሦስት  ዕሳቤዎችና ከእነዚህም ጋር ተያያዥ የሆኑ የኢኮኖሚክስ አስተምህሮዎችና መርሆዎች አሉ፡፡ እነዚህም የሚያጠነጥኑት፡-

 1. ኢትዮጵያ አትፈርስም፣
 2. ለኢትዮጵያ ዛሬም ቀዳሚ ሥራ መሆን ያለበት ሰላም፣ ደኅንነትና ሉዓላዊነትን ማስፈንና ማስጠበቅ ነው፡፡
 3. ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትና ብልፅግና ጉልበት፣ ሀብትና ዕውቀት ተቀናጅተው፣ ብቃት ባለው አመራር በቀልጣፋና ውጤታማ ሥራ ላይ መዋል አለባቸው የሚሉት ናቸው፡፡

በማትፈርስ፣ አንድነቷና ሰላሟ በተረጋገጠላት ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለንተናዊ ዕድገት፣ ልማትና ብልፅግና ዕውን ሊሆን የሚችለው ሕዝቡና መንግሥት ያላቸውን ጉልበት፣ ሀብትና ዕውቀት አቀናጅተው ለቀልጣፋና ለውጤታማ ሥራ ሲጠቀሙበት ነው፡፡ ይህ እንዲሆን ግን ትኩረት ተሰጥቶት በቅድሚያ ሊሠራበት የሚገባው የሰላም፣ የደኅንነትና ሉዓላዊነትን የማስፈንና የማስከበር ሥራ ነው፡፡ እነዚህ ዕሳቤዎች በጦርነት ውስጥ ባልተዘፈቀ አገርና ኢኮኖሚ ውስጥም አስፈላጊ ናቸው፡፡ እነዚህ ሦስት ዕሳቤዎችና መርሆዎች አጠር ባለ አቀራረብ እንደሚከተለው ተብራርተዋል፡፡

 ኢትዮጵያ አትፈርስም

ብዙዎቻችን (እኔን ጨምሮ) ኢትዮጵያ አትገነጣጠልም፣ አትፈርስም በሚል በተለያዩ የውይይት መድሮኮችና ሚዲያዎች ላይ እንናገራለን፡፡ ጥቂቶች ደግሞ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች፣ እየፈረሰችም ነው ብለው ይሞግታሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ክርክሩ ኢትዮጵያ አትጠብም ወይስ ትጠባለች በሚለው ላይ መሆን አለበት ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ የእነዚህን ፅንፍ የያዙ ሐሳቦችንና ሙግቶችን አነፃፅሮ ማቅረብና መተንተን የዚህ ጽሑፍ ዓላማና ተልዕኮ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ሲጤን ግን ከ2013 ዓ.ም. ጥቅምት ወር ጀምሮ በተደረገው ጦርነትና ዛሬም ድረስ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ቀጥለው ያሉ ግጭቶች ምክንያት በርካታ ዜጎችና እንስሳት ሞተዋል፣ ንብረት፣ ሀብትና ተቋማት ፈርሰዋል፣ ወድመዋል፡፡ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ፣ የባህላዊ የሃይማኖታዊና አስተዳደራዊ ተቋማት ፈርሰዋል፣ ወድመዋል፣ ከጥቅም ውጭ ሆነዋል፡፡ በጥቅሉ የብዝኃ ዓውድና ዘርፍ ውድመት በተለያዩ አካባቢዎች ደርሷል፡፡ በርካታ ከተሞችና ገጠራማ አካባቢዎች በተለይ በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ ፈርሰዋል፣ ጠፍተዋል፡፡

ከተደረጉት ግድያዎችና ውድመቶች ውስጥ አንዳንዶች በጣም አሰቃቂ ነበሩ፡፡ ሰው ቤተሰቡ፣ ወገኑ፣ ዘመድ አዝመዱ እያየው ተረሽኗል፣ ታርዷል፣ በግፍ በእናት በአባት፣ በሚስት በባል፣ በእህት በወንድሙ ፊት ተገድሏል፡፡ ሴቶች ከሕፃናት እሰከ አዛውንት፣ ከ80 እስከ 90 ዓመት መነኩሲት ሳይቀሩ ተደፍረዋል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች እርሻዎች ወድመዋል፣ የደረሰ እህል ተዘርፏል፣ ተቃጥሏል፡፡ ከብቶች፣ በግ፣ ፍየል፣ ዶሮ፣ የአፋር ሕዝብ የህልውና ምልክት የሆነው ግመል ጭምር ተረሽነዋል፣ ተገድለዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ኢትዮጵያ አልፈረሰችም፡፡ እነዚህ አሰቃቂና ዘግናኝ ድርጊቶች ሁሉ ተደምረው ኢትዮጵያን አላፈረሷትም፡፡ ዛሬ አገሪቱ ካለችበት ሁኔታ አንፃርም ትፈርሳለች ወደ የሚል ድምዳሜ ለመድረስ አያስችሉም፡፡  

አንዳንዶች የጥፋቱንና ውድመቱን ዓይነትና መጠን በመግለጽ ኢትዮጵያ አትፈርስም የሚለውን ዕሳቤና አስተምህሮ ለመሞገት፣ ብሎም አለመፍረስ ማለት ከዚህ በላይ ምንድነው በማለት የመንግሥትን ስትራቴጂካዊ የተጣመረ ጦርነቱን የመመከት ብሎም የማጥቃትና ሊያፈርሷት የተነሱትን ኃይሎች ያዝን ካሏቸውና ውድመት ካስከተሉባቸው ከተሞችና አካባቢዎች ወደ ኋላ እንዲመለሱ ያደረገበትን ሒደት ለማጣጣል ሲሞክሩ አስተውያለሁ፣ አድምጫለሁ፡፡

በእኔ እምነት ግን ከላይ የተዘረዘሩት ውድመቶችና ጥፋቶች ተከሰቱ እንጂ ኢትዮጵያ አልፈረሰችም፣ አትፈርስምም፡፡ የፈረሱት፣ የወደሙት ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ እንዲሁም አስተዳደራዊ ተቋማትና መሠረተ ልማቶች ሰላምና ደኅንነቱ እየተመለሰ ሲሄድ መልሰው ይገነባሉ፣ ይቋቋማሉም፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ በኢኮኖሚ ውስጥ ያሉ ተዋንያን ተገቢ ሥራን በተገቢ ሥፍራና ጊዜ በቅልጥፍናና በውጤታማነት እየሠሩ፣ ለሰላምና ደኅንነት ጠንካራ መሠረት ሲጥሉ ነው፡፡

ሰላምደኅንነት

ሰላምና ደኅንነት በሁሉም አካባቢዎች በአንፃራዊነት በመጠንም ሆነ በስፋት ቀላል በሚባሉ ግጭቶች ደረጃ ብቻ ውስን አስኪሆን ድረስ ጉልበትን፣ ሀብትንና ዕውቀትን አጣምሮ ውጤታማ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ልማት ሥራን ጀመሮ ማሳካት አይቻልም፡፡

በሕወሓት/ትሕነግ በ2013 ዓ.ም. ጥቅምት ወር ውስጥ በሰሜን የመከላከያ ዕዝ ላይ በተደረገው አሰቃቂ ግድያ ጀምሮ፣ እሰከ 2014 ዓ.ም. የመጀመርያዎቹ ወራት የዘለቀው ጦርነት መቋጫ እያገኘ ነው ወደ የሚባል ደረጃ ደርሷል፡፡ ይሁን እንጂ በአንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶች ቀጥለዋል፡፡ ጦርነቱ አለቀ ማለትም ሰላምና ደኅንነት በመላው የአገሪቱ ክፍል ተገኘ ወይም አለ ማለት አይደለም፡፡ በአንዲት ወረዳ ብቻ እንኳ የሚኖር ግጭት ወይም ጦርነት በአጠቃላይ የአገሪቱን ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ልማት ሥራዎችንና መስተጋብሮችን ያደናቅፋል፡፡ የመንግሥትን በጀትና የሕዝብን የተከማቸ ሀብት ከልማታዊ ሥራ ወደ ጥፋተኞች መታደግና ጦርነት ያዞራል፡፡ በአጠቃላይ ዕድገትና ብልፅግናችን ዕውን እንዳይሆን ያደርጋል፡፡

ሕወሓት ቢሸነፍም ከእሱ ጋር በምዕራቡ የአገሪቱ ክፍል ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ሥጋትና ለመሠረተ ልማት አውዳሚነት የሚንቀሳቀሱት እንደ ሸኔ፣ የቤኒሻንጉል አማፅያን፣ በሶማሌም ሆነ በደቡብ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላምና ደኅንነት ኃይሎች ከእኩይ ተግባራቸው እስካልታቀቡ ድረስ፣ በተለያዩ አካባቢዎች ተስፈንጣሪ (Great Leap) የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ልማት ሥራ ለመሥራትና ውጤት ለማምጣት ቀላል አይሆንም፡፡ በሌላ በኩል የሰላምና ደኅንነት አናጊ ኃይሎች አሉ ተብሎ፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ልማት ሥራው ከመከናወን አይቆምም፡፡ ከእነሱ ጋር ከመፋለም ጎን ለጎን የልማት ሥራው መቀጠል የግድ ነው፡፡ በተጠበቀውና በሚፈለገው መጠን የዕድገትና ብልፅግና ውጤት ለማስመዝገብ ደግሞ ሥራው ከጠንካራ የሰላምና ደኅንነት ተቋም፣ አደረጃጀትና አሠራር ሥርዓት ጋር ተቆራኝቶ በሚመለከታቸው የመንግሥትና የግል ዘርፍ አካላት የሚከወን መሆን አለበት፡፡

በአጭሩ በማትፈርሰዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ብልፅግና ዕውን ይሆን ዘንድ፣  በቅድሚያ ተግተን መገንባትና አስተማማኝ ደረጃ ማድረስ ያለብን ኢኮኖሚውን፣ ከዚህም ጋር ተጎዳኝቶ የሰላምና ደኅንነት ተቋማትን ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በሚከተሉት ሁለት ዓበይት ጉዳዮች ውስጥ የቀረቡትን ምክረ ሐሳቦች በዕውቀት፣ በጥበብና በበሰለ በሰላ አመራር አቅዶ መተግበር ይሻል፡፡

 1. አገሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት፣ የሰው ኃይል፣ የፋይናንስ አቅም ከአገር ውስጥ ከሚመነጭ አገራዊ ዕውቀት፣ ጥበብና ቴክኖሎጂ ወይም ከውጭ ከሚሸመት ዕውቀትና ቴክኖሎጂ ጋር አዋህዶ በኢትዮጵያውያን የሚመራ ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚ መገንባት፣
 2. ጠንካራ ኢኮኖሚን ለመገንባት ሆነ ከተገነባው ኢኮኖሚ የሚገኝ ጥቅምን ለአገሪቱ ዜጎች ሁለንተናዊ ልማትና ብልፅግና ለማዋል ደግሞ የሚከተሉትን መገንባት ሲቻል ነው፡፡
 • በሰው ኃይሉና በቴክኖሎጂ ትጥቁ የጎለበተ የአገር መከላከያ ሠራዊት፣
 • የክልል ልዩ ኃይሎች፤
 • የሚሊሺያ አደረጃጀት፣
 • ዜጎችን በብሔራዊ ውትድርና ሥርዓት አፈጻጸም ለአገር ጥበቃ ተግባር ዝግጁ ማድረግ፣
 • የነፍስ ወከፍ የጦር መሣሪያ ባለቤትነትንና አጠቃቀምን ሥርዓት ማስያዝ፣
 • የመረጃ አሰባሰብና አጠቃቀም ሥርዓትን መዘርጋት፣
 • ተጓዳኝ የዲፕሎማሲ ሥረዎችን መሥራት፣
 • የተግባቦትና የሚዲያ (ኤሌክትሮኒክስና ኅትመት) በመንግሥት፣ ሕዝባዊና የግል አደረጃጀት፣ ሶሻል ሚዲያውን ጨምሮ ለአዎንታዊ የአገር መንግሥት ግንባታና ለኢኮኖሚና ማኅበራዊ ልማትና ብልፅግና ማደራጀትን ይጠይቃል፡፡

 ጉልበት፣ ሀብትና ዕውቀት ተናጠላዊ ይዘት፣ ጥምረትና መስተጋብር

ምንም እንኳ የጉልበት፣ የሀብትና የዕውቀት ጥምረት አስፈላጊነት ከጦርነቱ ዋዜማ ጀምሮ በተደጋጋሚ ቢነሳም፣ በፖለቲካ ሳይንስና በኢኮኖሚክስ ትምህርታዊ ጽሑፍ ጸሐፊዎች በኩል የእነዚህ ጥምረት ለኢኮኖሚና ለማኅበራዊ ዕድገትና ልማት አስፈላጊነት መገለጽ ከጀመረ ዘመናት አልፈዋል፡፡ በተለይ ጉልበት፣ መሬትና ካፒታል በእነ አዳም ስሚዝና ሪካርዶ ጊዜ በአውሮፓ ዕድገትና ልማት ጥናትና ትንታኔ ላይ በሰፊው ትኩረት የተቸራቸው ወሳኝ ግብዓቶች ነበሩ፡፡ በ2013 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ውስጥ በሰሜኑ ክፍል በተከሰተው ጦርነት ምክንያት የጉልበት፣ የሀብትና የዕውቀት ዕሳቤና አስተምህሮ በተናጠልም ሆነ በትስስር ስለሚኖራቸው ጦርነቱን የማሸነፍ ሚና በፖለቲካ አመራሩ ባሉ አንቂዎች እየጎለበተ ሲመጣ፣ ከመሠረቱ ግን ከላይ የተገለጸውን የኢኮኖሚክስ ትምህርት አገላለጽን ሳያናጋ ነው፡፡

ጉልበት እንደ ግብዓት በጦርነት ወቅት የአገር መከላከያ አቅም ግንባታ ላይ ዜጎች በውትድርና ሥራ መሠማራት እንዳለባቸውና ይህ ግብዓትም ጦርነቱን ለማሸነፍ ወሳኝ እንደሆነ ለማሳወቅ በሚያስችል አገላለጽ፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ ለመፍጠር ተችሏል፡፡ ከጦርነቱ መከሰት ማግሥት ጉልበት ያለህ በጉልበትህ ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ለኢትዮጵያውያን ጥሪ ሲያቀርብ ቀዳሚ ዕሳቤው ለውትድርና ሥራው ነበር ለማለት ቢቻልም፣ ዕሳቤው ግን ከመከላከያና ከፀጥታ ሥራው በተጨማሪ ለግብርና፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለአገልግሎት ሰጪ ዘርፍ ተቋማት የሠለጠነም ሆነ ያልሠለጠነ፣ የተማረም ሆነ ያልተማረ የሰው ኃይል ፍለጎትንና አቅርቦትንም አካቶ የያዘ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በጦርነቱ ወቅትም ሆነ በሰላሙ ጊዜ እንዳስፈላጊነቱ በዘመቻ መልክ ለተለያዩ ልማታዊ ሥራዎች በተለያዩ ኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ የሚሠማራን የሰው ኃይል የሚያካትት ዕሰቤ ነው፡፡ ለምሳሌ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በጦርነቱ መገባደጃ ሰሞን አስፈላጊ ሆነው ለተሰማሩበት የእርሻ መስክ ሥራ ሥምሪት፣ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ ለአገር ልማት አስተዋጽኦ አድርግ የሚለው ዕሳቤና አስተምህሮ ተግባራዊ መገለጫ ነው፡፡ ከጉልበት ዕሳቤ ጋር ተጣምሮ ሌላው የልማትና የብልፅግናችን ቁልፍ ግብዓት ተደርጎ በጥቅል የሚገለጸው ሀብት የሚለው ዕሳቤ ነው፡፡ ይህ ዕሳቤ መሬትን ጨምሮ ተጓዳኝ ግብዓቶችን የሚያካትት ሲሆን፣ ከዚህም በተጨማሪ ፋይናንስን/ገንዘብን የሚያካትት ነው፡፡ ከጉልበትና ሀብት ጋር ተጣምሮ በጦርነቱ ወቅት ዜጎች እንዲያንቀሳቅሱትና ጥቅም ላይ እንዲውል ጥሪ የተደረገለት ሌላው ግብዓት ዕውቀት ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ ባለው አረዳድ፣ ዕውቀት፣ 

 • በመደበኛ ሆነ መደበኛ ባልሆነ የትምህርትና ሥልጠና አደረጃጀትና መስተጋብር የሚገኝ በአዕምሮ ውስጥ የሚከማች የልማትና ብልፅግና ግብዓት ሆኖ፣ ሰው አንድን ነገር በተለያየ መንገድ፣ ወይም በአንድ መንገድ የተለያዩ ነገሮችን የመመልከት፣ የመዳሰስና የፈጠራ ችሎታውን (በተለምዷዊ አገላለጽ የቴክኖሎጂ ግኝትን) የመጠቀም አቅሙንና ችሎታውን፣ እንዲሁም ብቃቱን የሚያመላክትና የሚያካትት ዕሳቤና አስተምህሮ ነው፡፡
 • በተጨማሪም ከአዕምሮ ማከማቻ ውስጥ ወጪ ተደርጎ፣ ከመከላከያ መሣሪያዎች አስከ እርሻ ሥራ ቁሳዊ ግብዓቶች፣ ከኑክሌር ቦምብ እሰከ ኃይል ማመንጫ ግድቦችና መሣሪያዎች፣ ከማጭድ እሰከ ጠረፍ አቋራጭ መንኮራኩርና አውሮፕላን፣ ወዘተ. ውስጥ ታምቆ በቁስ ነገር የሚከሰትና አንድን የጦርነት ሆነ የሰላም ጊዜ የልማት ሥራ በተቀላጠፈና በትንሽ ግብዓት ከፍተኛ ውጤት የማግኘት ዘዴንና ችሎታን የሚገልጽ ዕሳቤና አስተምህሮንም የያዘ ቃል ነው፡፡

ዕውቀት በቴክኖሎጂ ተመንዝሮ፣ ቴክኖሎጂ ከጉልበትና ሀብት ጋር ተጣምሮ፣ እንደ ሁኔታዎችና ኩነቶች ክስተት ሕገራዊ ጥበብ ታክሎበት ጥቅም ላይ ከዋለ ተዓምራዊና ዕምርታዊ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ልማት ሥራዎችን ለመከወን፣ ብሎም የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል፣ በጥቅሉም ሕዝብንና አገርን ወደ ከፍተኛ የብልፅግና ማማ ላይ ለማድረስ የሚያስችል ወሳኝ ግብዓት ነው፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ግን የኢኮኖሚ ተዋንያን ሚናቸውን በሚገባ አውቀውና ለይተው እንዳስፈላጊነቱ በተናጠልም ሆነ በጋራ በተቀናጀ መንገድ ሲሠሩ ነው፡፡

 1. ጦርነት በኋላ በሚያገግም ኢኮኖሚ ውስጥ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዛሬ ላይ ከጦርነት ድባብ ተላቆ፣ ግጭቶች ግን በአራቱም የአገሪቱ ምድራዊ አቀማማጥ የተለያዩ አካባቢዎች ቀጥለው ወደ ጦርነት ማግሥት እንቀስቃሴ ውስጥ ገብቷል፡፡ ለዚህ እንቀስቃሴ አዎንታዊ ሒደት ካላይ የተገለጹት ዕሳቤዎችና መርህዎች ተግባራዊ መሆን አስፈላጊነት እንዳለ ሆኖ፣ ሌሎች የጦርነት ማግሥት ኢኮኖሚን የመምሪያና የማደራጃ ተሞክሮዎችንና ዘዴዎችን መረዳትንና መገንዘብንም ይሻል፡፡ ይህ ደግሞ የሚጀምረው በጦርነቱ ወቅት ከተከሰቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች መዛባት ሆኖ በመቀጠልም ከጦርነቱ ማግሥት ጀምሮ መዘጋጀትና መተግበር ስለአለባቸው የኢኮኖሚ ማገገሚያ ፕሮግራሞችና ዕቅዶች ላይ ያጠነጥናል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ቀጣይ ንዑስ ክፍሎች እነዚህ ተዳሰዋል፡፡

የሀብት ድልድልና ወቅታዊ ዳሰሳ

በታሪክ ወደኋላ ለሺሕ ዓመታት ተጉዘንም ብናጠና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከግጭትና ከጦርነት ተሸካሚነት ያረፈበት አንድም ሙሉ አሥር ዓመት የለም፡፡ በእኔ ዕድሜ፣ ስለበርካታ ግጭቶችና ጦርነቶች ብሰማና ብመለከትም፣ በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተከሰተው የአገር ውስጥ የእርስ በርስ ግጭትና ጦርነት ግን በታሪክ አንብቦቴና ግንዛቤዬ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በርካታ ችግሮችንና አፍራሽ ኩነቶችን በመሸከም በጣም የተፈተነበት ጊዜ ነው ብዬ እገምታለሁ፡፡ ይህም የተከሰተው በአብዛኛው በመንግሥት መንበረ ሥልጣን ላይ በነበረው የፖለቲካ ድርጅት ማለትም በኢሕአዴግ አመራርና ውስጣዊ ድርጅታዊ ችግርና ተቃርኖዎች ነው፡፡

የአንድ አገር ኢኮኖሚ የጦርነት ኢኮኖሚ ሲሆን፣

 1. የመንግሥት በጀት፣ የመጠባበቂያና የተከማቸ ሀብት ጦርነቱን ለመምራትና ተገቢውን የፀጥታና ደኅንነት ሥራ ለማሠራት ይውላል፡፡
 2. ለልማት ሥራዎች የተመደበ የመንግሥት በጀትም እንደተፈለገው መጠን ወደ ጦርነቱ ሥራ ይዞራል፡፡
 3. አገሪቱ በሕዝቦቿ፣ በግለሰብና ቤተሰብ ደረጃ ያላት ሀብት ከአራቱም አቅጣጫ ወደ ጦር ግንባር ይፈሳል፡፡ የሀብት ፍሰቱ በገንዘብም ሆነ በዓይነት (በቁሳቁስና እንስሳት መዋጮና ተዋፅኦ) ጭምር ይሆናል፡፡ በኢትዮጵያም ከ2013 ዓ.ም. የጦርነቱ ጅማሮ ጀምሮ ሕዝባዊ ተዋፅኦው በተለይ የኢትዮጵያን ሕልውናና አንድነት በቀዳሚነት ለማስጠበቅ፣ በአገር አትፈርስም ንቅናቄ እየተመራ ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነትና አደራ ለተጣለበት የፀጥታ ኃይል (መከላከያን ጨምሮ) እንዲውል ተደርጓል፡፡
 4. ጦርነቱን ከመዋጋት በተጨማሪ ደግሞ ከኢትዮጵውያን፣ ከአገር ውስጥ ሆነ ከውጭ አገር (ከዳያስፖራው) በገንዘብ ሆነ በዓይነት የተሰበሰበው ሀብት በጦርነቱ ለተፈናቀሉና ለተጎዱ ኢትዮጵያውያንም የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታና ለመልሶ ማቋቋሚያ እንዲውል ተደረጓል፡፡
 5. ለጦርነቱም ሆነ ለአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታና ለመልሶ ማቋቋሚያ ከገንዘብና ከዓይነት የሀብት አጠቃቀም ጋር ተቆራኝቶ የአገሪቱ የጉልበት ሀብት (Labour Resource) በተለያየ ይዘት ለጦረነቱ ሥራ ጠቀሜታ ላይ ይውላል፡፡

በገጠርና በከተማ ያለ ለውጊያ የሚያስፈልግ፣ በተለይ የወጣቱ የሰው ኃይል ክፍል ወደ ውትድርና ሲነጉድ፣ ቀሪው በገጠር የእርሻ ሥራ እንዳይስተጓጎል አጋዥ ሆኖ ተሠማርቷል፡፡ በተመሳሳይም በኢንዱስትሪና አገልግሎት ዘርፉ ውስጥ በተደረገ የጉልበት ሥራ ዘመቻ የኢኮኖሚውንና የማኅበራዊ ዓውድ እንቅስቃሴዎችን በጦርነት ኢኮኖሚ ውስጥ አገራዊ ጠቀሜታን እንዲያስገኝ ተደርጎ ተንቀሳቅሷል፡፡

ከላይ በአጭሩ ለመግለጽ እንደተሞከረው አዎንታዊ እንድምታ ያላቸው የሀብት ማሰባሰብና አጠቃቀም ላይ በጦርነቱ ወቅት የተሠሩ ሥራዎች እንዳሉ ሁሉ፣ በዚሁ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ልማት ዘርፎች የሀብት ይዘት፣ ክምችት፣ ድልድልና ተደራሽነት ላይ ጦርነቱ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል፡፡ ጦርነቱ በዜጎች ሕይወት፣ ሥነ ልቦናዊ አቋምና ሞራላዊ ልዕልና፣ እንዲሁም በእንስሳት፣ በንብረትና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና አጠቃቀም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አስከትሏል፡፡

የመንግሥትና የሕዝብ ሀብትን ከልማት ወደ ውጊያና ተጓዳኝ እንቅስቃሴዎች በማዞሩ ከተቋረጡ ወይም እክል ከገጠማቸው እንደ ጤናና ትምህርት የመሳሰሉ  አገራዊና ሕዝባዊ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ መሠረተ ልማቶት ተቋማትና አገለግሎታቸው በተጨማሪ በበርካታ የግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ንግድና ሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ በእርሻ ሥራዎች ላይ ውድመቱ በአዝመራ ወቅት የደረሱ ሰብሎችን የማቃጠልና፣ የማውደም ክስተት ጭምር ያሳየ ሲሆን፣ የእርሻ መሬትና መሣሪያዎች በተለይ ከብቶችና ሌሎች የቤት እንስሳት፣ ሞፈር ቀንበርና ተዛማጅ የግብርና ሥራ መከወኛ ቁሶች ላይም ጉዳትና ውድመት አስከትሏል፡፡ በአማራና አፋር ክልል በበርካታ ሰውና እንስሳት ላይ ሞት አስከትሏል፡፡ በርካታ ዜጎችን አካለ ስንኩልም አድርጓል፡፡ በጦርነቱ ሳቢያ በተለያዩ ክልሎችና አካባቢዎች፣ ነባርና አዳዲስ የታሪክና የተፈጥሮ ይዘት የነበራቸው የቱሪስት መዳረሻዎች፣ የከተሞች መሠረተ ልማቶችና የመፈብረኪያ ኢንዱስትሪዎች ወድመዋል፡፡ ይህ በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ ጎልቶ ተከስቷል፡፡ በትግራይ ውስጥም በተወሰነ ደረጃ ሆኗል፡፡ ውድመቱ በገንዘብ ሲተመንም በትሪሊዮን ብር የሚቆጠር ሊሆን እንደሚችል የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ ግምት ሲሆን፣ ግምቱን በርካታ የኢኮኖሚክስና የፋይናንስ ባለሙያዎች የሚጋሩት ነው፡፡ 

ከአማራና በአፋር ክልሎች ውጪ በጦርነቱ ከሕወሓት ጋር በተሠለፉ ፀር ሕዝብና አገር ኃይሎች በቤኒሻንጉልና በኦሮሚያ ክልሎችም በርካታ ሕይወትና ንብረት ወድሟል፡፡ በእነዚህም ሆነ በአማራና በአፋር ክልሎች በተለያዩ አካባቢዎች በጦርነቱ ሳቢያ በተፈጠሩ ችግሮችና አሻጥሮች፣ በተለይም የምርትና አገልግሎት አቅርቦት መስተጓጎል፣ ወይም ድበቃ፣ ሸማቹ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሸቀጦችና በአገልግሎቶች የዋጋ ግሽበት ክፉኛ ተጠቅቷል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች የዜጎች መፈናቀልና ሥራ አጥ መሆን ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ቀውስ አስከትሏል፡፡ በተለይ በአማራና በአፋር ክልሎች የተካሄደው ግልጽ ጦርነት ቀዝቀዝ ሲል፣ በምዕራብ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብና በኦሮሚያ ክልሎች በሸኔ አማካይነት ሁለንተናዊ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ችግሮች አስከትሏል፡፡ እነዚህ ክስተቶች ዜጎችን በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውና በድህነት አረንቋ ውስጥ የሚገኙትን የመኖር አቅማቸውን በእጅጉ ተፈታትኗል፡፡ ዛሬም ድረስ እየተፈታተናቸው ነው፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ከጦርነቱ ጋር ተያይዘው በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በተፈጠሩ ጊዜያዊ ሥራዎች ሳቢያ ሥራ አጥነት ረገብ ያለ ቢመስልም፣ ጦርነቱ እየቀነሰ ሲሄድ እንደ ገና ሥራ አጥነትና ተጓዳኝ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና አስተዳደራዊ ችግሮች አንሰራርተዋል፡፡

የወቅቱን ሁኔታ ለሚከታተልና ከታሪክ ጋር እያዛመደ ለሚያጠና፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ምንጊዜም ሰላም እንዳይኖር በሚፈልጉ የውጭ ኃይሎችና በእነሱ በሚታገዙ የውስጥ ባንዳዎች ምክንያት ግጭቶችና ጦርነት የሚቆሙ ባይመስልም፣ በ2013 ዓ.ም. ጥቅምት ወር ላይ ጀምሮ እስከ ኅዳር 2014 ዓ.ም. ከጁንታው ሕወሓትና ከእርሱ ጀርባ ካሉ የውጭ ኃይሎች ጋር የሚደረገው የፊት ለፊት ጦርነት ከታኅሳስ ወር ጀምሮ ረገብ እያለ መጥቷል ለማለት ያስደፍራል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ከጦርነት ኢኮኖሚ ዕሳቤ ውስጥ ወጥተን ስለኢከኖሚው ማገገም፣ ስለማኅበራዊ ተቋማትና አገለግሎቶች መልሶ ማቋቋምና ሥራ ማስጀመር፣ የሃይማኖታዊ ተቋማትንና የባህላዊና ሥነ ልቦናዊ ማግኛ ሥፍራዎችን መልሶ መገንባትና ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ በአጠቃላይ በእነዚህ ዙሪያ የተፈጸመውን ውድመት፣ ስፋትና ጥልቀት አጥንቶ ወደ መልሶ ማቋቋምና ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ማገገመ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ፣ ፕሮግራም ዝርጋታ፣ ይህንንም  በጊዜ ከፍሎ፣ ማለትም የአስቸኳይ፣ የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ዕቅድ አዘጋጅቶና ለአፈጻጸም ቅደም ተከተል አውጥቶ ወደ ትግበራ መግባት ግድ እንደሚል ያስገነዝባል፡፡ ግንዛቤው ከተፈጠረ በኋላ ደግሞ ኢኮኖሚው ያገግም ዘንድ ምን፣ የት፣ መቼና እንዴት፣ በማን ሀብትና መሪነት ይሠራ የሚሉት ጥያቄዎች ተነስተው ተገቢው ምላሽ በፖሊሲ፣ በስትራቴጂ፣ በፕሮግራምና በኢንስቲትዩሽን (ፖስፕኢ) ክለሳና ማሻሻያ ታግዞ መስጠትና መሠራት ያለባቸው ሥራዎች ሁሉ፣ በሁሉም ዓውድ በቅደም ተከተል መሠራት አለባቸው፡፡ የሚከተለው ክፍል በዚህ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ይዟል፡፡ (ሳምንት ይቀጥላል)

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ‹‹ኢኮኖሚው – ሦስቱ ፖለቲከኞችና ፖሊሲ፣ እንዲሁም ኮርፖራቶክራሲ›› የተሰኙ መጻሕፍትን ለአንባቢያን ያቀረቡ አንጋፋ የኢኮኖሚ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...