Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትእናት አገርና ዴሞክራሲያችን ዛሬም ‹‹መጀመርያ የመቀመጫዬን›› ይላሉ

እናት አገርና ዴሞክራሲያችን ዛሬም ‹‹መጀመርያ የመቀመጫዬን›› ይላሉ

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ትልቁና ዋናው የአገር አጀንዳ፣ ጨዋታና አውራው መሠረታዊው ፍልሚያ ወይም ቅራኔ በሚካሄድበት ግብግብ ውስጥ ብዙ የማይናቁ፣ ነገሮችና ጥፋቶች ሲካሄዱ ይታየናል፡፡ ያናድዱናል፡፡ ያበሳጩናል፡፡ ጤና ይነሱናል፡፡ ከዋናው ጉዳይ ግን ያዘናጉናል፡፡ ትኩረታችንን ከዋናው ጉዳይ ይነቅሉታል፡፡ ትክታችንን ያናጉታል፡፡ ዋናውን አጀንዳና ትግል ባለቤት የለሽ ያደርጉታል፡፡ አመጣጣቸው ድንገትና በአጋጣሚ እንኳን ቢሆን፣ ሆን ተብለው ከዋናው ግብግብ የሚያዘናጉ የትግል መሣሪያ ይሆናሉ፡፡ ለዚህ ነው ሕማማት ውስጥና ትንሳዔ መዳረሻ ላይ፣ እንዲሁም ረመዳን የመጨረሻዎቹ አሥር ቀናት ሒደት ውስጥ ውኃና መብራት ዝም ብለው ሳያስታውቁ አድራሻቸውን ሲያጠፉ፣ መነጫነጫችንን ልክ የለሽ የሚደርጉትና ጨዋነት የሚያሳጡት፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ዋናውን ትግል የሚጎዱት፡፡ ክፋቱ ደግሞ ይህን የሚያግዝ ብዙ የይፋው የአገርና የለውጡ ጎራ እንከን፣ ፋውል፣ ስህተት፣ ጥፋት፣ መጥፎ ዓመል፣ ገመናና ነውር ሃይ ላይትና ሪፕሌይ እየተደረገ በገደል ማሚቱ ድምፅ እያስተጋባና እየተመላለሰ ይመጣል፡፡ የማሰብና የማመዛዘንን ሚዛናችንን ያናጋል፡፡

በዚህ መካከል ነው እንግዲህ በዚህ ወሳኝ ወቅት እንጭፍጫፊዎቹ ዋናው ጉዳይ ሆነው የሚመጡትና መንገድ የምንለቀው፡፡ ዛፉን ከእነ ቅርንጫፉ ትተን ዓይናችንን ከዚያ ነቅለን ውዳቂው ጭራሮው ላይ እንረባረባለን፡፡ አዎ ጋዛ በሚባል ከ70 ዓመት በላይ ችግር ባለበት የአገር ክፍል ውስጥ ምናልባትም ኪቭና ማርዮፖል ላይ መብራት ሳይጠፋ አዲስ አበባ (ለዚያውም አዲስ አበባ) ትንሳዔንና የረመዳንን የጨመረሻ የፆም ቀናት መሸከም የሚችል የኤሌክትሪክ መብራትና ኃይል አገልግሎት ከውኃ ጋር ሲጠፋ፣ በዚህም ላይ ቄሱም፣ መጽሐፉም ዝም ሲል፣ የአዳነች አቤቤ መስተዳድር በተቋምነትና እሳቸውም በግል ዋናውን የኮንትራት ግዴታቸውን ትተው ወይም በእሱ ፈንታ ዘይት ሲያድሉ፣ ቤት ሲሰጡ፣ ‹‹ብስጭትጭት›› እንላለን፡፡

እና ዋናው ጉዳይ የሕዝብን ሆድ እየቆረጠ፣ የመላውን የዴሞክራሲን ኃይል እያንገበገበ ያለው የለውጡን የአመራር ኃይል ዋና ሥራ፣ አጀንዳና አደራ፣ እንዲሁም ጥያቄ የሆነው ዴሞክራሲን ለማቋቋም የሚያስችል ለውጥ ውስጥ ነን ወይስ እዚያ ውስጥ ባሉ እንጭፍጫፊ ጉዳዮች፣ እርጋፎዎች ላይ ሆነ ከዚያ ውጭ ባሉ ጉዳዮች ላይ እየተትረከረክን ነው? የሚለው ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል እሑድ በዕለተ ፋሲካ ላይ የሰማነው ዜና፣ የእኛ ‹‹ምላሽ›› ሁለመናችንን፣ ሁለንተናችንን ይነግረናል፣ ይነግርብናል፡፡ ችግራችንን በሚገባ የተረዳነውና የያዝነው አለመሆኑ ነው፡፡ በዚህ ዜና መሠረት 4,200 ያህል ብዛት ያለው አቢዬ ላይ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰላም አስከባሪ ሆኖ ሲሠራ የቆየው ኃይል፣ በታወቀ ማለትም በእኛና በሱዳን መካከል በተፈጠረ የግንኙነት መሻከር ምክንያት በሌሎች አፍሪካውያን አገሮችና ባንግላዴሽ ባዋጡት ሠራዊት እንዲተካ ሲደረግ፣ መጨረሻ አፈጻጸሙ ላይ ከ4,000 ኢትዮጵያውያን መካከል 528 ወደ ኢትዮጵያ አንመለስም ብለው ጥገኝነት ሲጠይቁ ተደናግጠናል፡፡ ተደናግጠንም ‹‹ተስፋ መቁረጥ›› ውስጥ ገብተናል፡፡ ከዕይታችን፣ ከትክታችንና ከትኩረታችን ወጥተናል፡፡ ኢሕአዴግ 27 ዓመታት ሙሉ ሲገዛ የነበረው እኮ በሕወሓት ቁጥጥር ሥር በነበረ መንግሥታዊ አውታር ላይ ሆኖ ነው፡፡ ዴሞክራሲን ለማቋቋም የሚያስችል ለውጥ ውስጥ መግባት ማለት፣ ከየትኛውም ፓርቲ ወገንተኛነትና ባለቤትነት ነፃ አውታረ መንግሥት የመገንባት ዋና ሥራ ውስጥ መግባትና መጠመድ ነው፡፡ የዴሞክራሲያችን ተልዕኮ፣ የዴሞክራሲያዊ ትግላችን ዝርዝር ጉዳይ ያለው እዚህ ውስጥ ነው፡፡ እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያ መንግሥታዊ የሥልጣን መዋቅራት ከአንድ ፓርቲ ወገናዊነት ተላቀው ባለመደራጀታቸው ነው፡፡ ባለመደራጀታቸው ነው ማለት ሲበዛ የተድበሰበሰ ቋንቋ ነው፡፡ ጭራሹኑ የፓርቲ ሀብት፣ የፓርቲ መሣሪያ ሆነው ተጠፍጥፈው መሠራታቸውና መቃኘታቸውን ትክክለኛና አስፈላጊ አድርጎ ከመዋቀራቸውም በላይ፣ የሕዝብን ማኅበራዊ ህሊና አስተሳሰብ መቆጣጠርን ትግሌ ብሎ የያዘ ፖሊሲ ነው ሰፍኖና ተንሰራፍቶ የኖረው፡፡ የችግራችን አናት ይኼው ነው፡፡ ትግላችንንም የትግላችንን ጉዞና ዕርምጃ ሁሉ ኢንፎርም ማድረግ ያለበት፣ የእግር መንገድ የዓይን ብርሃን ሆኖ ማገልገል ያለበት ይህ ተልዕኮ ነው፡፡ የኢትዮጵያን አውታረ መንግሥት ገለልተኛ አድርጎ ማነፅና በዚያ ላይ ዴሞክራሲን ማቋቋም ነው፡፡

ይህንን ዋና አደራው፣ አጀንዳውና የአገር ዋና ግብ አድርጎ የተነሳ የለውጥ ኃይልና ንቅናቄ ሁሉ ትኩረቱን እዚህ ላይ ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ በዚህ መፍትሔና መድኅን ላይ እንዲያነጣጥር ያደረጉንን ሕመሞቻችንን በሙሉ ያውቃል፡፡ ከ4,000 (አራት ሺሕ) በላይ ቁጥር ካለው አካል ውስጥ 528 መክዳታቸው አይገርመውም ብቻ ሳይሆን፣ ዜና መሆኑ አዲስ ነገር አይሆንበትም፡፡ ምክንያቱም ከሞላ ጎደል የተሠራ ነው እንደዚያ ሆኖ ነውና፡፡ እንዲያውም ከ4,200 ያህል አንድ ቡድን ውስጥ ጥገኝነት የጠየቁት የ‹‹ቤተሰብ›› አባላት ቁጥር እንዴት በ528 (ማለትም በ12.5 በመቶ) ብቻ ተወሰነ ብሎ መጠየቅ፣ ብሎ መገረም የበለጠ ይገርማል፡፡ ለምን ቢሉ ሥርዓቱ እንዲያ ሆኖ የተዋቀረ ነበርና፡፡ በመብት መደለልና ማንጓለል ‹‹ሙያ››ውና ጥበቡ ነበርና፡፡ ሁሉንም (ግለሰብንም ይሁን፣ ቡድንንም) በእኩል ዓይን የማየትና የማስተናገድ ብቃትን የነሳው የገዛ ራሱ ፍጥርጥር ነው፡፡ የጥበብ መጀመርያውና ፖሊሲው አድሏዊ ነው፡፡ የእኩልነት ዕይታ የለውም፡፡ ዴሞክራሲያዊ እኩልነትና ፍትሐዊነት ጠላቶቹ ናቸው፡፡

ታዲያ ዋናው ጉዳይ ውስጥ የገባ፣ ዋናው አደራ ውስጥ ያተኮረ፣ እንጭፍጫፊ ጉዳዮች የሚያደናግጡት 528 ወታደር ‹‹ከዳ›› ቢባል ብርክ የማይዘው፣ አዲስ ነገር መጣ ብሎ መርዶ አድርጎ የማይቆጥረው አስቀድሞ ትግሉን ሲጀምር ትግሉን እጀምራለሁ ሲል ቆጥሮ የተረከበው፣ ቆጥሮ የተረከበው ችግር ውስጥ ተቀርቅሮ፣ ተጠቅሎ፣ ተድበስብሶና ተለባብሶ የተቀበለው ዕዳ ስለሆነ ነው፡፡

እንደገና ልበለው፡፡ ተደጋግሞ መባልና መጠናት ያለበት ጉዳይ ነውና መልሼ ልበለው፡፡ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ትግል ዋነኛ ችግር ገለልተኛ ሆኖ የታነፀ አውታረ መንግሥት አለመኖሩ ነው፡፡ የቡድኖች መንግሥታዊ ገዥነት ከነፃና ከትክክለኛ ምርጫ መመንጨት የሚችለው፣ ራሱ የቡድኖች ህልውናና ነፃ ምርጫ የሚኖረው፣ የድምፅ ብልጫ አግኝቶ ፍላጎትን ውሳኔ ማድረግ የሚያስችል የጨዋታ ሕግ የሚኖረው፣ መጀመርያ አገረ መንግሥቱን ነፃና ገለልተኛ አድርገን ስናንፀውና ስናዋቅረው ነው፡፡ የአንድ ቡድንን ጥቅም የማስጠበቅ ዋናና ተቀዳሚ ዓላማ የነበረው በጠባብ ማንነት መሥፈርቶች ላይ የተደራጀ ቡድን በአገር ውስጥም፣ በመላው ዓለምም የዘራውና የጠመደው ፈንጂ በታየ፣ በታወቀና በፈነዳ ቁጥር ይህንን ከመገንዘብ፣ ከቁጥር ከማስገባትና ከመመዝገብ፣ በዚያውም መሠረት በዋናው ዓላማ እዚያ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ፣ ዴሞክራሲን ለማቋቋም የሚያስችል ለውጥ ውስጥ ሆኖ እዚያ ውስጥ ተወስኖ መታገል እንጂ ልቃሞውን፣ ጭራሮውንና እርጋፎውን ሁሉ የፖለቲካ ደረጃ ሰጥቶ ማራገብ የተገኘውንና ያለውን ዴሞክራሲ የግርግር መደገሻ አድርጎ መማገጥ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በገዛ ራሱ ምክንያት መራር ፅዋ ያስጠጣል፡፡

እውነት ነው እዚህ አገር ውስጥ የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ መሥሪያ ቤት የሚገዛው ሕግ እንዳለ፣ ከሕግ በታች መሆኑን፣ በዚህ ረገድ ተደጋግሞና ትርጉሙን አጥቶ፣ ከትርጉሙና ከሚያስከትለው ውጤት፣ ጣጣና መዘዝ (ማስጠየቅ ማስቀጣት) ተጣልቶ እንደሚባለው ‹‹ሁሉም በሕግ ፊት እኩል›› መሆኑን አያውቅም፣ እኛም አናውቅም፡፡ ሕጉ እኛ የምናውቀውንና ለቢል ክፍያ፣ ለአቤቱታ፣ በተለይም ለ‹‹መብራት ጠፋብን›› አቤቱታ ስልክ የምንደውልበትን መሥሪያ ቤት ‹‹ባለ ፈቃድ›› ብሎ ነው የሚጠራው፡፡ ኤሌክትሪክ የማመንጨት፣ የማስተላለፍ፣ የማከፋፈልና የመሸጥ የሥራ ፈቃድ የተሰጠው ማለት ነው፡፡ ሕጉ ‹‹ባለሥልጣን›› ብሎ የሚጠራው የዚህን ባለ ፈቃድ ተቆጣጠሪ ነው፡፡ ይህን ልዩነት ደንበኛና ሕዝብ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ይህንን ሕግ በማያውቅ፣ ቢያውቅም ደንታ በሌለው የባለ ፈቃድ መሥሪያ ቤትና ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን አድራጊ ፈጣሪ በሆኑበት አገር ውስጥ እንኖራለን፡፡

እዚህ ጽሑፍ ላይ እውነቱን ለመናገር እኔ ራሴ ኤሌክትሪክ/መብራት መጥፋት ችግራችን ላይ ይህን ያህል አመራለሁ ብዬ አልተነሳሁም ነበር፡፡ ምክንያቱም ችግሮቻችን ሁሉ ለዋናው የአገር ችግር መገበር አለባቸው፡፡ ተቃውሟችንም፣ መፍትሔውም በዚያ ማዕቀፍ ውስጥ መታየትና መቃኘት አለበት፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ይህም ሆነ ሌላ ‹‹ጊዜያዊ›› ችግር ከዋናው ዓላችንና ግባችን ውጪ የሚያደርገን የግርግር መደገሻ መሆን የለበትም ብዬ ስለማምን ነው፡፡ እና የጀመርኩትን እንድጨርስ ይፈቀድልኝና ሕጉ ‹‹ባለ ፈቃድ›› ብሎ የሚጠራውን መሥሪያ ቤት እንዴት አድርጎ አስተዳድረዋለሁ እንደሚለው እንመልከት፡፡ አገር በሕጉ ‹‹ባለ ፈቃዱ የኤሌክትሪክ አገልግሎቶችን የሚያቋርጥባቸው ሁኔታዎች››ን ሲደነግግ፣

  1. ባለ ፈቃዱ በሚከተሉት ምክንያቶች ካልሆነ በስተቀር የኤሌክትሪክ አገልግሎቶችን ሊያቋጥር አይችልም፡፡

ሀ) የኤሌክትሪክ ዕቃዎችን ወይም መስመሮችን ለመፍተሽ፣ ለመጠገን፣ ለማደስ፣ ለማስተካከል ወይም ተያይዥነት ያላቸውን ሌሎች አስፈላጊ ሥራዎችን ለማከናወን፣

ለ) እንደ ውኃ ሙላት፣ የመሬት መናድና መንቀጥቀጥ ያሉ ወይም ከባለ ፈቃዱ አቅም በላይ የሆኑ ሌሎች በተፈጥሮ አደጋዎች ሊከሰቱ፣

ሐ) ደንበኛው ክፍያ ሳይፈጽም ሲቀር፣

መ) ደንበኛው ስምምነት ካደረገበት ግዴታዎችና ሁኔታዎች ውጪ ያልተፈቀደለትን ኤሌክትሪክ ሲጠቀም ወይም የገባለትን የኤሌክትሪክ ቆጣሪ ሲያሰናክል፣

  1. ባለ ፈቃዱ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) (ሀ) በተደነገገው መሠረት የኤሌክትሪክ አገልግሎቱን ከማቋረጡ አስቀድሞ በዚህ አዋጅ መሠረት በሚወጣው ደንብ በተገለጸው ጊዜ ውስጥ ለኅብረተሰቡ ማስታወቅ አለበት፡፡
  2. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1)፣ (ለ)፣ (ሐ) እና (መ)  የተመለከቱት ሁኔታዎች እንደተስተካከሉ ባለ ፈቃዱ የኤሌክትሪክ አገልግሎቱን ወዲያውኑ መቀጠል አለበት፡፡

ይላል፡፡ በዚህ ዋና ሕግ መሠረት የወጣው ደንብ ደግሞ የታቀደ የኤሌክትሪክ ማቋረጥን ከሰባ ሁለት ሰዓታት በፊት ለደንበኞች እንዲያስታውቅ ያስገድዳል፡፡

በምሳሌነት ከተነሳው የመብራት ጉዳይ ጋር ውኃውንም ማንሳት ይቻላል፡፡ የእነዚህ የበላይ የሆኑ የባለሥልጣኖቻቸውንም ሕግ የማክበር የቀን ተቀን የሥራ አፈጻጸምና ባህርይም ትዝብት ዝም ብሎ እንዳላዩ ማለፍ አይቻልም፡፡ ዋናው ጥያቄ፣ ዋናው ግብግብና መሠረታዊው ግብግብና ቅራኔ ውስጥ መታየት አለባቸው እንጂ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምሳሌ ያህል የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 11 አላውቀውም፣ ወይም ልብ አላልኩትም ማለት አይችሉም፡፡ እንዲያውም በቅርብ ቀን አንቀጽ 11ን የገዛ ራሳቸው መከላከያና መከራከሪያ አድርገው ሲያቀርቡ ሰምተናል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የ‹‹ግል›› ሃይማኖታዊ አቋም ግን ብዙ ጊዜ ምናልባትም ሁልጊዜ ከአንቀጽ 11 ጋር ሲያላትማቸው እናያለን፡፡ የዚህን አደጋ፣ ጣጣውንና መዘዙን ዶ/ር ዮናስ ብሩ በደንብ ገልጸውታል፡፡ በዚህ ዓመት የገና (ዋዜማ) ዕለት አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ወይም የገነነ ድምፅ ያለውና የኢትዮጵያ ሰው ያስደነገጠውንና አሁንም ድረስ አጥጋቢ ምላሽ አላገኘም የተባለውን የመንግሥትን (የተወሰኑ) እስረኞች መፍታት ለዳያስፖራው ሲያብራሩ የሰጡትን ምላሽ እንዳለ ጠቅሰው፣ ‹‹እኔ እንዴት [ጦርነቱን] እንዳሸነፍኩ አውቀዋለሁ፡፡ ፈጣሪዬ ከእኔ ጋር ባይሆን ኖሮ አይሆንም… እኛ ብቻ ታገልን የምትሉ ሰዎች እውነት ነው ታግላችኋል፡፡ ከእናንተ በላይ ግን ከእኔ ጋር የታገለውን ስለማውቀው እናንተን ብቻ አላደምጥም ለማለት ነው፤››

ብለው የተናገሩትን አስታውሰው፣ ሕገ መንግሥታዊ አደጋውንና አንድምታውን ነግረውናል፡፡ የሚያከራክር ነገር አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩና የቅርብ አማካሪዎቻቸው ከሕገ መንግሥት በታች መሆን የሚያስችለውን በኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ጊዜ መፈክርና መመርያ ሆኖ የኖረውን ሃይማኖት የግል ነው፣ አገር የጋራ ነውንን መማር፣ መልመድና እንዴት መኗኗሪያ ማድረግ እንደሚቻል ማወቅ፣ ለሕግ የመገዛትን መሠረታዊ እምነት ከየትኛውም እምነት በላይ ማድረግ አለባቸው፡፡ ከሰው መርጦ ለሹመት ዓይነት ተግባር ላይ የታየው ዓይነት ግልጽ ሕግን ያላንዳች ኮሽታ (የቦርድ አባላት ከሚሾሙለት ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ጀምሮ ዕጩ ተሿሚዎችን ራሳቸውን ጨምሮ፣ የፓርላማውን ኮሚቴ፣ መላ ፓርላማውን አካቶ የእነዚህ ሁሉ ዝምታ፣ ርጭታ፣ ፍዘት፣ ድንዛዜ) መፅደቅ ያለብንን ችግር ገና ያላወቅነውንና የተዘፈቅንበትን ችግር ስፋትና ግዝፈት የሚሳይ ነው፡፡ ይህን ሁሉ በዝርዝርና በነቂስ ማቅረብ ይቻላል፣ ይገባልም፡፡ እነዚህ የሚገለጹበት የሚሰሙበት የሚተነፍሱበት ማዕቀፍ ግን ልክና መልክ አለው፡፡ እነዚህን መግለጽና ማጋለጥ ያለብን በዋናው የኢትዮጵያ ዓብይ የለወጥ ትልምና ማዕቀፍ ውስጥ ነው፡፡ ለውጡ፣ ዴሞክራሲ የመገንባት ዋናው ግባችን፣ ለውጡን ራሱንና የለውጡን ኃይል የሚከፋፍሉ ጉዳዮችን የሚሸሽና የለውጡን ቅድሚያ መጠናከር የሚፈልጉ ጥያቄዎችን የሚያሳድር የጋራ መግባባትን መፍጠርና መልመድ አለበት፡፡ ይህ እስካልሆነ ድረስ የምንታገለው፣ ሥርዓቱ ራሱ የፈጠረውና ያከማቻቸው ችግሮች መከላከልና መመከት አይቻልም፡፡ ዱብ ዕዳዎችን ሳይከሰቱ ማምከን፣ ከተከሰቱም ደግሞ እንደ ፍጥርጥራቸው ማስተናገድ የሚቻለው እንዲህ ያለ የጋራ አደራ ውስጥ ስንገናኝ ነው፡፡ የለውጡ፣ ማለትም የዴሞክራሲን ህልውና ማረጋገጥ የሚችል የገለልተኛ አውታረ መንግሥት እነፃ ሥራ ጠላቶችና ተጠናዋቾች ልዩ ልዩና ዓይነተ ብዙ ናቸው፡፡ ሁሉንም ያዋደዳቸው ግን በምንም ዘዴና በየትኛውም የመስዋዕትነት ክፍያ ሕዝብን አከፋፍሎ፣ አከታልፎና አሳክሮ በመማገድ ጭምር የለውጡን ኃይልና አመራር የማስወገድ ቅብጥብጥነት ነው፡፡ ይህንን መሠረታዊ ችግር ካልተረዳን ከዋናው ዕይታችንና ከዋናው አደራችን እንወጣለን፡፡ ከአውዳሚነት የራቀ፣ ሕገወጥነትን የትግል ሥልት አድርጎ ከመረቀ ባህል አንወጣም፡፡ የመንግሥታዊ፣ የፀጥታና የሕግ አስፈጻሚ/አስከባሪ ኃይሉና የሙያ ብቃቱ፣ ዝግጁነትና ስላቱን ጭምር የሚፈታተኑ ብልሽቶችን እንዳያራግፍ ደንቃራ እንሆንበታለን፡፡ ባልተለመደና በሚያስደንቅ ሁኔታ አገራችን ውስጥ እያበበ የመጣውን የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች ህልውና ወደነበሩበት ድቅድቅ ጨለማና የለየለት ውሸት ውስጥ እንዶላቸዋለን፡፡ በአሸናፊነትና በድል አድራጊነት እየወጣ ያለውን ብሔራዊ የመብት ተቆርቋሪ ተቋም ስለዕድገቱና ስለአስተዋጽኦው የክብር ምሥጋና ከመስጠት ጋር ሌሎችም የመብት ተቋማት ያለባቸውን የሥምሪት ስፋት፣ የአድሏዊነት ችግርና የተደማጭነት ድክመት እንዲሻሻልና እንዲመነደግ ማድረግ የምንችለው፣ ከዋናው ጉዳያችን ከሚያዘናጉን በአንፃራዊነት እንክትካችና እንጭፍጫፊ ጉዳዮች ስንርቅ፣ እነሱን በአቅማቸውና በልካቸው ስንይዝ ነው፡፡ እነሱ ላይ ብቻ እንዋደቅ ማለት ለዚያውም ከዋናው የአገር አደራና አጀንዳ ውጪ ዋናውን መንገድ መሳት ነው፡፡ ከዋናው የጉዞ መስመር መውጣት ነው፡፡ ዋናው ሥፍራና ቦታ አለመገኘት፣ አለመገናኘት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ለምሳሌ በከፍተኛ ደረጃ የተደገሰልንን፣ ቀለስ መለስ እያለ እየታለለና እያባበለ የተጠመደልንን በአሜሪካ አማካይነት የተቀመመልንን የማዕቀብ ሴራ በዋዛ ፈዛዛ እያየነው ነው፡፡  

አገራችን እዚህ አዲስ ትግል ውስጥ የገባችው ‹‹ጉልቻ ለመለወጥ›› አይደለም፡፡ ሃምሳ ዓመት ሊሞላው የተቃረበው የየካቲት 1966 ዓ.ም. አብዮት መግቢያ ምዕራፍ ላይ ጀምሮ ‹‹ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም››ን ብሂል እናውቀዋለን፡፡ ድምፅ መስጠት የሚባል የትም አገር ሕገ መንግሥት ውስጥ በወረቀት ላይ ሠፍሮ የሚገኝ መብት ትርጉም ያለው እንዲሆንና የሕዝብ ድምር ፍላጎትን መግለጽ የሚችል፣ ከሕዝብ ፈቃድም ጋር የተግባባ እንዲሆን መብታችንና ነፃነታችን ሕገ መንግሥት ላይ ከመጻፍ በላይ፣ ዴሞክራሲንና ሪፐብሊክን ከማወጅ የዘለቀ የሥርዓት ግንባታ ያስፈልገናል፡፡ ሕዝብ ራሱን በራሱ ማስተዳደር ጀመረ፣ ተማረ፣ መንግሥታዊ ሥልጣን ከሕዝብ ሿሚነትና ጠያቂነት ጋር ተገናኘ፣ ሕዝብ ተወካዮችን፣ ተወካዮች አስፈጻሚውን መግራትና መቆጣጠር አወቁበት ብሎ እርግጠኛ ለመሆን ሲበዛ፣ አውታረ መንግሥቱን ከወገንተኛነትና ከፓርቲ ባለቤትነትና ተቀፅላነት ማፅዳትና አዲስ ግንባታ መጀመርና መፈጸም አለብን፡፡ ዴሞክራሲን ለማቋቋም የሚያስችሉና የሚያበቁ እንዲህ ዓይነት የሪፎርምና የግንባታ ተግባር ውስጥ በመግባታችን ነው ክህደትና የውስጥ ወረራ ያጋጠመን፡፡ በሕወሓት ቁጥጥር ሥር በነበረ መንግሥታዊ አውታር ላይ ሆኖ ሲገዛ የኖረው ኢሕአዴግ ውስጥ የደረሰውን መገለባበጥ፣ ማስተናገድና መቋቋም ብቻ ለውጡ የሚጠይቀው ግዳጅ አልነበረም፡፡ ትናንት እሱ በገዥነቱ ቁንጮ ላይ ሆኖ የሰቀዛቸውን መብቶች አሁን የበላይነቱና አቅጣጫ ሰጪነቱ ሲናጋ፣ ግፋ በለው እያለ ከውድመትና ከአመፅ ጋር ያቀጣጠላቸውን የነፃነት ጥያቄ ያስቀደሙና በእሱ ስም በተለኮሱ አመፆችና ሽብሮች ሕግ በማስከበር መቋቋም አንዱ አዲሱ ግዴታ ነበር፡፡ አውታረ መንግሥቱን የማፅዳት ዋነኛው ሥራም ከዚሁ ጋር አብሮ ይሠራል፡፡

ይህን የመሰለ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሆድ እየቆረጠ ያለ ዋናው አደራና ግዳጅ እያለ፣ ሌሎች ነገሮች ትኩረታችንን መግፈፍ፣ እንጭፍጫፊውን ጉዳይ ከዋናው ተልዕኳችን ማምታታት የለባቸውም ብለን ደጋግመን ተናግረናል፡፡ ይህ ማለት ግን እነዚህ የሁለተኛ ደረጃና ከዚያ በታች የሆኑ ተግባራት ዝም ይባላሉ፣ ጭራሽ ከንግግር በላይ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ‹‹አላዋቂ ሳሚ››ዎች የሚፈጥሯቸውን እነዚህን ችግሮችም፣ ችግር ፈጣሪዎችንም፣ ይልቁንም አዲስ ‹‹እሺ አትበሉኝ የንጉሥ ዶሮ››ዎችን ራሳቸውንም በልክና በመልካቸው መናገር አለብን፡፡ እንዳላየ ማለፍ የሚጠይቁ ብዙ ነገሮች ቢኖሩም እኛም መናገር አለብን፣ እነሱም መነገር አለባቸው፡፡ ከሕግ በታች መሆንን፣ በሕግ ሥር ማደርን፣ ሳይጠየቁ መቅረትን፣ እንቢ ማለትን መኗኗሪያና መተዳደሪያ የምናደርገው ወደፊት ሲደላ አይደለም፡፡ አሁኑኑና ሁልጊዜም ነው፡፡ ባለፈው ወር ፓርላማ ውስጥ የሹመት ማፅደቅ አሠራር ውስጥ እንዳየነው ስህተትንም ሆነ ጥፋትን፣ እንዲሁም ተጠያቂነትን አድበስብሶ ማለፍ፣ በዚያ መልክ የታየውን ያህል ዘፈቃዳዊ የሥልጣን ጣልቃ ገብነትን በግልጽነትና በዴሞክራሲነት መመከት አለመቻል፣ በቀላልና በተራ ቋንቋ ለመናገር ቦሎ የሚያስከለክል ጥፋት ነው፡፡ ይህን የምናደርገው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር የማያውቀውን ዴሞክራሲ (ቀስ በቀስና በየደረጃው) ለማስተማርና ለማለማመድ ብቻ ሳይሆን፣ ዋናውን አደራችንን ራሱን የሚበላና አሳልፎ የሚሰጥ የበለጠ አደጋ ለመከላከል ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን ካሰነካከለ አፈናና ጥርነፋ ገለልተኛ ተቋማት በመገንባት አማካይነት፣ በዚህ በኩል ወደ ዴሞክራሲ የማለፍ ጉዞ ውስጥ ያለው ለውጥና ሽግግር ወዳጅና ጠላት ማወቅ አለበት የምንለው በዚህ ትልቅ ማዕቀፍ ውስጥ ሆነን ነው፡፡

ይህን በመሰለ የውጭ ደመኛ ጠላት ጭምር አዳፋዋለሁ በሚለው ዴሞክራሲን የማጥናት የለውጥና የሽግግር ጊዜ ውስጥ፣ ሕይወትና አብሮ መኖር መኗኗሪያ አድርገው የሚያነሷቸው የመብትና የነፃነት ነባርም አዲስ መልክ ይዞ የመጣ የአፈጻጸም ጥያቄዎች ያነሳሉ፡፡ እዚህም ላይ አስተዋዮች፣ የለውጡ ወገኖች ዴሞክራሲን መሠረት እናስይዛለን ብለው ከምር የቆረጡ ሰዎች፣ በተለይ በዚህ ጊዜ መብቴ ነው ባይነትን ኃላፊነቴ ነው ከማለት ጋር የማስማማትና የማጣጣም አደራ አለባቸው፡፡ መብቴ ነው ነፃነቴ ነው ማለት ኃላፊነቴም ነው ከማለት ጋር ካልተግባባ ዴሞክራሲው፣ ጅምሩ ዴሞክራሲ፣ የጥላቻና የርኩቻ ማምረቻ፣ የፍጅት መደገሻ መድረክ መሆን ይችላል፡፡

ይህ ሆነ ማለት ደግሞ የማናችንም ትርፍ አይደለም፡፡ የሁሉም፣ የአገርም ኪሳራ ነው፡፡ አዎ አስደሳችና አስደናቂ፣ የዓለምን ትኩረትና አድናቆት ጭምር ያተረፈ የለውጥና የሽግግር እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተን ነበር፡፡ ተቀናቃኞቹ፣ ጠላቱ፣ አሰናካዩ ቢበዛም ፈተናና አደጋ ውስጥ ቢገባም ይህ ለውጥና ሽግግር ግን አሁንም አለ፡፡ ትናንትም ሆነ ዛሬ በየትኛውም የለውጡና የሽግግሩ ደረጃ ለውጥና ማሻሻዎችን ማካሄድ ማለት ከየአቅጣጫው ለሚመጡ ጥያቄዎች እየተዋከቡ መገበር ማለት አይደለም፡፡ ትንሹንም ትልቁንም ጥያቄ እያግተለተሉ አዙሪት መፍጠር ዋናውንና ተቀዳሚውን የለውጥ ተግባር/ዴሞክራሲን ማቋቋም፣ አውታረ መንግሥቱን ገለልተኛ አድርጎ ማነፅ/ከዕይታ ያጠፋል፣ መንገድ ያስታል፡፡ ዋናው መገናኛችን በወቅቱ ዋና ተግባር ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር ነው፡፡ የአገሪቱ ሕመም፣ የሕዝቡም ሆድ ቁርጠትና ደዌ ዴሞክራሲን ለማቋቋም የሚያስችል መሠረተ የሌለን መሆኑ ነው፡፡ አውታረ መንግሥቱ፣ የመንግሥት ዓምዶች በሙሉ ከፓርቲ ገለልተኛ ሆነው አለመዋቀራቸው ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ይታገሉልናል፣ እርስ በርስ እየታገሉም ከፍትጊያቸው ውስጥ እሳት ሳይሆን ብርሃን ያፈልቁልናል የምንላቸው ፓርቲዎች ገና የተወሰነ፣ መነሻ የዴሞክራሲያዊ አመለካከትና ድርጅታዊ የአኗኗር መለኪያን አልፈው ወደ የሚቀጥለው እርከን ሲሸጋገሩ አላየንም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እስካለፈው ሳምንት መገባደጃ ድረስ የምንሰማውና የማናነበው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተለያዩ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባዔ ግምገማ ውጤት (ሪፖርት ካርድ) ዜናና ሪፖርት ‹‹ለክፉ ባይሰጥ››ም፣ የሚያበረታታ አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ በየአካባቢያችንና ከእያንዳንዱ የሚመለከተው የፖለቲካ ፓርቲ አኳያ የሚሰማውን ‹‹የቤተ ዘመዱ ይታያል ጉዱ›› ሆታም ሆነ ዋይታ የምንከታተለው ምቾት በሚሰጥ ስሜት ውስጥ ሆነን አይደለም፡፡ ገዥውን ፓርቲ ማለትም ብልፅግናን የመሰለ በጠቅላላ ጉባዔው ከቻይና፣ ከደቡብ አፍሪካ ፓርቲዎችን መጋበዝ ድረስ ተከነዳሁ ያለ የፖለቲካ ፓርቲ ሳይቀር፣ የምርጫ ቦርድን ተራ የኢንስፔክሽን ሥራ ሲያሳስን እያየን ነው፡፡ ፓርቲዎቻችን መንግሥታዊ ዙፋንንና ቢሮክራሲውን በፍላጎታቸው ልክ ቀርፀውና ጠፍጥፈው ሠርተው እዚያ ውስጥ ከመንፈላሰስ፣ እዚያ ውስጥ ተዘፍቀው በልሽቀትና በንቅዘት ከመበላሸት ነፃ የሚወጡት አውታረ መንግሥቱን የማንፃት ሥራ ዋና ጉዳያችን ሲሆን፣ ፓርቲዎችም ለዚህ ሲተጉና ምቹ ሲሆኑ፣ ይህንንም ማገዝ የሚችል መንዕስ የዴሞክራሲ አመለካከትና የአኗኗር ድርጅታዊ መለኪያን ሲያሟሉና ሲያልፉ ነው፡፡

በዚህ የዴሞክራሲ ጭላንጭል ውስጥ የተከፈተውን የፖለቲካ ሥፍራ የግርግር መደገሻ፣ የእርስ በርስ ዕልቂት መጠንሰሻ ከሚያደርጉ ጥያቄዎች ይልቅ ዋናው ተግባር ላይ እናተኩር የምንለው ሌላው ፍላጎትን ማስፈጸም፣ የሥልጣን ፍላጎትን ጭምር ኋላ ላይ ስለሚመጣ ነው፡፡ መጀመርያ የመቀመጫዬን ያለችውን የዝንጀሮዋን ብልጠት ያህል ፓርቲዎችና ንቅናቄዎች እንዴት አጡ የምንለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...