Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ለውይይት ወደ እኛ የሚመጣን ማንኛውንም አካል የመቀበል ኃላፊነትና ግዴታ አለብን›› መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር)፣ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር

በአንጋፋዮቹ ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤትና ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የተማሩና የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሒደት መልክ በቀየረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ጊዜ ውስጥ ያለፉ ሰው ናቸው፡፡ ለትምህርት ወደ ሩሲያ አቅንተው የተመደቡበትን የመካኒካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት ትተው በቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ ለሰባት ዓመታት ሕክምና ተምረዋል፡፡ በ1972 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ በአዲግራትና ደሴ ተዘዋውረው ሠርተዋል፡፡ ኋላም የአማኑኤል ሆስፒታል ዳይሬክተር ሆነው ካገለገሉ በኋላ ወደ ኔዘርላንድስ አቅንተው በአዕምሮ ሕክምና ስፔሻላይዝ አድርገዋል፡፡ መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) የአዕምሮ ሕክምና፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርነታቸው አንቱ የተባሉ ናቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በአገር ሽማግሌዎች መድረክ ሰብሳቢነት፣ የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አባል በመሆን አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሲሳተፉ ቆይተዋል፡፡ የካቲት 14 ቀን 2014 ዓ.ም. አስቸኳይ ስብሰባውን ያካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደግሞ ብዙ ሲጠበቅ የነበረውንና ከፍተኛ ኃላፊነት የተጣለበትን የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በዋና ኮሚሽነርነት እንዲመሩ ሾሟቸዋል፡፡ መስፍን (ፕሮፌሰር) ስለተሰጣቸው ኃላፊነት፣ ስለሚመሩት ኮሚሽንና ስለሚነሱበት ጥያቄዎች ከአማኑኤል ይልቃል ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- በሕክምና በተለይም በአዕምሮ ሕክምና ብዙ የሠሩ ባለሙያ መሆንዎን ብዙዎች ያውቃሉ፡፡ በሕክምናው ዘርፍ የሰጡት አገልግሎት ብዙ ጊዜ ተደጋግሞ የሚነሳ ነው፡፡ አሁን ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ትልቅ ኃላፊነት ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ከዚህ ቀደም ሲል የነበረዎትን የፖለቲካ ልምድና ተሳትፎ ምን እንደነበር ቢያነሱልን?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- ፖለቲካ ላይ ያን ያህል ነኝ፡፡ በሃያዎቹ ዕድሜዬ ውስጥ እያለሁ ኢሕአፓና መኢሶን የሚባሉ ፓርቲዎች ስለነበሩ ከእነሱ ለአንደኛቸው የተለየ ስሜት ማሳደር ነበረብን፡፡ እዚያ ውስጥ መጽሔቶችን በማንበብ፣ ወደ አንዱ በማድላት በተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ ወገንተኛ ነበርኩ፡፡ ያም ሆኖ ግን የዚህም ሆነ የዚያኛው አባል አልነበርኩም፡፡ ወገንተኛነቴ ግን በተማሪዎች እንቅስቃሴ ወስጥ ነበር፡፡

ሐኪም ከሆንኩ በኋላ በነበረው ሥርዓት ኢሠፓ የሚባል ነበረ፡፡ እሱንም ተዓምር በሚመስል ሁኔታ አባል ሳልሆን አልፌዋለሁ፡፡ ከ1983 ዓ.ም. በኋላ በተለያዩ ፓርቲዎች መድበለ ፓርቲ ሥርዓት ሲመሠረትም ፍላጎቱ አልነበረኝም፣ መሽቶ ነበር፡፡ ምክንያቱም በሕክምናዬና በማስተማር ብሠራ ሙያዬ ዞሮ ዞሮ ከአዕምሮ ጋር የሚገናኝ ስለሆነ በራሱ በቂ ነበር፡፡ አዕምሮ በውስጡ ሃይማኖት፣ ፖለቲካ ውስጡ ብዙ ነገሮች አሉበት፡፡ ስለዚህ ይኼንን ያህል የፖለቲካ ፍላጎቱ አልነበረኝም፡፡ ነገር ግን የአገሬ ጉዳይ ያሳስበኛል፣ ያንገበግበኛል፣ ያስጨንቀኛል፡፡ እነዚህ ነገሮች ሁሌም አብረውኝ አሉ፡፡ በተለይ ኢትዮጵያዊነት የሚለው ነገር ያመኛል፡፡ ምክንያቱም አንድ አገር ነው ያለኝ፣ ልዋጭ አገር የለኝም፡፡ እስካሁን ኖሬባታለሁ፣ ተምሬ ሠርቼባት አገልግዬባታለሁና በሚቀረኝ ዕድሜ ለወጣቶች ውርስ የሚሆን፣ ሰላማዊ ነገር ትቼ ብሄድ ደስተኛ እሆናለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ እንደዚህ ነው የእኔ አካሄድ፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎና ሌሎች አሥር ሰዎች ኮሚሽነር ሆናችሁ የመጣችሁበትን መንገድ ከግልጽነትም አንፃርም ሆነ በሌላ ጉዳዮች ጥያቄ የሚያነሱ ወገኖች አሉ፡፡ ኮሚሽን የማዋቀር ሒደቱን እንዴት ተመለከቱት?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- እንደ እነዚህ ዓይነት ጥያቄዎች ተደጋግመው ይነሱልኛል፡፡ መነሳታቸውም ተገቢ ነው፡፡ ኅብረተሰቡም ማወቅ አለበት፡፡ መስፍን ምንድነው? የሚለውን ሳይሆን ማነው? የሚለውን ነገር ማወቃቸው ትክክል ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ መስፍን እዚህ ሥራ ውስጥ ቢገባ ምን አስተዋፅኦ ይኖረዋል? ምን ሊሠራ ይችላል? ምን አቅም አለው? የሚለው መታወቅ አለበት፡፡ ምክንያቱም ይኼ ኮሚሽን የተቋቋመው በአዋጅ ነው፡፡ አዋጁ ደግሞ ይኼን ይኼንን ትሠራላችሁ ብሎ 12 ተግባራትን ቆጥሮ ሰጥቷል፡፡ ሌላው ትልቁ ነገር እዚህ ኮሚሽን ውስጥ የሚገቡ ኮሚሽነሮች አካታች፣ ገለልተኛ፣ ሚዛናዊ መሆን አለባቸው ይላል፡፡ አዋጁን ጥሩ አድርገው ነው ያዘጋጁት፣ ውስጡ ብዙ ነገሮችን ይዟል፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሥራዎች ሊሠራ የሚችል ሰው ነው ወይ? ተብሎ መጠየቅ አለበት፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ እንዴትና በማን ነው የተመረጡት? እንዴት 11 ዕጩዎች ውስጥ ገቡ? የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ በእርግጥ ይኼንን ሒደት እኔ መመለስ ይጠበቅብኛል ብዬ አላስብም፡፡ ምክንያቱም እኔ ራሴ ተወዳድሬ፣ እዚህ ቦታ ካልገባሁ ብዬ፣ የሥራ ልምዴን አቅርቤና ከሌሎች ጋር ተፎካክሬ፣ ይኼ ይደረግልኝ፣ ይኼንን እሠራለሁ ብዬ አይደለም የገባሁት፡፡ ይኼ አዋጅ ከወጣ በኋላ በአዋጁ መሠረት ሕዝብ ይጠቁም ተባለ፣ ሕዝብ ጠቆመ፡፡ ከተጠቆሙት 632 ሰዎች ውስጥ እንደነበርኩም አላውቅም ነበር፡፡ አንዳንድ ሰዎች እየደወሉ ‹‹ልንጠቁምህ ነው›› ቢሉኝም በቁምነገር አልወሰድኩትም ነበር፡፡ እንደሚጠቁሙኝ ቢገባኝም እዚህ ቦታ ውስጥ ብገባ በትክክል ልሠራ እችላለሁ? ብዬ ራሴን እጠይቅ ነበር፡፡ 42 ተጠቋሚዎች ከተለዩ በኋላ ነው እዚህ ውስጥ መግባቴን በትክክል ያወቅሁት፡፡ 42 ሰዎች ይፋ ከመደረጋቸው በፊት በማኅበራዊ ትስስር ገፆች ወጥቶ የነበረ አንድ የዕጩዎች ዝርዝር ውስጥ ስላልነበርኩ፣ ‹‹እንኳን አልተመረጥሁ›› ብዬ ደስ ብሎኝ ሁሉ ነበር፡፡ ኋላ ትክክለኛው ዝርዝር ወጥቶ እንዳለሁበት ሲነገረኝ፣ ‹‹ካለሁበት እንግዲህ ለአገሬ ምን ልሠራላት እችላለሁ?›› ብዬ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ የእኔ ምኞትና ፍላጎት የነበረው ጡረታ ስለወጣሁ በራሴ ሥራ እያስተማርኩ፣ እያከምኩ፣ ሰፋ ያለ ጊዜ ስለሚኖረኝ ያሉኝን ብዙ የመጻሕፍት ክምችት ማንበብ፣ ብችል ደግሞ ብጽፍ ነበር፡፡ መናገር የምችለውን ያህል መጻፍ መቻሌን እርግጠኛ ባልሆንም ለመሞከር እፈልጋለሁ፡፡ አንዳንድ ነገሮችን ለቀጣዩ ትውልድ ትቶ የማለፍ ፍላጎት ስለነበረኝ እዚህ ላይ እሠራለሁ ብዬ ነበር ያሰብኩት፡፡ በተለይ ደግሞ እንደ ገዳማት ባሉ ትልልቅ የሃይማኖት ቦታዎች ላይ መንፈሳዊነት ከአዕምሮ ጋር ያለውን ተያያዥነት የማጥናት ፍላጎት ነበረኝ፡፡ እነዚህን ሁሉ ባሰብኩበት ጊዜ ነው እንግዲህ ይኼ ነገር የመጣው፡፡

ይኼ ነገር መጥቶ 42 ውስጥ ነህ ስባል 11 ውስጥ የመግባት ዕድሌ ጠባብ ነው ብዬ ‹‹እሺ›› አልኩ፡፡ 11 ውስጥ መግባቴ የተነገረኝ በዋዜማው ነው፡፡ ቆይቶ ደግሞ ዋና ኮሚሽነር ነህ ተባልኩ፡፡ ይኼ ደግሞ ኃላፊነቱ ከባድ ነው፡፡ 11 ኮሚሽነሮች ስንመረጥ በሩቁ ከመተዋወቅ ውጪ በቅርብ አንተዋወቅም፡፡ 11 ሰው አብሮ መሥራት ቀላል አይደለም፣ በጣም ከባድ ነው፡፡ ኮሚሽነሮቹ የተለያየ ልምድ ይዘው መምጣታቸውን እያየሁ ስሄድ እየተበረታታሁ መጣሁ፡፡ ዋና ኮሚሽነር ባልሆን ደስ ይለኝ ነበር፡፡ እንደ ሌሎቹ ባልደረቦቼ ኮሚሽነር ብቻ ሆኜ እየተሳተፍኩ የአቅሜን አስተዋፅኦ ባደርግ፣ የማስተባበሩ ሥራ ባይኖርብኝ ሥራው ይቀልልኝ ይሆናል የሚል እምነት ነበረኝ፡፡

ስለዚህ ስለሒደቱ ሁሌ ይጠየቃልና በአዋጁ መሠረት 632 ሰዎች ተመረጡ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከዚህ ውስጥ 75 ሰዎችን መረጠ፣ ከዚያም ውስጥ 42 ቀሩ፡፡ ይኼም የሆነው ቁጥሩን አሳንሶ መጨረሻ ላይ የሚቀርቡትን 14 ዕጩዎች አዘጋጅቶ 11 ሰዎችን ለመምረጥ ነው፡፡ ሒደቱ ይኼ ነበር፡፡ እንደተነገረኝ ከሆነ በዚህ ሒደት ውስጥ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ሴቶች፣ አክቲቪስቶች፣ ወጣቶች፣ የሚመለከታቸው ከትግራይ ክልልና አንዳንድ ችግር ካለባቸው አካባቢዎች ወጪ ከመላው ኢትዮጵያ መጥተው፣ በተለይ በ42 ዕጩዎች ላይ ሐሳብ እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ ይኼ ይውጣ፣ ይኼ ትክክል አይደለም፣ ይኼ ኢትዮጵያዊ ዜግነት የለውም እያሉ በአዋጁ መሠረት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ሴቶችና ወጣቶች ቁጥራቸው አንሶ የነበረ ይመስለኛል፡፡ ከ75 ስብስብ ውስጥ አንዲት ሴትና ሁለት ወጣት ወንዶች እንዲገቡ ተደረገ፡፡ ሦስቱም 632 ሰዎች ውስጥ ነበሩ፡፡ አንዲት ሴት መገኘቷም ደስ ብሎኛል፡፡ ይኼንን ሒደት እኔ የመግለጽ ኃላፊነት የለብኝም፡፡ እንደተናገርኩት ‹‹በእነዚህ ሒደቶች መጥተሃል›› ተብሎ ነው የተነገረኝ፡፡ መጥቼ ሥራዬን ጀምሬያለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን የተቀመጡበት ኃላፊነት ሥራው ገና ጅማሬ ላይ ቢሆንም መውጣት መውረድ፣ ብዙ ሰዎችን ማነጋገርና ማግባባት፣ አጀንዳዎችን ለመቅረፅ የተለያዩ ቦታዎች መዘዋወርን ይጠይቃል፡፡ ከዚህ አንፃር እርስዎ ለዚህ ኃላፊነት ያለዎትን ተገቢነት እንዴት ያዩታል?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- ከእኔ የተሻሉ ብዙ ሰዎች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ምናልባት እኔና ሌሎቹ ኮሚሽነሮች ከብዙዎቹ የምንለየው ‹‹ተጠቁማችኋልና ወደዚህ ሥራ ኑ›› ስንባል እሺ ማለታችን ነው፡፡ ዋናው ፈቃደኝነት ነው እንጂ ኢትዮጵያ የወላድ መካን አይደለችም፡፡ ብዙ የሚገርም ሐሳብ ያላቸው አሉ፡፡ ምናልባት የተጠቆሙት 632 ሰዎች አብረውን እንዲሠሩ የማድረግ ፍላጎት አለን፡፡ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ያግዙናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እንዲህ ዓይነት አገራዊ ጥያቄ እስኪመጣም መጠበቅ አያስፈልግም፡፡ ‹‹እኔ ልሠራው ይገባል›› ብሎ መምጣት ያስፈልጋል፡፡ የመሥራት ፍላጎት አለን ብለው የሚመጡ ሰዎች አሉ፡፡ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ሁኔታዎች በሚፈቅዱ ጊዜ ለእነዚህ ሰዎች ጥሪ የማናደርግበት ምክንያት የለም፡፡ እኔ እንደዚህ ዓይነቱ ሥራ በጭራሽ ይመጣል ብዬ ጠብቄ አላውቅም፡፡ ነገር ግን የተባለው ሥራ ውጤታማ ከሆነ ለአገራችን የሚገርም ነው የሚሆነው፡፡ በጠመንጃ፣ በጎራዴና በገጀራ አየነው፡፡ በእኛ ጊዜ ተደርጎ ሳይሆን ሊታሰብ የማይችሉ ነገሮችን በዚህ ጊዜ ተመልክተናል፡፡ ብዙ ዕልቂትና መፈናቀል አስተናገድን፡፡ እዚህ ላይ ረሃብ ሲጨመርበት፣ ስደት ሲገባበት ኢትዮጵያችንን በጣም ጨለምተኛ አገር ነው የሚያደርጋት፡፡ ከዚህ ለመውጣት የሚኖረው አማራጭ ውይይት ይሁን ተብሎ ከአሁን በፊትም በተቃዋሚ ፓርቲዎች ሐሳብ ይቀርብ ነበር፡፡ አሁን ያለው መንግሥት ይኼንን ተቀብሎ ለውይይት ዝግጁ ነኝ፣ ይኼ መድረክ ይዘጋጅ፣ ጣልቃ አልገባም፣ ነፃ ሆናችሁ ሥሩ፣ የሚያስፈልጋችሁን ነገር አመቻችላችኋለሁ ብሎ መፍቀዱ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ የማንም ጣልቃ ገብነት ሳይኖር ሁላችንም ወደ ንግግር ከመጣን ውጤቱ ጥሩ ይሆናል፡፡

ውይይት ለእኛ ለኢትጵያውያን አዲስ ነገር ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ብዙ ጊዜ እንደምናገረው እኛ አገር የተለመደው ውይይት ወይም ንግግር ከላይ ወደ ታች ነው፡፡ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ሀይራርኪካል (ተዋረዳዊ) ነው፡፡ ሁልጊዜ የበላይ አለው፡፡ ለምሳሌ ቤት ውስጥ አባት የበላይ ሊሆን ይችላል፡፡ አባት በሌለበት ታላቅ ወንድም ወይም እህት ልትሆን ትችላለች፡፡ ሁልጊዜ በዕድገታችን ላይ ተፅዕኖ ወይም መጫን አለ፡፡ በውይይት ግን መጫን የለም፡፡ በውይይት እኩልነት አለ፡፡ ለምሳሌ እኔና አንተ የማያግባቡን ነገሮች ኖረው እነሱ ላይ እንወያይ ከተባለ የሚያስፈልገን አንድ አወያይ ብቻ ነው፡፡ አወያዩ ሥራው በመረጥነው ርዕስ ላይ ሕግ ሳንጥስ ተከባብረን መግባባት ላይ አስክንደርስ እንድንወያይ ማድረግ ነው፡፡ መጀመሪያ እኔና አንተ ወደ ውይይት መድረክ እንምጣ ብለን ስንወስን፣ አዎንታዊ በሆነ መንገድ ነው የመጣነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ነገር ላይ እንደርሳለን፡፡ እኛ በዚህ ዓይነት መንገድ ስንመጣ ሳይፈርጅ ወደ አንድ ሰው ሳያጋድል የሚያወያየን ሰው ያስፈልጋል፡፡ በዚህ መንገድ የምንወያይባቸው ነገሮች በትክክል አንድ መልካም ነገር ላይ ያደርሱናል፡፡

ብዙውን ጊዜ እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ሲካሄዱ ከላይ ያሉት ሰዎች ይጠልፉታል፡፡ ማኅበራዊ አንቂዎች፣ ሐሳብ አፍላቂዎች፣ የፖለቲካ መሪዎች፣ የመንግሥት አካል ወይም የቀበሌ ኃላፊዎች እነዚህን አጀንዳዎች ይነጥቁና የራሳቸውን ውሳኔ ወስነው፣ ማኅተም አድርገው ወደሚቀጥለው ደረጃ ይወስዱታል፡፡ ውይይት ማለት ግን ይኼ አይደለም፡፡ ለዚህ ነው ለእኛ አዲስ ነገር ነው ያልኩት፡፡ በእርግጥ አልፎ አልፎ በተለያዩ ቦታዎች ሊተገበር ይችል ይሆናል፡፡ ግን እኔ እስካሁን ባደረግኩት ንባብ አላጋጠመኝም፡፡ ሁልጊዜ የበላይነት ባለበት ሥርዓት ውስጥ ሁኔታዎች ለውይይት ምቹ አይደሉም፡፡ እኛ ግን በዚህ ውይይት አጀንዳዎቹን ከታች ከማኅበረሰቡ ጀምሮ ነው የምናመጣቸው፡፡ ኮሚሽኑ ከአጀንዳዎቹ ውስጥ የቅድሚያ ቅድሚያ የመስጠት መብት አለው፡፡ በአገራችን ዋነኛ አጀንዳ ሊሆን የሚገባው ምንድነው? አጀንዳዎችን ከሁሉም ነቅሶ ካመጣ በኋላ የሚለይበትን መሥፈርት ያወጣል፡፡ ለምሳሌ ሰላም የሚያደፈርሱ፣ የማያግባቡን የውይይት አጀንዳዎች የትኞቹ ናቸው? ብሎ ነቅሶ ያወጣና ወደ መሀል ያመጣቸዋል፡፡ ሁሉም ተወያይቶ አንድ ነገር ላይ እንዲደርስ ያደርጋል፡፡ አካባቢያዊ የሆኑ የቀበሌ፣ የወረዳ፣ የጎጥ አጀንዳዎች ሲኖሩ በተነሱበት አካባቢ ሊያልቁ ይችላሉ፡፡ አንዳንድ አጀንዳዎች ግን ከዚያም አልፈው ወደ ዞን ይሄዳሉ፡፡ በዞን ደረጃ የማያልቁና ወደ ክልል የሚሄዱ አጀንዳዎችም ሊፈጠሩ ይችላል፡፡ ከክልል አልፈው ወደ ፌዴራል ደረጃ የሚመጡ አጀንዳዎች ደግሞ ሁልጊዜ አገርን አስቀጣይ የመሆንና ያለ መሆን አቅም አላቸው፡፡

አሁን አገራችን ውስጥ (በአንዳንድ ቦታዎች) ሰላም ደፍርሷል፡፡ አንዳንዶቹ የደፈረሱ ሒደቶች የራሳችንን ዕድል በራሳችን እንወስናለን እስከ ማለት የደረሱ ናቸው፡፡ አገርን የሚነኩ ናቸው ማለት ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ በየደረጃው ኅብረሰተቡ የሚወስንባቸውና እየተግባባቸው የሚሄድባቸው ናቸው፡፡ የውይይት ሒደቶች ብዙ ናቸው፡፡ የቅድመ ዝግጅት፣ የዝግጅትና የውይይት ሒደቶች ይኖራሉ፡፡ ከውይይት ሒደት ቀጥሎ የሚጠበቀው የትግበራ ወቅት ነው፡፡ ውይይቱ ከተደረገ በኋላ የተነሳው ሐሳብ ተሰባስቦ ወደ መሀል ኮሚሽኑ ጋ ይመጣል፡፡ የኮሚሽኑ ምክር ቤት በደንብ አስቦበትና ዘክሮበት ከውሳኔ ሐሳብ ጋራ ለመንግሥትና ለሕዝብ ይመልሰዋል፡፡ በእነዚህ ውይይቶች መሠረት ሕዝብ መግባባት ላይ የደረሰባቸው እነዚህ እነዚህ ናቸው ተብሎ ይቀርባል፡፡ የባንዲራን ጉዳይ በምሳሌነት ብናነሳ፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ አይቀጥል ወይም ይቀጥል የሚለው ላይ መቶ በመቶም ባይሆን በአጠቃላይ የሚያግባቡ ጉዳዮች ላይ ተደርሶ ከሆነ፣ መንግሥት ሆይ ባንዲራን በተመለከተ ሕዝቡ ይኼንን ብሏል፡፡ ሕዝብ ሆይ ባንዲራን በተመለከተ ይኼንን ብለሃል እናቀርባለን፡፡ ሕዝብ ይኼንን ብዬአለሁ ሲል መንግሥት ደግሞ መተግበር ይኖርበታል፡፡ መንግሥትም ሰምቶ መተግበተሩን የመከታተል ኃላፊነት በአዋጁ ተሰጥቶናል፡፡ ስለዚህ ይኼንንም እንከታተላለን፡፡ የመጀመሪያዎቹ ዕርምጃዎች ላይ በሚገባ ካልተዘጋጀን ወደ ውይይቱ በምንገባበት ጊዜ ውጤታችን ደካማ ይሆናል፡፡ ይኼንን የሥራ ሒደት ከአሥሩ ባልደረቦቼ ጋር አብሮ ለመተግበር ወደፊት ከሚመጡ የሚዲያ ሰዎች፣ የተለያየ ዕውቀት ካላቸው ባለሙያዎች፣ በአገር ውስጥም በውጭ ካሉ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን፣ ምሁራንና ልሂቃን ጋራ አብሮ ከተሠራ ወደ ውጤት ይደረሳል ብዬ ነው ወደዚህ የገባሁት፡፡ እንግዲህ መስፍን ማለት ያ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አስቀድመው እንደተናገሩት የተመረጣችሁት ሰዎች ራሳችሁን አቅርባችሁ በውድድር ስላልገባችሁ ሒደቱ ላይ ምንም መናገር አይችሉ ይሆናል፡፡ ተመርጣችሁ ወደ ሥራ ከገባችሁ በኋላ ግን ሁላችሁም ኮሚሽነሮች ስላላችሁ ገለልተኝነትና ሚዛናዊነት ላይ እርስ በርስ ንግግርና ግምገማ አድርጋችኋል? ካደረጋችሁስ ምን ዓይነት ድምዳሜ ላይ ደረሳችሁ?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- የመጀመሪያውን ከአንድ ሳምንት በላይ የሚሆን ጊዜ የወሰደብን እርስ በርስ መተዋወቅ ነው፡፡ መተዋወቁ ‹‹መስፍን እባላለሁ፣ እንደዚህ ነኝ›› ማለት ሳይሆን ከዚህ በላይ በቤተሰብ ድረስ፣ ምን እንወዳለን? ምን እንጠላለን? ለዚህ ኮሚሽን ምን አስተዋፅኦ ማድረግ እንችላለን? አቅማችን ምን ድረስ ነው? የሚለውን ያካትታል፡፡ ምክንያቱም አሥራ አንዳችንም ከተለያየ ማኅበራዊ መሠረት ነው የመጣነው፡፡ እኔ ሐኪም ነኝ፡፡ በዚያ ያሉት በጥብቅና፣ በዳኝነት የነበሩ የሕግ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ በውጭ ዓለም አቀፍ ትልልቅ ድርጅቶች ላይ የሠሩ፣ አምባሳደሮች የነበሩም አሉ፡፡ ከተለያዩ ሙያዎች የመጣን ነንና ይዘነው የመጣነው ልምድ ለዚህ ምን አስተዋፅኦ ይኖረዋል? ወጣቶቹም እንደ ዕድሜያቸው ሳይሆን ትልቅ የትምህርት ደረጃ ላይ ደርሰው የመጡ ስለሆኑ፣ አስተዋጽኦዎችን ምን ሊሆን ይችላል? የሚለውን ዓይተናል፡፡ አቋማችንስ ምን ይመስላል? ሚዛናዊ ለመሆን ምን ያህል ዝግጁ ነን? ምን ያህል ገለልተኛ ነን? ግንኙነት አለን ወይ? የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ አለን ወይ? እስከዚህ ድረስ በግልጽ ተነጋግረናል፡፡ የሚመለከተው ክፍል አጣርቶ ስለመረጠን ይኼንን የግድ የመጠየቅ ኃላፊነት የለብንም ነበር፡፡ ግን እኛም ብናውቀው በሚል ነው፡፡ እኔ እንደተናርኩት በልጅነቴ ግራ ዘመም የፖለቲካ ሒደቶችን ስከታተል፣ ስዘምር ወይም ወረቀት ሳነብ ነበር፡፡ መሬት ላራሹ ሲያቀነቅኑ አብሬ ነበርኩ፡፡ በጊዜው በነበረው ሒደት ከዚያ ውጪ መሆን አይቻልም ነበር፡፡ በኋላ ትምህርቴን ጨርሼ ደግሞ በተለምዶ የደርግ መንግሥት በሚባለው ጊዜ ሐኪም ሆኜ ሰሜን ትግራይ፣ ወሎ ሄጄ ሠርቻለሁ፡፡ ሥራዬ ነው፣ ስለዚህ ሥራዬን እሠራለሁ፡፡ በዚህ ሁሉ ሒደት ውስጥ የዚህ ወይም የዚያኛው ፖለቲካ የሚል ነገር ስላልነበረኝ አልገባሁም፡፡ ያ ማለት ግን የግድ ሁላችንም ከበፊት የፖለቲካ አባልነት ንፁህ እንድንሆን ይጠበቅብናል ማለት አይመስለኝም፡፡ ዋናው ነገር አሁን የፖለቲካ ወገተኝነት አለን ወይ? የፖለቲካ ፓርቲን ሐሳብ እንናቀነቅናለን ወይ? የሚለውን ነገር በትክክል መተያየት ጥሩ ነው፡፡

ከዚህ ውጪ ደግሞ ብሔረሰቦቻችንም የተለያዩ ናቸው፡፡ እኔ ለነገሩ ለረዥም ጊዜ በብሔረሰብ አላምንም ነበር፡፡ አሁንም ብዙ ችግሮቼ እዚያ ላይ ናቸው፡፡ ምክንያቱም እኔ ከሁሉም ቅድሚያ የምሰጠው ኢትዮጵያዊነት ዜግነቴ ላይ ነው፡፡ ቢሆንም ግን ዞሮ ዞሮ መነሻ ይኖረኛልና ለመነሻዬ ብዬ ወደ እዚህ አልመጣሁም፡፡ እኔ የመጣሁት ኢትዮጵያ ለምትባለው አገር ነው፡፡ የእኔ ሙያ ሕክምና ነው፡፡ ሕክምና ደግሞ ያስተማረኝ፣ ቃለ መሃላም የፈጸምኩት፣ ‹‹ስታክም ሰውን ሰው ብለህ አክመው›› በሚለው ነው፡፡ ስለዚህ ፈረንጅ ነህ፣ ጥቁር ነህ፣ ቢጫ ነህ፣ ቻይናዊ ነህ ብዬ አይደለም የማክመው፡፡ ወይም ከዚህ ወይም ከዚያኛው ብሔረሰብ መጥተሃል ብዬ አይደለም የማክመው፡፡ የእኔ ሥራ ከመጀመሪያውም አንስቶ ሰብዓዊነትና ሰውነት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ያ ይጠቅመኛል፡፡ በእርግጥ ሌሎቹም ኮሚሽነሮች ወደ እዚህ ሲመጡ ሌሎች ካባዎቻቸውን እዚያው አስቀምጠው ነው፡፡ ምክንያቱም ለዚህ ኮሚሽን ሥራ መሳካት ሕዝብ ፊት በገባነው ቃለ መሃላ መሠረት የተሰጠንን ተግባራት እንተገብራለን ብለው ነው የመጡት፡፡ ያለ ምንም ጥርጥር በሚዛናዊነት ወገናዊ ላለመሆን መጥተዋል፡፡ መነሻ ብሔራቸውም፣ ጎሳቸውን ወይም መንደራቸውን ሳይሆን ትልቋን ኢትዮጵያ ለማየት ቃል ገብተው መጥተዋል፡፡ ያንን ሥራ ነው የሚሠሩት፣ እኔም ራሴን ከትቼ የማየው በዚህ መንገድ ነው፡፡

ይልቅ አሁን የሚያጨናንቀው ነገር አንዳንድ ጊዜ የሕዝብ ጥባቆ (expectation) ከመጠን በላይ የናረ መሆኑ ነው፡፡ ብዙዎች ውይይት ምን እንደሆነ ገና ጠልቆ አልገባቸውም፡፡ እንኳን እነሱ እኛም የተመረጥንና የታዘዝን ሰዎች ገና ሥራችንን አብላልተን መቶ በመቶ አውቀናል ለማለት አልደፍርም፡፡ ከሕዝብ ጋር ደግሞ ብዙ ዓውደ ጥናትና ሲምፖዚየሞች ይካሄዳሉ፡፡ አንዳንዱ የዚህ ኮሚሽን ውይይት የሚመስለው የተለያዩ የተጣሉ የክልል መንግሥታትን አምጥቶ ማስታረቅ ይመስለዋል፡፡ አንዳንዱ ‹‹አንተም ተው አንተም ተው›› የማለት የሽምግልና ሥራ የምንሠራ ይመስለዋል፡፡ ሌላኛው ደግሞ የድርድር ሥራ የምንሠራ ይመስለዋል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች የእኛ ሥራዎች አይደሉም፡፡ በጣም ትልቁ ሥራና ኃላፊት የተሰጠን ውይይቱን በትክክል ማሳለጥ ነው፡፡ ይኼ ነው ከባዱ ሥራ፡፡ እንጂ ጉልበት ወይም ገንዘብ ካለህ ሁለት የተጣሉ ሰዎችን አስቀምጠህ፣ ‹‹ከዛሬ ጀምሮ እንዳትጣሉ፣ ይኼንን አድርግላችኋለሁ፣ ተጨባበጡ›› ማለት የመጨረሻው ቀላል ሥራ ነው፡፡ ሁለቱን ሰዎች ግን ቁጭ አድርጎ ‹‹መሠረታዊ ችግራችሁ ምንድነው? ከዜሮ ጀምራችሁ ተወያዩና ፍቱት›› ብሎ ረዥም የሆነ ጊዜና ቦታን መስጠቱ ነው ከባዱ፡፡ ያለ ገንዘብ፣ ያለ ጉልበት፣ ያለ ማስፈራራት በመሳሰሉት የሚከናወን ሥራ ነው፡፡

ለውይይታችን የሚጠቅሙ ሰነዶችን ስናገላብጥ ብዙ ድርድሮችን ዓይተናል፡፡ የየመን አካሄዱ ጥሩ ሆኖ የውጭ እጅ ነበረበት፡፡ የባህረ ሰላጤው አገሮች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉልበት ነበራቸው፡፡ አንዳንዶቹ ለውይይት ሲነሱ ወይ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ወይም ለሌላ ዓላማ ብለው ነው፡፡ እዚህ ላይ ግን ለ100፣ ለ150፣ ለ500 ወይም ላለፉት 30 ዓመታት እንዳንግባባ ያደረጉን መሠረታዊ ችግሮች ምንድናቸው ብሎ አጀንዳ ለመቅረፅ ወደ ኅብረተሰቡ ሲወረድ፣ ምን ያህል አጀንዳዎች እንደሚመጡ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ አንድ ሺሕ ወይም መቶ ሺሕ አጀንዳ ሊመጣ ይችላል፡፡ እነዚህን ሁሉ ነቅሶ አምጥቶ የሚጣል አጀንዳ ባይኖርም፣ በትክክል ከዚህ ውስጥ አጣርቶ ቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት ማለት በጣም ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ እስካሁን ድረስ በዚህ ዙርያ የተሠሩ ምርምሮች ካሉ፣ አልያም በድርድር፣ በሽምግልና በዕርቅ ዙሪያ የተሠሩ ሥራዎችን በሙሉ ከሠራን በኋላ ለራሳችን ግብዓት መጠቀም ይኖርብናል፡፡ ከዚህም በላይ እኛ አገር ትልቅ ብሔረሰቦች ትንንሽ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚባሉ አሉ፡፡ ማንም ቢሆን አንተ ትንሽ ሕዝብ ነህ ሳይባል፣ ከትልልቆቹ ብሔሮች እኩል አጀንዳውን አውጥቶ የመወያየት አቅም ሊኖረው ይገባል፡፡ ይኼንን ለማድረግ በቅድሚያ ኅብረተሰቡን ውይይት ስንል ምን ማለታችን ነው? የት ድረስ ይኼዳል? ምን ጉልበት አለው? የሚለውን ማስተማር ይኖርብናል፡፡ የተጠቆሙት 632 ሰዎች በዚህ ሊረዱን ይችላሉ፡፡ 75 እና 42 ሰዎች ደግሞ አወያዮችን በማስተማርና በማሠልጠን ሊያግዙን ይችላሉ፡፡ ሥራው በጣም ሰፊ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የምክክር ኮሚሽኑ ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደ መሆኑ፣ ኮሚሽነሮቹ ሥራችሁ ምንድነው ለሚለው የተሰጣችሁ ማብራሪያ እንደሚኖር ይጠበቃል፡፡ የሥራችሁ ዝርዝር ምንድነው? ለሥራ ወሰናችሁና መሄድ ስለምትችሉበት ጥግ የተሰጣችሁ ማብራሪያ ምንድነው?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- የሥራ ወሰናችን አዋጃችን ነው፡፡ አዋጅ ተሰጥቶን ያንን አዋጅ የማስፋት መብት ተሰጥቶናል፡፡ ሥራዎችና ተግባራትን የመጨመር መብት ተሰጥቶናል፡፡ ተጠሪነታችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ነገር ግን ምክር ቤቱን በየጊዜው ማግኘት ስለማንችል ምክር ቤቱን ወክሎ ከአፈ ጉባዔው ጽሕፈት ቤት ጋር ቅርብ ግንኙነት አለን፡፡ ሥራችንን የተመቻቸ እንዲሆን በሚያስፈልግበት ጊዜ ከጽሕፈት ቤቱ ኃላፊዎች ጋር በየጊዜው እንገናኛለን፡፡ ከአፈ ጉባዔው ጋርም አንድ ሁለት ጊዜ ተገናኝተናል፡፡ አሁንም በቅርቡ እናገኛቸዋለን፡፡ በአዋጁ ላይ በየጊዜ የሥራ ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴው ያቀርባል ይላል፡፡ በዚያ መሠረት የሥራችን ሦስት ወራት ሲገባደድ ዕቅድና ስትራቴጂዎቻችንን በሙሉ አዘጋጅተን ከጨረስን በኋላ ሪፖርት እናደርጋለን [ባለፈው ሳምንት ሪፖርቱ ቀርቧል]፡፡ ከዚህ በፊት ግን በየጊዜው የደረስንበትን ነገር ለአፈ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት እናሳውቃለን፡፡ ዞሮ ዞሮ ነፃነት አለው፡፡ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየጊዜው እየተደወለ ‹‹ይኼንን አድርጉ፣ ይኼንን አታድርጉ›› የሚል ጣልቃ ገብነት በጭራሽ የለብንም፡፡ እንደሚታወቀው ምክር ቤቱ አንዱ የመንግሥት ክንፍ ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ራሱ ጣልቃ እንዲገባ ራሱም አልፈቀደም በአዋጁም አልተፈቀደለትም፡፡

ገና በጀታችን አልተሠራም፣ ግንቦት መጨረሻ ላይ ቀርበን በጀታችንን ማፀደቅ ይኖርብናል፡፡ የመጋቢት ወርን ብቻ ነው በሙሉ የሠራነው፡፡ በቀረው ጊዜ ውስጥ ቶሎ ሥራዎቻችን ተነድፈው በጀት ማዘጋጀት አለብን፡፡ እንደ ሌሎች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በመስከረም ይኼንን ሥራ ጀምረነው ቢሆን ሰፋ ያለ ጊዜ ይሰጠን ነበር፡፡ ይኼ አጣዳፊ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ የሕዝብ ጥበቃም አለ፣ መንግሥትም ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ቶሎ ወደ ትግበራ እንዲገባ ይፈልጋሉ፡፡ ቶሎ መግባቱ አንድ ነገር ሆኖ በጥንቃቄ ቅድመ ሥራዎቹን አከናውኖ መግባት ደግሞ እኛን የበለጠ  ውጤታማ ያደርገናል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ኮሚሽነሮች ከተሾማችሁ በኋላ የካቲት 16 ቀን 2014 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተደረገው የመጀመሪያ የሥራ ትውውቅ ፕሮግራም ላይ፣ መንግሥት በኮሚሽኑ አሠራር ውስጥ ጣልቃ የሚገባ ከሆነ ኃላፊነትዎን እንደሚለቁ ተናግረው ነበር፡፡ ምን ለማለት ፈልገው ነው ይኼንን የተናገሩት? መንግሥት ጣልቃ ገብቷል የሚባለው ምን ነገሮችን ሲያደርግ ነው?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- ‹‹እንዲያው መንግሥት ጣልቃ ቢገባብዎት ምን ያደርጋሉ?›› የሚል ጥያቄ ተነስቶ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥቼ ነበር፡፡ ምላሼ መንግሥት ለምን ጣልቃ ይገባል የሚል ነበር፡፡ መንግሥት ጣልቃ ለመግባት ቢፈልግ ኖሮ መጀመሪያውኑ ይኼ ኮሚሽን እንዲቋቋም አይፈቅድም ነበር፡፡ ዝም ብሎ አራቱን ዓመት ዛሬ ነገ እያለ መጨረስ ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን የዚህ ኮሚሽን መቋቋም ለራሱ መንግሥትም ቀጣይነት፣ ለአገር ግንባታም ስለሚመቸው ይኼ ኮሚሽን እንዲቋቋም ፈቅዷል፡፡ ይኼንን በፈቀደበት ሁኔታ ጣልቃ ይገባል ብዬ አላስብም አልኩ፡፡ ‹‹የምትጠቀሙት እኮ የመንግሥትን ንብረትና ቢሮ ነው፣ ሁሉም ነገር የመንግሥት ስለሆነ መንግሥት እንዴት ጣልቃ ላይገባ ይችላል?›› የሚል ጥያቄ ተነሳ፡፡ በወቅቱ ለዚህ ምላሽ ስሰጥ፣ መንግሥት ብቻውን የቆመ ነገር አይደለም፣ በመጀመሪያ ደረጃ መንግሥት ከየት አምጥቶ ነው ለእኔ ገንዘብና ቢሮ የሚሰጠኝ? የሕዝብ ገንዘብ፣ የምንከፍለው ታክስ ነው ብያለሁ፡፡ እኔ 40 ዓመት ሙሉ ታክስ ስከፍል ነበር፡፡ እዚህ አገር ትክክለኛው ታክስ ከፋይ ደመወዝተኛው፣ ከደመወዝተኛውም የመንግሥት ሠራተኛው ነው፡፡ የሚያመልጥበት ምንም መንገድ የለውም፡፡ ከማትረባ ደመወዜ ላይ ታክስ ስከፍል ኖሬአለሁ፡፡ መንግሥት ቢሮ ቢሰጥ ሁኔታዎችንም ቢያመቻች በሕዝብ ገንዘብ ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ጣልቃ ሊገባ አይችልም፣ ይፈልጋልም ብዬ አላስብም፡፡ ነገር ግን ይኼንን ሁሉ ትቶ ‹‹አይ የለም›› የሚል ከሆነ ለራሱ ለመንግሥት ቀርቶ ለተፎካካሪ ፓርቲዎችም አይጠቅምም፡፡ የተረጋጋ መንግሥትና የተጠናከረ ሕዝብ ካለ ነው ከሦስት ዓመት በኋላ ተፎካክረው መንግሥት መሆን የሚያምርባቸው፡፡ ይኼንን ሁሉ አልፎ የሚመጣ ከሆነ ግን የታወቀ ነው፡፡ ጣልቃ አልገባብህም ብሎኝ ነው የመጣሁት፣ ሥራዬንም የጀመርኩት በዚህ አግባብ ነው፡፡ ይኼ የማይሆን ከሆነ አልፈለገኝም ማለት ነው፡፡ እኔ ደግሞ ካልፈለገኝ ሐኪም ነኝ፣ መምህር ነኝ፣ የፈለኩት ቦታ ሄጄ አገልግዬ መኖር እችላለሁ በሚል ዓውድ ነበር የተናገርኩት፡፡

ሪፖርተር፡- ከገዥው ውጪ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን በመቀበል ምክረ ሐሳቦቻቸውን የሚለግሱ አካላት ይታያሉ፡፡ ከዚህ በተለየ ደግም ሰፊ የሕዝብ መሠረት እንዳላቸው የሚታመኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የኮሚሽኑ የመቋቋም ሒደት ላይ ጥርጣሬ በማንሳት በምክክሩ ውስጥ ለመሳተፍ እንደሚቸገሩ ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ላይ ያለዎት ሐሳብ ምንድነው?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- ቅሬታቸውን በግልጽ ማቅረብ ይሻላል፡፡ ቅሬታን ማቅረብ ተገቢ ነው ብዬአለሁ፡፡ ግን ብዙውን ጊዜ ቅሬታዎች ሲቀርቡ ከእነ ሙሉ ማስረጃ ወይም ምክንያት ቢሆን ደስ ይለኛል፡፡ ለምሳሌ 42 ዕጩዎች ተመርጠው የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት ሲያደርጉ፣ እኛ የመረጥነው ሰው ለምን አልገባም ማለታቸውንና እያንዳንዳችን ላይ ሐሳብ መስጠታቸውን ሰምቻለሁ፡፡ ሒደት ውስጥ ስላልነበርኩ ምንም መናገር አልችልም፡፡ ግን በተለይ እኔን በተመለከተ ‹‹እርሱ እንዲህ ነው›› የሚል ትክክለኛ መረጃ ካለ እኔ እዚህ ምን እሠራለሁ? ሲናገሩ ከእኔ የተሻለ ሰው አዕምሮአቸው ውስጥ ኖሮ ወይም አዋጁን የተስማሙበት ይመስለኛል፡፡ በዚያ መሠረት እኔ ያላሟላሁት እነሱ የሚፈልጉት ነገር ካለ በማንኛውም ጊዜ ሥራዬን በፈቃዴ ለመልቀቅ ዝግጁ ነኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ራሱ አዋጁ ላይም ጥያቄ የሚያነሱ አሉ፡፡ እርስዎ አዋጁን የማውጣት ሒደት ውስጥ ባይሳተፉም ምክክሩ ግን ሁሉንም የሚያካትት መሆን አለበት፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን፡- እዚህ ላይ ምንም የምለው ነገር የለኝም፡፡ በእርግጥ 87 ብሔረሰቦችን የሚወክሉ 87 ኮሚሽነሮች ሊኖሩ እንደማይችሉ ይገባኛል፡፡ የተለያዩ የኅብረሰብ ክፍሎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች ቢበዙ ደስ ይለኛል፡፡ የተለያዩ ብሔረሰቦች፣ አካል ጉዳተኞች፣ የአዕምሮ ጉዳተኞች፣ አርብቶና አርሶ አደሮች እዚህ ቢወከሉ ደስ ይለኛል፡፡ መቼም ኢትዮጵያ ሁላችንንም ትመለከተናለችና ሁሉም ቢገቡ ደስ ይለኛል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን እነዚህ የኅብረሰተብ ክፍሎች መሳተፋቸው አይቀሬ ነው፡፡ ይኼ አንድ ነገር ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በኮሚሽኑና በጽሕፈት ቤቱ እንሳተፍ የሚሉትም ተገቢ ነው፡፡ እንደ አስፈላጊነቱ ቅርንጫፍ በየክልሉ ይኖረናል፣ ወረዳና ዞን ድረስ እንሄዳለን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ 1,047 ገደማ ወረዳዎች አሉ፡፡ ከእዚህ ውስጥ 52 የሚሆኑት ይመስለኛል ትግራይ ክልል ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ ምናልባት ትግራይ ውስጥም ሆነ ሌሎች ችግር ያለባቸው አካባቢዎች በእግዚአብሔር ዕርዳታ ችግራቸው ቢቀረፍ 1,047 ወረዳዎች ይሳተፋሉ፡፡ ከወረዳም በታች ወርደን እንሄዳለን፡፡ በዚህ ሁሉ ሒደት ውስጥ ተዋንያን የሚሆኑት ሚሊዮኖች ናቸው፡፡ ስለዚህ ማንም የሚቀር የለም፡፡ ሁልጊዜ የምለው፣ ‹‹ይኼ ነገር አልገባንም ትክክል አይደለም›› የሚሉት ተጨባጭ የሆነ ማስረጃ ካመጡ፣ እዚህ ምንም የተለየ አጀንዳ የለንም፡፡ አጀንዳችን አገር ነውና ተተክቶ የሚሠራ ሰው ካለና አዋጁ የሚደግፈው ከሆነ እኛም የሰየመን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ጉዳዩን በድጋሚ የሚያጤነው ከሆነ፣ እዚህ ውስጥ ምንም የምንለው ነገር የለም፡፡ እኛ ቢያንስ እኔ የምለው ነገር ፍላጎቱ ካለ ከእነሱ ጋር ለመሥራት ዝግጁ ነን፡፡

ወደፊት ደረጃ በደረጃ የትውውቅና የሥራ ሒደቶቻችንን የማስተዋወቅ ሒደት ላይ ነን ያለነው፡፡ ከሚዲያ ባለሙያዎች ጋር ተገናኝተናል፡፡ ቀስ በቀስ ደግሞ ከሌሎችም ተቋማት፣ ከሲቪል ማኅበረሰቦች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከማኅበራዊ አንቂዎች፣ ከሐሳብ አፍላቂዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች ጋር ተገንኝተን የአጋርነት ሒደታችንን እንወያያለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከኢትዮጵያ አስቀድመው ብሔራዊ ምክክር ያደረጉ አገሮች ሒደቱን በተለያየ መንገድ አካሂደውታል፡፡ አንዳንዶቹ አገሪቱን ይዘውራሉ ባሏቸው ልሂቃን መካከል ውይይት ሲያደርጉ፣ ሌሎች ደግሞ ውይይቱን ሕዝቡ ጋ አውርደውት እንዲነጋገርበት አድርገዋል፡፡ ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊያደርግ ያሰበው አገራዊ ምክክር ምን ዓይነት ቅርፅ ይይዛል?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- ወደፊት እየረቀቀ የሚሄድ ቢሆንም፣ የእኛ ከእነዚህ ሁሉ አገሮች ልምዶችን ወስዶ፣ በጣም የተለየና ከተሳካልን ተምሳሌታዊ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ በሌሎች አገሮች ብዙውን ጊዜ ከላይ ወደ ታች የሚደረግ ነው፡፡ የእኛ ከታች ወደ ላይ ነው የሚሆነው፡፡ አንደኛ አጀንዳው የሚመጣው ከታች ነው፡፡ አጀንዳው ከላይ ተቀርፆ በዚህ ጉዳይ ላይ ተወያዩ አይባልም፡፡ የኢሕአዴግም ሆነ የቀደመው መንግሥት ሕገ መንግሥቶች ሲረቁ አስታውሳለሁ፡፡ ሕገ መንግሥቱን አርቅቀው ወደ እኛ አመጡት፣ በየቀበሌው ተሰብስበን ተወያዩ ስንባል ሐሳብ ሰጠን፡፡ የእኛ ሐሳብ ግን ከዚያው ውይይት አላለፈም፡፡ መጨረሻ ላይ ፀደቀ፡፡ ኋላ ላይ ግን የራሱን ችግሮች አመጣ፡፡ ይኼ ግን አጀንዳው በራሱ ከታች ነው የሚመጣው፡፡ ኅብረተሰቡን ‹‹የቅድሚያ ቅድሚያ የምትሰጣቸው፣ መግባባት ላይ መድረስ የምትፈልግባቸው አጀንዳዎች ምን ምንድናቸው?›› ተብሎ ይጠየቃል፡፡ በዚህ መሠረት ተደራሽነቱ በጣም ሰፊ ነው የሚሆነው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ብዝኃነት በጣም የበዛባት አገር ነች፡፡ ብዙ ሃይማኖቶች አሉን፡፡ ብዙ የሚያምሩ ብሔረሰቦችም አሏት፡፡ 70 በመቶ የወጣቶች አገር ናት፡፡ 52 በመቶ ሴቶች ናቸው፡፡ እንደ ሌላው አገር ፋብሪካ የተስፋፋበት አይደለችም፡፡ አርብቶና አርሶ አደር ይበዛታል፡፡ እነዚህን ባገናዘበ ከታች ወደ ላይ ተቀርፆ የሚመጣው አጀንዳ የሚሳካ ከሆነ፣ ወደፊት ብዙ የሚያወያይና በተምሳሌትነት የሚወሰድ ነው የሚሆነው፡፡ የተለየ የሚያደርገው ይኼ ነው፡፡

ነገር ግን ብዙ ተግዳሮቶች ይኖሩታል፡፡ አልፎ አልፎ ያሉ ግጭቶችና የሰላሙ አለመርገብ ራሱን የቻለ ችግር ነው፡፡ በአገራችን ሰፊው ሕዝባችን 120 ሚሊዮን መሆኑ፣ የበጀትና የመሳሰለው ላይ ያለን አቅም ሁሉ በተግዳሮትነት ልንወስዳቸው የምንችላቸው ናቸው፡፡ አሁን ያለንበት ሁኔታ ረሃቡ፣ ችግሩ፣ መከፋታችን፣ መሰደዳችን፣ መፈናቀላችን፣ የተለያዩ ትርክቶች መኖራቸው፣ በተለያዩ ቦታዎች ተጀምረው መፍትሔ ያላገኙ የማንነት፣ የወሰን፣ ራስን በራስ የማስተዳደርና ሌሎች ተዳፍነው የነበሩና እንደ ቋያ የተቀጣጠሉ ነገሮች የውይይት ሒደቱ ላይ ተግዳሮት ሊሆኑ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ እነዚህን እንዴት እንፍታ የሚለውን በሒደት ጥናት ላይ ተመርኩዘን እንወጣቸዋለን የሚል ሐሳብ አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ውይይቱ ከመደረጉ በፊት አጀንዳዎቹ በራሱ ከሕዝቡ እንደሚሰበሰቡ ተገልጿል፡፡ እነዚህ አጀንዳዎች ከተሰበሰቡ በኋላ በምን ዓይነት ሁኔታ ነው ቅድሚያ የሚሰጣቸውና የሚለዩት?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- ቅድሚያ የመስጠቱ ሥራ የሚከናወነው የተሰበሰበውን አጀንዳ ካየነው በኋላ ነው፡፡ ቅድሚያ የሚሰጠው የሰላም ጉዳይ ነው ከተባለ በሰላም ዙሪያ የመጡ አጀንዳዎች ቅድሚያ ይሰጣቸዋል፡፡ ቅድሚያው የልማት ነው ከተባለም የልማት አጀንዳዎች በውይይቱ ላይ ቅድሚያ ያገኛሉ፡፡ ነገር ግን ዝም ብሎ መገመት እንዳይሆንብኝ እንጂ፣ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡት በሰላም ዙሪያ ያሉት አጀንዳዎች ይመስሉኛል፡፡ እነሱ ናቸው አገርን ለመቀጠልም ሆነ ለማደናቀፍ ጉልበት ያላቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ይኼ ኮሚሽን ኃላፊነቱ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት የማዘጋጀትና የማሳለጥ መሆኑን እርስዎም በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ጠመንጃ ያነገቱ አካላት ወደ ውይይቱ እንዲመጡ፣ ተሳትፈውም ሐሳባቸውን እንዲገልጹ ሳይደረግ ምክክሩና የኮሚሽኑ ሥራ የተሳካ ይሆናል ብለው ያስባሉ? ይኼንንስ እንደ ትልቅ ተግዳሮት አይቆጥሩትም?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- የዚህ ኮሚሽን ሥራ የውይይት መድረክን መፍጠር ነው፡፡ ስለዚህ ማንኛውም አካል ግለሰብም ሆነ ቡድን ወደ እዚህ ውይይት መምጣት እፈልጋለሁ ብሎ በሚመጣበት ጊዜ አንከለክልም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት የሚባል አለ በአገራችን፡፡ መንግሥት እኛን ሲያቋቁመን አካታች ሁኑ፣ አታግሉ፣ ሥራችሁን በትክክል ፈጽሙ፣ ለዚህ አጋዥና አጋር ነኝ ብሎ አዋጅ ሰጥቶናል፡፡ አዋጃችንን ነው የምንከተለው፡፡ ስለዚህ ለውይይት ወደ እኛ የሚመጣ ማንኛውም አካል የመቀበል ኃላፊነትና ግዴታ አለብን፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ወደ ውይይት የሚመጣው ምን ዓይነት ሰው ነው? ሁልጊዜ ውይይት ማለት ወደ መግባባት እንደርሳለን የሚሉ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች የሚገናኙበትና በአወያያቸው ውይይት የሚያካሂዱበት መድረክ ማለት ነው፡፡ እኔና አንተ እንወያይ ስንባባል ሽጉጤን ይዤ እመጣለሁ ብልህ አንተም ይዤ እመጣለሁ ብለህ ጠረጴዛ ላይ ሽጉጥ አድርገን የምንነጋገር ከሆነ ውይይት አይባልም፡፡ መጀመሪያውኑ ለሰላም የተዘጋጀ ውይይት አይደለም ማለት ነው፡፡ ነገር ግን እኔ ሽጉጥ አያስፈልገኝም፣ የውይይቴ አላማም ሽጉጥ አያስፈልግም የሚል ነው ብለህ የምትመጣ ከሆነ እኔም ሽጉጥ አይኖረኝም፡፡ አወያያችንም ‹‹ተወያይተው አንድ ነገር ላይ ለመድረስ ለሰላም ነው የመጡት›› የሚል እርግጠኝነት ይኖረዋል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ከሆነ ይኼ ኮሚሽን የመቀበል ኃላፊነት አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- መሣሪያ ያነገቡት በራሳቸው ሳይመጡ ሌሎች ተወያይተው ጨርሰው፣ ብሔራዊ ምክክሩ ተጠናቀቀ ከተባለ ሁሉም አካል ሳይካተትበት አገራዊ ሁሉን አቀፍ ውይይት ነው ማለት ይቻላል?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- ለውይይት ዋናው ቅድመ ሁኔታ የውይይትን ጽንሰ ሐሳብ በሚገባ ተረድቶ ሰላማዊና ውይይት ማዘጋጀት ነው፡፡ እነዚህ ካሉና ዓለማው ግልፅ ከሆነ ሲመጡ መጀመሪያውኑ ለሰላም መጥተዋል ማለት ነው፡፡ መጀመሪያውኑ ‹‹እኔ አልወያይም›› የሚል ካለ ወደ ውይይቱ አልመጣም ማለት ነው፡፡ አሁን ባነሳኸው ጉዳይ ላይ ተስፋ የምናደርገው ከደቡብ እስከ ምሥራቅ፣ ሰሜንና ደቡብ ያሉት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንና ሕዝቦቻችን ጦርነት ሰልችቷቸዋል፣ ሰላም ይፈልጋሉ የሚለውን ነው፡፡ ችግሩ ሰላም እንዴት ይመጣል የሚለውን አላወቁትም ወይም አውቀውት እንዴት እንደሚገቡበት አልገባቸውም፡፡ ላለፉት 40 እና 50 ዓመታት ተዋግተን ምንም ያተረፍነው ነገር የለም፡፡ ስለዚህ እንወያይ፡፡ አንተ ያነሳኸውን ጉዳይ ላይ ሊያግዙ የሚችሉ የተለያዩ ተቋማት አሉ፡፡ የሃይማኖት ተቋማት፣ የአገር ሽግሌዎች ምን ይሠራሉ? ያደራድራሉ፣ ያስታርቃሉ፡፡ ተደራድሮና ታርቆ ወደ ውይይት መምጣት ይቻላል፡፡ እኔና አንተ ተጣልተን ሽማግሌዎች መጥተው አንተም ተው፣ አንተም ተው ብለው ያስታርቁናል፡፡ ዕርቃችን ግን ዕድሜ ላይኖረው ይችላል፡፡ ምክንያቱም መሠረታዊ ችግሩን ተወያይተን በመግባባት አልፈታነውም፡፡ ስለዚህ የታረቅነው በተፅዕኖ ነው ማለት ነው፡፡ አገራችን ውስጥ እንዲህ ዓይነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዕርቆች ተካሂደዋል፡፡ በየቦታው ለሚፈነዱ ፀቦች በሬ ይታረዳል፣ ዱአ ወይም ፀሎት ተደርጎ ይለያያሉ፡፡ ከአንድና ሁለት ወር በኋላ ሌላ ችግር ፈንድቶ ታገኛለህ፡፡ የውይይት ዓላማው እነዚህ በየጊዜው የሚፈነዱ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ ዋነኛው ሥራ ሁሉም ተዋንያን ወደ መድረኩ እንዲመጡ ማድረግ ነው፡፡ ለዚህ ነው ወደ ሕዝብ የሚኬደውና ለሕዝብ ቅድሚያ የተሰጠው፡፡ እኛ አሁን እያነጋገርን ያለነው የሲቪል ማኅበረሰቦችን ነው፡፡ ብልፅግናን ወይም ሌሎቹን ፓርቲዎች አላነጋገርንም፡፡ እነዚህ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ናቸው ታች ድረስ ወርደው ከኅብረተሰቡ ጋር ያሉት፡፡ ይኼ ይኼ ስላለ አሁን ያነሳኸውን ጉዳይ ይኼ ነው ብሎ አሁን ላይ መገመት ይከብደኛል፡፡ ማለት የምችለውም እዚህ ድረስ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ብሔራዊ ምክከር ያደረጉ ብዙ አገሮች እዚህ ሒደት ውስጥ የገቡት በድኅረ ጦርነት ወይም ግጭት ጊዜ ትልልቅ ጉዳዮች መቋጫ ካገኙ በኋላ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ከዚህ የተለየ ነው፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ያልተጠናቀቀ ጦርነት አለ፡፡ ኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ውስጥ እስካሁን ግጭቶች አሉ፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ባሉበት ምክክር ማካሄድ ይቻላል? በታጣቀዊዎች ቁጥጥር ሥር ባሉ ቦታዎች ላይስ እንዴት ተንቀሳቅሳችሁ ውይይት ልታደርጉ ነው?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- መሀል አገር ያለን ሰዎች በየቦታው እየሄድን እናወያያለን ማለት አይደለም አናወያይም፡፡ እኛ ሥራችን ሕጉን ቀርፀን ታች ያለው ኅብረተሰብ ድረስ እንዲደርስ ማድረግ ነው፡፡ አዋጁ ጉልበት ሰጥቶናል፡፡ በአዋጅ መሠረት ደንብ እንዲረቅ ሁኔታዎችን ታመቻቻላችሁ፣ እሱን አዋጁን አንጥራችሁ ደግሞ ወደ ውሳኔ እንዲኬድ ወደ ውይይት የምትመልሱት እናንተ ናችሁ ተብለናል፡፡ ስለዚህ ኃላፊነት አለብን፡፡ ከዚያ በኋላ የውሳኔ ሐሳቡ መተግበሩን የመከታተል ኃላፊነትም ተሰጥቶናል፡፡ ሰላም በደፈረሰባቸው አካባቢዎች የሚሠሩ ሥራዎች አሉ፡፡ የደፈረሰው ሰላም እንዴት ጋብ ሊል ይችላል? እንዴት ሁላችንም ወደ ውይይት ልንመጣ እንችላለን? በመጀመሪያ የውይይትን ጽንሰ ሐሳብ ወደ ታች እናሰርጻለን፡፡ እኛ ወሰን ልናካልል አይደለም፣ አንተ ይኼ ነህ ይኼ አይደለህም ለማለትም አይደለም፡፡ አንተ ራስህ ይኼ ነኝ ወይም ይኼንን እንዳልሆን እነዚህ ነገሮች እንቅፋት ሆነውበኛልና ልወያይባቸው ብለህ፣ ራስህ ተወያይተህ ወደ መፍትሔ የምታመጣባቸው ብለን እንናገራለን፡፡ ለዚህ ነው አዋጁም ለሕዝብ ቅድሚያ የሰጠው፡፡ ሕዝብ የሚለው ነገር በማኅበራዊ አንቂዎች፣ በፖለቲካ መሪዎች፣ ጉልበትና አንደበት ባላቸው የተወሰነ ተፅዕኖ አይደርስበትም እያልኩ ግን አይደለም፡፡ ለዚህ ነው ብዙ ሥራ ይጠይቃል የምንለው፡፡ ዞሮ ዞሮ ልናገር የምፈልገው ሰላም አስፈላጊ መሆኑን ነው፡፡ ሰላም የደፈረሰበት አካባቢ ሄደህ ና ላወያይህ ብትለው በመጀመሪያ በአካባቢው ጦርነት መቆሙን፣ በአካባቢው መሠረታዊ ነገሮችን ማግኘቱን ሊፈልገው ይችላል፡፡ እነዚህ ሥራዎች ግን በሌሎች ተቋማት እየተሠሩ ነው፡፡ በሚገባ ይሠራሉ፣ ውጤታማም ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ ድርድሩ፣ ዕርቅ መፈጸሙና መግባባቱ ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር ተቀራራቢነት ያላቸው ሥራዎችን ለመሥራት በመንግሥት የተቋቋሙ ሁለት ሁለት ኮሚሽኖች ነበሩ፡፡ እንደ ማይንድ ኢትዮጵያ ያሉ ብሔራዊ ምክክር ለማድረግ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ ተቋማትም አሉ፡፡ የእነዚህን ተቋማት መዛግብትና ሰዎች ለኮሚሽኑ ሥራ እንዴት ግብዓት ይሆናሉ?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ውስጥ ኮሚሽነር ነበርኩ፡፡ የኮሚሽኑ ሪፖርት አሁን ለሕዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ይቀርባል፡፡ ከቀረበ በኋላ ሪፖርቱን እንጠቀምበታለን፡፡ ከማይንድ ኢትዮጵያ ጋር አሁንም የጀመርናቸው ሥራዎች አሉ፡፡ በቅርቡ መጥተው አንዳንድ ነገሮችን አቅርበውልናል፡፡ በዚህ ዙሪያ የሠሩ ተቋማት፣ ወጣቶች፣ ፍላጎቱና ቅንነቱ ያላቸው ካሉ እናሳትፋለን፡፡ ይኼንን ሥራ እኛ ብቻችንን የምንሠራው አይደለም፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ...

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ...

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19...

‹‹የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ መፍቀድ ከፍተኛ ጥቅም አለው›› ቆስጠንጢኖስ በርሃ (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ ከእነዚህ የውይይት መድረኮች መካከል ከከፍተኛ የግብር ከፋዮች ወይም ታማኝ ግብር ከፋዮች...