Saturday, April 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማኅበር በወቅታዊ የኢኮኖሚ ቀውሶች ዙሪያ ያደረገው ጥናትና ግኝቶቹ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ወቅታዊ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ዘርፈ ብዙ ሆነዋል፡፡ በተለይ የዋጋ ንረቱ አሳሳቢ ከሚባል ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ለዚህ ችግር መፍትሔ ለመስጠት በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም፣ እስካሁን ይኼ ነው የሚባል መፍትሔ አልመጣም፡፡ ችግሩ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችን ጭምር እየፈተነ ነው፡፡ ሰሞኑን የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማኅበር በወቅታዊ አገራዊ ኢኮኖሚ ላይ ያጠናውን ጥናት መሠረት በማድረግ የሰጠው መግለጫም ለኢኮኖሚያዊ ችግሮቹ መፍትሔ ለማበጀት የተደረጉ ጥረቶችና የተወሰዱ ዕርጃዎች እስካሁን ይኼ ነው የሚባል መፍትሔ ያለማምጣታቸውን የሚያመለክት ነው፡፡  

የማኅበሩ የምርምርና የፖሊሲ ጥናት ዳይሬክተር ደግዬ ጎሹ (ዶ/ር) እንደገለጹትም፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የገጠመውን ወቅታዊ ችግር ለመፍታት ያስችላሉ የተባሉ በርካታ ጥናቶች ቢካሄዱም ሁነኛ መፍትሔ አልተገኘም፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ማኅበሩ ጨምሮ መንግሥትና ሌሎች በርካታ አካላት ለችግሩ መፍትሔ ለማምጣት ብዙ ጥረት ሲያደረጉ ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን እስካሁን የተደረጉ ጥረቶች ለችግሩ መፍትሔ ማምጣት አልቻሉም፡፡ በመሆኑም ጠቅለል ባለ መንገድ መሠረታዊ ችግሩን ተረድቶ፣ ሁሉን አቀፍ ጥናት በማካሄድ፣ የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጥ ለነገ የማይባል አንገብጋቢ ጉዳይ እንደሆነ አመልክተዋል።

ባለፉት ጊዜያት የተካሄዱት በርካታ ጥናቶች ሙሉ በሙሉ ችግሩን ለመቅረፍ ስላልቻሉ የተሟላ ጥናት እንዲካሄድ በተወሰነው መሠረት ማኅበሩ ያጠናውን ጥናት ይፋ አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ችግሮች በሆኑት የዋጋ ግሽበትና የፖሊሲ አማራጮች ላይ ባለፉት ስድስት ወራት ሰፊ ሽፋን የሰጠ ጥናት ማኅበሩ እንዳካሄደ ተገልጿል፡፡

በማኅበሩ የተደረገው ጥናት ባለፈው ረቡዕ በተካሄደ መድረክ ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ በዕለቱ የቀረበው ሙሉ ጥናቱ ባይሆንም ኢኮኖሚው የገጠመው ምንድነው? የሚለውንና እስካሁን በተበጣጠሰ መልኩ ይቀርብ የነበረውን በተሟላ መልኩ ለማቅረብ ዕድል የሰጠ ነበር፡፡ ለችግሩ መንስዔ የሆኑ ተጠርጣሪ ናቸው የተባሉ ምክንያቶችን በሙሉ በዚህ ጥናት በመለየትና በመተንተን የቀረበ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህም መነሻነት ‹ወሳኙ ጉዳይ የት ጋር ነው ያለው› በማለት የመፍትሔ ሐሳብ የቀረበበት፣ ይህ የማኅበሩ ጥናት መሠረታዊ የተባሉ ችግሮች ላይ ሰፊ ትንታኔን የሰጠ ነበር። በዚህ ጥናት ከ40 የሚበልጡ የዋጋ ግሽበትና ሌሎች ችግሮችን በመለየት ስድስት ዋና ዋና ጉዳዮች በትኩረት ሊሠራባቸው ይገባል ተብሏል፡፡፡ ማኅበሩ በዚህ ጥናት በተለይ የዋጋ ንረትን በተመለከተ የሰጣቸውን ትንታኔዎችና እንደ መፍትሔ ካስቀመጣቸውን አንኳር አንኳር ጉዳዮች ውስጥ የተወሰኑትን እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል፡፡   

አቅርቦት 

ማኅበሩ ለወራት ባደረገው ጥልቅ ጥናት ለወቅታዊ የዋጋ ንረት ዋነኛ ምክንያት ናቸው ብሎ በቀዳሚነት ያስቀመጠው በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ያለው ሰፊ ክፍተት ነው፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከምርት አንፃር በአቅርቦት እየተሰቃየ ነው፤›› ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በተለይ የእህል አቅርቦት እየቀነሰ መምጣቱ ወቅታዊውን የዋጋ ንረት ሊያብሰው ችሏል፡፡ የእህል አቅርቦት ለረዥም ጊዜ እየጨመረ እንደነበር መረጃዎች የሚያሳዩ ቢሆንም፣ እ.ኤ.አ. ከ2011 በኋላ ግን የእህልና የሌሎች የግብርና ምርቶች አቅርቦት የመቀነስና የመኮማተር አዝማሚያ ማሳየቱ ለዋጋ ንረቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው ጥናቱ አሳይቷል ተብሏል፡፡ 

እንደ እህል አቅርቦቱ መኮማተር ሁሉ፣ በኢንዱስትሪ ዘርፍም ተመሳሳይ ችግር መታየቱ ኢኮኖሚው ላይ ጫና ከመፍጠር በላይ የዋጋ ንረቱን ከፍ እንዲል አስተዋጽኦ አድርጓል ተብሏል፡፡ የኢንዱስትሪ ዘርፉ እ.ኤ.አ. እስከ 2004 ድረስ ብዙ ትኩረት የተሰጠው እንዳልነበር ያስታወሱት ዶ/ር ደግዬ፣ ከ2010 ዓ.ም. በኋላ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ከዝቅተኛ መጠን ጀምሮ ዕድገት እየታየበት መምጣቱንም አክለዋል፡፡ 

ይህም እ.ኤ.አ. እስከ 2018 ድረስ ዓመታዊ የምርት መጠኑ እየዋዠቀም፣ ቢሆንም ዕድገት ነበረው፡፡ ከዚያ በኋላ ግን አስገራሚ በሆነ ሁኔታ ወደ አደገኛ ቁልቁለት መውረዱን አሶሴሽኑ ባደረገው ጥናት ማወቅ መቻሉን አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም የኢንዱስትሪ ምርቶች በከፍተኛ ሁኔታ ዋጋቸው ቢጨምር አስገራሚ አለመሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ደግዬ፣ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ባልተጠበቀ ሁኔታ ማዘቅዘቅ አጠቃላይ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ መዋቅር እንዲለዋወጥ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አወቃቀር ዋና ዋና ዘርፎች የሚባሉት ግብርና፣ አገልግሎትና ኢንዱስትሪ ዘርፎች ሲሆኑ፣ የእነዚህ ዘርፎች ኢኮኖሚዊ ድርሻ ተለዋውጦ፣ በአሁኑ ጊዜ የአገልግሎት ዘርፉ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ መሪ መሆኑ ለችግሩ በማስረጃነት ቀርቧል፡፡  

እ.ኤ.አ. ከ2001 እስከ 2011 ድረስ ግብርናና አገልግሎት ዘርፉ ቅድሚያ ለመውሰድ ከፍተኛ ፉክክር ውስጥ እንደነበሩ የገለጹት ዶ/ር ደግዬ፣ መጨረሻ ላይ ግን የአገልግሎት ዘርፉ በ2014 ዓ.ም. ኢኮኖሚውን መምራት እንደጀመረ ገልጸዋል፡፡

ወቅታዊው መረጃ የሚያሳየውም ከጠቅላላ የአገሪቱ ኢኮኖሚ 55 በመቶ የሚሆነው የአገልግሎት ዘርፍ ድርሻ እንደሆነና ይህም የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ደረጃ መውረድ የዋጋ ንረቱን አብሶታል የሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ያስችልላል ብለዋል፡፡ 

‹‹የአገልግሎት ዘርፉ ማደግ ፍላጎትን ይፈጥራል እንጂ አቅርቦትን አያመጣም፣ በዚህ ላይ ደግሞ የኢንዱስትሪ ዘርፉ መዳከም ሲታከልበት ለዋጋ ንረት ምክንያት ነው እንላለን፤›› በማለት የጥናታቸውን ውጤት ገልጸዋል፡፡ 

ግብርና በዋናነት ዋጋን ለማረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የነበረው ቢሆንም፣ አሁን ላይ የግብርና ምርት በነፍስ ወከፍ ሲለካ በፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ በመምጣቱ በሚፈለገው ደረጃ ዋጋን ሊያረጋጋ አለማስቻሉን የማኅበሩ ትንታኔ አመላክቷል፡፡ 

‹‹የግብርና ዘርፉ እየተኮማተረ የአገልግሎት ዘርፉ እየሠፋ በመሄዱ ኢኮኖሚው በአገልግሎት ዘርፍ እየተመራ ነው ማለት ነው፤›› የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ አሁን ላይ ያለውን ዋጋ ለመቆጣጠር የሚያስችል ኢኮኖሚያዊ መሣሪያ የለም የሚል መደምደሚያ ላይ ስለመድረሱ ገልጸዋል፡፡

ኢምፖርት

 

ሌላው ለዋጋ ንረት የተጠቀሰው ከውጭ የሚገባ ምርት (ኢምፖርት) ነው፡፡ ይህ ዘርፍ ለዋጋ ንረቱ መባባስ ያለው ድርሻ ሲታይ፣ የአገር ውስጥ ፍላጎቱን የመጠነ የገቢ ምርት ባለመኖሩ የዋጋ ንረቱን አባብሶታል፡፡ ‹‹ከውጭ የሚጣው ምርት ፍላጎት በጣም ከፍተኛ ስለሆነ እ.ኤ.አ. እስከ 2016 ድረስ የኢትዮጵያ መንግሥት ፍላጎቱን ለማሟላት በከፍተኛ ሁኔታ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፤›› ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በተለይ እ.ኤ.አ. ከ2018 በኋላ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የገቢ ምርት ፍላጎት መጠን ምንም ይሁን ምንም ማሟላት የማይቻልበት ደረጃ መደረሱን ጠቁመዋል፡፡ 

በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ ከኢኮኖሚያዊ አንፃር ከአፍሪካ ዝቅተኛ የገቢ ንግድ ካላቸው አገሮች አንዷ እንደሆነች ጠቅሰው፣ የውጭ ምርት ፍላጎትና አቅርቦት የተጣጣመ ባለመሆኑ የገባው ምርት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ቢጨምር አስገራሚ መሆን እንደሌለበትም አመልክተዋል፡፡ 

የውጭ ምንዛሪና ዲቫሉዌሽን 

ለወቅታዊው የዋጋ ንረት የውጭ ምንዛሪና ዱቫሉዌሽን (የብር የመግዛት አቅም እንዲቀንስ ማድረግ) የራሳቸው አስተዋጽኦ እንደነበራቸው የማኅበሩ ጥናት አመላክቷል፡፡ በዚህ ረገድ ጥናቱ የ60 ዓመታት ጉዞን በመፈተሽ ችግሩን መለየት መቻሉን ይጠቅሳል፡፡

በየጊዜው የሚደረገው ዱቫሉዌሽን ለዋጋ ንረት ቀጥተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው ያብራሩት ዶ/ር ደግዬ፣ በተለይ እ.ኤ.አ. በ2018 የአንድ ዶላር የምንዛሪ ዋጋ 20 ብር እንዲሆን ከተደረገ በኋላ የዋጋ ንረቱን እንዳባባሰው ገልጸዋል፡፡ እንዲህ ያለው አካሄድም የውጭ ምንዛሪ ክምችት ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩንም ጠቁመዋል፡፡ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከፍተኛ ደረጃ የደረሰው እ.ኤ.አ. በ2004 ላይ እንደነበር የገለጹት ዶ/ር ደግዬ፣ በዚያን ወቅት የወጪ ንግዱ ኢኮኖሚያዊ ድርሻው 16 በመቶ ደርሶ እንደነበር አመልክተዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2020 ላይ የወጪ ምርቱ ለኢኮኖሚያ ዕድገቱ የነበረው አበርክቶ አሽቆልቁሎ ሦስት በመቶ ብቻ እንደነበር፣ ይህም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ችግር ዘርፈ ብዙ እንዲሆን ማድረጉን ገልጸዋል። የውጭ ምንዛሪ ክምችቱ አሁን ምን ላይ እንደደረሰ የሚያውቀው መንግሥት ብቻ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ችግሩ ግን በጣም የከፋ እንደሆነ መረዳት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡ ይህ ችግር ካልተፈታ ደግሞ የሚፈለጉትን ብቻ ሳይሆን በጣም ወሳኝ የሆኑና ኢኮኖሚውን ሊደግፉ የሚችሉ አስፈላጊ የሆኑ ምርቶችን እንኳን ለማስገባት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ሊያደርስ ይችላል የሚል ሥጋታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡

ታሪፍና ዋጋ 

የማኅበሩ ጥናት ለወቅታዊው የዋጋ ንረት እንደ ምክንያት ያቀረበው ሌላው ግኝት ደግሞ ከውጭ በሚገቡ (ኢምፖርት) ሸቀጦች ላይ የሚጣሉ ታሪፎች ከፍተኛ መሆንን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ታሪፍ ከሚያስከፍሉ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ አንዷ መሆኗን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ በኢትዮጵያ በአማካይ ከ12 በመቶ በላይ ታሪፍ በገቢ ምርቶች ላይ እንደሚከፈል ጠቁመዋል። ስለዚህ ከውጭ የሚገባ ሸቀጥ በሙሉ ገና አገር ውስጥ ከመግባቱ በፊት በታሪፍ ምክንያት ዋጋው በ12 በመቶ ይጨምራል፡፡ ይህ ከሌሎች ክፍያዎች ጋር ተደማምሮ የዋጋ ንረቱን እንዳባባሰው ማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ 

የዋጋ ንረትና የአገር ውስጥ ግጭት 

በኢትዮጵያ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚከሰቱት ግጭቶች አሁን ለተከሰተው የዋጋ ንረት አስተዋጽኦ እንደነበር የማኅበሩ ጥናት አመላክቷል፡፡ ዶ/ር ደግዬ፣ ‹‹እንደ እኛ ባለ ሰፊ ብዝኃነት ባለበት አገር ግጭት ይጠበቃል፡፡ ግን ባለፉት 20 እና 30 ዓመታት በነበሩ ግጭቶች መረጃ የሚያሳየው በዋጋ ንረት ላይ ያን ያህል ተፅዕኖ አያስከትሉም ነበር፤›› ይላሉ፡፡ 

ግጭት የተለመደ ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ የነበሩት ግጭቶች ይዘትና ደረጃ የተነሳ ዋጋ ላይ ብዙ ለውጥ ሳያመጡ ያልፉ እንደነበር ገልጸዋል።

እ.ኤ.አ. ከ2015 ጀምሮ ከፍተኛ የሆኑ ግጭቶች በኢትዮጵያ በስፋት መከሰታቸው ለዋጋ ንረት መባባስ ምክንያት ወደ መሆን መሸጋገራቸውን ጥናታቸው አሳይቷል፡፡ ጥናቱ እንዳመለከተውም፣ በ2021 ብቻ 1,129 ፖለቲካ ነክ ግጭቶች ተከስተዋል። ንፁኃን ዜጎችን ዒላማ ያደረጉ ወደ 424 ግጭቶች ደግሞ በአንድ ዓመት ብቻ መከሰታቸውን ያመለከተው ጥናቱ፣ በከፍተኛ መጠን የቀጠለው ግጭት ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እየመጣ እንደሆነ አመልክቷል፡፡ የግጭቶቹ መብዛት በቀጥታ ከዋጋ ንረቱ ጋር የሚያያዝበት ዋናው ምክንያት ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሁሉ የማምረቻ ቦታንና ምርትን መጉዳቱ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ምርት በአገር ውስጥ እንዳይሠራጭ ማድረጉን ይህም የምርት አቅርቦትን በማስተጓጎል የዋጋ ንረትን እንደፈጠረ ይገልጻል፡፡ የተከሰቱት ግጭቶች ያስከተሉት መጠነኛ የዋጋ ጭማሪን ሳይሆን፣ ዋጋ ንረት በአንዴ እንዲገነፍል ማድረጋቸው ተመልክቷል፡፡ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥም የዋጋ ዕድገት አስገራሚ በሚባል ደረጃ እንዲጨምር ምክንያት ከሆኑት አንዱ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ 

ከ100 እስከ 150 የሚደርሱ ግጭቶች በዓመት ውስጥ ተከስቶ በነበረበት ሰዓት ያን ያህል የዋጋ ንረት አለማስከተላቸውን የሚገልጸው የማኅበሩ ትንታኔ፣ አሁን ላይ ያለው የግጭቶችና የዋጋ ንረት ትስስር ከዚህ ከፍ የሚል የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በአጠቃላይ እንደሚያናጋ አስምሮበታል፡፡ 

የነፍስ ወከፍ ገቢ ዕድገት

አሶሴሽኑ የኢትዮጵያ የነፍስ ወከፍ ገቢ ዕድገት ለወቅታው የዋጋ ንረት ምክንያት ናቸው ብሎ ከጠቀሳቸው ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ‹‹የግለሰቦች ገቢና ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል፤›› ያሉት ዶ/ር ደግዬ፣ ይህ ዋጋ እንዲጨምር ማድረጉ ግልጽ ነው፡፡ መንግሥትም በተደጋጋሚ የዋጋ ንረቱን ያመጣው የኢኮኖሚ ዕድገት ነው ብሎ መግለጹም ስህተት እንዳልሆነ የገለጹት ዶ/ር ደግዬ፣ ነገር ግን የዚህ አስተዋጽኦ ምን ያህል ነው የሚለው መለየት ይኖርበታል፡፡ በተለይ እ.ኤ.አ. ከ2018 በኋላ የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ በማደጉ ለዋጋ ንረቱ አስተዋጽኦ ማድረጉን፣ ይህ ማለት ግን ጥቅል ችግሩ የመጣው የነፍስ ወከፍ ገቢ በመጨመሩ ብቻ አለመሆኑ ግንዛቤ መውሰድ አለበት ብለዋል፡፡ 

የወጪ ንግድ 

በማኅበሩ ጥናት የወጪ ንግድ አፈጻጸም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አንድ ችግር ሆኖ ቀርቧል፡፡ ‹‹የወጪ ንግድ ገቢ ማደግና መቀነስ የሚለካው ከምጣኔ ሀብቱ መጠን ተነፃፅሮ ነው፡፡ ብቻውን ተወስዶ እያደገ ነው ቢባል ትርጉም የለውም፤›› ተብሏል፡፡ ከጠቅላላ የኢትዮጵያ የምርት ዕድገት አንፃር የወጪ ንግድ ድርሻ በ2011 ወደ 17 በመቶ እንደነበር የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ይህ የወጪ ንግድ ድርሻ አሁን ላይ ወርዶ በ2020 ከሰባት በመቶ በታች መሆኑ፣ በዚህም ዘርፍ ቁልቁል እየተሄደ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ስለዚህ ኤክስፖርት የማድረግ ችሎታችን በጣም እየወረደ መምጣቱ ኢኮኖሚው ላይ ጫና እንደፈጠረ ጥናቱ አመላክቷል፡፡ ችግሩ በዚህ ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን የዋጋ ንረትን እያባባሰም ነው፡፡ ለዚህም እንደ ምሳሌ የቀረበው ትንታኔ በአገር ውስጥ የሚፈለጉ፣ በተለይ የግብርና ምርቶችን ለውጭ ገበያ ማቅርብና እነዚህን ለመተካት መልሶ ማስመጣት ችግር በመሆኑ ነው፡፡ እንዲህ ያለው አሠራር አቅርቦትን ለማሻሻል ካለማስቻሉም በላይ ለዋጋ ንረት ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡  

በጥቅሉ ከማኅበሩ ትንታኔ መረዳት እንደሚቻለው የግብርና ጥቅል ኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ የኢንዱስትሪ መቀዛቀዝ የገንዘብ አቅርቦት፣ የማበደሪያና የቁጠባ ወለድ ምጣኔ አለመመጣጠንና የመሳሰሉ ጉዳዮች ኢትዮጵያ ውስጥ 65 በመቶ የሚሆነውን የዋጋ ንረት ያመጡ መሆናቸውን በጥናታቸው ማየታቸውን ገልጸዋል፡፡ ባለፉት 25 – 30 ዓመታት እነዚህ ቢስተካከሉ ኖሮ ከፍተኛ መፍትሔ ይመጣ ነበር ተብሏል፡፡ 

የዋጋ ንረቱ ያስከተለው ተፅዕኖ በጨረፍታ 

የዋጋ ንረቱ በኢኮኖሚውና በማኅበረሰቡ ላይ ምን ተፅዕኖ አደረሰ የሚለው የአሶሴሽኑ የጥናት አካል ነበር፡፡ የዋጋ ንረቱ የሕዝብን ዌል ፌር በጣም ነክቷል የሚል ውጤት ተገኝቷል፡፡ በተለይ ከዝቅተኛ እስከ መካከለኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች በእጅጉ ጎድቷል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የዋጋ ግሽበት ሁሉንም ማኅበረሰብ በተመሳሳይ መልኩ ያጠቃ ያለመሆኑን ደግዬ (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡ ከክልሎችም አንፃር ሲታይ የዋጋ ንረቱ በተለያየ ገጽታ ያለው ሲሆን፣ በገጠርና በከተማ ያደረሰው ጉዳትም የተለያየ ምሥል በከተማ አካባቢ ደግሞ ፈጣን ጉዳት ታይቷል፡፡ 

ከቀረቡ የመፍትሔ ሐሳቦች ጥቂቶቹ

አሶሴሽኑ ለአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ችግሩና ለዋጋ ንረቱ እንደ መፍትሔ ያስቀመጣቸው በርካታ ነጥቦች ቢሆኑም፣ በዕለቱ የቀረቡት ግን ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ያላቸውን ብቻ ነው፡፡

ማኅበሩ ባደረገው ምርመራ ስድስት ጉዳዮች የኢትዮጵያን መዋቅራዊ ችግርና የዋጋ ንረት ለመፍታት በጣም ወሳኝ ናቸው ብሎ ያምናል፡፡

ከእነዚህም መካከል በመጀመርያ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ከመሬት ጋር በተያያዙ ያሉ ችግሮችን መፍታት ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው ደግሞ ከሰው ኃይል ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ሦስተኛው ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ዕድገቶችን ማምጣት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ ሌላው የወለድ ምጣኔ ነው፡፡ በማበደሪያና የማስቀመጫ ወለድ መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት ማጥበብ የግድ መሆኑን አስቀምጧል፡፡ ግጭትን ማስወገድና የገቢ ምርቶች ላይ የተጣለው ከፍተኛ ታሪፍ ማሻሻል ከተቻለ ብዙ ችግሮችን ማቅለል እንደሚቻል ማኅበሩ ገልጿል።

‹‹ሌሎቹ ችግር አይደሉም ማለት አይደለም፤›› ያሉት ዳይሬክተሩ፣ አንዱ ችግር ከተፈታ ሌላውም ችግር የመፈታት ዕድል ስላለ በተመረጡት ቦታዎች ላይ ሪፎርም ማድረግ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ ሌላ ግን በጣም በአስቸኳይ መፍታት አለበት የተባለው ገበያው አቅርቦቱን በአግባቡ መምራት ስለማይችል ይህንን የሚመራ አካል መቋቋም አለበት የሚል ነው፡፡ 

ሌላው ለብዙ ችግሮች መፍትሔ ነው ተብሎ በማኅበሩ የቀረበው የመፍሔ ሐሳብ የባንክ ተቀማጭ ገንዘብ ወለድ እንዲጨምር ማድረግ ነው፡፡ የማበደሪያ ወለድ ደግሞ እንዲቀንስ በመፍትሔ ሐሳብነት ቀርቧል፡፡ 

ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ታሪፍ ከቀነሰ የመንግሥት ገቢ ይቀንሳል የሚለው አተያይ ትክክል እንዳልሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ይልቁኑም ይህንን ታሪፍ በመቀነስ የገቢ ምርት እንዲጨምር ማድረግ እንደሚቻል ተጠቁሟል፡፡ ታሪፍ ቀነሰ ማለት የገቢ ምርት እንዲጨምርና የዋጋ ንረቱን እንዲረግብ የማድረግ ውጤት ይኖረዋል ተብሏል፡፡ ግጭቶችን ማስወገድና ተያያዥ ችግሮችን በቶሎ መፍታት ማኅበሩ ካቀረባቸው ምክረ ሐሳቦች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ማኅበሩ በምክረ ሐሳቦቹ ብቻ ሳይወሰን እነዚህን ለመተግበር የሚቀረፁ ፖሊሲዎች በመረጃ ላይ መመሥረት እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል፡፡ ሥራው በስሜት መመራት እንደሌለበት አሳስቧል፡፡ እስካሁን የተወሰዱ ዕርምጃዎች መፍትሔ ስላላመጡ ማኅበሩን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ሊሠሩ የሚገባም አስታውቋል፡፡

ዋናው ጉዳይ የሚጠበቀው ውጤትን በአግባቡ መለካት ስለሆነ፣ የፖሊሲ ሪፎርሞቹ ጥቅምና ጉዳታቸው በደንብ እየተገመገመ አኃዛዊ መረጃ እየቀረበባቸው መቀጠል እንደሚኖርባቸው በማሳሰብ፣ ይህንን ለማድረግ ተባብሮ መሥራት የግድ መሆኑን ሳይጠቅስ አላለፈም፡፡ የማኅበሩ ጥናት ለመንግሥት የሚቀርብ እንደሆነ ገልጾ፣ እስካሁን ባሉ አገራዊ ኢኮኖሚያዊ የጉዳዮች ላይ አሶሴሽኑ ከመንግሥት ጋር በቅርበት እየሠራ መሆኑንም ገልጿል፡፡ 

የፖሊሲን ዕርምጃዎችን ሥራ ላይ የማዋል ኃላፊነት የመንግሥት ቢሆንም፣ ጉዳዩ በመንግሥት አቅም ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ ቦርዱ መንግሥትን ሊያግዝ የሚችል መሆኑን በመጠቆም፣ ቦርዱ በአስቸኳይ መቋቋም አለበት የሚል ምክረ ሐሳብ ቀርቧል፡፡ ይህ ቦርድ የተለያዩ ዋጋን የሚያረጋጉ ሥራዎችን የሚሠራ ነፃ ተቋም ሆኖ የአገር ውስጥና የገቢ ንግድ አቅርቦትን የማስተዳደር ሁሉ ኃላፊነት ይኖረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች