የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ በተመለከተ የመጨረሻ ‹‹አገኘኋቸው›› ያለውን ትምህርቶች ማስተዋወቂያና ማጠናቀቂያ ዓውደ ጥናት ሐሙስ ሚያዝያ 20 እና 21 ቀን 2014 ዓ.ም. አካሄደ፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ በሁነቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ከዚህ ሁነት በኋላ ስለቀጣይ ምርጫ ወይም ሕዝበ ውሳኔ እንጂ፣ ስለስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ውይይትም ሆነ ምክክር እንደማይኖር አስታውቀዋል፡፡ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. እና መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ድምፅ የተሰጠበትን ስድስተኛው አጠቃላይ አገራዊ ምርጫ ላይ የታዩ ስኬቶች ወደሚቀጥለው ምርጫ እንዲሸጋገሩ ጥፋት፣ ስህተት፣ ወይም በተሻለ መንገድ መሠራት እየተቻለ ያልተሠሩ ሥራዎች ደግሞ እንዳይደገሙ ለማድረግ ዓውደ ጥናት መካሄዱን አስረድተዋል፡፡
ምርጫ ቦርድ ለሁለት ቀናት የቆየውን ዓውደ ጥናት ያካሄደው በየካቲትና መጋቢት ወራት ውስጥ ባዘጋጃቸው ፕሮግራሞች የፖለቲካ ፓርዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና የፍትሕ አካላት ካሉ ከ400 በላይ የሚሆኑ ባለድርሻ አካላት ከሰበሰባቸው መረጃዎች ያገኛቸውን ምክረ ሐሳቦች መልሶ ለባለ ድርሻዎቹ ለማቅረብ ነው፡፡ የተሰበሰቡ መረጃዎችን የያዘ ረቂቅ ሪፖርት ሚያዝያ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ለቦርዱ አመራሮች መቅረቡም ታውቋል፡፡
ለሁለት ቀናት በቆየው ዓውደ ጥናት የሕግ ማዕቀፍን ጨምሮ፣ ተቋማዊ የማሻሻል (ሪፎርም) ሥራና የምርጫ አካሄድ ባሉ ሰባት ዘርፎች የተገኘው ምክረ ሐሳብ ለተሳታፊዎች ቀርበዋል፡፡ ምክረ ሐሳቡ መልሶ የቀረበው የተሰጡት ምክረ ሐሳቦችን በማዳበር የመጨረሻ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ መሆኑን ሰብሳቢዋ ወ/ሪት ብርቱካን ለተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡
በዚህ ውይይት የተደረሰበትን ድምዳሜ ይዞ ምክረ ሐሳቦቹን ወደ ተግባር የመለወጥ ሥራ በዋነኛነት የቦርዱ፣ የመንግሥት፣ የፖለቲካ የፓርቲዎች፣ እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አክለውም፣ ‹‹ይኼ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ በተመለከተ በጣም ትልቅ፣ አስቸጋሪና ፈታኝ፣ ግን ታሪካዊ የነበረን ፕሮጀክት በተመለከተ፣ የምንነጋገርበት የመጨረሻው ሁነት ነው፤›› በማለት፣ ከዚህ በኋላ ስደስተኛውን አገራዊ ምርጫ በተመለከተ ሌላ ንግግር እንደማይኖር አስምረውበታል፡፡
ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ሰኔ 2014 ዓ.ም. በመጀመርያው ድምፅ መስጫ ቀናት ድምፅ ባልተሰጠባቸው ወይም ውጤታቸው በተሰረዘባቸው ቦታዎች ላይ፣ መስከረም 2014 ዓ.ም. ድምፅ ቢሰጥም፣ በፀጥታ ችግር ምክንያት በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ ባሉ የተወሰኑ የምርጫ ክልሎች ምርጫ አልተካሄደም፡፡
ቦርዱ ታኅሳስ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. በክልሉ ምርጫ ለማካሄድ የምርጫ ሰሌዳ አውጥቶ ዝግጅት ላይ የነበረ ቢሆንም፣ ጥቅምት 25 ቀን 2014 ዓ.ም. አገር አቀፍ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመታወጁ የተነሳ የምርጫ ሰሌዳና ዝግጅቱን ማቋረጡ ይታወሳል፡፡