Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊዕውቀትና ክህሎት የጨበጡ መሪዎችን ማፍራት እንዳልተቻለ ምሁራን ተናገሩ

ዕውቀትና ክህሎት የጨበጡ መሪዎችን ማፍራት እንዳልተቻለ ምሁራን ተናገሩ

ቀን:

ኢትዮጵያ በአመራር ዘርፍ ዕውቀትና ክህሎት የጨበጡ መሪዎችን ማፍራት ባለመቻሉ ኢትዮጵያ ችግር እየገጠማት መሆኑን ምሁራን ተናገሩ፡፡ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በሥራ አመራር ዘርፍ ለተመራቂ ተማሪዎች ሚያዝያ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. በሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ለግማሽ ቀን አዘጋጅቶት በነበረው ሴሚናር ላይ የዘርፉ ምሁራን እንዳመለከቱት፣ ሥራ አመራር ዘርፍ በሳይንስና በዕውቀት ያልተደገፈ መሆኑን አስቀምጠዋል፡፡ በሰው ሀብትም ሆነ ንብረት አስተዳደር ዘርፍ የሚፈለገውን ዓይነት ዕውቀትና ክህሎት የጨበጡ መሪዎችን ማፍራት በኢትዮጵያ ችግር መሆኑም አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

ለ34 ዓመታት በአስተዳደር ዘርፍ በማማከርና በማስተማር ጭምር የሠሩት የመጀመርያው ጥናት አቅራቢ የነበሩት ተገኝ ወርቅ ይርጋ ‹‹አስተዳደር ማለት የመሥሪያ ቤት ሐኪም ማለት ነው፤›› ሲሉ የዘርፉን አስፈላጊነት አስቀምጠዋል፡፡ የአመራርነት ሥራን በተለይ በሰው ሀብትና በንብረት አስተዳደር ዘርፍ ያለውን ግልጋሎት በጥልቀት የፈተሹት አቶ ተገኝ ወርቅ፣ ዘርፉ በአገሪቱ ያለበትን ክፍተት አስቀምጠዋል፡፡

‹‹መሥሪያ ቤት (ተቋም) ሲታመም የሥራ ተነሳሽነት ይቀንሳል፡፡ ትርፍ እየቀነሰ ኪሳራ ይጨምራል፣ ግጭትና አለመግባባት ይነግሣል፡፡ መሥሪያ ቤት/ተቋም ሲታመምና እነዚህን ምልክቶች ሲያሳይ አመራርን ማከም ግድ ይላል፤›› በማለት የተናገሩት አቶ ተገኝ ወርቅ፣ የማኔጅመንት (አስተዳደር) ሳይንስ ለዚህ አስፈላጊ መሆኑን ነው ያሰመሩበት፡፡

ጥናት አቅራቢው ‹‹የሰው ሀብት ክህሎትና ዕውቀትን በየጊዜው መለካት (Skill Inventory) ለተቋማት ሥራ አመራር ዘርፍ ጤናማነት እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው፤›› በማለትም ዘርፉ ጤናማ ሆኖ እንዲቀጥል መደረግ ያለበትን አስቀምጠዋል፡፡ አመራርነት ታማኝነት ላይ ያለውን ተፅዕኖ በሰው ሀብትና በንብረት አስተዳደር ከፋፍለው ፈትሸዋል፡፡ በተቋማት ውስጥ አመራሩ የሠራተኛውን ተነሳሽነት፣ ታማኝነትና ውጤታማነት እንዴት መጠበቅ እንደሚችልም አቶ ተገኝ ወርቅ በዘርፉ ካካበቱት ልምድ በመነሳት ሰፊ ሐሳብ አጋርተዋል፡፡

በኦርጋናይዜሽናል ሊደርሽፕ ላይ በሥልጠናም በሥራም ሰፊ ልምድ ያካበቱት ሁለተኛው ጥናት አቅራቢ አብዱል ኸሊቅ ረሺድ በበኩላቸው፣ ‹‹መሪነት ከራስ ይጀምራል›› ሲሉ አስቀምጠውታል፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች ለመሪነት የሚታጩትና አመራር እየተባሉ የሚሞካሹት በንግግራቸው፣ በባህሪያቸውና በአካላዊ ሁኔታቸው እየታዩ መሆኑን ያመለከቱት አብዱል ኸሊቅ፣ ግን ሁሌም ትክክል እንደማይሆን ጠቅሰዋል፡፡ ለመሪነት መሥፈርቱ ብዙ ቢሆንም ነገር ግን በትምህርትና በዕውቀት በመታገዝ እየዳበረ የሚሄድ ክህሎት ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹መሪነት ስለሚመሩ ሰዎች (ስለሌሎች) እንጂ ስለእኛ አይደለም፡፡ መሪነት ማገልገል እንጂ መገልገል አይደለም፡፡ መሪነት አንድን ስኬት ለማስመዝገብ አስቦና አቅዶ መፈጸምን ይጠይቃል፡፡ መሪነት ያልሆኑትን ነገር በቃል ማነብነብ ሳይሆን በተጨባጭ ሆኖ መገኘትን (መኖርን) ይጠይቃል፤›› በማለት ነው ጥናት አቅራቢው አቶ አብዱል ኸሊቅ የመሪነት መሠረታዊ ባህሪያትን ለተማሪዎቹ ያስረዱት፡፡

በዚሁ ሴሚናር አስፈላጊነትና ይዘት ላይ ማብራሪያ የሰጡት የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አረጋ ይርዳው (ዶ/ር) በበኩላቸው ‹‹መድረኩ ለተማሪዎቻችን ከቀለም ወደ ሥራ ዓለም መሸጋገሪያ ድልድይ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹በእኛ አገር አለቅነት ማዘዝ ላይ እንጂ ገና ማገልገል ላይ አልደረሰም፤›› ሲሉ የተናገሩት አረጋ (ዶ/ር) ‹‹መገልገል የሚፈልግ ሁሉ ግን ማገልገል ምን እንደሆነ መልመድ አለበት፤›› ሲሉ ጠቅሰዋል፡፡

በአመራር ዘርፍ ባለመተኮሩና የበቃ የሠለጠነ የሰው ኃይል ባለመፈጠሩ አገሪቱ መጎዳቷን አረጋ (ዶ/ር) አመልክተዋል፡፡ በተቋማት ደረጃ በሰው ሀብትም ሆነ በንብረት አስተዳደር ዘርፍ ብዙ ችግሮች እንደሚታዩ ያመለከቱት አረጋ (ዶ/ር) ‹‹በአገር ደረጃም ቢሆን በአመራር መስክ ሰፊ ክፍተት አለብን፤›› በማለት የዘርፉን አስፈላጊነት ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ተረፈ ዘለቀ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በ1949 ዓ.ም. የተመሠረተው ኢንስቲትዩቱ ባለፉት 60 ዓመታት አመራሮችን በማፍራት ሰፊ ሥራ መሥራቱን አመልክተዋል፡፡ ‹‹ችግር ፈቺ አሠራሮችና ምርምሮችን በማፍለቅ፣ በተግባር ተኮር ሥልጠናና በማማከር መንግሥታዊና መንግሥታዊ ላልሆኑ ተቋማት አገልግሎት እንሰጣለን፤›› ሲሉ የተናገሩት ተረፈ (ዶ/ር) ለዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የማኔጅመንት ተማሪዎች ያመቻቹት ሴሚናርም የዚሁ ሥራቸው አካል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...