ከሚያዝያ 19 እስከ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ለሁለት ቀናት በተስተናገደው የአፍሪካ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኮንፈረንስ፣ የታዳጊ አገሮች የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተባብረው መሥራት ባለመቻላቸው፣ የተማረ ሰው ኃይል ኩብለላ ለዘርፉ ከባድ ፈተና መሆኑን በቀረቡ ጥናቶች ተገለጸ፡፡ ይህ የተገለጸው ቅድስተ ማሪያም ዩኒቨርሲቲ ለ20ኛ ጊዜ ባስተናገደው የአፍሪካ የግል ትምህርት ተቋማት ኮንፈረንስ ላይ ነው፡፡
የታዳጊ አገሮችን የአካዴሚ ትብብሮች የተመለከተ ጥናት ያቀረቡት ከህንድ ብሔራዊ የትምህርት ዕቅድና አስተዳደር ኢንስቲትዩት የመጡት ቫርጌስ (ፕሮፌሰር)፣ ታዳጊ አገሮች በአካዴሚክ ብቻ ሳይሆን በጥናትና ምርምሮች መተባበር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የዘላቂ ልማት ግቦች ላይ፣ ‹‹ማንም አገር ወደ ኋላ መቅረት የለበትም›› የሚል መርህ መሥፈሩን፣ በመላው ዓለም ቢፈለግ ደግሞ ማንም አገር ፍፁም በዕውቀት የበላይነት ኖሮት እንደማያውቅ፣ በዚህ የተነሳ ‹‹አገሮች በትምህርት መተጋገዛቸውና መተባበራቸው አስፈላጊ ነው፤›› ያሉት ቫርጌስ (ፕሮፌሰር)፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ አገሮች አካዴሚያዊ ትብብሮችን እንዲያጠናክሩ ነው ያሳሰቡት፡፡
በዚሁ መድረክ ጥናት ያቀረቡት ከአሜሪካ ኢንዲያና ዩኒቨርሲቲ ተሾመ ይዘንጋው (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የአካዴሚ ትብብሮች በልማትና ዕድገት ላይ ያላቸውን ተፅዕኖ አቅርበዋል፡፡ በአብዛኛው የኢትዮጵያና የአፍሪካ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካዴሚያዊ ትብብር ፍለጋ ወደ ውጭ በተለይ ወደ ምዕራቡ ዓለማት ያማትራሉ በማለት ነው ይዘንጋው (ዶ/ር) የተናገሩት፡፡ በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከውጭ አገሮች አጋር አካላት ጋር ተባብሮ የመሥራት ታሪካቸውንም ምሁሩ አስገንዝበዋል፡፡ ከዚህ በመነሳትም የደቡባዊ ክፍለ ዓለማት (ታዳጊ አገሮች) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግንኙነት መጠናከር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ነው ይዘንጋው (ዶ/ር) ያሰመሩበት፡፡
ከካናዳ ኦታዋ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ትውልደ ሴኔጋላዊው አብዱላዬ ጉዬ (ፕሮፌሰር)፣ በተለይ የተማረ ሰው ኃይል ፍልሰት ላይ አተኩረው ተናግረዋል፡፡ የታዳጊ አገሮች የአካዴሚ ወይም የምርምርና ጥናት ትብብር ጉዳይ ከምሁራን ፍልሰት ተነጥሎ መታየት አይችልም ብለዋል፡፡
ታዳጊ አገሮች ውድ የአገር ሀብት እያፈሰሱ የሚያመርቷቸውን ጥቂት ምሁራን የበለፀጉ አገሮች በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ይነጥቋቸዋል የሚሉት አብዱላዬ (ፕሮፌሰር)፣ ይህ አስቸጋሪ ፈተና ባለበት ሁኔታ የታዳጊ አገሮች የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግንኙነት መጠናከር እጅግ ፈታኝና በእጅጉም አስፈላጊ እንደሆነ አስምረውበታል፡፡
ኮንፈረንሱ በኢንተር ሌግዢሪ ሆቴል ሲከፈት የቅድስተ ማሪያም ዩኒቨርሲቲ መሥራችና ፕሬዚዳንት ወንድወሰን ታምራት (ዶ/ር)፣ ስለኮንፈረንሱ አስፈላጊነት አብራርተዋል፡፡ ‹‹ዘንድሮ የላቲን አሜሪካና የእስያ አገሮች የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ከአፍሪካ ተቋማት ጋር ከሚያሰባስበው ከደቡብ አፍሪካው ኢንስቲትዩሽናል ኔትወርክ ፎር አፍሪካ ተቋም ጋር በጋራ እየሠራን ነው፤›› ሲሉ የገለጹት ወንድወሰን (ዶ/ር)፣ ለሃያ ዓመታት ኮንፈረንሱን ማዝለቅ ፈታኝ ቢሆንም ዝግጅቱን ለማስቀጠል ብዙ እንደታገሉ አስረድተዋል፡፡
‹‹የግልና የመንግሥት፣ የምርምርና ጥናት ተቋማቶች በኮንፈረንሱ ተጋብዘዋል፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ከአካዴሚና ምርምር ተቋማት በተጨማሪ ኢንዱስትሪዎችም መጋበዛቸውን አመልክተዋል፡፡
በሌላ በኩል በአገሪቱ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በመንግሥት ስለሚደረግላቸው ድጋፍና ማበረታቻ የተጠየቁት የወንድወሰን (ዶ/ር)፣ ‹‹ሕጎቹ ቢዘረጉም በተጨባጭ ወደ መሬት ወርደው በተግባር መተርጎማቸው አነስተኛ ነው ብለዋል፡፡ አገር አቀፍ ችግሮችን የሚፈቱ ምርምሮችና የጥናት ውጤቶች ላይ ዩኒቨርሲቲያችሁ ለምን አያተኩርም? ለተባሉት ደግሞ፣ ‹‹እኛ በተለይ የዘርፋችን የትምህርት ሴክተር ላይ በማዘንበል ነው የምንሠራው፤›› ሲሉ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የቅድስተ ማሪያም ዩኒቨርሲቲ ኮንፈረንስ ከተለያዩ አገሮች የመጡ ምሁራንን ብቻ ሳይሆን፣ ከትምህርት ጋር የሚሠሩ የመንግሥት ተቋማት ሥራ ኃላፊዎችንም ያሳተፈ ነበር፡፡