Friday, December 1, 2023

ሚዲያዎች ከመንግሥት ተቋማት መረጃ ለማግኘት ፈተና እንደሆነባቸው የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አስታወቀ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የመገናኛ ብዙኃን ከተቋማት መረጃ የማግኘት ጉዳይ ፈታኝ እንደሆነባቸው የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

የመንግሥት ተቋማት ለሚሠሩት ሥራ ተገቢውን መረጃ የመስጠት ኃላፊነት ቢኖርባቸውም፣ ፈቃደኛ አለመሆናቸውንና ጉዳዩ አዳጋች በመሆኑ ለሚዲያዎች መረጃ በማይሰጡ አካላት ላይ ተጠያቂነት የሚረጋገጥበት ሥርዓት እንዲዘረጋና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአትኩሮት እንዲሠራበት፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ኢድሪስ ጠይቀዋል፡፡

መረጃ በሌለበት ሁኔታ ‹‹ሚዲያዎች ይህን አላደረጋቸሁም ወይም የዜና ሚዛን አልጠበቃችሁም፤›› የሚባለው ጉዳይ እንደማያስኬድ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣  ባለሥልጣኑ በሚያደርገው ክትትል ሚዲያዎች በአብዛኛው የሚዲያ ተቋማትን ‹‹በዘገባችሁት ዘገባ ጥሰት ፈጽማችኋል›› ብሎ በሚጠይቅበት ወቅት የሚቀርበው ምላሽ ‹‹ከተቋማት መረጃ ፈልገን ስንጠይቅ ቀጠሮ ይሰጡናል፣ በቀጠሮ አልሆን ሲለን በደብዳቤ ጠየቅን፣ በዚህ ሒደት መልስ ስናጣ ዜናውን ሠራነው፤›› የሚል መልስ እንደሚሰጡ ጠቁማዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ይህን የተናገሩት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ዓርብ ሚያዝያ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. የመገናኛ ብዙኃን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን በገመገመበት ወቅት ነው፡፡

 በመንግሥት ተቋማት ጉዳይ ትልቁ የመረጃ ባለቤት የሆነው መንግሥት፣ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ለኅብረተሰቡ ለማድረስ ቃል የገባ በመሆኑ፣ ይህን የማያደርጉ አካላት በሕግ የሚጠየቁበት ሥርዓት ካልተፈጠረ ችግሩ እንደማይቀረፍ ተናግረዋል፡፡

ባለሥልጣኑ እንኳን ይህን ችግር ለመፍታት የሚዲያ አካላትን ከመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ጋር በመሆን የሚያገናኝ መድረክ ለመፍጠር መሞከሩንና የሚዲያ ተቋማት መረጃ የሚያገኙበት መንገድ የማመቻቸት ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

ባለሥልጣኑ በመንግሥት ፈቃድ ያገኙ የሚዲያ ተቋማት ሁሉ መረጃ እንዲያገኙና መረጃ በሚፈልጉበት ጊዜ እንዲስተናገዱ የተቋማቱን ስም ዝርዝር ለሁሉም የመንግሥት ተቋማትና የክልል መንግሥታት እንዲደርሰ እያደረጉ መሆኑን በመግለጽ፣ ‹‹እኛ በበኩላችን ሚዲያው መረጃ አግኝቶ ሚዛናዊ የሆነ መረጃ እንዲያቀርብ እንደግፋለን፤›› ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ የሚዲያ ተቋማት ስለሚያስተላልፉት መረጃ ኃላፊነት መውሰድ እንዳለባቸውና ውጪ ላይ ያለው የፖለቲካ ትኩሳትና የግጭት፣ በንግድ ሚዲያ ተቋማት ላይ እንዲንፀባረቅ እንደማይጠበቅ፣ ተቋማቱ በገለልተኝነት ሕግንና ህሊናን መሠረት በማድረግ ለአገር መወገን እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል የክልል የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን ተቋማት ከጅምሩ ሲቋቋሙ በአዋጅ በተቀመጠው መሠረት ትኩረታቸው መሆን ያለበት 70 በመቶ ለተቋቋሙለት ሕዝብ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች እንዲሁም 30 በመቶውን ለቀሪ ጉዳዮች እንዲያደርጉ ተብሎ ቢሆንም፣ የእነዚህ መገናኛ ብዙኃን ትኩረት በአጠቃላይ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተጠምደው እንደሚታዩ አብራርተዋል፡፡

የሚዲያ ባለሙያዎች ዕይታ መስተካከል እንዳለበት የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ሆቴል ለሆቴል ከመዘዋወር ባለፈ ፕሮጀክት ቀርፀው ለሕዝብ ማገልገል እንዳለባቸው የክልል ምክር ቤቶችም እንዲመክሩበት ጠይቀዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ ዕፀገነት መንግሥቱ ለተነሳው ጉዳይ ማብራሪያ ሲሰጡ፣ መረጃ በማይሰጡ ተቋማት ማወቅ ያለባቸው የመረጃ ነፃነት ጉዳይ የጋራ ኃላፊነት እንጂ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም ለኢትዮጵያ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ብቻ የሚሰጥ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባለሥልጣኑም ሆነ ሚዲያዎች ብዙውን ጊዜ የተቋም ስም ጠቅሰው መረጃ ከለከለ ብለው በይፋ እንደማይናገሩና በጅምላ ተቋማት መረጃ ከለከሉ ብለው ማቅረባቸው መቅረቡ ፓርላማው ወይም ዕንባ ጠባቂ ተቋም ለብቻው የሚሠራው ነገር አይኖርም ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -