Monday, July 22, 2024

የፌዴራልና የክልል መንግሥታት በሃይማኖት ሰበብ ደም ለማፋሰስ በሚሠሩ አካላት ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወስዱ ተጠየቀ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ዜጎችን ደም ሊያፋስሱ በሚሠሩ አካላት ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወስዱ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔን ጨምሮ፣ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎችና የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በየፊናቸው ባወጡት መግለጫ ጠየቁ፡፡

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ የተፈጸመውን ጥቃትና የደረሰውን ጉዳት፣ እንዲሁም በደቡብ ክልል በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ የደረሰውን የአብያተ ክርስቲያናት ቃጠሎና ውድመትን አስመልክቶ ተከታታይ መግለጫዎችን አውጥቷል፡፡

ጉባዔው ያወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በጎንደር ከተማ በሚገኙ የእስልምና ዕምነት ተከታዮች ላይ ባለፈው ሳምንት በተፈጸመው ግድያ፣ የመስጊድ ቃጠሎ፣ የሙስሊም ግለሰቦች ንብረት ውድመትና ዘረፋ በሃይማኖት እጅግ የከፋ ኃጥያት መሆኑን፣ በፈጣሪም ዘንድ የሚያስጠይቅ ፀያፍ ድርጊት እንደሆነ አስታውቋል፡፡

የሰው ሕይወት በማጥፋት፣ እንዲሁም በብዙ ልፋትና ጥረት የተገኘን የንፁኃንና የአገር ሀብት በማውደም ለግጭት ምክንያት የሆኑ ችግሮችን መፍታት እንደማይቻል ሁሉም ሊገነዘበው እንደሚገባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ አስገንዝቧል፡፡

በሌላ በኩል ዓርብ ሚያዝያ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በደቡብ ክልል በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተ ክርስቲያናትና በፕሮቴስታንት አማኞች ቤተ አምልኮዎች ላይ የተፈጸመውን የወንጀል ድርጊት ጉባዔው በእጅጉ እንደሚወገዝ አስታውቋል፡፡ ድርጊቱ በየትኛውም ሃይማኖት ተቀባይነት የሌለው ከመሆኑም በላይ፣ ደረቅ ወንጀልና በሕግ ሊያስጠይቅ የሚገባው መሆኑን በፅኑ እንደሚያምን ገልጿል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በጎንደር ከተማ የተፈጠረውን ችግር አስመልክቶ፣ ችግሩ ከተከሰተበት ሰዓት ጀምሮ ያለውን መረጃ ካሰባሰበና ሁኔታዎችን ከገመገመ በኋላ የሐዘን መግለጫና ለክልሉ ሕዝብና መንግሥት ጥሪ  አቅርቧል፡፡

 በታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ የተፈጠረውን ችግርና በሙስሊምም ሆነ በክርስቲያን አማኞች ላይ የተፈጸመውን የእኩያን የወንጀል ድርጊት አጥብቆ እንደሚያወግዝ ያስታወቀው ፓርቲው፣ አስቸኳይ ምርመራ ተደርጎ በችግሩ የተሳተፉና ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የመንግሥት አካላት ሳይቀሩ ሕግ ፊት እንዲቀርቡና ለፈጸሙት ወንጀልም ተመጣጣኝ ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው ጥሪ አቅርቧል፡፡

በጎንደር ከተማ ሰሞኑን የተፈጠረው ችግር መነሻው በከተማው በተለምዶ አዲስ ዓለም የሙስሊሞች መካነ መቃብርና በአበራ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ በነበረ ቆየት ባለ የይዞታ ይገባኛል ጥያቄ ጋር በማያያዝ፣ በእስልምናና በክርስትና እምነት ተከታዮች መካከል ግጭት እንዲፈጠር የሚፈልጉ አካላት የቀሰቀሱትና ያባባሱት መሆኑን ፓርቲው እንደሚገነዘብ አስታውቋል፡፡ በአገሪቱና በአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአምልኮ ሥፍራዎች አካባቢ የሚነሱ የይዞታና የወሰን ይገባኛል ጥያቄዎች እየበዙ፣ በተለያዩ አካባቢዎችም የመካረርና አልፎ አልፎም የግጭት መንስዔ እየሆኑ እንደመጡ አብን ገልጿል፡፡

የአማራ ክልላዊ መንግሥት መሰል ጉዳዮች ባሉባቸው አካባቢዎች ያሉ ችግሮችን ከሥር መሠረቱ ለመቅረፍ ተጨባጭ የተግባር ዕርምጃ መውሰድ እንዲጀምር ጥሪ ያቀረበው አብን፣ በአገር አቀፍ ደረጃ እያደገ ያለው የሃይማኖት አክራሪነትና መንግሥት ለጉዳዩ የሰጠው ትኩረት ማነስ ችግሩን እንዳባባሰው አስረድቷል።

አብን በመግለጫው እንዳስታወቀው፣ አንዳንድ የሃይማኖት አመራሮችና መምህራን የሚያደርጉት ለከት ያጣ የጥላቻ ቅስቀሳም ሃይማኖትን ሰበብ ላደረጉ ግጭቶች መበራከት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በጎንደር ከተማ ሚያዝያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. የተፈጠረውን ግጭትና የጠፋውን የሰው ሕይወት ድርጊት እንደሚያወግዝ ያስታወቀ ሲሆን፣ መንግሥት ጉዳዩን በፍጥነት አጣርቶ አጥፊዎችን ለፍርድ እንዲያቀርብ፣ እንዲሁም ችግሩ እንዳይስፋፋና የበለጠ ጥፋት እንዳያመጣ እንዲቆጣጠር ጠይቋል፡፡

በሌላ በኩል የባልደራስ ፓርቲ  በአማራ ክልል፣ ጎንደር ከተማ በተነሳ ግጭት በርካታ አማኞች በመሞታቸው፣ መስጊዶች በመቃጠላቸው፣ በግለሶቦች ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በመድረሱ ሐዘኔታውን ገልጾ፣ ግጭቱ እንዳይሰፋና የፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች መጠቀሚያ ላለመሆን የሚመለከታቸው የክልሉ የፍትሕ አካላት፣ የእምነት አባቶችና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በሙሉ በአስቸኳይ የተቀናጀ እንቅስቃሴ አድርገው የከተማውን ፀጥታ ለማስጠበቅ መረባረብ አለባቸው ብሏል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉበዔ (ኢሰመጉ) በጎንደር ከተማ ሸሕ ኤሊያስ እየተባለ የሚጠራ የእስልምና እምነት ተከታዮች የቀብር ቦታ እንደሚገኝ፣ በዚህም ቦታ አዋሳኝ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የፀበል ቦታ እንዳለ፣ በዚህ አካባቢ ላይ በድንበርና በመሬት ይገባኛል ምክንያት በተደጋጋሚ አለመግባባቶች ሲነሱ መቆየታቸውን ካሰባሰባቸው የመረጃ ምንጮች እንደተረዳ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ከሰሞኑም በጎንደር ከተማ ለተፈጠረው ግጭት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለችግሩ የሰጠው ፈጣን ምላሽ አለመኖሩን በመግለጽና መንግሥት እንደ መንግሥት ችግሮች ከቁጥጥር ውጪ ሳይሆኑ፣ የሰው ሕይወት ሳይጠፋ፣ አካል ሳይጎዳና ንብረት ሳይወድም አስቀድሞ የመፍታት ኃላፊነት እንዳለበት በመረዳት ይህን ኃላፊነት ለመወጣት በአግባቡ እንዲንቀሳቀስ ኢሰመጉ አሳስቧል፡፡ 

በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አብሮ የመኖርና የመቻቻል ባህልን በመዘንጋት በሃይማኖት ሽፋን እየተነሱ ያሉ ግጭቶች እየተደጋገሙ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ይህ ችግር በቂ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ኢሰመጉ አስታውቋል፡፡ ስለሆነም ችግሮች ሳይፈጠሩና በአለመግባባቶች ምክንያት የሰዎች ሕይወት ሳይጠፋ፣ አካል ሳይጎዳና ንብረት ሳይወድም በሰላማዊ መንገድ ለአለመግባባቶች ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት እንዲቻል ጥያቄ አቅርቧል፡፡

የፌዴራልና የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት የተፈጠረውን ችግር በማባባስ፣ በሕዝቡ መካከል ተጨማሪ ደም መፍሰስን ለማምጣት እየሠሩ ያሉትን አካላት በአግባቡ በመለየት ከጥፋት ጉዟቸው እንዲመለሱ ማድረግ እንደሚገባቸው የተገለጸ ሲሆን፣  እንዲሁም የሰው ሕይወት በማጥፋትና ንብረት በማውደም ተግባር ላይ የተሳተፉና ትብብር ያደረጉትን አካላት በሕግ አግባብ በማጣራት ሕጋዊና አስተማሪ ዕርምጃ በመውሰድ ለኅብረተሰቡ እንዲያሳውቁ ኢሰመጉ ጠይቋል፡፡

በሌላ በኩል የፌዴራል የደኅንነትና የፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል እንዳስታወቀው፣ በጎንደር ከተማ ከቀብር ሥፍራ ጋር በተያያዘ በክርስትናና በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የተቀሰቀሰውን ግጭት መነሻ በማድረግ በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎችም በሃይማኖት ሽፋን ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር ፀረ ኢትዮጵያ የሆኑ ኃይሎችን ፍላጎት ለማሳካት በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ዕርምጃ እየወሰደ ነው፡፡

የጋራ ግብረ ኃይሉ ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ኅብረተሰቡ ለዓመታት በገነባው ጠንካራ የሆነ የጋራ እሴት ሙከራቸው የከሸፈባቸው ኃይሎች ቀሪውን የሃይማኖት ካርድ በመምዘዝ በተለያዩ እምነት ተከታዮች ዘንድ መጠራጠርና ጥላቻ እንዲፈጥር፣ ብሎም ወደ ግጭት እንዲያመራ በተለያዩ መንገዶች ሲቀሰቅሱ ቆይተዋል ብሏል፡፡

በጎንደር የተከሰተው ግጭት በአማኞች መካከል ግጭት በመቀስቀስ ወደ አገራዊ ቀውስ እንዲያመራ የሚደረገው ሴራ አካል መሆኑን ያስታወቀው ግብረ ኃይሉ፣ በዚህ ድርጊት በተሳተፉ አካላት ላይ ተገቢ ዕርምጃ መወሰድ እንደ ጀመረና በጎንደር በተከሰተው ግጭት የተሳተፉና ሁከቱን ለማባባስ የተንቀሳቀሱ 280 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ማድረጉ ታውቋል፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎችም የእምነት ተቋማትና ግለሰቦች ላይ ጥቃት በመፈጸም ግጭቱ አገራዊ ቅርፅ እንዲኖረው ሙከራ እየተደረገ ነው ያለው ግብረ ኃይሉ፣ የፌዴራል የደኅንትና የፀጥታ መዋቅር በድርጊቱ በሚሳተፉት ላይ ብቻ ሳይሆን ከኋላ በመሆን በሚዘውሩት ላይ በቂ መረጃና ማስረጃ ያለው በመሆኑ ተከታታይ ዕርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ አስታውቋል።

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሳምንቱ መጨረሻ መግለጫ መስጠታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በመግለጫቸውም መንግሥት የግጭቱ ምክንያት ምንም ይሁን ምን ድርጊት የሚወገዝና ተቀባይነት የሌለው አሳፋሪ ተግባር ነው ብሎ እንደሚያምን ተናግረዋል።

ጎንደር ከተፈጠረው ክስተት ጋር በተያያዘ እስካሁን በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም ለገሰ (ዶ/ር) ያስታወቁ ሲሆን፣ ችግሩን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት እየሠሩ ያሉ አካላትን መንግሥት እንደማይታገስ በማስታወቅ፣ ወንጀልን በወንጀል ለማካካስ የሚደረግ ማንኛውም ጥረት ከወንጀል ፈጻሚነት ተለይቶ አይታይም ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት በጎንደር ከተማ ታዋቂ የነበሩት ሼክ ከማል ለጋስ ሥርዓተ ቀብር እየተፈጸመ በነበረበት ሰዓት፣ ከቀብር ቦታው ጋር ድንበርተኛ ከሆነው ቤተ ክርስቲያን ለቀብር የሚሆን ድንጋይ ‹‹እናነሳለን››፣ ‹‹መስጊዱ ክልል ነው አታነሱም የቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ነው፤›› በሚል በተወሰኑ ግለሰቦች መካከል የተጀመረው ግጭት ተስፋፍቶ፣ በርካታ ሰዎች ሕይወታቸው እንዲያልፍ ከማድረጉ ባሻገር፣ የአካል ጉዳትና የተለያዩ ንብረቶችና ቤተ እምነቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -