Sunday, February 5, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢትዮጵያውያን ከፋፋይ ሴራዎችን ማክሸፍ አለባቸው!

በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በየትም ሥፍራ በሰብዓዊ ፍጡራን ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በጋራ ማውገዝ አለብን፡፡ በተለይ ደግሞ ዘርን፣ እምነትን፣ ፆታን፣ ቋንቋን፣ ባህልንም ሆነ ሌሎች ማንነቶችን ለይቶ ማጥቃት ውግዝ የሆነ ድርጊት ስለሆነ ሕገወጦችን በሕግ አደብ ማስገዛት የግድ መሆን አለበት፡፡ ሰሞኑን በጎንደር በሙስሊም ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመው ጥቃትም ሆነ ግድያ፣ በመላ ኢትዮጵያውያን መወገዝ አለበት፡፡ ኢትዮጵያውያን በማንነታቸው ምክንያት ተነጥለው ጥቃት ሲፈጸምባቸው የመከላከል ኃላፊነት የመንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ በዚህች አገር ውስጥ የሚኖሩና በመላው ዓለም የሚገኙ ወገኖቻችን ጭምር ነው፡፡ ሰብዓዊ ፍጡራንን በማንነታቸው ምክንያት ማጥቃትም ሆነ መግደል አስነዋሪ ድርጊት በመሆኑ፣ ለሰው ዘር የሚቆረቆሩ በሙሉ እንዲህ ዓይነቱን አሳፋሪ ቅሌት በግልጽና በድፍረት ሊጋፈጡት ይገባል፡፡ በተጨማሪም እንዲህ ዓይነቱን አስነዋሪ ድርጊት ሕግ ፊት ማቅረብ ሲገባ፣ ተመሳሳይ ወንጀል መፈጸም መወገዝ አለበት፡፡ አሁንም በሙስሊም ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በተባበረ ድምፅ ማውገዝ፣ እንዲሁም የጥቃቱ ፈጻሚዎች ለሕግ እንዲቀርቡ በአንድነት መቆም የግድ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ሕገወጥ ድርጊት ውስጥ መገኘት ነውረኝነት ነው፡፡ ስለዚህ ፍትሕ እንዲሰፍን ከፋፋይ ሴራዎችን ማክሸፍ ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል መሆናቸው መረጋገጥ አለበት፡፡ ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ በሕግ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ በዘር፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ አመጣጥ፣ በሀብት፣ ወይም በሌላ ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ እኩልና የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት አላቸው፡፡ ከሕግ በተቃራኒ በመንግሥትም ሆነ በማንኛውም ወገን የሚፈጸም ድርጊት ወንጀል ነው፡፡ በአገሪቱ በሁሉም ሥፍራ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሕግ ጥበቃና ከለላ አግኝተው፣ በመረጡት የሥራ ዘርፍ ተሰማርተውና እንደፈለጉ ተዘዋውረው ሀብት የማፍራት መብት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ሠርተው የመኖር መብታቸው መረጋገጥ አለበት፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን አንዳችም የእምነትም ሆነ የብሔር ተፅዕኖ ሳይኖርባቸው መንቀሳቀስ መብታቸው ነው፡፡ ለአንዱ የእምነት ተከታይ የተፈቀደው ለሌላኛው ሲከለከል፣ አንዱ አጥቂ ሆኖ ሌላኛው ተጠቂ ሲሆን በዜጎች መካከል ልዩነት በመፍጠር የአገሪቱን አንድነት ያናጋል፡፡ እኩልነትና ፍትሐዊነት የሚረጋገጡት በወረቀት ላይ ሳይሆን በተግባር ብቻ ነው፡፡ ሕገወጥነት አደብ እንዲገዛ የሕግ ተጠያቂነት ይኑር፡፡ 

አገራችን እንድታድግ፣ የዜጎቿ የጋራ መኖሪያ እንድትሆን፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር፣ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብቶች መከበር ስሟ እንዲታወቅ፣ የጥቂቶች ሳይሆን የብዙኃን እንድትሆን የምንፈልግ ከሆነ ውስጥ ለውስጥ የሚገዘግዟትን ነውሮች እናስወግድላት፡፡ በዚህ ዘመን አንገቷን ቀና ቀና ለማድረግ ብትሞክርም፣ እነዚህ ነውሮች ግን መልሰው አንገቷን ያስደፏታል፡፡ አገራችን በዓለም አደባባይ ግርማ ሞገስ የሚያጎናፅፏት በርካታ ስኬቶች ያሏትን ያህል፣ በኃፍረት አንገቷን የሚያስደፏት እንከኖችም ሞልተዋታል፡፡ በዚህ ዘመን ኢትዮጵያችን ለዘመናት ከነበረችበት አስከፊ አረንቋ ውስጥ በመውጣት፣ ክብርና ዝና የሚያጎናፅፋት ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ ርቀት ይቀራታል፡፡ በረሃብና በልመና የምትታወቅ አገር የተበላሸ ገጽታዋ እንዲለወጥና በአፍሪካ አኅጉር ከቀዳሚዎቹ ተርታ ለማሠለፍ ከባድ ትግል ይጠይቃል፡፡ ለዜጎቿም መነቃቃት በርካታ ሥራዎች መከናወን አለባቸው፡፡ እየታየ ካለው ተስፋ በስተጀርባ የመሸጉ ነውሮች የኢትዮጵያን አንገት እያስደፉ ነው፡፡ እነዚህ ነውሮች ኢትዮጵያን ግማሽ ልጩ ግማሽ ጎፈሬ አድርገዋታል፡፡ ለእነዚህ ነውሮች መፍትሔ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሕገወጦችን ሕግ ፊት በማቅረብ መፋረድ ተገቢ ነው፡፡

የመንግሥት ሥልጣንን የዝርፊያ ማዕድ አድርገው የኖሩ የለውጡና የሽግግሩ እንቅፋቶች፣ የኢትዮጵያ ልማትና ዕድገት የህልውናችን አደጋ ነው ብለው የተነሱ የትኛውንም ዓይነት የውስጥ ተቃውሞ ከመቦጥቦጥና ከመጥለፍ እንደማይቦዝኑ፣ በኢትዮጵያ ላይም መሣሪያ ከመደቀን አፍረው ወይም አርፈው የማያውቁ ታሪካዊ ጠላቶች ወጥመድ እንዳዘጋጁ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ሳሩን ዓይተን ገደሉን ሳናይ የምንገባበትንና ገብተንም የምንጠፋበትን ጥፋት ስለደገሱልን መጠንቀቅ ይበጃል፡፡ ይህንን አደገኛ የጥፋት ድግስ በራሱ ምክንያት ብቻ እንቢ ማለት አለብን፡፡ ሰሞኑን የምናስተውላቸው ችግሮች ግን ከዚህም በላይ በሌሎች በርካታ ምክንያቶች፣ መከላከልና መቋቋም የምንችላቸው ነበሩ፡፡ እዚህ ላይ መገንዘብ የሚገባን አሁን የምንገኘው ገና መሬት ያልነካ የዴሞክራሲ ጭላንጭል ውስጥ እንደሆነ ነው፡፡ የአፈናውና የጥርነፋው መነሳት የፈጠረው ወጋገን ውስጥ ነን፡፡ እየነጋ ይሁን እየጨለመ፣ ወይም እየመሸ እንደሆነ ገና አላወቅንም፡፡ በማያውቁት ዴሞክራሲ ውስጥ መብቴ ነው ማለትን ኃላፊነቴ ነው ከማለት ጋር ካላጣጣምነው፣ መንጋቱ ቀርቶ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንወድቃለን፡፡ ዴሞክራሲን ማቋቋም የምንችለው ሥርዓተ መንግሥቱን ስናውቅበት ነው፡፡ አንድ ሐሳብ ላይ ለመድረስ ሳንጨነቅ፣ የተለያዩ ሐሳቦችን መለዋወጥ ሳንለማመድ፣ የግድያና የውድመት ወንጀልን የትግል ዘዴ ማድረግ እርም ሳንል ዴሞክራሲን መሸከም የሚችል ተቋምም ሆነ ባህል መገንባት በህልምነት ይቀራል፡፡ ለዚህ መፍትሔው የሕግ የበላይነት ማስፈን ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነት ለታሪካዊ ጠላቶች የተንበረከከበት ጊዜ ተሰምቶ አይታወቅም ነበር፡፡ ኢትዮጵያም በታሪኳ ስትወረር እንጂ በወራሪነት አትታወቅም፡፡ ለወረራ የመጡ ኮሎኒያስቶችና የተለያዩ ዓላማ የነበራቸው ጠላቶች አፍረውና ተዋርደው ተመለሱ እንጂ፣ በቅኝ ገዥነት አልቆዩባትም፡፡ ይህ ኩሩና ጀግና ሕዝብ አገሩን አንዴም አስደፍሮ አያውቅም፡፡ በታሪክም አልተመዘገበም፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን አገራችንን ከባዕዳንና ከወራሪ ኃይሎች ስንከላከል፣ ከእነ ማንነቶቻችን በጋራ ሆነን ነው በጀግንነት ስንፋለም የምንታወቀው፡፡ ከልዩነታችን ይልቅ አንድነታችን ይበልጥ ያስተሳስረናል፡፡ ነገር ግን የዚህ ዘመን ልዩነት ከመነጋገርና ከመደማመጥ በላይ እየሆነ ክፍተት እየፈጠረ ነው፡፡ ይህ ክፍተት ደግሞ ሕዝባችን የሚታወቅበትን የአትንኩኝ ባይነትና አገርን በጋራ የመጠበቅ አኩሪ የጋራ እሴት እየተገዳደረ ነው፡፡ ልዩነትን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ከማስተናገድ ይልቅ፣ እርስ በርስ መቋሰልና መበላላት ልማድ እየሆነ ነው፡፡ ለዘመናት አብረው የኖሩ ወንድማማቾችንና እህትማማቾችን በብሔርና በእምነት ለመለያየት የሚያደቡ በርክተዋል፡፡ ይኼ ፀንቶ ለኖረው ለኢትዮጵያውያን አንድነት አይስማማውም፡፡ አሁንም እንላለን ወንድማማች ክርስቲያኖችንና ሙስሊሞችን ለማፋጀት ግርግር መፍጠር አስነዋሪ ወንጀል ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች ይህንን ደባ በመገንዘብ በአንድነት ቁሙ፡፡ ለዘመናት አብረው የኖሩ ክርስቲያኖችንና ሙስሊሞችን እርስ በርስ ለማፋጀት የሚፈልጉ፣ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ተላላኪዎች መሆናቸውን ተገንዘቡ፡፡ ኢትዮጵያውያን በብሔርም ሆነ በእምነት ምክንያት ሳይለያዩ አንድ ሆነው ዘመናትን የተሻገሩት፣ በአርቆ አሳቢነታቸው በገነቡዋቸው የጋራ ማኅበራዊ እሴቶቻቸው እንደሆነ የዘመኑ ትውልድ ይወቅ፡፡ ኢትዮጵያውያንን ለመከፋፈል ከሚዘረጉ ወጥመዶች ራሱን ይጠብቅ፡፡ ከሰብዓዊነት ጋር የተጣሉ የፖለቲካ ነጋዴዎች አገርን ለታሪካዊ ጠላቶች አሳልፎ የሚሰጥ አሳፋሪ ድርጊት ውስጥ መሆናቸውን መገንዘብ የግድ ይላል፡፡ የገዛ ወገናቸውን በብሔሩ ወይም በእምነቱ ምክንያት የሚገድሉ፣ የሚያፈናቅሉና የሚያሳድዱ ኃይሎችን ለይቶ ያጋልጥ፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚያሰቃየው የፖለቲካ ነጋዴዎችና ታሪካዊ ጠላቶች ተባብረው በሚሸርቡት ሴራ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ከእንዲህ ዓይነቱ አደገኛ ሴራ ራሳቸውን መከላከል የሚችሉት፣ አገር አጥፊው ወጥመድ ማንንም የማይምር መሆኑን በመገንዘብ ነው፡፡ የወራቤውንም ነውረኛ ድርጊት በጋራ በማውገዝ ኢትዮጵያውያን ከፋፋይ ሴራዎችን ማክሸፍ አለባቸው! 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

ከውጭ ይገቡ የነበሩ 38 ዓይነት ምርቶች እንዳይገቡ ዕግድ ተጣለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 38 ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ላይ ዕገዳ...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

መንግሥት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያስቆም ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ...

አዲስ ሲኖዶስ አቋቁመዋል በተባሉና በኦሮሚያ መንግሥት ላይ ክስ ለመመሥረት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ከገባችበት አረንቋ ውስጥ በፍጥነት ትውጣ!

የአገር ህልውና ከሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ አገር ሰላም ውላ ማደር የምትችለው ደግሞ የሕዝብ ደኅንነት አስተማማኝ ሲሆን ነው፡፡ ሕዝብና መንግሥት በአገር ህልውና...

የፈተናው ውጤት የፖለቲካው ዝቅጠት ማሳያ ነው!

በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከአጠቃላይ ተፈታኞች ውስጥ 3.3 በመቶ ያህሉ ብቻ ማለፋቸው፣ የአገሪቱን የትምህርት ጥራት ደረጃ በሚገባ ያመላከተ መስተዋት እንደሆነ አድርጎ መቀበል ተገቢ ነው፡፡...

የምግብ ችግር አገራዊ ሥጋት ስለደቀነ ፈጣን ዕርምጃ ይወሰድ!

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ልጆችን አቅም በብርቱ እየፈተኑ ያሉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከችግሮቹ ብዛት የተነሳ አንዱን ከሌላው ለማስቀደም የማይቻልበት ደረጃ ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ የምግብና የሰላም...