Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሲሚንቶ መሸጫ ዋጋን የሚቆጣጠር የግብይት መመርያ በድጋሚ ተዘጋጀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት በሰው ሠራሽ ምክንያቶች የሚፈጠረውን የሲሚንቶ እጥረት ለመቅረፍ በማለት ነሐሴ 2012 ዓ.ም. ያወጣውን የሲሚንቶ ግብይት መመርያ፣ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ በሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም. በመሻር በድጋሚ የሲሚንቶ ግብይት መመርያ እያዘጋጀ መሆኑ ተገለጸ፡፡ መመርያውን እያዘጋጀ ያለው ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሲሚንቶ ሽያጭ የሚከናወንበት የነፃ ገበያ ሥርዓት ለቁጥጥር አመቺ ባለመሆኑ፣ የትርፍ ህዳግን በመወሰን የመሸጫ ዋጋ ላይ ቁጥጥር ለማድረግ ማሰቡን አስታውቋል፡፡

ነጋዴዎች በሚፈጥሯቸው የተለያዩ ዘዴዎች ምክንያት የሲሚንቶ ግብይትን በሚፈለገው ሁኔታ መቆጣጠር አለመቻሉን ለሪፖርተት የተናገሩት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሀሰን መሐመድ፣ ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ዕርምጃዎች ቢወሰዱም ውጤታማ እንዳልሆኑ ገልጸዋል፡፡ አቶ ሀሰን ሲሚንቶ አንድ ሺሕ ብር እየተሸጠ መሆኑ ቢታወቅም፣ ሚኒስቴሩ ቁጥጥር ሲያደርግ ገበያው ውስጥ  የሚያገኘው ደረሰኝ 600 እና 700 ብር የተሸጠበትን መሆኑን በማሳያነት አውስተዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ሚኒስቴሩ የሲሚንቶ ሥርጭትንና የትርፍ ህዳግን በመወሰን የመሸጫ ዋጋን የሚቆጣጠር መመርያ አዘጋጅቶ እያጠናቀቀ መሆኑን፣ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥም ለማክሮ ኢኮኖሚክ ኮሚቴ እንደሚያቀርብ አስታውቀዋል፡፡

እንደ ሌሎች የግንባታ ግብዓቶች ሁሉ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የታየበት ሲሚንቶ በገበያው ላይ ካለመገኘቱም ባሻገር፣ በኩንታል 1‚100 ብር ገደማ ሲሸጥ ሰንብቷል፡፡ የሲሚንቶ ገበያው ውስብስብ የሆኑ ችግሮች፣ ረዣዥም እጆችና ብልሹ አሠራር ያለበት መሆኑን ለሪፖርተር ያስረዱት አቶ ሀሰን፣ አሁን ግን የአቅርቦትና የፍላጎት አለመመጣጠኑ ለዋጋ ንረት ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ‹‹ሲሚንቶ የሚከዝኑ (የሚሸሸጉ) ነጋዴዎች ሊኖሩ ይችላል›› በሚል ዕሳቤ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከአዲስ አባባ ንግድ ቢሮ፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጋር በመሆን ያደረገው ኦፕሬሽን እንዳልተሳካ ተናግረዋል፡፡ ይህም ችግሩ የምርት እጥረት መሆኑን እንዳሳየና አብዛኞቹ ፋብሪካዎች በፀጥታ ምክንያት ምርት ማቆማቸው እጥረት እንዲከሰት ማድረጉን አክለዋል፡፡

የምርት እጥረት በተፈጥሮ ወደ ዋጋ ጭማሪ እንደሚመራ ያስረዱት ሚኒስትር ዲኤታው፣ ሲሚንቶ እንደ ዘይት፣ ስኳርና ስንዴ መሠረታዊ ሸቀጥ ታይቶ በሚኒስቴሩ የትርፍ ህዳግ እንዲወጣለት ጥያቄ እንደሚቀርብ ተናግረዋል፡፡

አሁን ባለው ውሳኔ ሚኒስቴሩ እያዘጋጀ ያለው የትርፍ ህዳግ ጅምላና ችርቻሮ ነጋዴዎች ላይ ያነጣጠረ መሆኑን የተናገሩት አቶ ሀሰን፣ ፋብሪካዎች ሲሚንቶውን የሚሸጡበት ዋጋ ተመጣጣኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ይሁንና ሚኒስቴሩ ከሚመለከተው የመንግሥት ተቋም ጋር ተነጋግሮ በፋብሪካዎቹ ላይ የሚያጣራው ጉዳይ እንዳለ፣ ማጣራት ተደርጎም የትርፍ ህዳጉ ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም እየወጣ ያለው የግብይት መመርያ የሲሚንቶ ምርት ሥርጭትን ለመቆጣጠር እንደሚያገለግል፣ ሲሚንቶ ከምርት እስከ ሽያጭ ሒደቱ ክትትል እንደሚደረግበት አስታውቀዋል፡፡ እንደ አቶ ሀሰን ገለጻ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ሁሉም መሠረታዊ ሸቀጦች ላይ ሥርጭት ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችል ዲጂታል ሥርዓት እያዘጋጀ ነው፡፡ ዲጂታል ሥርዓቱ ተግባራዊ ሲሆን ምርቱ ለማንና የት እንደሸጠ የሚታይ በመሆኑ ሚኒስቴሩ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የፌዴራል ፖሊስና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በጋራ ክትትል ማድረግ እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡

የቀድሞው ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሲሚንቶ ከፋብሪካዎች ወደ ተጠቃሚዎች የሚደርስበት የግብይትና ሥርጭት ሒደት ከፍተኛ ችግር ያለበት እንደሆነ በመግለጽ፣ ነሐሴ 2012 ዓ.ም. ያወጣውን የሲሚንቶ ግብይት መመርያ ያነሳው ከአንድ ዓመት በኋላ ነበር፡፡ ሚኒስቴሩ መመርያውን ሲሽር የክረምት ወቅት በመሆኑ የፍላጎት ማነስ የሚከሰት መሆኑን፣ አምራች ኢንዱስትሪዎች አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች ሲሚንቶ ባልተጋነነ ዋጋ ለመሸጥ መስማማታቸውንና ፋብሪካዎች ቁጥጥር ለማድረግ ስምምነት ማድረጋቸውን በምክንያትነት ጠቅሶ ነበር፡፡

በ2012 ዓ.ም. ወጥቶ የነበረው መመርያ፣ በሲሚንቶ ገበያ ውስጥ ውስብስብ ችግሮችና ብልሹ አሠራር እንዳይሳካ መደረጉን የተናገሩት አቶ ሀሰን፣ አሁን ያለው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ የተለየ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሚኒስትር ደኤታው እየተዘጋጀ ያለው መመርያ ሚኒስቴሩም አባል ለሆነበት ማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ ቀርቦ ውሳኔ ሊሰጥበት እንደሚችል፣ አልያም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ አስረድተዋል፡፡ ውሳኔው ሲፀድቅ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ባለድርሻ አካላት ተጠርተው ግንዛቤ ማስጨበጫ እንደሚሰጣቸው አክለው ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች