- መነሻ ዋጋ 70 ብር እንደሚሆን ተገልጿል
ሊፍት ኢትዮጵያ አይሲቲ ቴክኖሎጂ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በአሁኑ ወቅት ለማኅበረሰቡ ተደራሽ እየሆኑ ከሚገኙ የሳሎን ታክሲዎች (የሜትር ታክሲ) አገልግሎት ሰጪዎች የዋጋ ቅናሽ በማድረግ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተሻለ አማራጭ ለማቅረብ የታሰበ መሆኑን ተቋሙ ዓርብ ግንቦት 12 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቋል፡፡
የማኅበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙኒብ አብዱልከፍር እንደገለጹት፣ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የትራንስፖርት አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ተቋሙ ትልቅ አማራጭ ይዞ መጥቷል፡፡
በተለይም የትራንስፖርት አገልግሎቱን የሚሰጡ አሽከርካሪዎች (ሾፌሮች) የዚህ ተጠቃሚ እንደሚሆኑና በወር ለተቋሙ የሚከፍሉት ገቢ 449 ብር ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የትራንስፖርት አገልግሎት ተደራሽ በሚደረግበት ወቅት በተመሳሳይ መንገድ የሚሄዱ ግለሰቦች በአንድ ላይ በመሄድ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ እነዚህም ተጠቃሚዎች የተጓዙበትን ዋጋ በጋራ መክፈል ይችላሉ ብለዋል፡፡
አገልግሎቱን ለመስጠት የሚመረጡ ተሽከርካሪዎች እ.ኤ.አ ከ2000 በኋላ የተመረቱና ቀለማቸውም ቢጫ፣ በቀይ እንደሚሆን እንዲሁም እስከ ሰባት ወንበር ተሽከርካሪዎች አገልግሎቱን መስጠት እንደሚችሉ አክለዋል፡፡
በዚህም መሠረት በአሁኑ ወቅት 1,800 አሽከርካሪዎች መመዝገባቸውን የተናገሩት አቶ ሙኒብ፣ የማኅበረሰቡን የትራንስፖርት ችግር ጥያቄ ለመመለስ መነሻ ኪሎ ሜትር ከ70 ብር እንዲጀምር መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
የትራንስፖርት አገልግሎቱን የሚሰጡ አሽከርካሪዎች ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት ማሟላት የሚገባቸውን ነገር እንዲያሟሉ ጊዜ እንደሚሰጣቸው አቶ ሙኒብ አብራርተዋል፡፡
ተቋሙም በቀጣይ በኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚሰጡ አሽከርካሪዎችን እንደሚያስገባም፣ ይህም በከተማዋ በከፍተኛ ሁኔታ እየታየ ያለውን የትራንስፖርት አገልግሎት በተወሰነ ደረጃ የሚቀርፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡