Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ህልውና ዕውን የሚሆነው መቼ ነው?

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዓለሙ ሁሉ፣ ዘመን በተቆጠረ ዓመት በተቀመረ ቁጥር ግንቦት 10 ቀን (ሜይ 18) ላይ ሲደርስ ‹‹ዓለም አቀፍ የሙዚየም ቀን›› ብሎ ያከብረዋል፡፡ ዓለማቀፉ የሙዚየሞች ምክር ቤት (አይኮም) ከ1969 ዓ.ም. ጀምሮ የዓለም አቀፍ የሙዚየምን ቀን (ዓሙቀ) በየዓመቱ በተለያዩ መሪ ቃሎች ሲያከብረው ቆይቷል፡፡ ዘንድሮ መሪ ቃሉን የሙዚየሞች ልዕልና/ኃይል (The Powers Of Museums) በማድረግ አስቦታል፡፡

ኢትዮጵያም ቀኑን ማክበር ከጀመረች ከሁለት አሠርታት ያልበለጠ ሲሆን፣ መሪ ቃሉንም በራሷ ቅኝት ‹‹የሙዚየሞች ተፅዕኖ ፈጣሪነት›› (በመፈክራዊ አገላለጽም ‹‹ሙዚየሞች ከትናንት እየተማርን ነገን አሻግረን››) በሚል ኅብረተሰቡ ሙዚየሙን በነፃ እንዲጎበኝ ማድረግን ጨምሮ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እስከ ግንቦት 14 ቀን 2014 ዓ.ም. እያከበረችው ነው፡፡

በዓሉን ማክበር በጀመረችበት ዘመን ስታከብር የነበረው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም በሚባለው ተቋሟ አማካይነት ነበር፡፡ በአንድ ቅጥር ግቢ ውስጥ ያሉት የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን (ቅጥጥባ) እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም በ2003 ዓ.ም. በተተገበረው በቢፒአሩ አደረጃጀት መሠረት ባለሥልጣኑ በተለያዩ ዳይሬክቶሬቶች ሲዋቀር በዋና ሥራ አስኪያጅ ይመራ የነበረው ሙዚየሙ የባለሥልጣኑ አንድ ዳይሬክቶሬት ሆኖ ተደራጅቷል፡፡ ስሙም ከብሔራዊ ሙዚየምነት ወደ ‹‹የተንቀሳቃሽ ቅርስ ልማት ኤግዚቢሽን ዳይሬክቶሬት›› ተለውጧል፡፡ ኃላፊውም በባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሥር ሆኖ ዳይሬክተር ተብሏል፡፡

ይህ አዲሱ ስያሜ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮና ከሙዚየሞች ወካይነት አኳያ ብዙም የማያስኬድ ስያሜ በመሆኑ በየጊዜው በመድረኩ ትችትና ተቃውሞ እየተሰነዘረበት መጥቷል፡፡

ነባሩ ሙዚየም በአሁን አጠራሩ ‹‹… ዳይሬክቶሬት›› ስለ ሰው ዘር አመጣጥና ሌሎችም የኢትዮጵያ ታሪክና ባህል የሚያንፀባርቁ እነ ሉሲ፣ ሰላም፣ አርዲ፣ ወዘተ ቅርሶች የሚጎበኝበት ቢሆንም፣ ብሔራዊ ሙዚየም የሚለውን ዕውቅና የማጣቱ ጉዳይ የበርካቶች መጋገሪያ ከመሆን አላመለጠም፡፡

በየዓመቱ ግንቦት 10 ቀን (ሜይ 18) የሚከበረውን የዓለም ሙዚየም ቀን ኢትዮጵያ ስታከብር፣ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የብሔራዊ ሙዚየም ስያሜ ጉዳይ ሳይነሳ ያለፈበት ጊዜ አልነበረም፡፡ ለምን? ተብሎ ሲጠየቅም ‹‹እየተጠና ነው›› የሚል ምላሽም ሲሰማበት ኖሯል፡፡ ዘንድሮም ያነሱ አሉ፡፡

እንዲያውም ኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም የሚለው መጠርያ ሳይኖራትና የሙዚየምነት ዕውቅና ሳትሰጥ የሙዚየም ቀንን በየዓመቱ ማክበሯን ተቃርኖ (ፓራዶክስ) ነው የሚሉም አልታጡም፡፡

በተለይ የዓለም ሙዚየም ቀን በሚታሰብበት ዕለት ጎልቶ ይሰማል፡፡ ዓምና ቀኑን  ባለሥልጣን እንደወትሮው ሲያከብረው ባይታይም ቀኑን ግን በዚያው ዓመት የተመሠረተው የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማኅበር (ኢባቱጋማ) ከአዲስ አበባ ሙዚየም ጋር በመተባበር ማክበሩ ይታወሳል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም›› ዳግም ዕውን እንዲሆንም ለቀረበው ጥሪም ጆሮ የሰጠም የለም፡፡

  ‹‹የገናና ታሪክ ባለቤት ነን እያልን ብሔራዊ ሙዚየምን ያህል ተቋም በሕግ ማዕቀፍና በአዋጅ ለማቋቋም እየተደረገ ያለው ጥረት መጓተቱን መንግሥት በመረዳት፣ ፈጣን  ምላሽ እንዲሰጠውና ኢትዮጵያ በተሻለ ሁኔታ የሚደራጅ የብሔራዊ ሙዚየም ባለቤት የሚያደርጋትን ሥራ እንዲሠራ ለመጠቆም እንወዳለን፤›› ሲል በወቅቱ ኢባቱጋማ መጠየቁ አይዘነጋም፡፡ ማኅበሩ አያይዞም ዘርፈ ብዙ ሙዚየሞች አለመኖራቸውን ነባራዊ ሁኔታን በመጥቀስ ከማስገንዘብ አላለፈም፡፡ ‹‹የሦስት ሺሕ ዓመት የግብርና ታሪክ ኖሮን የግብርና ሙዚየም፣ የረዥም ዘመን የነፃነትና የድል አድራጊነት የጦርነት ታሪክ ባለቤቶች ሆነን የጦር ሙዚየም፣ ከኪነት ጋር የቀደመ ዝምድና እንዳለን ሕዝቦች የጥበብ ሙዚየም የለንም፡፡››

ዘንድሮ ቀኑን ቅጥጥባ፣ በአዲስ መልክ በመቋቋም ላይ ካለው የአገር መከላከያ ሚኒስቴር የወታደራዊ ቅርስ ጥበቃና ሙዚየም ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር ባከበረበት አጋጣሚ በተዘጋጀው ዓውደ ጥናት ላይ የአገር መከላከያ ሠራዊት ሙዚየምን ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡

‹‹የተንቀሳቃሽ ቅርስ ልማትና ኤግዚቢሽን›› ሙዚየምን መተካት ይችላልን?

ከዓለም አቀፉ የሙዚየም ድርጅት (አይኮም) የሙዚየም ትርጓሜ በመነሳት ‹‹የተንቀሳቃሽ ቅርስ ልማትና ኤግዚቢሽን›› በምን ሥሌት ነው የሙዚየምን ጽንሰ ሐሳብና ተልዕኮ በምልዓት ሊተካ የሚችለው? የሚሉ ጠያቂዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡

መንግሥት የኢትዮጵያ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣንን በ1992 ዓ.ም. ያቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 209/1992 ስለቅርስ ጥናትና አጠባበቅ የሚናገር ነው፡፡     በአዋጁ አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ 12 ድንጋጌ ሙዚየምን እንዲህ ተርጉሞታል፡፡ ‹‹ሙዚየም ማለት ለትርፍ የተቋቋመ ድርጅት ያልሆነ ቅርሶችን የሚሰበስብ፣ የሚጠብቅና የሚጠግን፣ ለምርምርና ለጥናት፣ ለማስተማሪያና ለመዝናኛነት ስብስቦችን በሚገባ አዘጋጅቶ ለኅብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ነው፡፡›› ለዚህ የሙዚየም ትርጓሜ መሠረት ነው ተብሎ የሚታሰበው በቀዳሚው የአይኮም ድንጋጌ ላይ የወጣው የሙዚየም ምንነት ነው፡፡

‹‹ሙዚየም ማለት ዓላማው በትርፍ ላይ ያልተመሠረተ ለማኅበረሰብ ዕድገት አገልግሎት የሚያበረክትና ለኅብረተሰቡ ክፍት የሆነ፣ ለጥናት፣ ለትምህርትና ለህሊናዊ ዕርካታ ሊውሉ በሚችሉበት ሁኔታ የሰው ልጅና የአካባቢውን ቁሳዊ መረጃዎች የሚያሰባስብ፣ የሚያከማችና የሚንከባከብ ምርምር የሚያካሂድ በኤግዚቢሽን ወይም አግባብነት ባለው መንገድ የሚያስተዋውቅ ተቋም ነው፡፡››

እ.ኤ.አ. በ1946 የተመሠረተው አይኮም የሙዚየም ትርጓሜን በየዓረፍተ ዘመኑ ማሻሻሉን አልተወም፡፡ በኦስትሪያ ቪየና ነሐሴ 18 ቀን 1999 ዓ.ም. ባደረገው 22ኛው ጠቅላላ ጉባዔው ነባሩን ድንጋጌ እንዲህ አድርጎ ዘርዘር በማድረግ አሻሽሎታል፡፡

‹‹ሙዚየም ማለት ለትርፍ ያልተቋቋመ፣ ለኅብረተሰብ አገልግሎትና ለልማቱ የተሰማራ፣ የሰው ልጆች የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን (Tangible and Intangible Heritage)  የሚጠብቅ፣ የሚንከባከብ ምርምርና ጥናት የሚያደርግ፣ ለሕዝቡ ክፍት ሆኖ በዓውደ ርዕይ የሚጎበኝ ብሎም ለትምህርት፣ ለጥናትና ለተድላ ደስታ (ለመዝናኛ) የሚያውል ቋሚ ተቋም ነው፡፡››

አይኮም ያደረገውን የትርጉም ማሻሻያ ኢትዮጵያ አለመመልከቷ ወይም አለማሻሻሏ የሚያሳየው፣ በቀደመው ትርጉም ብቻ በመመሥረት ብሔራዊ ሙዚየምን የተንቀሳቃሽ ቅርስ ልማትና ኤግዚቢሽን ዳይሬክቶሬት ብላ መሰየሟ ነው፡፡ ዳይሬክቶሬቱ የማይንቀሳቀሱ (የሚዳሰሱ) እንዲሁም የማይዳሰሱ ቅርሶችን  አይመለከትም ማለት ነው፡፡

ዓለም አቀፉ የሙዚየም ድርጅት ከአሥራ ሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላ የሙዚየምን ትርጉም ዳግም አሻሽሎታል፡፡  የሥራ አስፈጻሚ ቦርዱ በሐምሌ 2011 ዓ.ም. በፓሪስ ባደረገው 139ኛው ስብሰባው በደረሰበት ውሳኔ አዲሱን የሙዚየም ብያኔ ይፋ አድርጓል፡፡

‹‹ሙዚየሞች ዲሞክራሲያዊ፣ ሁሉን አካታች ስላለፉት  ዘመናትም ሆነ ስለመጪው ዘመን የሚያወሱ፣ የሒሳዊ (ክሪቲካል) ውይይቶች መድረክ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ አሁን ያሉትን ግጭቶችና ተግዳሮቶች በመገንዘብ በመፍትሔነት በማኅበረሰቡ ውስጥ እምነት የሚያሳድሩ የዕደ ጥበባት ውጤቶችንና ናሙናዎችን ይይዛሉ፡፡ ለመጪው ትውልድ ብዝኃ ትውስታዎችን በመጠበቅ ለሁሉም ሕዝብ ያለ ልዩነት በእኩል መብቶችና በእኩል ተደራሽነት ያስተናግዳሉ፡፡ ዋስትናም ይሰጣሉ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ህልውና ዕውን የሚሆነው መቼ ነው? | Ethiopian Reporter | ሪፖርተርየኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ህልውና ዕውን የሚሆነው መቼ ነው? | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

‹‹ሙዚየሞች በትርፍ ላይ ያልተመሠረቱ አሳታፊና ሥራቸው ግልፅ የሆነ ነው፡፡ እንዲሁም ለሰው ልጅ ክብርና ማኅበራዊ ፍትሕ፣ ለዓለም አቀፍ እኩልነትና ለዓለም ደኅንነት ንቁ አስተዋጽዖ የሚያደርጉት ብዝኃነትን ባማከለ መልኩ የተለያዩ ማኅበረሰቦችን ቅርስ የመሰብሰብ፣ የመጠበቅ፣ ጥናትና ምርምር የማድረግ፣ የመተርጐም፣ በዓውደ ርዕይ በማሳየት ነው፡፡

ይህ አዲሱ ማሻሻያ ከመውጣቱ ከአሥራ አንድ ዓመታት በፊት የዓለም ሙዚየም ቀን በኢትዮጵያ «ሙዚየሞች ለማኅበራዊ ለውጥና ዕድገት አጋዥ ኃይሎች» በሚል መሪ ቃል ሲከበር በተዘጋጀው ሲምፖዚየም ላይ፣ የሙዚየም ተልዕኮ መስፋት እንደሚገባው በኢትዮጵያውያን ምሁራን ተንፀባርቆ ነበር፡፡

በወቅቱ የታሪክና አርኪዮሎዢ ምሁሩ ካሳዬ በጋሻው (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ ሙዚየም ብዙ ጊዜ የሚታወቀው ሥራው መሰብሰብ፣ መሰነድ፣ መጠበቅ፣ ጥናትና ምርምር በየዕለቱ ማከናወን ናቸው፡፡ አሁን ባለንበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ሙዚየም ምን ሆኖ መገኘት ይገባዋል፣ ምን ዓይነት አስተሳሰብ ይኖረዋል የሚለው ተተኳሪ ነጥብን አንስተዋል፡፡

 ሙዚየሞች ምን ሆነው መገኘት አለባቸው? የሙዚየም ብያኔ ዛሬ ያለንበትን ሁኔታ ይዳስሳል ወይ፣ ነባሩ ብያኔ ግማሽ ምዕት ዓመት አሳልፏል፡፡ አሁን የምንለውን መሸከም ይችላል ወይ? ሙዚየሞች የመገናኛ ቦታ፣ ሐሳብ መለዋወጫ ችግርን የመቅረፊያ መድረኮች ናቸው፡፡ ባላቸው ስብስብ በመገናኘትና ታሪክና ባህልን ብቻ በማሰባሰብ ሳይወሰኑ ሌሎች ዘርፎችን እንደ ማዕድን፣ ኢነርጂን ማካተትና ገንዘብን የማስገባት ለቱሪዝም ዕድገት የሚበጁ መሆናቸውን ማወቅ ይገባል ይላሉ ምሁሩ፡፡

ሙዚየም የአገሪቷን ችግር በኤችአይቪ፣ በሥነ አካባቢ፣ በፖለቲካ ቀውሶች ላይ የሚነጋገሩበት መድረክ መሆን እንደሚገባው የሌሎችን አገሮችን ተሞክሮ በምሳሌነት በማቅረብ ያብራራሉ፡፡

ለማኅበራዊ ለውጥ በምናስብበት ጊዜ ሕንፃውን፣ ቅርሶችን ብቻ ሳይሆን የሚያንቀሳቅሰው ክፍልንም ጭምር ነው፡፡ በሁለተኛነት የሚያሳየው ሙዚየሙ ማኅበራዊ ለውጥ ለማምጣት አቅም አለው ወይ፣ ራሱስ ሳይለወጥ ሌላውን መለወጥ ይችላል ወይ፣ ለለውጥስ ተዘጋጅተዋል ወይ፣ ይኸንን የሚሸከም ኅብረተሰብ አለ ወይ፣ መንግሥትስ ይህን ሐሳብ ይገነዘባል ወይ? እነዚህን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ምሁሩ በወቅቱ አጽንዖት ሰጥተውበት ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች